ገደብ የሌለው ድንቁርና ! ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

September 18th, 2016 ይመይሉ ይመይሉ ያትሙ ያትሙ

መግቢያ

ካለፈው ህዳር ወር ጀምሮ እስከ ዛሬ ነሃሴ ወር ድረስ በአገራችን ምድር በህዝባችን ላይ አንድን አገር አስተዳድራለሁ ከሚል፣ ከዘጠና ሚሊዮን በላይ የሚቆጠርን ህዝብ ብቻ ሳይሆን፣ የሚቀጥለውንም ተከታታይ ትውልድ ህይወትና ዕድል የሚወስን አገዛዝ በጭፍን የሚያካሂደው ጭፍጨፋ፣ መደብደብና ማሰቃየት፣ እንዲሁም ካለምንም ማስረጃ እስርቤት ውስጥ መክተት አብዛኛዎቻችንን ያንገበግበናል፣ ያስለቅሰናልም። ማንኛውምን ከህዝብ ወገን የሚነሱ ቅሬታዎችን አዳምጦ በሰላም ማስተናገድና መፍታት እንደ መሞከር ይልቅ አገዛዙ ሆን ብሎ የያዘው ህዝብን ማስፈራራት፣ ማንገላታት፣ መግደልና፣ የተቀረውን ደግሞ እስርቤት ውስጥ መወርወር ሆኗል።

ባለፉት 25 ዓመታት ይህ አገዛዝ ጸባዩን እንዲያሳምር፣ ህብረተሰብአዊ ባህርይ እንዲኖረውና፣ የህዝብን ቅሬታዎችና የሚደርስበትን በደል ሰላማዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ እንዲያስተናግድ ያላደረግነው ጥረት ይህ ነው አይባልም። ከሌሎች ሁለት አገዛዞች ጋር ሲወዳደር ይልቅ ይህንን አገዛዝ በተቻለ መጠን እሹሩሩ በማለት ጸባዩን በማሳመርና ህዝባዊ ባህርይ ኖሮት የህዝብ ቅሬታዎችን በስነስርዓት እንዲያስተናግድ ሁላችንም በመሰለን መንገድ ድምጻችንን አሰምተናል። በአብዛኛዎቻንንም ዘንድ እንደዚህ ዐይነቱን ሰላማዊና የማስተማር መንገድ እንድንከተል ያስገደደን፣ አንድም ስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ በታሪክ አጋጣሚ ሆኖ ከአንድ ብሄረሰብ የተውጣጣ በመሆኑ ትግላችን ወደ ማይሆን መንገድ እንዳይሄድ ለማድረግ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ ባለፈው 40 ዐመታት ህዝባችን ብዙ ስቃይንና ፈተናን የቀመሰ ስለሆነ ያለው አማራጭ መንገድ ሌላ ሳይሆን በማስተማርና በመቻቻል ላይ የተመሰረተ ሰላማዊ ትግል ከማካሄድ በስተቀር ሌላ አማራጭ ሊኖር አይችልም ብለን በመገንዘባችንም ጭምር ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ከብዙ አገሮችና ከአገራችንም ልምድ እንዳየነውና እንደተማርነው ከጦር ትግል ይልቅ በአርቆ አስተዋይነትና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ትግል ለአንድ ህብረተሰብ ዕድገት አማራጭ የሌለው ዘዴ መሆኑን በመረዳታችን ነው። ከተለያየ አካባቢና ብሄረሰብ የመጣንና የተለያየ ቋንቋ የምንነጋገርም ቢሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ ሁላችንንም የሚያስተሳስሩን ብዙ ነገሮች አሉ። በታሪክ ሂደት ውስጥ እየተዋሃድንና አንድ ሁላችንንም የሚያግባባ ቋንቋ፣ ኋላችንንም የሚያስተሳስረን ባህል፣ የምግብ ዐይነት፣ የአለባበስ ዘዴና ሌሎች ልዩ ልዩ ነገሮች የሁላችንም መግለጫ እየሆኑ የመጡበትን ሁኔታ እንመለከታለን። ስለሆነም የአንድን ህብረተሰብ ህግ ሂደት ካለመረዳት የተነሳ ባለፉት መቶ ዐመታት በተለያዩ አገዛዝ ጭቆናዎችና በደሎች ቢደርሱም ከህብረተሰብ ምስረታና ከሳይንስ አንጻር ልንክደው የማንችለው ሁኔታ ተፈጥሯል። ይኸውም ኢትዮጵያን እንደ አገራችንና እንደ አንድ ወጥ ህብረ-ብሄር፣ ይሁንና ግን ደግሞ የተለያዩ ብሄረሰቦችን ያቀፈች መሆኗን አምነን የተቀበልን ብዙዎቻችን ነን። ይሁንና ግን ይህ ያልተዋጠላቸውና ጊዜን የሚጠባበቁ ኃይሎች አጋጣሚን በመጠቀም እነሱ ከሌሎች ጋር ሲወዳደሩ በታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ መልክ ከፍተኛ ወንጀል እንደደረሰባቸው በማውራትና፣ በወጣቱና በተከታዩ ትውልድ ጭንቅላት ውስጥ በመትከል አንድ ህዝብ መስራት ያለበትን ታሪካዊ ስራ እንዳይሰራ አድርገውታል፤ እያደረጉትም ነው። ተጠራጣሪ በማድረግ በራሱ ላይ ዕምነት እንዳይኖረው እያደረጉ ነው። የህብረተሰብ ህግና ዕድገት አስቸጋሪ ሁኔታ ባለማጤን ወጣቱ የዝቅተኛ ስሜት እንዲኖረው የሚሆነውን የማይሆነውን በማውራት መተባበርና መከባበር እንዳይኖር አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ፈጥረዋል። በዚህም አካሄዳቸው በወንድማማች ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ጥላቻንና አለመተማመንን ፈጥረዋል። ለውጭ ኃይሎች የተገዙና ልዩ ተልዕኮዎች ያላቸው ይመስል ሆን ብለው የያዙት ስራ አንዱን ጎሳ ከሌላው ማጋጨትና ደም እንዲፋሰስ ማድረግ ነው። በሃማኖትና በጎሳዎች መሀከል የባሰውኑ ክፍፍል እንዲኖር በማድረግ ህዝባችን በዘለዓለማዊ ፍጥጫ ውስጥ እንዲኖር የማይሰሩት ሰይጣናዊ ስራ የለም።

ከዚህ ስንነሳ የወያኔ አገዛዝ ስልጣን ላይ ከወጣበት እስከዛሬ ድረስ ኢትዮጵያችንን እንደ አገሩ፣ ህዝባችንን እንደ አካሉና ስልጣን ላይ ያለ ኃይልም በመሆኑ የታሪክና የህዝብ ግዴታ እንዳለበት በፍጹም የተገነዘበ አይመስልም። ተጠሪነቱ እሱን አምነው ለሚከተሉት ጥቂት አጎብዳጆችና ለውጭ ኃይሎች ይመስል ባለፉት ሃያ አምስት ዐመታት በታሪካችንና በህዝባችን ላይ በቀላሉ ሊቀረፍ የማይችል በደል ሰርቷል፤ ዛሬም እየሰራ ነው። ህዝባችንና አገራችንን መሳቂያና መሳለቂያ አድርጓል። እንደ አንድ የገዢ መደብ የአገራችንን ብሄራዊ ነፃነታችንን ከማስከበርና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ አገር ለመገንባት ማንኛውንም ጥረት ከማድረግ ይልቅ ከውስጥ ተዳክማ በውጭ ኃይሎች በቀላሉ እንድትጠቃ ያላደረገው አገርን የማዳከም ስራ የለም። ይህንን አካሄዱን እንዲያርም ያላደርግነው ጥረት ይህ ነው አይባልም። ይሁንና ግን አገዛዙ የባሰውኑ በማምረር አገርን በማዳከምና፣ ህዝብን በመበደልና በማሰቃየት ገፍቶበታል። እንዲያውም ተፋለሙኝ በማለት የራሱን የግል ጦር በመመስረት ከህዝብ ጋር ግብ ግብ ለማድረግ ተዘጋጅቷል። ባለፈው ህዳር ወርና አሁን ደግሞ በያዝነው ነሃሴ ወር የሚታየው የአገዛዙ ድርጊት ይህ አገዛዝ በፍጹም ከስህተቱ ሊማር እንደማይችልና፣ የህዝባችንን ቅሬታ፣ በተለይም የወልቃይትን ጸገዴንና በኦሮሞ ክልል የተከሰተውን ተቃውሞ በአጠቃላይ ጦርነት ለማዳፈን ወይንም ለመደምሰስ የተዘጋጀ መሆኑን ነው። በተጨማሪም በነሃሴ 15 ፣ 2008 አዲስ አበባ ላይ ሊደረግ የታቀደውን የእንቢ በይ የቀይ ካርድ የይዞ መውጣት ሰልፍ አስመልክቶ ጥሪውን ለማክሸፍ ያሰማራው እስከ 120 000 የሚጠጋ ወታደር የሚያረጋግጠው አገዛዙ የቱን ያህል አረመኔያዊ እንደሆነና ወደ ፋሺስታዊ ድርጊት እያመራ መሆኑን ነው። ይህ አካሄዱና ጠቅላላው ዝግጅቱ ያንን አካባቢ ብቻ የሚመለከት ሳይሆን ጠቅላላውን ህዝባችንንና የአገራችንን የወደፊት ዕድልና ዕድገት የሚመለከት ስለሆነ ዝምብለን ልናልፈው የምንችለው ነገር አይደለም። ስለሆነም አገዛዙንና የውጭ ኃይሎች አገራችንን የማዳከምና የመከፋፈል ህልምና ዕቅድ ማክሽፍ አለብን። ለዚህ ደግሞ የግዴታ ከመቼምውም የበለጠ በአንድ ርዕይ ስር በመሰባሰብና ኃይላችንን በማጠናከር የግዴታ የአገራችንን ክብር ማስመለስ አለብን። የአገር መቆራረስና መከፋፈል፣ እንዲያም ሲል በህዝባችን ላይ የሚደርሰውን በደልና ግድያ ዝም ብለን ማየት የለብንም። አገራችንን ከጥፋት የማዳን ታሪካዊና የትውልድ ግዴታ አለብን።

ሰውን ከእንስሳ የሚለየው ምንድነው ?

