“የኢትዮጵያ የባህር በር መሰናክሎች ሻቢያና ህወሓት ናቸው” - አቶ ገብሩ አስራት ከኢትዮሚድያ ሪፖርተር (መቀሌ)
“የኢትዮጵያ የባህር በር መሰናክሎች ሻቢያና ህወሃት ናቸው” በማለት የገለጹት አቶ ገብሩ አስራት “ሕሊናየን ሽጨ ይቅርታ ብጠይቅ ከአባይ ፀሀዬና ሀሰኝ ሽፋ የበለጠ ስልጣንና ገንዘብ ላገኝ እችል ነበር ….ነገር ግን ለእኔ ይህ አያስፈልገኝም ከህንጻና ከገንዘብ ይልቅ ለእኔ ነጻነቴ ይበልጥብኛል” ሲሉም ያላቸውን ህዝባዊ አቋም ጨምረው ያረጋገጡት የቀድሞው የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንትና የዓረና ትግራይ ሊቀመንበር ይህን የገለጹት በአዲግራት ከተማ ለተሰበሰበው ህዝብ ባደረጉት ንግግር ላይ ነው።
አቶ ገብሩ አስራትና የሥራ ባልደረቦቻቸው በሕወሓት በብቸኝነት ተጠርቅሞ የተዘጋውን የትግራይ ክልል የፖለቲካ ትኩሳት በተቃውሞ የፖለቲካ ዘርፍ ያለውን ሂደት እንዲገነዘብ እያነቃቁትና ነብስ እየዘሩብት ይገኛሉ።
ሕወሓት በኃይል ጨምዶ የያዘው የትግራይ ህዝብ ከገባበት የፖለቲካ እስር ቤት ሊላቀቅ የሚችልበትን የፖለቲካ ሥራ በማከናወን ላይ የሚገኘው ዓረና ትግራይ የክልሉ ህዝብ ወደ ስብሰባ እንዳይገባ ባለስልጣናት ቀድመው ቢያስፈራሩት፣ እገዳ ቢጥሉበትምና የሆነ ያልሆነ ምክንያት እየፈጠሩ መሰናክል ቢያዘጋጁም ህዝቡ ግን አሁንስ በቃ የሚል መልስ በመስጠት ወደ ስብሰባ አዳረሾቹ በመገኘት የቀረበለትን አማራጭ የፖለቲካ ሂደት በስፋት በመከታተል ላይ ይገኛል።
በዚህ ረገድ ባለፈው ታህሳስ 4፣10 እና 11 ቀን 2002 ዓ.ም በሽሬ በማይጨውና በአዲግራት ከተሞች ዓረና ትግራይ በጠራው ታላቅ ህዝባዊ ስብሰባ ያሳየው ተሳትፎ በበቂ መረጃነት የሚጠቀስ ነው። በትግራይ ክልል እየተዘዋወረ የፖለቲካ ሥራ በማከናወን ላይ ለሚገኘው የዓረና ትግራይ ድርጅት ባለስልጣናት የስብሰባው ተሳታፊዎች ድርጅቱ ግልጽ እንዲያደርግላቸው የሚፈልጉትን ጥያቄዎች በባለቤትነት ስሜት ሲያቀርቡ ተስተውሏል። በአዲግራት፣ በማይጨውና በሽሬ ከተሞች የተደረጉት ስብሰባዎች ሶስት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ያነጣጠሩ ሀሳቦች ነበሩ የተስተናገዱት ማለት ይቻላል።
ሀ/ የስብሰባው ተሳታፊዎች በቅንነት ላይ ተመስርተው ማወቅ የሚፈልጓቸውን ሀሳቦች እንዲብራሩላቸው የቀረቡ ጥያቄአቸው፣
ለ/ አቶ ገብሩ አስራት ከህወሃት ጋር ሲሰሩ በነበረበት ወቅት ስለሰሩት ሥራ የሚሰማቸውንና ለምን ጥለው እንደወጡ ብሎም ከወጡ በኃላ የሚከተሉት ፖሊሲ ፣
ሐ/ የህወሀት ደጋፊዎችና አባላት በስብሰባዎች ሰርገው በመግባት ዓረና ትግራይን ለማሳጣት የቀረቡ ጥያቄወች ነበሩ።
ምንም ይሁን ምን ለቀረቡት ጥያቄዎች በዓረና ትግራይ ባለስልጣናት የተሰጠው መልስ ግን የሰከነና ሚዛኑን የጠበቀ ነበር። በቅድሚያ ታህሳስ 11 ቀን 2002 ዓ.ም በአዲግራት ከተማ በተደረገ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ስብሰባውን የመሩት አቶ ገብሩ አስራት ሲሆኑ እኔ እንደታዘብኩት ይላሉ አንድ የስብሰባው የቅርብ ተመልካች “ወደ ኣዳራሹ ለመግባት ሰዎች ሲመጡ የከተማው ከፍተኛ ካድሬ ኣቶ ተክላይ ሃድጉ ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ህዝቡ ወደ ኣዳራሽ እንዳይገባ ሲከለክል አይቻለሁ። የህዝቡ ስሜት ደግሞ የባለስልጣኖቹ ማገድ ሙከራ ሳይበግራቸው በአዳራሹ ከ800 በላይ ተሰብሳቢ ነበር። አቶ ገብሩ ወደ አዳራሽ ሲገቡ በስብሰባ ኣዳራሽ የነበረው ሕዝብ ከወንበሩ በመነሳት በጭብጨባና በእልልታ ተቀበላቸው”።
