ለ እህቶቻችን ልንደርስ የምንችልባቸው ኣምስት መንገዶች! ገለታው ዘለቀ

October 15th, 2012 ይመይሉ ይመይሉ ያትሙ ያትሙ

በኣረብ ኣገራት ለግርድና የሚሄዱትን እህቶቻችንን የሚደርስባቸውን ስቃይ መናገር መነሻዬ ኣይደለም። ያልፍልኛል፣ እናት ኣባቴን እጦራለሁ እያሉ ወደ ሊባኖስና ሌሎች የኣረብ ገልፍ ኣገራት የሚጎርፉት እህቶቻችን ከሰባዊነት ደረጃ ዝቅ ብለው ሲሰቃዩ ሌላው በተለያየ የኣለም ክፍል ያለው ኢትዮጵያዊ ከንፈሩን ከመምጠጥ ያለፈ ብዙ ነገር ሲያደርግ ኣይታይም። እግዚኣብሄር ይባርካቸውና የተለያዩ ሰባዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የቻሉትን ሁሉ እየታገሉ ነው። ግን ኢትዮጵያዊው የበኩሉን ለመወጣት ከማንም በላይ የሞራልም የዜግነትም የውዴታ ግዴታ ኣለበት።

የዛሬው ጽሁፌ በሌላው ኣለም ያለው ኢትዮጵያዊ ምን ሊያደርግ ይችላል? በሚል ተግባራዊ ዘዴዎችን ለመጠቆም ነው።
በመሆኑም ለእህቶቻችን በሚከተሉት መስመሮች ልንደርስላቸው እንችላላን።

1) ለወገን ለሃገር ተቆርቋሪ በሆኑ ኢትዮጵያዊያን የተቋቋመው ኢሳት ቴሌዚዥን ድርጅት በኣፋጣኝ መቀመጫውን ሊባኖስ ያደረገ የሪፖርተር ቡድን ሊልክ ያስፈልጋል። ይህ ቡድን በየጊዜው የሚደርሰውን በደልና እንግልት እየዘገበ በማጋላጥ ችግራቸውን ሊቀንስ ይችላል። ኣንዱ ትልቁ ችግራቸውም በየሜዳው እየሞቱ ወደ ሚዲያ ስለማይወጣ ነው። ይህ ቡድን በየጊዜው በሚያደርገው ኢንቬስትጌቲቭ ሪፖርት ለኣለም ኣቀፉም ሆነ ለ ኢትዮጵያዊያን ያሳውቃል። ኣንዱ ችግር የኢንፎርሜሽንም ነው። ባለፈው እህታችን ኣለም ደቻሳ የሞተች ጊዜ ነው ትንሽ የተደናገጥነው። ያ ወደ ሚዲያ ስለወጣ እንጂ ሚዲያ ሳያውቃቸው የሚገደሉ የሚሰቃዩ ብዙ ናቸው።

ባለፈው የ ሂውማን ራይት ዎች ባውጣው ዘገባ ላይ እንደሚያሳየው በየ ሳምንቱ ኣንድ የቤት ውስጥ ሰራተኛ ተፈጥሮኣዊ ባልሆነ መንገድ ይሞታል። እንግዲህ ልብ በሉ በሊባኖስ ውስጥ ወደ 200 ሺህ የሚጠጋ የቤት ውስጥ ሰራተኛ ያለ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ከ 60 እስከ 70 ሺህ የሚሆኑት ኢትዮጵያዊያን ናቸው። ይህ ማለት በየ ወሩ ሁለት የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ወይ ተገለው፣ ወይ ታመው ፣ወይ የሚያሳክማቸው ኣጥተው፣ ወይ ራሳቸውን እንዲያጠፉ ተገደው ይሞታሉ ማለት ነው። ከዚህ የከፋ ነገር የለምና ኢሳት ባስቸኩዋይ ደርሶ ወገንተኛነቱን፣ ኢትዮጵያዊነቱን ማሳየት ኣለበት።

2) በ ኣሜሪካን ኣገር ኣዲስ የተቋቋመው የሴቶች መብት ድርጅት ኣስቸኳይ የቤት ስራው ሊሆን የሚገባው የህግ ባለሙያ የያዘ ኣንድ ቡድን መላክ ነው። በርግጠኝነት ለመብታቸው ለሚሟገት በደላቸውን ወደ ብርሃን ለሚያወጣ ድርጅት ወጪውን እንደሚሸፍኑ እምነቴ ጽኑ ነው። ከሚያገኙዋት ጥቂት ገንዘብ ላይ እያዋጡ ወጪውን ሊሸፍኑ ስለሚችሉ ድርጅቱ በባጀት በኩል ስጋት የሚገጥመው ኣይሆንም። የተጨነቁ እህቶች ኣለን የሚላቸው ካገኙ የሚከፈለውን መስዋእትነት ይከፍላሉ። እነዚህ እህቶች ከ ኤምባሲ ያጡትን የምክር ኣገልግሎትና ፍቅር ይህ ለመብታቸው የቆመ ድርጅት ይክስላቸዋል።