ለመሆኑ ዝም ብለን ከመኖር በስተቀር በህይወታችን እኛን ከእንስሳ የሚለየን ምንድነው ብለን ጠይቀን እናውቃለን ወይ? የኑሮአችንን ትርጉምና ዓላማ ለመረዳት እየደጋገምን ጥያቄዎች እናነሳለን ወይ? በተለይም ፖለቲካ የሚባለው ነገር ከሰው ህይወት፣ የኑሮው ፍልስፍናና የአኗኗር ዘዴ ተነጥሎ በሚታይበት ዓለም ውስጥና፣ ጥቂት ጉልበተኞች የብዙ ሚሊዮንን ሰዎች ዕድል በአሉታዊም ሆነ በአዎንታዊ መንገድ በሚወስኑበት ዓለም ውስጥ የሰውን ልጅ ትርጉምና ያሉትን ባህርያቶች እያነሳ የሚጠይቅ በፍጹም ያለ አይመስለኝም። ከዚህም በላይ ከአርቆ-አስተዋይነት ይልቅ ስሜታዊነት ሁሉንም ነገር በሚወስንበት ዓለም ውስጥ የሰውን ልጅ ሚናና የህይወቱን ትርጉም እየመላለሱ የሚጠይቅ የለም። የሰው ልጅ ጭንቅላት ብዙ ውስጣዊ ባህርያት ቢኖሩትም፣ ሰው እንደመሆኑ መጠን እነዚህን ውስጣዊ ባህርያት የሚጠቀም በጣም ጥቂቱ ብቻ ነው። ስለሆነም አንዱ ሌላውን ሲንቀውና ሲያንቋሽሸው፣ ካለምንም ምክንያት እንደጠላት አድርጎ ሲቆጥረውና ሲያሳድደው፣ እንዲያም ሲል የሚኖርበት አካባቢ ለእሱ ብቻ የተፈጠረች ይመስል በጉልበቱ በመመካት ሁሉንም ነገር ቀምቶ ወደ ድህነት ዓለም ውስጥ ሲገፈትረው፣ እነዚህና አያሌ ነገሮች የአንዱ ደስታ የሌላው ስቃይ ሆነው እንደ ተፈጥሮአዊ ህግ በሚወሰዱበት ዓለም ውስጥ የሰውን የማሰብ ኃይል ጉዳይ እየመላለስን እንድንጠይቅ እንገደዳለን።

ሁሉም ሰው በእግዚአብሄር አምሳል ነው የተፈጠረው ተብሎ በሚሰበክበት ዓለም ውስጥና፣ ይህም ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ያለውና፣ በየአገሮች ህገ-መንግስት ተቀባይነት አግኝቶ የሰፈረ ቢሆንም፣ ጥቂቶች ጊዜው የኛ ነው ብለው የየአገራቸውን ህዝቦች ዕድል እነሱ በሚረዱበትና በሚፈልጉት መንገድ በሚወስኑበት ዘመን የሰው ልጅ እግዚአብሄር የሰጠውን ልዩ ልዩ ባህርያት እንዳይጠቀም ተገዷል። ከዚህ ስንነሳ ባለፉት አስር ወራት በአገራችን ምድር የተከሰተውና በአገዛዙ ያላግባብና ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ በህዝባችን ላይ የሚፈጸመው የግድያ፣ የአፈና፣ የማሰርና የማሰቃየት ድርጊቶች የግዴታ እነዚህን መሰረታዊ ጥያቄዎች እንድናነሳ እንገደዳለን።
ዛሬ በአገራችን ምድር የተከሰተውን ሁኔታ አብዛኛዎቻችን ከስርዓት መበላሸትና ከዲሞክራሲ እጦት ጋር ነው የምናያይዘው። በመስረቱ ግን ሁኔታውን ጠለቅ ብለን ማየት ያለብን ይመስለኛል። ባለፈው አርባ ዐመታት በአገራችን ምድር የተከሰተውን አስቀያሚ ሁኔታ በዲሞክራሲ እጦት ምክንያት ነው ብለን የምናሳብብ ከሆነ ለተወሳሰበው የአገራችን ችግር በፍጹም መፍትሄ የምናገኝ አይመስለኝም። በእርግጥ ዲሞክራሲያዊ መብቶችና ለህዝባችንም የሚስማማ ስርዓት መፈጠርና መዋቀር ያለባቸው ይመስለኛል። ይህ ጉዳይ እስከዚህም ድረስ የሚያጣላን አይመስለኝም። ጥያቄው ግን ለምንድነው ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዳንገነባ ያልቻልንበት ምክንያት? በተለይም ስልጣን ላይ የተቀመጡ ሰዎችም ሆነ ቡድኖች ለምድንነው ዲሞክራሲን አጥብቀው የሚጠሉት? ለምንድነው የሰው ልጅ ህይወት የቅንጣትም ያህል የማይሰማቸው? ብለን እየደጋገምን መጠየቅ ያለብን ይመስለኛል። በተለይም መንግስትና አገር የጥቂት ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች የግል ሀብት ሆነው በሚቆጠሩበት እንደኛውና በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ተራ ዲሞክራሲያዊ መብቶች በራሳቸው ትርጉም አይኖራቸውም። ስለሆነም የነገሩን ውስብስበነት ከዲሞክራሲ ባለመኖር ባሻገር ማየት ያለብን ይመስለኛል። ወደ ዋናውም መሰረተ-ሃሳቤ ልግባ።