በስብሰባ ወቅት የተነሱት ጥያቄዎች መካከል ስለ ኤርትራ ጉዳይ፣ ስለ ትእምት (EFFORT)፣ ስለ አቶ ገብሩ ግል ጉዳይ፣ ስለ ረሃብ፣ ቀይባህር ተፈጥሮ የቸረን የኢትዮጵያ ድንበር ነው፤ ወድብ አልባነታችን እንዴት ሊቀለበስ ይችላል? የመጭዋ ኢትዮጵያ እድል ምን ይመስላል? የትግራይ ህዝብ እየተዋረደና እየተገፋ ነው ያለው። ኤርትራውያን ቢንቁን አይፈረድባቸውም፤ ምክንያቱም የትግራይ ህዝብ መሪ የለውም። እናንተ ከህወሀት ጋር እያላቹ ምን ሰርታቹ ነበር? ዲሞክራሲ በትግራይ ሽፋን ነው፡፡ ለምን ከህወሓት ለቀህ ወጣህ? ለምን ከትግራይ ህዝብ ጠላቶች ጋር ተሰለፋችሁ? እነ ዶክተር መራራ ጉዲና ለትግራይ ህዝብ ያላቸው ኣመለካከት እንዴት ነው? መድረክ የስነ ምግባር ኮድ ውይይት ለምን ረግጦ ወጣ? ይህ ማድረጉ ለህዝቡ ችግር ኣያመጣምን? ለሉኣላዊነት ያላችሁ አቋም ምንድን ነው? የዋጋ ግሽበትና የስራ ኣጥነት መፍትሄው ምንድ ነው? የጎልጎል ራያ ፕሮጀክት ለምን ተዘጋ? ትእምት የማን ነው? የትግራይ ህዝብ ነው ወይስ የህወሓት? ሃቁን ንገሩን? እነዚህና በ93 ዓ/ም የነበረው ክፍፍል አስመልክቶ ብዙ ተመሳሳይ ጥያቄዎች በተሰብሳቢው ሕዝብ ቀርበዋል።
አቶ ገብሩ ስለ ኤርትራ ጉዳይ ሲመልሱ አሁንም የኤርትራን ነፃነት እቀበላለሁ ካሉ በኋላ ነገር ግን በነፃነቱ ጊዜ የኢትዮጵያ ጥቅም ኣላስከበርንም፡፡ ኢትዮጵያ ያለባህር በር ኣስቀርተናታል። ይህም ስህተት ትልቅ ጠባሳ በህይወቴ አኑሮዋል፡፡ እኔ ይህንን በማድረጋችን ለኢትጵያ ህዝብ በይፋ ይቅርታ ጠይቄያለሁ፡፡ በህ.ወ.ሓ.ት ፓርቲ አመራር ላይ ያሉት ግን እስከ አሁን ለኢትዮጵያ ህዝብ ምንም አይነት ይቅርታ አልጠየቁም፡፡ አሁን ያ ሁሉ ችግር ቢያልፍም፣ አንድ ትልቅ ያልተወራረደ ሂሳብ አለን፡፡ ይኽውም ከኤርትራ ጋር የወደብ ጉዳይና የባህር በር ስናነሳ ዋናው ተቋዋሚያችን ህ.ወ.ሓ.ትና ሻዕቢያ ናቸው፡ እነሱም ጦርነት ናፋቂዎች፣ ፀረሰላም ሃይሎች እያሉ በቴሌቪዥን ይቀሰቅሱብናል ያልሆነ ስም ይለጥፉብናል። እኔ የህወሃት አባል በነበርኩበት ወቅት ከትግል ጓደኞቼ ጋር በመሆን በኤርትራ ጉዳይ የምንከተለው ፖሊስና አመለካከት እንፈትሽ ስንል ነው ዋና የመለያየታችን ሁኔታ የተፈጠረው ብለዋል፡፡
ሕወሃት ውስጥ እያለሁ ፓርቲው ከፈፀማቸው ስህተቶች መካከል የምካፈላቸው የድንበር እና የወደብ ስሕተቶች ናቸው ሲሉም አረጋግጠዋል፡፡ የትግራይን ህዝብ 97 ምርጫ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ፓርቲዎች ሲሰድቡት ለምን አልተቃወምክም? ከትግራይ ህዝብ ጠላቶች ጋር ተባብረሀል ለሚለው ክስ ሊመልሱ፣ የትግራይ ህዝብ ዋና ጠላቶች እነ ኣዲሱ ለገሰ ናቸው፡፡ ምክንያቱም በክፍፍሉ ጊዜ ሕዝብና ካድሬዎችን ሰብስበው ከሕወሃት የወጡን የበላይ ኣመራር አካላት ለትግራይ ብቻ የሚያደሉ ናቸው፣ ብዙ ተጠቅመዋል፣ የኢትዮጵያ ንብረት ወደ ትግራይ አጓጉዘዋል፣ ለትግራይ ልዕልና የሚንቀሳቀሱ ናቸው በማለት ከቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊነጥሉን የዘመቱብን እነ አዲሱ ለገሰና ባለደረቦቹ ናቸው፡፡ በተቃራኒው የትግራይ ህዝብ ከየኢትዮጵያ ህዝብ እንዲነጠል እነመለሰ ዜናዊ ትልቅ ደባ ፈጽመውበታል በማለት መለስ ሲሰጡ በሰብሰባው የነበረው ህዝብ በጭብጨባ ድጋፉን ገልጿል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ስምንት ድርጅቶች ያቀፈ መድረክ በኢትዮጵያ ህብረ ብሄራዊ የሆነ ፓርቲ መድረክ መቋቋሙን በማስረዳት እነዚሀ ፓርቲዎች ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት በመቀበል በጋራ የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውና መድረኩም ለሚመጣው ምርጫ ለመወዳደር ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ለስብሰባው ተሳታፊዎች ሰፋ ያለ ማብራሪያ ተሰቷል። ማንኛው ዜጋ በነፃነት እንዲያስብና ለሃገሩ እንዲቆረቆር፤ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለሃገራቸው እንዲሰሩ የመድረክ ህልውና ትልቅ ኣስተዋፅኦ ኣለው ካሉ በኃላ ስለዚ ለአንድነታችንና ሉኣላዊነታችን ትልቅ ትኩረት እንደሰጡት በማብራራት የመጪውን ኢትዮጵያ ሁኔታ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሰተውበታል።
አቶ ገብሩ ማብራሪያቸውን በመቀጠል አንተ ህወሃት ውስጥ እያለህ ምን ሰርተህ ነበር ተብለው ለተጠየቁት ሲመልሱ ስሚንቶ ፋብሪካ፣ ኣልመዳ ጨርቃጨርቅ፣ መስፍን ኢንጂነሪንግ፤ ኣሁን በስራ ላይ ያሉ የትእምት /EFFORT/ ድርጅቶች ማን ነው ያቋቋማቸው? በማለት ተሰብሳቢዎቹን ከጠየቁ በኃላ ንግግራቸውን በማራዘም የሜድሮክ ህንፃ ሪፈራል ሆሰፒታል ማነው ያሰራው? የተከዜ ግድብ ማነው ጥናቱን ጨርሶ ያስረከበው? እኛ አቅደነው የነበረው እስከ ኣሁን ያልተሰራ የጎልጎል ራያ ፕሮጀክት፣ በዕዳጋ ሓሙስ (በኣዲግራት ኣከባቢ) ኣንድ ትልቅ የመሰትዋትና ብርጭቆ ፋብሪካ፣ ወልቃይትና ሸሬ የሽንኮራ አገዳ (ስኳር ፋብሪካ) ናቸው፡፡ ሲሉ የአሁኖቹ ባለስልጣናት እኮ ይላሉ በተቃራኒው የመቀሌ ስታዲዬምን እንኳን ሰርተው መጨረስ ያቃታቸው ናቸው ሲሉ አጣጥለዋቸዋል።
ለምን ከህ.ወ.ሓ.ት ለቀህ ወጣህ? አወጣጥህስ በተሃድሶ ምክንያት ነው ወይስ በሙስና? ለሚለው ደግሞ ፓርቲ ሃይማኖት አይደለም፤ እምነት ነው። በመሆኑም እኔ ያላመንኩበትን ነገር መፈፀም አልፈልግም፤ የህዝብ ጥቅምን ነው የማስቀድመው፡፡ ስለዚህ ህ.ወ.ሓ.ት የህዝብ ጥቅም አያስቀድምም፡፡ እኔ በህ.ወ.ሓ.ት ውስጥ ህሊናየን ሽጨ ህንፃና ብዙ ብር ስልጣንም ቢሆን አልፈልግም በማለት የልዩነታቸውን መሰረታዊ ባህሪ አብራርተዋል።፡፡
ህሊናየ ሽጬ በአንዲት ብጣሽ ወረቀት ይቅርታ ብጠይቅ ኖሮ ከአባይ ፀሃዬና ሃሰን ሽፋ የበለጠ ስልጣንና ገንዘብ ላገኝ እችል ነበር፡፡ ይቅርታ በልና ወደ ነበርክበት እንመልስህ ብለው ብዙ ሽማግሌዎች ልከውብኛል፡፡ በመኪና መሄድ መጠቀም ብፈልግ ኖሮ ይህ ለኔ በጣም ቀላል ነበር ነገር ለኔ ይህ አያስፈልገኝም ለእኔ ከህንፃና ገንዘብ ይልቅ ነፃነቴ ነው የሚበልጥኝ፡ ሲሉ ያላቸውን መሰረታዊ እምነት ከአስረዱ በኃላ ሰላማዊ ኖሮ መኖር ምን ያህል ነጻነት እንደሚያጎናጽፍ ሲያሰምሩበት አሁን እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ያለምንም ስጋት በታከሲና፣ በአውቶብስ እሄዳለሁ በማንኛውም ሆቴል አደራለሁ የህዝብ መገናኛ ቦታዎች ሁሉ እገኛለሁ በዚህም እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ ብለዋል፡፡
እነ ዶ/ር መራራ የትግራይ ህዝብ እንዴት ነው የሚያዩት በጥላቻ ነው ወይስ በጥቅም? ተብለው ለተጠየቁት እኔ ከመራራ ጋር በብዙ ጉዳዮች ዙሪያ ተነጋግረናል ስለ ትግራይ ህዝብ መጥፎ ነገር ሲናገር ሰምቼም አላውቅም መጥፎ ነገርም የሚናገር ሰው አይመስለኝም፡፡ ዶ/ር መራራ ስለ ኢትዮጵያ የሚቆረቆር እንጂ ጠባብ ፓለቲከኛ ኣይደለም፡ በማለት ለተሰብሳቢው አስረድተዋል፡፡ ትእምት/EFFORT/ የማነው ለሚለው ሲመልሱ የትግራይ ህዝብ ነው፡፡ ማንኛውም ህዝብ የየራሱ ድርሻ አለው፡ ስለሆነም አንድ ብርም ትሁን ሌላም የትእምት ብር መከፋፈል ካለበት ተከፍሎ ለማንኛው መድረስ አለበት የሚል እምነት አለኝ ብለዋል፡፡ የህ.ወ.ሓ.ት መሪዎች አሁን እየመሩትና እየመዘበሩት ነው ያሉት ድርጅቱን በሚመለከት፡፡ ዓረና ሲመሰረትም ይህንኑ እምነታቸን በፕሮግራሙ ቀርፆት ነበር ሆኖም ምርጫ ቦርድ ከልክሎናል፡፡ አሁን መደረግ ያለበት ንብረቱ የህዝብ ነው መመራት የሚኖርበትም ከፖለቲካ ገለልተኛ በሆነ አካል ሲሆን ይኽውም ከሕዝብ በተመረጠ ቦርድ አማካኝነት መሆን ይኖርበታል የሚል እምነት አለን ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
