ከውጭ በርዳታ የሚገኘው በሙስና የተዘፈቀው ድጎማ (Safety Net) በኢትዮጵያ ምን ይምስላል? - ዶ/ር ሰዒድ ሃሰን
THE CORRUPTIVE STRUCTURE OF THE SAFETY NET PROGRAM IN ETHIOPIA.
A Testimonial Letter from Amare Mammo – a former cadre of the EPRDF who used to work for the Ethiopian Agricultural and Food Organization
Letter addressed to: Dr. Seid Hassan – Murray State University. Received: November 23, 2009.
ጤና ይስጥልኝ ዶ/ር ስይድ።
ኢትዮጵያን እያሽመደመደ የሚገኘውን ሙስና በሚመለከት ትኩረት ሰጥተው በመያዘዎ አመሰግናለሁ። በድጎማ መልክ ለገበሬው የሚሰጠውን ገንዘብ በሚሚለከት ግንዛቤ እንዲኖረዎትና፤ መረጃ እንዲሆንዎት የግሌን ለማበርከት/ለመወጣት ይህችን ደብድዳቤ ጽፌአለሁ። ስለ እኔ ትንሽ ለማለት ያህል፤ ወደ አሜርካ ከመጣሁ ይኸውና ሁለተኛ አመቴ ነው። በግብርና እና የምግብ ድርጅት የገበሬዎች የእርሻ አማከሪ ሆኘ በተለያዩ የደቡብ ኢትዮጵያ ወረዳዎች ሠርቻለሁ።
ከላይ በተገለፀው አርዕስት ያለውን ሁኔታ ከመግለፄ በፊት፤ ከ1997 ዓ/ም ምርጫ በኋል፤ የገጠሩ ሕዝብ ኢሕአደግን የመረጠው ለማስመስልና ከተሜውን ለማሸበር ይነገሩ በነበሩት ግጥሞች መካክል ልጀምር፤
መራቡን ይራበው- የከተማ ሕዝብ፤
የዋህ ገጠሬ ሕዝብ- ይብላ ይደልብ።
ንብ ትነድፋለች አለ- የከተማ ሰው?
በልቶ ይመርቃል - ድሀ ገበሬው።
እንደሚታወቀው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር የኢዮጵያ ገብሬ በርሀብ ተጠቅቶ እንዳይሞት፤ ከውጭ አገር በሚደርግ ድጎማ ሳያሰልስ “እየተረዳ” ነው። ይህ ድጎማ በእንግሊዝኛው ሴፍቲ ኔት (Safety Net) የሚባለው ተቋም ነው። ፕሮጀክቱ በአብዛኛው የሚመራውም በመንግሥት ካድሬዎች ሲሆን የድርጅታዊ አወቃቀሩና አከፋፈሉም እንደዚህ ነው።
ሀ) ሴፍቲ ኔት (Safety Net) ከ7 ተኩል እስከ 14 ሚሊዮን የሚሆነውን የገጠር ሕዝብን ያቀፈ ፕሮግራም (ተቋም) ነው። ፕሮግራሙ ከ1997 እስከ 2002 ዓ/ም ለአምስት ዓመት የሚቆይ ነው። [ለአንባቢያን ማሳወቂያ፡ - የዚህ ድጎማ ለጋሾች በአብዛኛው የዓለም ባንክና የአሜሪካ መንግሥት ሲሆኑ፤ አሁን በቅርቡ የዓለም ባንክ ያደርግ የነበረውን ድጎማ አሁን እንደገና አዲሷል። በድጎማው 292 ወረዳዎች እነደሚረዱም ገልጿል።] ድጎማው የሚያተኩርባቸው አካባቢዎች ድርቅ ያጠቃቸው ቢሆኑም በየክፍለ ግዛቱ ለሚጋኙት ሁሉ ነው። ለዚህ ድጎማ ተጠቃሚ የሚሆነውን አርሶ አደር የመመልመያ መለኪያዎች እነዚህ ናቸው፤