ሰው ለመሆናችን በሚታየው አካላችን ብቻ የሚወሰን አይደለም። ሰው መሆናችን በአለን አካልና ሁሉንም ነገር አጠቃሎ በያዘው ጭንቅላታችን የሚወሰን ነው። ይህም ማለት የፈለግነውን ያህል ብናምር፣ ብንወፍርና ጉልበትም ቢኖረን፣ እንዲያም ሲል በሀብት የናጠጥንም ብንሆን የማሰብ ኃይላችንን መጠቀም እስካልቻልን ድረስ ከእንስሳም እምብዛም የምንለይ አይደለንም። በመሆኑም፣ ወደድንም ጠላንም፣ ተጠቀምንበትም አልተጠቀምንበትም የሰው ልጅ ልዩ ልዩ ባህርዮች አሉት። እነዚህም፣ አርቆ-ማሰብ፣ ሎጂካሊ ማሰብና አዲስ ነገር መፍጠር፣ ወይም ለሚታዩ ችግሮች መፍትሄ መሰጠት፣ ኮመን ሴንስ፣ ንቃተ-ህሊና(Potentially)፣ ኢንቲዩሽን፣ መሰማት(feeling)፣ ርህሩህነት፣ ማመዛዘን፣ መፍጠር መቻል፣ ኢንተለጀንስ፣ ምህራዊነት(በማንበብና በትምህርት የሚገኝ፟)፣ በጥልቀትና በሰፊው ማሰብ፣ ስነ-ምግባርነትና ግብረ-ገብነት፣ ማህበራዊነትና ህብረተሰብአዊ ኃላፊነት መሰማት… ወዘተ፣ እነዚህ ሁሉ አብረወን የተፈጠሩና በጭንቅላታችን ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ይሁንና ግን እነዚህ በጭንቅላታችን ውስጥ ያሉ ፖቴንሺያሎች ቢሆኑም ሊዳብሩና እያንዳንዱ ግለሰብ ራሱን ተገንዝቦ ህብረተሰብአብዊ ኃላፊነትን ሊቀበልና ህብረተሰቡን ሊለውጥ የሚችለው ጭንቅላቱ በትክክለኛ ዕውቀት ሲኮተኮት ብቻ ነው። ጭንቅላት በመጥፎ ነገሮች ተበርዞ አካባቢውንም ሆነ ጠቅላላውን ህብረተሰብ እንዳይመርዘውና እንዳያናገው ከተፈለገ አገርንና ህብረተሰብን የሚያፈርሱ አዳዲስ ሁኔታዎች በሚፈጠሩበት ጊዜ የእነዚህን ምክንያቶችና አመጣጣቸውን አጥንቶ ለመዋጋት ይቻል ዘንድ አዕምሮ የግዴታ በትክክለኛ ዕውቀት መኮትኮት አለበት። አዕምሮ የረጋ ባለመሆኑና፣ በሚሆኑ በማይሆኑ ነገሮች በመታለል ከትክክለኛውን ፈር ስለሚወጣ በየጊዜው መታደስ አለበት። ለዚህ ነው ሶክራተስ ሰውነታችን ለመንቀሳቀስና ለመስራት ጅምናስቲክ እንደሚያስፈልገው ሁሉ፣ ጭንቅላትም እንደዚሁ ጂምናስቲክ ያስፈልገዋል የሚለው። በተጨማሪም ሶክራተስ እንደሚያስተምረን የሰው ልጅ ህይወት መፈተን አለባት። ራሱን እንዲገነዘብና ህብረተሰብአዊ ኃላፊነትን ለመሸከም እንዲችል የግዴታ ህይወቱ ከአስቸጋሪ ሁኔታ ጋር መለማምድ አለባት። በሌላ ወገን ደግሞ ጭንቅላታችን ብዙ ጥሩ ፖቴንሺያሎች ቢኖሩትም እዚያው በዚያው ጭንቅላታችን አረመኒያዊ ባህርይ፣ ስግብግብበት፣ መቸኮል፣ አርቆ-አለማሰብ፣ ሎጂካል በሆነ መልክ ማሰብ አለመቻል፣ ስሜታዊነት፣ ህብረተሰብአዊ ኃላፊነት አለመሰማት… ወዘተ. በጭንቅላታችን ውስጥ ያሉ እጅግ አደገኛ ባህሪያችንና በየቀኑ የሚፈታተኑን ናቸው። ይህም ማለት ጭንቅላታችን ወይም መንፈሳችን እዚያው በዚያው በቅራኔ የተወጠረና በዘለዓለማዊ ግጭት ውስጥ የሚኖር ነው። በተለይም ከተወሰኑ ሁኔታዎች ጋር እየተለማመድን ካደግን የኑሮአችን ፍልስፍና በሙሉ ጤናማውን የሰው ልጅ ባህርያት የሚቃረን ይሆናል። ፍርደ-ገምድልነትን፣ መግደልን፣ ማሰቃየትን፣ መዋሸትን፣ አገርንና ህብረተሰብን ማዘበራረቅ ወይም ማፍረስ ዋናው የኑሮአችን ፍልስፍና በማድረግ ለሚያድገው ትውልድም እንዲተላለፍ ማድረግ እንችላለን።