ከ93 ዓ.ም በፊት በኣዲግራት ሕንጻዎች እንዳይሰሩ ከልከላቹሀል ተብሎ ለተነሳ ጥያቄ ሲያብራሩ በቅድሚያ ህንጻ እንዳይሰራ የከለከልንበት ምንም ማስረጃ የለም፤ እንደዚህ ለማድረግም የሚያስችል ህሊና የለኝም፤ ጉዳዬን ሳስበው አንድ የአማርኛ አባባል ነው ያስታወሰኝ ይኽውም “አንካሳ የወረወረውን ፈረሰኛ አይደርስበትም” የሚለውን አነጋገር ምክንያቱም ይህን የሚያሰወሩት የከሰሩ ፖለቲከኞች ብቻ ናቸው። የሚያወሩት ሁሉ ተራ ነገር ነው እኔ ፓርቲውን ከለቀቅኩ በኃላ ያልተበለ ነገር የለም፡፡ ጥቂቱን ልጥቀስ የዓጋሜ ህዝብ የትግራይ ጉራጌ ነው፡፤ ዓጋሜ የኢትዮጵያ ለውጥ ነው፡፤ የሚሉ አባባሎች ሰምቻለሁ በቅድሚያ የዓጋሜ ሕዝብ በስሌት ከሆነ አሁን በድርጀቱ ኣመራር ላይ ካሉ አካላት የበለጠ የሚቀርበው ለእኔ ነው ስለሆነም ሆነ ተብሎ ከህዝብ ጋር ለማጣላትና ለማታለል ነው ይህን ነገር የሚያወሩት በማለት ነገሩን አጣጥለውታል።
በእርሻ በኩል ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው የጎልጎል ራያ ፕሮጀክት ለምን ተዘጋ ለሚለው ሲመልሱም፤ ይህ ፕሮጀክት ቀዳሚ ሃሳቡ የእኛ ነው ስለሆነም ከድርጅቱ ከወጣን እኛ ያቀድነው ሁሉ መወገድ ነበረበት በማለት ከጠቀሱ በኃላ የታገደውም በዚሁ ሰንካላ ምክንያትመሆኑን አሳውቀዋል። የጎልጎል ራያ የውሃ መጠን በቻይናና ህንድ ባለሙያዎች ሁለት ጊዜ መጠናቱንና ተመሳሳይ የሆነ መረጃም በሁሉም ጥናት መገኘቱን ጠቅሰው፤ የውሃ መጠኑ ሁለት ቢሊዮን ኩቢክ በላይ መገመቱን አሳውቀዋል። ስለዚህ ጎልጎል ራያ በስራ ላይ ቢውል ለትግራይና ለቀሪው ኢትዮጵያ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው የእርሻ ፕሮጀክት እንደነበር አስታውቀዋል፡፡
በሽሬ ከተማ በተደረገው ስብሰባ ላይ የኢሃዲግ መንግስት ነፃነታችንን እየነጠቀን ነው በማለት ንግግር የጀመሩት አቶ አስገደ ገ/ስላሴ የአረና ትግራይ ከፍተኛ የአመራር አባል ሲሆኑ፡፡ መድረክ ይሁን ዓረና ትግራይ ከኢሃዲግ ጋር ለመደራደር ባለ 10 ነጥቦች የያዘ ሀሳብ ማቅረባቸውንና ሆኖም ግን በኢሃዲግ የሚመራው መንግስት በምርጫ ስነ ምግባር ብቻ ነው እንጂ በነፃነት አልደራደርም ማለቱን አበክረው በመግለጽ። መድረክ ሆነ ዓረና ትግራይ በሀገራችን ነፃነት እንደሌለ ያረጋገጡት ጉዳይ ነው ካሉ በኃላ፡ በምሳሌነትም ሲያስረዱ፤ በማይጨው ታሕሳስ 4፤ በሽሬ ታሕሳስ 10 እና በዓዲግራት ታሕሳስ 11 የዓረና ፕሮግራሙና ፖሊሲዎች ለህዝብ ለማሳወቅ ህዝባዊ ስብሰባ ለማድረግ ከክልሉ አስተዳደር ፍቃድ ማግኘታቸውን በዚህ ረገድ ለተደረገው ትብብር ምስጋና አቅርበዋል። በመቀጠልም ይህ ድርጊት ግን ኢሃዲግ በአንድ በኩል ለዲሞክራሲ የቆመ ለመምሰል ሲሞክር በሌላ በኩል አፈናውን በማጠናከር ዓረናና ህዝብ እንዳይገናኙ ሁሉንም የአፋና መሳሪያዎች ተጠቅሟል ሲሉ አማረዋል፡፡