1. ብዙ ልጅች ያለው ቤተሰብ፤
2. ኑሮው ዝቅተኛ የሆነ -ድህነት ያጠቃው - ለምሳሌ፤ ክብቶችና የቤት እንስሳት የሌለው፤
3. ቤቱ የተቃጠለበት፤
4. የቲም የሆኑ፤ አባት ወይም እናት የሌላቸው ልጆች፤
5. በእድሜ የገፉ አዣውንቶች፤
6. አካለ-ስንኩላን የሆኑና መሥራት የማይችሉ።
ለ) በድጎማው ተጠቃሚ ከሚሆነው አርሶ አደር የሚጠበቅበት ሥራ፤
አንድ የድጎማ (ሴፍቲ ኔት) ተጠቃሚ አርሶ አደር በወር ስድስት (6) ቀን ፤ በቀን 8 ሰዓት በራሱ ስም መሥራት አለበት። ባለቤቱም እንደዚሁ 6 ቀናት በቀን 8 ሰዓት መሥራት አለባት። እሷ መሥራት ካልቻለች፤ ባሏ በወር 12 ቀናት መሥራት አለበት።
ሐ) የሥራው ዓይነት፤
አብዛኛው ሰው የሚሠራው ለመኪና መሄጃ የሚሆን የመንገድ ሥራ ነው። የሚሠራ መንገድ ከሌለ የድርጅት ጽሕፈት ቤትን መሥራት፤ ይህ ካልሆነ ለአርሶ አደሩ መስብሰቢያ የሚሆን የፖለቲካ ድርጅት ጽ/ቤትን በመሥራት፤ በተለይም የዉሃ ማቆር ጉድጓድን በመቆፈር ይከናወናል።
መ) የአከፋፈል ዘዴ- ፓኬጅ ይባላል፡
- በሰው (ነፍሶከፍ) 30 ብር፤ ለምሳሌ አንድ አባዎራ 5 ቤተሰብ ካለው 150 ብር በወር ይከፈለዋል። ክፍያው ለአንድ ዙር ለ6 ወራት ይቆያል።
- ሌላው ደግሞ፤ የመጀመሪያው ፓኬጅ ተብሎ የሚጠራው 1,600 ብር ለአንድ አርሶ አደር በሁልት ዓመት የሚሚለስ ተብሎ በብድር የሚሰጠው ነው። ነገር ግን ይህንን ብድር የሚያገኙት ገበሬዎች ሁሉም ሳይሆኑ፤ ለሌላው አርዓያ ይሆናሉ ተብለው የተመረጡት ናቸው። የዚህ ብድር ተጠቃሚዎች አብዛኞቹ እርዳታው የማያስፈልጋቸው፤ ከሌላው ገበሬ ጋር ሲወዳደሩ “ሀብታም” ናቸው ሊባሉ የሚበቁ ናቸው። በሁለተኛው ፓኬጅ 4,000 (አራት ሽህ) ብር ይሰጣል - ከላይ እንደተጠቀሰው በብድር ነክ ሆኖ አርዓያ ይሆናሉ ተብለው ለተመረጡት ነው የሚሰጠው።
ለዚህ ገንዝብ አከፋፈል እንደ መመሪያ ሆኖ የሚያገለግል ተጠርዞ የሚታደል “መጽሀፍም” አለ። እንግዲህ ከላይ እንደተገለጸው፤ ለአንድ ሰው የሚሰጠው ክፍያ በቤተሰብ ልክ ስለሆነ፤ አንድ አባወራ በፕሮጀችቱ የሚሰጠውን ብር ለማበርከት በርከት ያሉ ልጆችን እንዲያፈራ ይጋብዘዋል ማለት ነው። ልጅ የሌለውም አንዳንድ ጊዜ ብሩን ለማግኘት ሲል ከጎርቤት ልጅ ይዋሳል/ያሳድጋል። እርዳታው የሚሰጠው “ከብት ለሌለው” ነው ስለሚልም፤ አንዳንድ ገበሬዎች እርዳታውን ለማግኘት ከብቶቻቸውን ይሸጣሉ። ቤቶቻቸውን አቃጥለውም ተጠቃሚ የሆኑም አልጠፉ።