3) ለሲቪክ ማህበራትና ለ ፓለቲካ ድርጅቶች።
ለግርድና የሄደችው እህታችን ስትሰቃይ ዛሬ ስትገደል ከንፈራችንን እየመጠጥን ችግሩ የሚፈታው የችግሩ ምንጭ የሆነው ኣምባገነን መንግስት ሲወገድ ነው ማለት ኣግባባ ኣይደለም። እሱን ማን ኣጣው? ኣሁን በመሃል ግን ድምጻቸው ታፍኖ ተዘልለው የሚያነቡትን እህቶች ኣይዙዋችሁ ማለት ግፋቸውን ማጋለጥ በርግጥ የህዝብ ፍቅር ያለው ድርጅርት ተግባር ነው ። የነሱን መከራና ግፍ ለፓለቲካ ፍጆታ መጠቀም ፈጽሞ ሊሆን ኣይገባም። በመሆኑም ሁለቱም ኣይነት ድርጅቶች በመገናኛ ብዙሃኖቻቸው ይህን በደል ማውጣት ማሳየት ሰላማዊ ሰልፍ ማቀድ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ሌላው ደሞ ለዚህ የዳረጋቸውን ኣስከፊ ስርኣት ለመለወጥ እንዲችሉ ሊያደራጁዋቸውም ይገባል።

4) ሌላው ከፖለቲካው ተገልሎ ያለው ኢትዮጵያዊ በሙሉ በያለበት ድምጹን በተለያየ መንገድ ማሰማት ኣለበት። በፌስ ቡክ በሰልፍ ወዘተ. ተቃውሞውን ማሰማት ኣለብት። ኣንዲት ኣረብ ኣገር የምትኖር እህታችን በስሜት ስትናገር እህቶቻቸውንና ሴቶቻቸውን ኣውጥተው ለግርድና የሰጡ ወንድሞች እንደ ኢትዮጵያዊያን ኣላየሁም ብላለች። ድሃ ኣገር እኛ ብቻ ኣይደለንም ግን እንደኛ ሴቶች ለግርድና ሄዶ የሚሰቃይ የለም ብላለች። በመሆኑም ኣለማቀፋዊ ተቃውሞ በማድረግ እህታችንን ልንደገፍ ይገባናል።
እነዚህ ከፍ ሲል ያነሳሁዋቸው ነጥቦች በውነት በጣም ቀላል ልንሰራቸው የምንችላቸው ናቸው።

እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!

  1. Mussa Keder
    | #1

    Mr Geleta Zeleke you are right my brother we must stand together.