በማይጨው፤ በሽሬና በአዲግራት ያደረግናቸውን ስብሰባዎች ለማደናቀፍ ሰብሰባዎቹ ከመካሄዳቸው አንድ ቀን በፊት ማለትም በዋዜማው ለሽሬ እንደስላሴ ከተማ ህዝብና በዞኑ ለሚገኙ ወረዳና ገጠር ቀበሌዎች፤ አስተማሪዎች፤ ተማሪዎች፤ አነስተኛ ድርጅቶች፣ የሴቶች፣ የሃይማኖት መሪዎች፤ የወጣቶችና ነባር ተጋዮችን ለየብቻቸው ሰብስባ በመጥራት በዕለቱ ማንኛው ሰው እነሱ በጠሩት ሰብስባ ከቀረ አስፈላጊ ቅጣት እንደሚሰጥና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችና የስራ ዋስትና እንደማያገኙ በማስፈራራት፤ ለነዋሪዎች ደግሞ በየቤቱ ወረቀት በመስጠት በሚሊሽያና በድህንነት አባላትን በመጠቀም የአረና ትግራይ ድርጅት በጠራው ስብሰባ ህዝብ እንዳይገኝ የሚቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል በማለት አቶ አስገደ ድርጊቱን በዝርዝር አጋልጠዋል።
ከዚህም በተጨማሪ መንግስት የጠራውን ስብስባ ጥሶ ለሚመጣ ከከተማ ይሁን ከገጠር ቀበሌዎች የወረዳዎችና የቀበሌዎቹ ኣስተዳደር፤ ደህንነቶች፤ ፖሊስ፤ የሲቪል ልብስ የለበሱ ሚሊሽያ የሚባሉ ታጣቂዎች፤ ካድሬዎችን ጨምሮ የስብሰባ አዳራሽ በሩቅና በቅርብ በመክበብ ወደ ዓረና ስብሰባ የሚመጣውን ህዝብ ተመለስ እያሉ እያስፈራሩ እንደነበር ያከባቢው ትራፊክ ፖሊስ ሳይቀር በኣዳራሹ ስብሰባ ሊገባ የተሰበሰበን ህዝብ በመበተን ግልፅ የሆነ አፈና አካሂደዋል ሲሉ አጋልጠዋል፡፡ ያም ሆኖ ግን ይላሉ አቶ ኣስገደ ከሁለት መቶ በላይ ህዝብ በስብሰባው ሲሳተፍ ሌላው ህዝብ ግን ባዘጋጁት የህዝብ ስብሰባ በካድሬዎችና ሚሊሽያዎች እስከ ቀኑ ዘጠኛ ሰዓትና 12 ሰዓት ድረስ አስገድደውና ከበውት እንደዋሉ ዘርዝረዋል፡፡
ሌላው ደግሞ 10/4/2002 ዓ/ም ለስብሰባ ቅስቀሳ በምናደርግበት ወቅትም ወደ ሸራሮ የላክነው አባላችን አቶ አረጋዊ ገ/ዮሃንስ ከሽረ እንዳስላሴ 90 ኪ/ሜትር ርቃ በምትገኝ ሸራሮ ከተማ ላይ የዓረና ማኒፌስቶ የስብሰባ ጥሪ ደብዳቤዎች ለምን ለሰዎች ሰጠህ በማለት በአካባቢው የህወሐት ሲቪል ታጣቂ አማካኝነት ለፖሊስ እንደተሰጠ በመጨረሻም ለ3 ሰዓታት አስረው ያለአንዳች ይቅርታ መፈታቱንና፡፡ የተሰማራበት ተልእኮም እንዲሰናከል መደረጉን፡፡ በሌላ በኩልም ስብሰባ በተደረገበት ወቅት አቶ ሃዱሽ ዘነበ የሚባል የሸሬ ከተማ አስተዳደር ባለስልጣን፤ መዝገበ የሚባል ካድሬ፤ ኪዳነማርያም ብርሃነ የሚባለ የድምፂ ወያኔ ሰራተኛ፤ አደራጀው የሚባል የከተማው ፍትህና ፀጥታ ባልደረባ ህዝቡ ወደ ኣዳራሽ እንዳይገባ በዋናነት ሲከላከሉ መዋላቸውን፡ ከዚህም በተጨማሪ ስብሰባ ለመጥራት የለጠፍናቸው ወረቀቶች በካድሬዎቹ ተቀደዋል፤ በመኪና ላይ ሆነን ድምጽ ማጉያ በመጠቀም እየተዘዋወርን ቅስቀሳ ስናደርግ መኪና የተከራየንበት ግለሰብ ስልክ በመደወል እርምጃ አንወስድብሀለን እያሉ ኣስፈራርተውታል፡፡ ስፒከር የተከራየናቸው ሰዎች ለምን አከራያችሁ በማለት ሲዝቱባቸው ባለ ንብረቶቹ በፍራቻ ከስብሰባው ኣዳራሽ ድረስ መጥተው የተከራየነው ስፒከር ሊነጥቁን ሞክረው ነበር ከዚያም አልፎ ለፖሊስም ከስውናል ሲሉ የደረሰባቸውን መዋከብ ዘርዝረዋል፡፡
ከስብሰባው በፊትና በኋላ የነበረ ወከባና ማስፈራራት በጣም ብዙ ነበር ይላሉ አቶ ገብሩ አስራት የድርጅቱ ሊቀመንበር በበኩላቸው ከአክሱም ኣከባቢ ወደ ሽሬ ለስብሰባ ተሳትፈው የተመለሱ ኣቶ አያሌው በየኔ በታህታይ ማይጨው የዓረና ተጠሪ ማኒፌስቶ ለህዝብ አድለሃል ተብለው በደህንነትና በፖሊስ ታስረው ተደብድበዋል ለሶስት ሰዓት ታስረው ተለቀዋል፡፡ አቶ አያሌው የደረሰበትን የመብት ጥሰት አቤትቱታ ለማቅረብ ወደ ፖሊስና አቃቤ ህግ ሂዶ ክስ ቢያቀርብም ክስህን አንቀበልም በማለት ወደ መስሪያ ቤቱ እንዳይቀርብ አባረውታል፡፡