ለሚሠራው የመንገድ፤ የዉሀ ማቆር፤ የፓርቲና የገበሬ ጽ/ቤት ሥራ አስተባባሪዎቹና አዛዦቹ ካድሬዎች ናቸው። እነዚህም ካድሬዎች በተለይ የግብርናን ሥራ አስመልክቶ ችሎታ የሌላቸው ስለሆኑ፤ ይጥቀምም ይጉዳ፤ እነሱ ከመሰላቸው ገበሬውን በማዘዝ ማስቆፈር ነው። ገንዘቡ የግድ ለገበሬው እየተሰጠ ነው መባል ስላለበትም ገበሬዎች መቆፈር አለባቸው። በሀላፊነት የተሾሙት ከሚያስቆፍሩትም አንዱ የውሀ ማቆር (ጉድጓድ) ስለሆነ፤ የሚቆፈሩት ጉድጓዶች እንዳው ይብዙ እንጂ ዉሀ የማይቆጥሩ ናቸው። እንዳውም “መሠራት አለበት” ተብሎ የሚቆፈሩት የውሃ ማቆሪያዎች ከመብዛታቸውም በላይ፤ ስለማይታጠሩ፤ ባልታጠሩት ጉድጓዶች ውስጥ ከብቶች እየገቡ በመሠበራቸውና በመሞታቸው የተነሳ ገብሬዎቹ በጣም ይማረራሉ። ገበሬውችም “ጉዷዶቹ ይደፈኑልን” ብለው ለካድሬዎቹ ጥያቄዎች ሲያቀርቡ በአብነት እኔ እመሰክራለሁ።
ለውሀ ማቆር መገንቢያ ተብሎ አንድ ጊዜ እኔ በነበርኩበት ቦታ በ8 የአይሱዙ (Isuzu) መኪናዎች 250 ኩንታል ሲሚንቶ ተልኮ ነበር። ሲሚንቶውን ፈርሞ የተረከበውም እንደኔ የግብርና ባለሙያ የተባለው እኔ የማውቀው ግለሰብ ነበር። ነገር ግን፤ ተከምሮ የነበረው አብዛኛው ሲሚንቶ የካብኔ አባላት ቤቶችን ማደሻና ማስጨረሻ ነው የሆነው። [ካብኔ ማለት በኢሕአደግ (በየወረዳው) የሚሾም ሥራ አስፈጻሚ ሰው ነው።] አብዛኛውን ሲሚንቶ የግብርና ባለሙያው ለካድሬዎቹ (ለካብኔ አባላቱ) በርካሽ ሸጠላቸው። የቀረው ለሙከራ ተብሎ ወድ የውሀ ማቆር ቦታ ተወስዶ ተከምሮ ለብዙ ጊዜ ስለቆየ ደርቆ ተበላሸ። በአጠቃላይ ሲታይ፤ በሀላፊነት ሲሚንቶውን የተረከበውም ሆነ የካብኔ አባላት ተጠቃሚ ስልሆኑ “ለጥፋቱ ተጠያቂ ማነው?” ብሎ የሚጠይቅ ማንም የለም ማለት ነው።
ከላይ እንደገለጽኩት አንዱና ዋናው ሥራ በየቀበሌው የሚገነባው የፖለቲካ ጽሕፈት ቤት ነው። ገበሬውን በነዚህ መሰብሰቢያ ቤቶች እያጎርን እንጨቀጭቀዋለን። እኛ ወደ ገጠር የተላክነው ዋናው ሥራችን ይህ ነው። እንዳውም አንድ ጊዜ አንዱ ፀሀፊያችን ይህንን አስመለክቶ በቀልድ አስመስሎ እውነቱን ለመናገር ሲነግረን “ኢትዮጵያ ሥብሰባ ማድረግን ስለምትችልበት ይህን ችሎታችንን አሽገን (“ስብሰባን ፓክ” አድርገን) ለውጭ ገባያ ብናቀርብ ብዙ ትርፋማ እንሆናለን እና ይታሰብበት” ብሎ ተናገረና በጣም አሳቀን።