ከዚህ ስንነሳ ባለፉት አርባ ዓመታት፣ በተለይም ደግሞ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የተፈጠረውን ኢ-ፍትሃዊ አስተዳደር፣ አገር አፍራሽ ድርጊት፣ እንዲያም ሲል በአንድ ጥቁር ህዝብ መሀከል ስምምነት እንዳይኖር ጎሳን ከጎሳና፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት ጋር እያጋጩ ህዝቡ የኑሮው ፍልስፍና አድርጎ እንዲወስደው ማድረግ ከዚህ የጭንቅላት መከስከስ ወይም ደግሞ ጭንቅላት ውስጥ አሉ የሚባሉት ጥሮዎች ባህርያት ሙሉ በሙሉ መውደም ጋር የተያያዙ ናቸው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። በዚህም ምክንያት የተነሳ ጭንቅላታችን አዳዲስ ነገሮች የመቀበል ኃይሉ ስለሚዳከም ከሌላ ሰው የመጣ አዲስና ገንቢ አስተሳሰብን ይቃወማል። ያገኘውን ዝና፣ የተጎናጸፈውን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ስታተስ ይቀናቀነኛል በማለት ህብረተሰብአዊ ለውጥ እንዳይመጣና በዚያውም መሰረትም በሳይንስና በቴክኖሎጂ አማካይነት የሰፊው ህዝብ ኑሮ እንዳይሻሻል ያግዳል። በተለይም በአሁኑ ዘመን ውስጣዊ አገዛዞች ከውጭ ኃይሎች ጋር በሺህ ድሮች ተሳስረው በሚገኙበት ዓለም፣ የውስጥ ኃይሎች የውጭውን ኃይል ተገን በማድረግ ከውስጥ መስረታዊ ለውጥ እንዳይመጣ፣ እንዲያም ሲል በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለና የተወሳሰበ ኢኮኖሚ እንዳይገነባ እንቅፋት ይሆናሉ። በዚህ ዐይነቱ የተቆላለፈ ሁኔታና በጥቅም መተሳሰር የተነሳ ጭንቅላት የባሰውኑ እየዛገና ለዕድገት እንቅፋት እየሆነ ይመጣል። ስለሆነም ይህንን አካሄድ የሚቃውም ኃይል ከውስጥ ሲነሳ ህገ-መንግስቱን የሚጻረር የሽበረተኞች አካሄድ ነው በማለት በማስፈራራትና፣ ይባስ ብሎም አንዳንድ ግለሰቦችን ወይም ደግሞ በጅምላ በመግደል ነገሩን ለማብረድ ይሞከራል። ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ አካሄድ ችግሩን የሚፈታ ሳይሆን የሚያባብስና ህብረተሰብአዊ ፍጥጫውን ልዩ ዕምርታ የሚሰጠው ይሆናል። ይህ ዐይነቱ ችግርን ከመፍታት የባሰውኑ ማባባስ በብዙ ኋላ-ቀር በሚባሉ አገሮች የሚታይ አደገኛ አካሄድ ቢሆንም፣ እንደወያኔ ያለውን አገዛዝ ባህርይና ስልጣን ላይ ቁጥጥ ብሎ ህዝብን ማሰቃየት በተራ የፖለቲካና ከውጭው ኃይል ጋር በመተሳሰር ብቻ የሚገለጽ አይደለም። ሁኔታው በከፍተኛ ደረጃ ከህሊና-ሳይንስ አንፃር መታየት ያለበትና ከዝቅተኛ ስሜት ጋር በመያያዝ፣ በአንድ በኩል በምንም ማስረጃ የማይደገፍ በአንድ ብሄረሰብ ላይ ያተኮረ የቂም በቀል „ፖለቲካ“ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ ይህንን ሁኔታ በመጠቀም የአንድን ጎሳ የበላይነት(Dominanz) አስፍኖ አንድን ብሄረሰብ ብቻ ሳይሆን ጠቅላላውን ህብረተሰብ ለማዳከምና ለመግዛት የሚካሄድ፣ ግን ደግሞ የመጨረሻ መጨረሻ የሚከሽፍ መጥፎ አካሄድ አድርጎ መረዳትም ያስፈልጋል። በሌላ አነጋገር፣ ባለፉት ሰላሳና አርባ ዐመታት በብዙ አገሮች አምባገነናዊ አገዛዞች የታዩ ቢሆንም አገሮቻችውን ለማዳከመና ለማፈራረስ የተነሱብት ጊዜ አልነበረም።