ጉዑሽ ገ/ፃድቅ የድርጅቱ ማእከላይ ኮሚቴ የሰሜን ምእራብ ዞን ተጠሪ ዓዲ ሃገራይ የምትገኘውን እህቱን ወንድምሽ የሽምጥ ተዋጊ (ድምሂት) የሚባል ድርጅት ተባባሪ ነው ፈንጂ ለማጥመድና የመንግሥት ሃብት ለማውደም አስቧል በማለት ካድሬዎች ከፍተኛ ወከባና ማስፈራራት ፈፅመውባታል ይህም እህቱን ለማስደንገጥና ለማስፈራራት እና ሽብር በቤተስብ አባላት ላይ ለመፍጠርና የታጋዮችን ሞራል ለመስበር የታቀደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ከዚህም ሌላ ከስብሰው በኃላ የሸሬ እንዳስላሴ የዓረና ፅ/ቤት ሃላፊ በሆኑት አቶ ሹሻይ አዘናው ወደ ቤተሰቡ ቤት በመሄድ ልጁን አባትህ በፀረ ህዝብ እንቅስቃሴ እየተሳተፈ ነው ይህንን እንቅስቃሴ እንዲተው ምከሩት ወይ እርምጃ ሊወሰድበት ነው በማለት ቤተሰቡ ለማስራራትና ለማስደንገጥ ሞኩረዋል በዚህም አልተገቱም ይላሉ አቶ ገብሩ አስራት መምህር ጉዑሽ ተስፋይ በኣስገደ ፅምብላ የሁለተኛ ደረጃ ኣስተማሪ ከዓረና ጋር የሚንቀሳቀስ ኣባላችን የሆነውን የወረዳው የትምህርት ቢሮ ሃላፊ ጠርቶው ማስጠንቀቂያና ዛቻ ኣድርሰውበታል፤ ለቤተሰቦቹንም እንዲታገስ ካልሆነ እርምጃ እንወስድበታለን የሚል ማስፈራርያ መልክት ተሰጥተዋል፡፡
በማጠቃለልም የተለያዬ ከተሞች የተደረጉት ስብሰባዎች ላይ ህዝቡ የተሰማውን ስሜት በግልጽ የገለጠበትና ማብራሪያ የሚያስፈልጉትን ጉዳዬች በመጠየቅ ከተሳተፈ በኋላ ከዓረና ትግራይ ድርጅት ጎን እንደሚሰለፍ አረጋግጧል ሲሉ አቶ ገብሩ አስራት ገልጸዋል።
ኤዲተር መላኩ ፀጋዬ መኮንን
ኢትዮሚድያ - ነፃ የህዝብ አስተያየት የሚንፀባረቅበት
ግንባር ቀደም የኢትዮጵያውያን ድረ-ገጽ ነው።



Wow! God bless you Gebru Asrat!
የወያኔ ተባባሪ ወይም ተመሳጣሪ የነበሩ ሰዎች; ጥፋታቸውን አውቀው; ለመስተካከል ልባዊ ፍላጎት ሲያሳዩ ማበረታታትና አክብሮ መቀበል የብልሕነት ዘዴ ነው:: የዚህም መሰረታዊ ጥቅም; ለቀድሞዎቹ ወያኔዎች; ኢሐድግ ከተገረሰሰ በሑዋላ በወንጀለኛነት ተጠይቀው ከመታሰርነት/ከመገደል;ቤተሰባቸውንም ከውርደት ሊያድና/ንላቸው ሲችል; የኢትዮጵያ ሕዝብም ጥፋታቸውን ያረሙ ግለሰቦች ከግል ጥቅማቸው በላይ ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም የሚሰሩ ሰዎች ሊያገኝ ስለሚችል ነው:: ቢሆንም; እንደነ ገብሩ አሥራት; ስየ አብርሃና ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ያሉ; ከወያኔ/ኢሐድግ ጋር በተባበሩባቸው ዘመናት ለፈጸሙዎቸው እጅግ ከባድ/አስጸያፊ ጥፋቶች/ወንጀሎች ባሁኑ ጊዜ ተጸጽተው በልባቸው እውነተኛ ለውጥ መስረጹን ለማረጋገጥ ተገቢ በሆኑ መስፈርቶች በመጠቀም መመርመር ያስፈልጋል:: ከነዚሁም መስፈርቶች ሊጠቀሱ የሚገባቸው;
(ሀ) ከዘረኛነት ይልቅ በኢትዮጵያዊነት የሚያምኑ መሆኑን ማረጋገጥ (በዚህ አጋጣሚ; ከላይ ስማቸው የተጠቀሱት ሶስት ግለሰቦች አሁንም የዘረኞች/የጎሳዎች ስብስቦች አባላት በመሆናቸው; አሁን የሚያንጸባርቁት አስተያየት; ለምሳሌ የገብሩ አሥራት ዓረና ትግራይ አባልነት; “አልሸሹም ዞር አሉ” ዓይነት ዘዴ ይመስላል::)
(ለ) እነዚህ ግለሰቦች በኢትዮጵያ ላይ ባደረሱዋቸው እጅግ ከባድ ውድመቶች; ለምሳሌ የኤርትራ መገንጠልና በዚህም ክፍተኛ ስሕተት ምክንያት; ሐገራችን ለዓረቦች (በጅቡቲ አማካኝነት) በየዓመቱ 1 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እየገፈገፈች ስለ መሆኑዋ; ክኤርትራና ከሱማሊያ ጋር በተከናወኑት የማያስፈልጉ ጦርነቶች ስለ ተሰዉት ከ100,000 በላይ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን; መሬትን የመንግሥት የግል ሐብት በማድረግ የኢትዮጵያን ሕዝብ በጪሰኝነትና በድሕነት አረንቁዋ ፍዳውን እንዲያይ ማድረጋቸው; ሥልጣናቸውንና ጥቅማቸውን ለማካበት; ዲሞክራሲና ፍትሕ በሌለበት ሥርአት በእሥራት; በአንግልት; በግድያ ስለ ተጠቁት ዜጎች; ብልሹ በሆነ የኢኮኖሚ ስልት በመጠቀማቸው 14 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በረሐብ አለንጋ እየተሰቃዩ ስለ መሆናቸው; እጅግ ሁዋላ-ቀር በሆነ ሥልት በመጠቀም ከፍ ያለ የአየርና የአካባቢ ብክለት በማስገኘት ስላስከተሉት ጠንቅ ሁሉ; የሐገራችንን አንጡራ ሐብትና መሬት ለሌሎች ሐገሮች; ለምሳሌ ለሱዳን; ለግል ጥቅም ብቻ; አሳልፈው ስለ መስጠታቸው; ወዘተ; ወዘተ; ስሕተቶቻቸውን አምነው የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ መጠየቅ;