በሴፍቲ ኔት (Safety Net) ተጠቃሚ የሆኑትም የኢሕአደግ አባላት እንዲሆኑ፤ በምርጫም ጊዜ ለዚሁ ፓርቲ ድጋፋቸውን እንዲሰጡ (እንዲመርጡ) ይጠየቃሉ፤ ይነገራቸዋል፤ ማስጠንቀቂያም ይሰጣቸዋል። ባይጠየቁም እራሱ ጥቅሙ ይገዛቸዋል ብየ አስባለሁ፤ ይህንንም በከፊል ተገንዝቤአለሁ። ድጎማውን አስመልክቶ ዋና ተጠቃሚና የከበሩ የካብኔ አባላት ለገበሬው ድጎማውን ሰጥተው እያባበሉም፤ ገና የምርጫ ጊዜው ሳይደርስ እነሱንና የእነሱን ፓርቲ ተዎካዮች እንዲመርጥም ያዋክቡታል። እነሱን ከመምረጥ ሌላ ምርጫ የለውም፤ በቃ!
- ሌላው መረሳት የሌለበት ደግም እንደኔ ላሉት ወደ ገጠር ለሚላኩት “ሙያተኞች” የሚሰጠው የቀን አበል (per dime) ነው። የዚህ አበል እኔም ተጠቃሚ ነበርኩ። ይህንን በሚመለከት እስቲ አንድ ጊዜ የሆነውን ላጫውተዎ። አንድ ጊዜ ለሥራ ወደ ገጠር ተላክን። የተላክነው ለሁለት ቀናት ብቻ ነበር። ነገር ግን ተጽፎ የወሰድነው አበል ለ10 ቀናት ሆኖ አገኘነው። ከ5 ቀናት በኋላም (የመጀመሪያውን ሳንጨርስ) ወደ ሌላ ቀበሌ ለተመሳሳይ ሥራ የ12 ቀናት አበል ተፃፈልን። እንደገናም ወደ ሌላ ቀበሌ ተልከን የ8 ቀን አበል ወሰድን። በአጠቃላይ፤ ሣንሠራ ሠርታችኋል፤ ባልሄድንበት ቦታ ሄዳችኋል ተብለን የ30 ቀናት አበለ ወሰድን ማለት ነው። በጋምቤላ አካባቢ አንድ የካብኔ አባል በአንድ ዓመት ውስጥ የ458 የቀን አበል፤ ሁለተኛው ደግሞ የ378 የቀን አበል በመውሰዳቸው ሁለቱም ከሥራ እንደተባረሩ አውቃለሁ። እንደዚህ አይኑን ያፈጠጠ የሙስና ተግባር ላይ በግልጽ የተሠማሩትና የታወቀባቸው “ሙያተኞች”፤ “ከሥራቸው ተባረዋል” ቢባልም፤ ነገር ግን አብዛኞቹ ቅጣት ሳይሆን ወደ ሌላ ወረዳ እንዲዛወሩ ነው የሚደረገው።
ረ) ሌሎችንም ልጨምርልዎ፤
1. አንዳንድ ገበሬዎች ምርጥ የዘር በጎች፤ የወተት ላሞች፤ የመሳሰሉትን ተገዝተው ይሰጣቸዋል። እነዚህን የቤት እንሥሳዎች ገበሬው ፈርሞ ሲወስድ ከተገዙበት በላይ ተጨምሮበት ነው። አንዳንድ ጊዜ ገበሬው የተገዙበትን ዋጋ ቢያውቅም አፉን ሸብቦ ከመቀበል ሌላ አማራጭ የለውም። ካጉረመረመ ሊያገኛቸው የሚችላቸውን እንሰሳዎች ከናካቴው ማጣት ስለሚሆንበት።