አብዛኛውን ጊዜ በብዙ የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮች ውስጥ ያለው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶች የሚታዩት አገዛዞቹ ባለማወቅ በተሳሳተ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሚሊታሪ ርዕዮተ-ዓለም ወይም ፖሊሲ ስለሚመሩ ነው። አብዛኛዎች አገዛዞች በዓለም አቀፍ ደረጃ በተዋቀረው የአገዛዝ ሂራርኪ ውስጥ ስለተካተቱና ወደ ታዛዥነት ስለተለወጡ ካለምንም ምሁራዊ ክርክር ሳያውቁ ተግባራዊ የሚያደርጓቸው ፖሊሲዎች ህብረተሰቦቻቸውን እንዲያናጉና ወደ አለመጋዝት እንዲያመሩ ያስገድዷቸዋል። በሌላ ወገን ወያኔ የሚያካሄደው ማንኛውም ፖሊሲ ሆን ብሎና በውጭ ኃይሎች ታግዞ የሚካሄድ በመሆኑ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የተከላቸው መዘዞች፣ ያሰራጫቸው የጥላቻ መርዞች በቀላሉ የሚነቀሉና የተወሳሰበውን የአገራችንን ችግር በቀላል ፎርሙላ መፍታት የማንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል።

ያም ሆነ ይህ፣ በተለይም ፊደል የቆጠረና ዩኒቨርሲቲም ገብቶ ትንሽም ዓመት ቢሆን ይህንንም ሆነ ያንን ትምህርት የተማረ ሰው ድርጊቱ በሙሉ ተንኮልና ጥፋት ከሆነ ይህንን ዐይነቱን ድርጊት ከአዕምሮ ባህርያት ሙሉ በሙሉ ተሟጠው ከመውደማቸው ጋር ማያያዝ ይቻላል። አንድ ሰው ተማረም አልተማረም የተወሰነ የሞራል ኮድ እንዲኖረው ያስፈልጋል። ወደ ትምህርት ቤት የሚኬደው እንዲያው ከተወሰነ ዐመት በኋላ ዲጊሪ አግኝቻለሁ ለማለትና ለመዘባነን ሳይሆን፣ የማሰብ ኃይሉን ለማዳበርና፣ አልተማረም ለሚባለው ዕውቀትን ለማስተላለፍና የኑሮን ትርጉም ተረድቶት ራሱን እንዲለውጥ ለማድረግ ነው። የመማር ትርጉሙ የአንድን ህብረተሰብና የተፈጥሮን ህግ በመረዳት አንድ ህዝብ ታሪካዊ ስራዎችን ይሰራ ዘንድ መንገዱን ማሳየት ነው። በሌላ አነጋገር፣ የመማር ትርጉሙ፣ አገር ማፈራረስ፣ ተንኮል መስራት፣ ስግብግብነት፣ ከሌላው በልጦ ለመገኘት ሲባል አንዱን ማጥፋት፣ በተለይም ስልጣን ጨብጬአለሁ ብሎ በጠብመንጃ ኃይል በመመካት ሰውን እያነጣጠሩ መግደልና የአንድን ቤተሰብ ህይወት እንዳለ እንዲፈራርስ ማድረግ አይደለም። የፈለገው ሰው ቢሆን፣ በተለይም ደግሞ የመንግስትንንም መኪና የጨበጠና አገርን አስተዳድራለሁ የሚል፣ አንድን ሰው ወይም ብዙ ሰዎችን እንደፈለገው የመግደል፣ የማሰቃየትና የማሰር መብት የለውም። እንደፈለግሁት አደርጋለሁ የሚል ሰው በመጀመሪያ ደረጃ ራሱ ሰው መሆኑን የማይረዳ፣ ወይም ደግሞ ራሱ ከማንኛውም ሰው በላይ ነኝ ብሎ የሚገምት ብቻ ነው።

በመሰርቱ የወያኔን ሰዎችን ባህርይ መረዳት የምንችለው በዲሞክራሲ መኖርና አለመኖር አይደለም። ሰውን ማሰቃየታቸው፣ መግደላቸው፣ ጎሳን ከጎሳ ማጋጨታቸው፣ እነሱ እያበጡ እገር እንድትፈራርስ ማድረጋቸው፣ በተለይም ወጣቱን ትውልድ የዕጽ ሱሰኛ አድርጎ የኑሮን ትርጉም እንዳይረዳ ማድረግ፣ ይህ ሁሉ ርኩስ ድርጊት ሊገለጽ የሚችለው ውጥንቅጡ ከወጣው ወይም በስነስስርዓት ካልተዋቀረው ባህርያቸው ጋር የተየያያዘ ሲሆን ብቻ ነው። ወያኔ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታትም ሆነ ከዚያ በፊት የፈጸማቸውን ወንጀሎችና በድሮ የትግል አጋሮቹ በየጊዜው የሚነገርንን ለማወቅ የግዴታ በኖይሮ ባዮሎጂስት ወይም በህሊና ሳይንስ መመረቅ ወይም መሰልጠን አያስፈልግም። ራሱ የምናየው ነገር፣ ህዝባችን የሚኖርበት ኑሮና የሚፈጸምባቸው ወንጀሎች ራሳቸው በቂ ትምህርት ስለሆኑና፣ ይህንንም ከኖርማል ሁኔታ ጋር በማመሳሰል የነዚህን ሰዎች የጭንቅላት ባህርይ ከሞላ ጎደል መረዳት ይቻላል። ብዙ መመራመር አይሰፈልገውም ማለት ነው። ባለፉት ሃያ ዓምስት ዓመታት ስለወያኔ አረመኔያዊነት ብዙ ተጽፏል፤ ብዙም ተነግሯል። ይሁንና ግን የሁላችንም ግምት ቀን እያለፈ በሄደ ቁጥር ማህበራዊ ባህርይ በመወሰድ ከዚህ አረመኔያዊ ባህርያቸው በመላቀቅ ከህብረተሰቡ ጋር ይቀላቀላሉ የሚል ግምት ነበረን። ስለሆነም አጻጻፋችን ከሞላም ጎደል በተቻለ መጠን ፈሩን እንዳይለቅና ትምህርታዊ በመሆን ግንዛቤ ሰጥቶአቸው ርህሩህ ባህርይ ያዳብራሉ የሚል ግምት ነበረን። እነሱ ግን ሆን ብለው የያዙት አንድም ሌላው ሞኝ ነው፣ በቀላሉ ልናታልለው እንችላለን በማለትና ለሆዱ ያደረውን በመግዛት፣በዚያም አማካይነት በህብረተሰብ ውስጥ ሚዛናዊነት ያለው ድርጊትና የሀብት ፈጠራ እንዳይካሄድ በማድረግ፣ በሌላ ወገን ደግሞ አልፎ የሄዳቸውን ይቀናቀነኛል ብለው በማሰብ እንዲጠፋ በማድረግ በፍጹም ሊማሩና ህብረተሰብአዊ ባህርይ ሊቀስሙ የማይችሉ ፍጡሮች እንደሆኑ ነው በየጊዜው ያረጋገጡልን። በተለይም ከነሱ ኢ-ፍህታዊ አገዛዝ የሚመነጨውን ግፍ የሚቃወመውን ሁሉ ትግሬውን ወንድሞቻችንም ሆነ እህቶቻችን፣ እንዲሁም እናቶቻችንና አባቶቻችንን የተቃወመ በማስመሰል ወይንም በነሱ ላይ የተለየ ጥላቻ እንዳለ በማስወራት የዋሁን ህዝብ በማሳሳት እስካሁን ድረስ እያወናበዱ መግዛት ችለዋል። ይሁ ሁሉ የመጥፎ ባህሪያቸው መግለጫ ነው።