(ሐ)ለወደፊቱም; ከተመሳሳይ ከባድ ጥፋት እንዲገለሉ ቃል መግባት ብቻ ሳይሆን; በዚሁ እጅግ ከባድ ጥፋት ተዘፍቀው የኢትዮጵያን ሕዝብ እያሰቃዩ ያሉትን; በመከላከያ; በፖሊስ; በጸጥታና በመሳሰሉት የሚገኙትን እንዲሁም ቀንደኞቹን አነመለስ ዜናዊን; ሥዩም መስፍንን; አባይን; ሳሞራን; ወዘተ; በወንጀለኛነት ከመያዛቸው በፊት ከማያዛልቅ የጥፋት ጎዳናቸው እንዲመለሱ ያልተቆጠበ ጥረት ለማከናወን ዝግጁ መሆናቸውን ማረጋገጥ;
(መ) ሐገራችን ኢትዮጵያ; ዲሞክራሲ; የሕግ የበላይነትና ፍትሕ; አንድነት; ልማትና ጸጥታ የስፈነባት እንድትሆን ያልተቆጠበ ጥረት የሚያደርጉ መሆኑን ማረጋገጥ;
እና በሌሎችም ተጨባጭ ውጤት በሚያስገኙ መስፈርቶች በመጠቀም እነዚህ የቀድሞ የኢሐድግ ተጠቃሚ የነበሩ የኢትዮጵያ ጠላቶች መታረማቸውን በማረጋገጥ ጥሩ የሐገር ዜጋዎች እንዲሆኑ ማድረግ ለዘለቄታው ብሔራዊ ጥቅም የሚያስገኝ ብልሕነት የተላበሰ ዘዴ ነው::
ውንድም ወገኒ ድንቅ ብለሃል!ዳሩ ግን ዲሞክራሲን ማስፈን ማለት የትላንት ስህተትን በዛሪ ይቅርታ ማለፍ ካልሆነ መገለጫው ምንድን ሊሆን ነው? ይትላንቱ ቅንጅት እንዳሸነፈ ወያኒ ስልጣኑን ቢለቅ ኖሮ መለስ በኢትዮጵያ በነጻነት ይኖር እንደነበር አታውቅም? ዳሩ ግን እድሉን ባለመጠቀሙ የአኢትዮጵያ ህዝብ ቀርቶ ዓለም ይቅር የማይለው ስህተት ሰራ:: እነገብሩ ና ስየ ግን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ይቅርታ በመጠያቅ ራሳቸውን ከህዝብ ቀላቀሉ::አዎ እንደኒ እምነት ይቅርታ መጥየቅ በሰሩት ስህተት መጸጸት ይመስለኛል, ስለዚህ ቢያንስ እነ መለስ የትግራይን ህዝብ ከሊላው ኢትዮጵያዊ እንደለዩት እንዳይቀሩ የጀመሩትን የትግራይ ህዝብ የፖለቲካ አማራጭ ሆነው ከሊሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር ይቀጥሉ ዘንድ እሰየው እንበላቸው::
Yes, the Tigray People needs change.STOP these ignorant rulers of the region.
ወገኒ አንተ ማን ነው ዳኛ ያረገህ?
Every time change for every thing
ውድ “Anonymous”,
ፋይዳ ከሌለው ጥያቄህ/ሽ ይልቅ የቀድሞዎቹም ሆኑ ያሁኖቹ የወያኔ ግፈኞች የግል ጥቅምና ሥልጣን ከማካበት የኢትዮጵያን ሕዝብ ወደ ማክበርና ወደ ማገልገል አድራጎት እንዲያዘነብሉ ለማድረግ ጠቃሚ የሆኑ ሀሳቦችህ/ሽን ብታካፍል/ይን! በነገራችን ላይ; በተለመደ ግድፈት “ን”ን ረሳህ/ሽ:: ስለዚህ ያንተ/ቺን ማንነት አልጠይቅም!
ውድ ወገኒ ጥሩ ብለሃል ከላይ የጠቀስካቸውን ሰዎች ማመን ከባድ ነው ትናንት ሲገሉን ሲያደሙን ያገራችንን ጥቅም አሳልፈው ሲሰጥኡ ቆይተው ዛሬ አለንልሕ ሲሉ አያፍሩም?ይቅር ማለት ባሕላችን ቢሆንም ያልጠረጠረ ተመነጠረ ነው ክባድ ጥንቃቂ ያስፈልጋል(የወያኔ ታክቲክ ሊሆን ይችላል)ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር
@ባልቻ
አቶ ገብሩ የህወሓት ባለስልጣን በነበሩበት ጥፋት አጥፍተው እንደነበሩ ይናገራሉ አሁንስ ምን ዋስትና አለንና አምነን ልንከተልዎት እንችላለን?