2. ሌላው ደግሞ ለድጎማው (ሴፍቲ ኔት) ተብሎ የተመደበውንና የሚላከውን ገንዘብ አስከትሎ ለፕሮጀችቶች (የፕሮግራሞች መጠቀሚያ) ተብሎ የሚከፍለው/የሚፈሰው የገንዝብ መባከን ነው። ይህን ለማስረዳት አንድ ምሳሌ ልጠቀማና፤ አንድ ጊዜ በርከት ያሉ ለገበሬዎች የሚሰጡ ምርጥ የዘር በጎች ተገዝተው ወደተፈለገበት ቦታ ጭኖ ለመውሰድ አንድ የግል የጭነት መኪና (Isuzu) ተከራየን። መክፈል የሚገባን የገባያ ዋጋ 1,800 (አንድ ሺህ ስምንት መቶ) ብር መሆን ሲገባው፤ ለነጋዴው 6,000 (ስድስት ሺህ) ብር ተሰጠው። ታዲያ ይህን ያህል ገንዘብ የተከፈለው የመኪና ነጋዴ በተዘዋዋሪ ለአለቆቻችን ያካፍል ይሆን፤ ወይስ ገንዘቡ የግል ስላልሆነ ነው እንደዚያ የሚረጨው? ድርጊቱ ሁለቱም ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ሁለቱም ጥፋት ነው። የመጀመሪያው ሙስናውና ከሱም ጋር ተያይዘው የሚመጡት የፖለቲካ፤ የኤኮኖሚና የባሕል የተወሳሰቡ አባዜዎች ሲሆኑ፤ ሁለተኛው ድርጊት በተናጠል ሲታይ ደግሞ ሀገሪቱን ወጥሮ ለያዛት ግሽበት ችግር አባባሽ ነው። ይህንን ጉድ በአርባ ምንጭ ዞን በኮምባ ወረዳ ከታዘብኩ በኋላ ወደ ሌላ ቦታ ለተመሳሳይ ሥራ ተዘዋወርኩ። ቦታው ወደ አዋሳ ቀርብ ያለ፤ በሲዳማ ዞን ቦርቻ ወረዳ ይባላል። እዚም ሆኘ እያየሁት ያለው ተመሳሳይ ጉድ ነው። በተጨማሪም፤ በዚህ አካባቢ አንድ ጊዜ የአህያና የፈረስ ጋሪዎች ከአዋሳ ከተማ ተሠርተውና ተገዝተው ለገበሬዎች እንዲሰጡ የሚያደርግና በተግባር ላይ የዋለ ፕሮጀክት ነበር። ነገር ግን ገበሬው እነዚህን ጋሪዎች ሲረከብ፤ ከተገዙበት ዋጋ ከ400 እስከ 500 ብር ድረስ ተጨምሮበት ነው። 500 ጋሪዎች ተገዝተው ሲታደሉ በዓይኔ አይቻለሁ። ይህንን ፕሮጀክት የቀረፀውም፤ በሥራ ላይ ያዋለውም ገንዘብ ያዡ ነው። ገበሬው ጋሪ ባያስፈልገውም፤ ወይም የጋሪው ብዛት ጥቅሙን ዋጋ-ቢስ ቢያደርገውም፤ የከብኔ አባላት ችግራቸው አይደለም። ለገበሬው ችግር አዋቂውች እነሱ ብቻ ስለሆኑ የገብሬው ሃሳብ ወይም ፍላጎት ከቁጥር አይገቡም። ቁም ነገሩ ግን በዚህ የጋሪ ማደል ፕሮጀክት ቢያንስ ወደ 200,000 (ሁለት መቶ ሽህ) ብር ለግል ጥቅም ስለሚሰበሰብ፤ በዚህ አንድ ፕሮጀክት ብቻ 16 የሚሆኑት ተባባሪ የካብኔ አባላት መካፈላቸው ነው። ከሥር ያሉት ደግሞ የሚካሄድውን ሙስና እንዳያጋልጡ፤ ከ20 እስክ 30 የሚሆን የቀን አበል ይጻፍላቸውና አፋቸው ይሸበባል። በነገራችን ላይ እኔ የአንድ አምስት የካብኔ አባላት መኖሪያ ቤቶችን ጎብቸ ነበር። የቤቶቻቸው ውበት ምን ልበለዎ! አንዳንዶቹም እስከ አምስት ቤት ድረስ እንዳላቸውም ተገንዝቤአለሁ። ብዙና ትርፍ ቤቶች አላችሁ እንዳይባሉም፤ ትርፍ ቤቶቻቸውን በልጆቻቸው ስም እንዲመዘገቡ ያደርጋሉ።