  2. ተንቤን
    | #2

    ሆድ ካዘነ ዕምባ አይገድም አይደል ነገሩ::እኔ በዚህ ሀሳብ ሙሉ በሙሉ የስማማ ስሆን በአሰራር ደረጃም አመች ይሆናል የምለውን ለመጠቆም እወዳልርሁ:
    1 ከተወሰኑ ሲብክ ማህበራት የተውጣጡ የአገር ልጆችና ባለሙያዎች ያሉበት ቡድን ይመሥረትና እነሱ በሚችሉት መንገድ በአረብ አገራት የሚኖሩና ተቀጣሪ እህቶቻችንን ማግኘትና ማደራጀት የሚቻልበት መንገድ የፈጠር:ማለትም የስልክና የመኖሪያ አድራሻ እርስበርስ እንዲለዋወጡና ከቡድን አባላትም ጋር ተዋውቀው አድራሻ መለዋወጥ እንዲችሉና አንዷ የሌላው ፈጥኖ ደራሺ ወሬና ዜና ነጋሪ መሆናቸውን ማስረዳት::
    2 ለራሳቸው ደህንነት ሲባል ተባብረው በየወሩም ሆነ በተወሰነ ጊዜ ለችግር መፍቻ የሚሆን ገንዘብ በሚፈልጉት አይነት ማሰባሰብ እንዲችሉ መምከር:;
    3 በተለያዩ ሀገሮች የሚሰሩት ተሰባስበው ከተዋውቁ በኋላ; አጠቃላይ በአረብ አገሮች ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያን ማህበር ለመመስረት እንዲችሉ መምከርና መርዳት::
    4 የሚሰበስቡት ገንዘብ በአጭበርባሪ ግለሰቦች እንዳይበላ አስቀድመው በመጠንቀቅ እንዴትና የት ማስቀመጥ እንደሚፈልጉ በደንብ እንዲያስቡበት ማስገንዘብ::
    ወገኖች ሁሉም ነገር ሃላፊና ቀሪ ነው:በነዚህ እህቶቻችን ላይ የሚደርሰው በደልና ግፍ ክብደቱንም አሳዝኝነቱን አስከፊነቱን በትክክል ሊገልጸውና ጉዳዩን በገሃድ ለወገን ማስረዳት የሚችል የታወቀና ታላቅ ደራሴ ቢሰራው ውስብስብነቱንና አሰቃቂነቱን ለመግለጽ ከአቅሙ በላይ እንደሚሆንበት እኔ አንገቴን እሰጣለሁ::ለትወሰኑ ቀናት ያለምንም ሥራ የሚሄዱትን ዜጎች ብዛትና ሁኔታ ለማየት ብቻ እዛች ያልታደለች የፓስፖርት ቢሮ ፊትለፊት ተቀምጨ;ወይ እግዚአብሄር ያልኩበትን ዕለቶች መቸም ቢሆን አልረሳቸው::ያን ያክል የበዛ የሴቶች ልጆች ክምችት አይቸ አልውቅም::በተለይ አንዷዋ ኦሮሚ ክልል በመዲሲን ዲፕሎማ ያላት አንድ ልጂ የወለደች; ሌላው ከአዲስ አበባ የታውቀ የግል ተቋም የጨረሰች;አጋጣሚው ፈቅዶልኝ ስንጨዋወት ምነ እናንተ እኮ የተማራችሁ ናችሁ ምነው? አልኳችው;;;አይ —አንዷ እህቴ መልስ የሚገርመኝ- ነበር–”ምነው ነገር ለማዋጣት ነው ወይስ ችግሩ አልታህ ብሎ” አለችኝ? ነገር አዋጣጭ አለመሆኔን በትክክል ተረድታኝ በችግሩ ዙሪያ ብዙ አወራን::አረብ አገር ያውም ለግርድና ለመሄድ; የአገሯ ልጆች ከ25-30ሺህ ብር በድለላ ይበሏት ልጂ ነች::
    ወኖቸ ይቻላል እንተባበር ወሬ ነጋሪና ተከታታይ ቡድን እናቋቁምላችው::

  3. ጉረኞች
    | #3

    አቶ ገለታው
    ይህ በጣም የሚደገፍ ሓሳብ ነው:: በተለይም ኢሳት ትልቅ አስተዋጾ ይኖረዋል ብየ አስባለሁ:: ለዚሕ ስራ ብቻ ማለትም ከአረብ አገር ለሚንቀሳቀስ የኢሳት ጣብያም ይሁን ሪፖርተር የሚውል ገንዘብ ማሰባሰብ ለኢሳት ቀለል ያለ ስራ ሊሆን ይችላል:: መታስብ ያለብት ግን ሪፖርተሩም ይሁን የኢሳት ጣብያ የሚመራው ያገሬው ሰው ማለትም በፖሊስ ይሁን በአገር ህግ ጠባቂዎች የሚደርስብትን ጥቃት መቅዋቅዋም የሚችል ይሆንበታል:: አለም አቀፍ ወቀሳን የሚያስነሳ ስለሆነ ጥቃቱ ቀላል አይሆንም::

  4. ዲጎኔ ሞረቴው
    | #4

    እነዚህ እህቶቻችን የሚደርስባቸውን ኢሰብአዊ ጥቃት ለሰላም ደጋፊ ሃይሎና መብት አስከባሪዎች ማሳወቅ የሁላችን ሃላፊነት ነው::ያለው መንግስትም ለስራ ወደውችህ የሚሄዱ ወገኖቻችን መብታቸው እንዲከበር የማስደረግ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ማሳሰብም ያስፈልጋል::በህግወጥ መንገድ የሚሄዱትን ደግሞ እንዲሁ መብታቸውን እንዲያስከብሩ በሚቻለው ማገዝ ያስፈልጋል::\
    እዚህ አምድ ላይ በግርድና የሚለው ትሰያፍ አባባል መታረም መቀየር አለበት

አስተያየት መስጫው ተዘግቷል።