አቶ ገብሩ አስራት የተናገሩትን እና ትግራይ ክፍለ ሃገር ውስጥ ያለውን ትግሬ አስተሳሰብ ካነበብኩ በኋላ በሁኔታው በጣም ቅር ተሰኝቻለሁ
1. ትግራዮች ሌሎች ጎሶች ይጠሉናል እያሉ ደጋግመው ጠይቀዋል, አቶ ገብሩ አስራት ግን ለዚህ ጥያቄ ተገቢ መልስ አልሰጡም
ትግሬዎች ያን አይነት ጥያቄ ሲያነሱ ወድያው ጠያቂ ትግሬዎችን ለምን የሚጠሉዋችሁ ይመስላችኋል ብለው ጥቃቄያቸውን በጥያቄ መመለስ ይገባቸዋል
ሌሎች ጎሶች ትግሬዎችን ቢጠሉ አይፈረድባቸውም, ያንን ትግሬዎችን መንገር ተገቢ ነበር እስከነ ምክንያቱ
ኢትዮጵያን የሚገዛው አምባገነን ከሃዲ እና ዘረኛ የወያኔ መንግስት ትግሬን እወክላለሁ ነው የሚለው, ኢትዮጵያዊ ህጻናትን እና ሴቶችን የጨፈጨፉት አጋዚዎች በሙሉ ትግሬዎች ናቸው,
በየዩኒቨርስቲው ሌላውን ጎሳ የሚሰልሉት ትግሬዎች ናቸው, ኢትዮጵያ ውስጥ ቁልፍ ቁልፍ ስልጣን የያዙት ትግሬዎች ናቸው, በስራ በከፍተኛ ትምህርት በንግድ ወዘተ ትግሬዎች ያልሆኑት
ከትግሬዎች ጋር እኩል እድል የላቸውም ወዘተ
እና ይህን ሁሉ አቶ ገብሩ አስራት ጠቅሰው ትግሬዎችን እወክላለሁ የሚለው ህወሃት ኢትዮይጵያዊያን ላይ ታላቅ ወንጀል እየሰራ እንደሆነ ጠቅሰው ይህ ጨቋኝ ስርአት እንዲፈርስ ትግሬዎች ከማንም በላይ አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚገባቸው ትግሬዎቹን መንገር ነበረባቸው
EFFORT ን በሚመለከት የተናገሩትም ትክክል አይደለም
EFFORT የትግራይ ጎሳ ንብረት ሊሆን አይችልም ምክንያቱም ገንዘቡ ሁሉ ከሌሎች የተዘረፈ በመሆኑ
አቶ ገብሩ አስራት ወያኔ የኢትዮጵያን ድንበር ለሱዳን ስለመስጠቱ,መለስ ግብጽን የአባይ ባለቤት መሆኗን ስለመስማማቱ, መለስ መሬት ለውጭ ዜጎች በርካሽ ስለመሸጡ ወዘተ ምንም የተናገሩት ነገር የለም ሆኖም እንደዛ አይነት የወያኔ ወንጀሎችን በየስብሰባው እየደጋገሙ መጥቀስ ግዴታቸው ነበር በተለይ ለትግራይ ሰዎች
ይህም ትግሬዎች ለህወሃት የሚሰጡትን ድጋፍ እንዲቀንሱ ይረዳል
“ለምን ከትግራይ ህዝብ ጠላቶች ጋር ተሰለፋችሁ?” እንዲህ አይነት ጥያቄ ትግሬዎቹ ማንሳታቸው ትንሽ ያስገርማል
ሌሎች ብለፉት 20 አመታት በትግሬዎች የተገደሉት,የታሰሩት,የተዋረዱት,እና ሌላም ጉዳት የደረሰባቸው ጎሳዎች ትግሬን በጅምላ አንጠላም ሲሉም ሲባሉም እየተሰማ እኒህ ሌላው ጎሳ ላይ ብዙ ግፍ የፈጸሙት ትግሬዎች ለምን ሌሎች ጠሉን ብለው ጥያቄ ማንሳታቸው እና ጥፋታቸውን
እስካሁን አለመገንዘባቸው እና ሌሎች ጎሳዎችን ይቅርታ አለመጠየቃቸው እነሱ በህወሃት ፕሮፓጋንዳ ምን ያህል እንደታወሩ ያሳያል
ትግሬዎች እዚህ ቦታ ለምን ይህ አልተሰራም እዚያ ለምን ይህ አልተሰራም ብለው ሲጠየቁ አቶ ገብሩ ትግራይ የሌሎችን ክፍለ ሃገሮች ንብረት እየዘረፈች መሆኑን አልተናገሩም,
ትግራይ ምንም እንኳ ድሃ ወይም ለሃገሪቱ የምታደርገው አስተዋጽኦ በጣም ትንሽ ቢሆንም ባለፉት 19 አመታት ከሁሉም ክፍለ ሃገሮች የበለጠ ገንዘብ የፈሰሰባት ሀገር መሆኗን እና ሌሎች
ክፍለ ሃገሮች የትግራይን 1/10 የሚሆን እንኳ ገንዘብ እንዳልፈሰሰባቸው መጥቀስ ይገባቸው ነበር
ኤርትራም መገንጠሏን አሁንም ትክክል ነው የምለው ያሉትን እኔ እቃወማለሁ,
ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት አልነበረችም, ይህን ሃቅ ማንም ህጻን ሊረዳው ይችላል
ሰለ ክልሎችም ምንም አልተናገሩም
ትግራይ ከጎንደር እና ወሎ በሃይል ነጥቃ ሰለ ወሰደችው መሬት
ወያኔ ኢትዮጵያን እየከፋፈለ ሃገሪቷ ውስጥ ብጥብጥ አለመተማመን እና ጥላቻ እያስፋፋ መሆኑንም ለትግሬዎች አልተናገሩም
በአጠቃላይ ተቃዋሚ ሃይሎች ትግራይ ክፍለ ሃገር ሄደው ወያኔ ሰለሚሰራቸው ወንጀሎች ጥፋቶች ወዘተ መናገር መቻላቸው ጥሩ ነው, ትግሬዎችን ከሌላው ተቃዋሚ ሃይሎች ጋራ እንዲቀላቀሉ ይረዳል, የ መተላለቅ አደጋን ይቀንሳል ወያኔም እንዲወድቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል
ሆኖም አቶ ገብሩ አስራት እላይ በቀረበው ሪፖርት ላይ ማየት እንደምንችለው ያገኙትን አጋጣሚ በአጥጋቢ ሁኔታ አልተጠቀሙበትም
ምናልባት ወደፊት ይሻሻሉ ይሆናል ብለን እናምናለን
እና ትግሬዎች የግድ በስማቸው የሚጠራው ህወሃት ወይም ወያኔ ኢትዮጵያ ላይ እየፈጸመ ስላሉት
ወንጀሎች ሊነገራቸው ይገባል::