3. በሄድኩበት ወረዳ ሁሉ በግብርናው ጽ/ቤት ሆነው የሚሠሩት አብዛኞቹ (ሁሉም ማለት ይቻላል) የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት አስተማሪዎች፤ ከሌሎቹ የሥራ ባለድረቦቻቸው ጋር ሲመጣጠኑም ብቃት ያነሳቸው፤ ይህንኑም ችሎታ/ብቃት ማነስ የተገነዘቡ፤ ነገር ግን በጋለ ምጣድ ላይ ሆኖ እንደሚቆላ ነገር ምላሳቸው የሚንጣጣ አፈኞች ናቸው። አንዳቸውም የግብርና ሙያ የላቸውም። እኔ እንደሚመስለኝ፤ አሁን ለተፈጠረው የእህል ዋጋ መናር እንደነዚህ ያሉት በደሎች ሁሉ ተጨማምረው ነው። ፖለቲካውም እንደዚህ አላግባብ በሆነ መልክ በከበሩ፤ ጥቂት ነቀርሳዎች ተወጥሮ ነው የተያዘው።
4. የገጠሩን ጉዳይ በዚህ ላይ ላቑምና በከተማው፤ በተለይ በአዲስ አበባ እያጋጠመን ያለውን ችግር በጥቂቱ ላካፍለዎ። እኔ እኖርበት በነበረው አካባቤ በሳምንት እስከ 5 ቀናት ድረስ መብራት ይቋረጣል። እንዳው ችግሩን ዘርዝሮ መግለጽ ስለማይቻል፤ እስቲ አንዳንዱን ልበል። በርካታ የቤተሰብ አባላት ያሏቸው ሰዎች ሥጋ ገዝተው ቤተሰቦቻቸውን በአንድ ሙሉ ኪሎ ሥጋ መመገብ ስለማይችሉ አንዱን ኪሎ ሥጋ ለ3 ሲቃረጡ ይታያል። ሁለት ጊዜ በልቶ ማደር ብርቅ እየሆነብን ነው ብለው የነገሩኝ ብዙ ናቸው። አንድ ጊዜ ብቻ በልቶ የሚያድረውን የሕብረተሰብ ክፍል ፈጣሪ ይወቀው። የጤፍ እንጀራን በዓመት አንድ ጊዜ እንኳ ያልቀመሰ ሰው እየበረከተ መምጣቱንም ተግንዝቤአለሁ። ከጥቂት አመታት በፊት አንድ “ደረቅ እንጀራ ይሸጣል?” ተብሎ ይጠየቅ የነበረው አሁን ያ ቋንቋ ተለውጦ “ደረቅ ምሳ ይሸጣል?” በሚል ተቀይሯል። ወጥ ከተጨመረበት ከአቅም በላይ ሰልሚሆን! በአንፃሩ ግን፤ ቡና ቤት ገብተው ውስኪያቸውን የሚያንቆረቁሩ፤ ምግብ ቤት ገብተው ጮማቸውን የሚቆርጡም አሉ። እንደነዚህ ያሉትን ጥጋበኞች የትካሻ/ጫንቃ ማበጥ የተመለከተ ሰው፤ የተራቡትን 5 ሰዎች ሊሸከም ይችላል ብሎ ማሰብ ይችላል።
ኤንግዲህ ሕዝባችን እንደዚህ ባለ የርሀብ አቸፈር እየተቆላ ነው “ጀግናው መሪያችን” ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ አይናቸውን ፍጥጥ፤ እያደረጉ፤ “ኢኮኖሚአችን በ 11.8% አድጓል” ብለው ሲናገሩ፤ በሰሙትም ሆነ ባልሰሙት ጉዳይ ላይ ሁለት እጃቸውን በጣም ከፍ አድርገው አውጥተው (ማጨብጨባቸው እንዲታወቅላቸም ይሆናል) የፓርላማ አባላት ሲያጨበጭቡላቸው፤ አቶ መለስ መነጽራቸውን ከፊታቸው ወረድ-ቀና፤ በእጃቸው ከፍ-ዝቅ እያደረጉ በጋለ መልክ ሲናገሩ ይታያሉ። ይህ እየሆነ እያለ፤ በአንፃሩ ደግሞ በርሀብ የተቆላው ሕዝብ አንጀቱ፤ እርር ይላል! በነገራችን ላይ የ97ቱን ምርጫ አስገድፎ የተመረጡት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትም የጭብጨው ውድድር ተካፋይ ስለሆኑ፤ በጭብጨባው ያላቸው ፉክክርና ትብብር አሳፋሪ እንዳይሆን ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ተብሎ በሰፊው ይነገራል። ማስጠንቀቂያውም፤ “ማጨብጨባችሁን ቀጥሉበት፤ ነገር ግን እንደበፊቱ ሳይሆን፤ ትንሽ የሚባለውንም እያዳመጣችሁ አድርጉት” ተብለዋል ነው የሚባለው።
እንግዲህ በአዲስ አበባ (እኔ እዚያ እንደነበርኩም ሆነ አሁን) በከተማው ሕዝብ የሚባለውን፤ ከእርሰዎ ሙያ ጋር የሚስማማውን ትንሽ ብየ ልጨረስ። ኢኮኖሚያቸውን በ11.8% ያሳደጉት የ”ጀግናው መሪያችን” መለስ ዘናዊ እውቅና በጣም እየናረና እየገነነ መጥቷል። በዚህም የተነሳ ተፈላጊነታቸው በዝቶ “ጀግናው መሪያችን” ግን የሚያናግሯቸውን ሰዎች ለመምረጥ ተገደዋል። የኢትዮጵያን ኤኮኖሚ 11.8% ያሳደጉት፤ ይህንንም በድፍረትና በመደጋገም የተናገሩትን “ጀግና” ለማናገር ተሠልፈው ከየሚገኙት መካከልም፤ የሀገራቸው ኤኮኖሚ ያሽቆለቆለው፤ የምዕራብ አገሮች ታላላቅ መሪዎች- አቶ ኦባንም ጨምሮ እንዲሚገኝ እየተነገረ ነው ያለው። እነዚህም የታላላቅ አገሮች መሪዎች እንደዚህ የደቀቀውን ኤኮኖሚያቸውን ለማቅናት ደፋ-ቀና እያሉ ከሚኳትኑ፤ እልቁንስ በ12% የሀገሩን ኤኮኖሚ እያሳደገ ያለውን “ጀግናውን የኢትዮጵያ” መሪ ጥቂት ደቂቃዎች ባልሞላ ጊዜ አማከረው መፍትሄ ቢያገኙ አይሻላቸውም? ይባልና፤ እንዳውም አንዳንዶቹ፤ ታወቅን የሚሉ የኤኮኖሚ ጠበብቶችም፤ የኤኮኖሚ እድገት ትምህርታቸውን ከልሰው እውቀታቸውን ለማዳበር “ከጀግናውና ከታላቁ የኤኮኖሚ ምሁር”- ከአቶ መለስ ለመውሰድ፤ ቦታው ሳይሞላ ተራቸውን ቢይዙ/ቢመዘገቡ ይሻላቸዋል! ብለው በድፍረት የሚናገሩም አልጠፉ።
አዎ፤ ይገባኛል! “የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ቀመሩ ተዥሞልሙሎ የተሠራው በነ አቶ መለስ መኝታ ቤት ስለሆነ፤ የእነዚህ የታላላቅ አገሮች መሪዎች ሕዝብ ይህንን ሲያውቅ፤ እንደሚቆጣባቸው፤ ከሥልጣን አሽቀንጥሮም እንደሚጥላቸው የአዲስ አበባ ሕዝብ እንዴት ይህንን ማሰታዎስ አቃተው?” ብለው ይጠይቁኝ ይሆናል። ቁጣን ካነሱማ፤ ከኛስ ሕዝብ ምን ቀርቶ። በወያኔ ካድሬ እየተገረፈ፤ እየተቃጠለ ያለ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ አንድ ቀን መገንፈሉ ይቀራል ብለው አያስቡም? በአገራችን አነጋገር፤ “ቡና እንኳ እሳት ላይ ብዙ ከቆየ መገንፈሉ አይቀርም” ይባል የለ?! ፈጣሪ ይርዳን።
በሌላ ርዕስ በሌላ ጊዜ እስከምንገናኝ እስከዚያው ቸር ይገጠመን።
አማረ ማሞ።
አንባቢ ሆይ፤
ከሚደርሱኝ ደብዳቤዎች መካከል ይቺ የአቶ አማረ ማሞ ደብዳቤ በገጠሩ አንሠራፍቶ ያለውን የፖለቲካና የኤኮኖሚ እውነታ ያንፀባረቀች ስለሆነች፤ አቶ አማረ በፋክስ የላከልኝን በእጅ የተጻፈ የስምንት ገጽ ደብደቤ እንደገና በኮምፑተር ጽፌ (ታይፕ አድርጌ) ለማካፈል ወስንኩ። የዚች ፀሀፊ ደብዳቤ ወደ ገጠሩ ወስድ አድርጎን፤ እየሆነ ያለውን ለሌሎቻችን ከማቅረቡም በላይ፤ ለምሳሌ፤ “ድጎማ” ተብሎ የሚሠጠው “እርዳታ” ምን እንደሚመስልና የሚያደርሰውን የለማኝነትና የጥገኝነት ስሜት አባዜ፤ አሁን የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች እንደሚነግሩንም፤ “ድጎማው” የፖለቲካ መጠቀሚያ መሆኑን፤ በገለማው ሙስና የከብሩና እየከበሩ ያሉ ግለስቦች እንዳሉ፤ በሕዝብ ሕይዎት የሚጫወት የአውሬነት/አረመኔነት ጠባይ ያለው የሕበረተሰብ ክፍል (ክላስ) እንደተፈጠረ፤ ለ”ድጎማ” ተብሎ የሚሰጠው ገንዘብ ለግሽበቱ አንዱ ምክንያት እንደሆነ፤ ወ.ዘ.ተ. ያሳያል።
ምስጋና ለአቶ አማረ ማሞና ኢትዮጵያን ወጥሮ እያብጠለጠላት ስላለው ሙስና መረጃን ለምትልኩልኝ ሁሉ!
I can be reached at africanstudies@murraystate.edu or
Seid.hassan@murraystate.edu.



What can i say the corruption is every where in the country. Because of that all the people who is involving on this end up loyal to woyane party. Now a day honest business people who refused to be corrupt will go bankrupt while the corrupt business man getting richer and richer. Every body is dependent on woyane’s corruption money to survive. OH God please give us and show us answer for suffering people???????????????????