አንዳንድ የድሮ ታጋይ ነን የሚሉና ዛሬ ያገሪቱ ሁኔታ ያሳሰባቸው እንደነ ጄኔራል ጻድቃን እንደሚነግሩን ወይም ለማረጋገጥ እንደሚሞክሩት ሳይሆን፣ በተለይም የኋላ ኋላ ቀስ በቀስ የበላይነትን እየተቀዳጁ የመጡት እንደነ መለሰ ዜናውና ስብሃት ነጋ፣ ሌሎችም ዛሬ በስልጣን ላይ ያሉት በሙሉ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሱት አረመኔያዊነታቸውን እያረጋገጡ ነው። በሌላ አነጋገር በዲሞክራሲያዊና በሰብአዊ መርሆች በመመራት ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመፍጠር አይደለም። ስለሆነም የጄኔራል ጻድቃን ድርጅቱን በአነሳሱ ዲሞክራሲያዊና አብዮታዊ አድርጎ ለማቅረብ መሞከሩ ቢያንስ ድርጅቱ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ ከሚያደርገው አረመኔያዊ ድርጊቱ ጋር በፍጹም የሚጣጣም አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ ድርጅቱ ዲሞክራሲያዊ ባህርይ ቢኖረው ኖሮ በትግሉ ዘመን በመሀከላቸው የነበረውን ቅራኔ ወይንም በሃሳብ አለመግባባት ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልክ መፍታት መቻል ነበረበት። በተጨማሪም በአንዳድ ግለሰቦች በሴቶች ላይ የሚደረገውን ግፍና ግድያ ወይም ወደ ገደል ውስጥ መውርወር ሲታይ ዝም ብሎ ማለፍ፣ ወይም እንደዚህ ዐይነቱ መጥፎ ድርጊት እንዳይደገም ወንጀሉን በፈጸመው ላይ ቁርጥ ያለ እርምጃ መውሰድ ሲገባ እነ ጄኔራል ጻድቃን ይህንን አጸያፊ ድርጊት ዝም ብለው የሚመለከቱ ነበሩ። ይህም የሚያሳየው የኋላ ኋላ ድርጅቱን በቁጥጥራቸው ውስጥ ያስገቡት እነመለስና ስብሃት ነጋ፣ እንዲሁም ሌሎችም አረመኔዎች እንደነበሩና የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ባህርይ እንዳልተዋሃዳቸው ነው የሚያረጋግጠው። ከዚህም ባሻገር ማንኛውም የዲሞክራሲን መፍክር ይዞ የሚነሳ ግለሰብም ሆነ ድርጅት ማሰብና ማቀድ ያለበት ስትራቴጂያዊ በሆነ መልክ ነው። በሌላ አነጋገር ማሰብ ያለበት ከስልጣን መያዝ ባሻገር ነው። የእነ መለስ ዜናዊና ስብሃት ነጋ እንዲሁም የተቀሩት የዛሬው ቱጃሮች ዕቅድ ማሰብ የሚችለውንና ትንሽም ቢሆን ከእነሱ የተሻለውን በማስወገድ ወደ ስልጣን የሚመጡበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነበር። ይህንን ዐይነቱንና በብዙ መልክ የሚወራውንና ዕውነትም የሆነውን ወንጀላቸውን ሁሉ የተከታተለ፣ የወያኔ ሰዎች አንድ ሰው እንዲኖረው የሚገባውን ከላይ የዘረዘርኳቸውን ጤናማ ባህርዮች በሙሉ አንድ በአንድ እያጡና የምናየው አካላቸው ብቻ የሚንቀሳቀስ ሆኖ የባሰ ስግብግብነትንና አረመኒያዊነትን ከሰውነታቸው ጋር እያዋሃዱ የመጡበትን ሁኔታ እንመለከታለን። በመሆኑም ከነሱ አስተሳሰብና የአኗኗር ስልት ውጭ ያለ በሙሉ ሰው አይመስላቸውም። ማንኛውም ሰው ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንደሚያስፈልገው የተረዱና የሚረዱ አይደሉም። በተለያዩ መልኮች የሚገለጸው ፍቅር ጭንቅላታቸው ውስጥ የሌለ በመሆኑ ለሰው ልጅ ርህራሄ የላቸውም። ኮመን ሴንስና ኢንቲዩሽን ከጭንቅላታቸው በሙሉ ተሟጠው ያለቁ ስለሆነ ስሜት የላቸውም። የሚመስላቸው እነሱ ጠላቴ ነው ብለው የሚገምቱትን በሙሉ እያሰቃዩ የሚኖሩና፣ በዚህም የሚደሰቱ በመሆናቸው፣ ፍልስፍና ካልነው ይህንን የኑሮአቸው ፍልስፍና አድርገውታል። ከዚህ ስንነሳ ዛሬ በአገራችን ምድር አፍጦ አግጦ የሚታየው የተበላሸ ሁኔታ፣ ህዝባችን ለድህነትና ለረሃብ መጋለጥ፣ ይባስ ብሎ በ21ኛው ክፍለ- ዘመን ተስቦና ኮሌራ ተስፋፍተው ብዙ ህዝብ ሲፈጁና ከተማው በሙሉ በቆሻሻ እቃ ሲሞላና፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ከቆሻሻ መጣያ ቦታ እየፈለገ ሆዱን ለመሙላት ሲታገል ስናይ፣ ይህ ሁሉ ሊገለጽ የሚችለው እንዲያው በመልካም አስተዳደር እጦት ሳይሆን አገሪቱ ሰብአዊነትን ባጡና ሌላው ፍጡር በሙሉ ሰው በማይመስላቸው ሰዎች እንደምትተዳደር ነው። አስተሳሰባቸውና ድርጊታቸው በሙሉ የህብረተሰብንና የተፈጥሮን ህግ የሚፃረርና አንድ ህዝብ በረጋ መንፈስ ታሪክን እንዳይሰራ የሚያግድ እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው።

ተፈጥሮአዊ ወይም ዩኒቨርሳል ህግ ምን ይለናል !

ታላቁ የሮማውያን የመንግስት ፈላስፋ ሴናካ የሚባለው ታላቅ መሪ እንደሚለን፣ ማንኛውም ህብረተሰብአዊ ችግሮችና ፖላቲካዊ ፍጥጫዎች የሚከሰቱት የተፈጥሮን ህግ ባለመረዳት ነው ። የተፈጥሮን ህግ ለመረዳት የማይችል ሰው ደግሞ የግዴታ የአንድን ህበረተሰብ ጤናማና ሚዛናዊ አካሄድን ያዘበራርቃል። የዕድገትና የሰላም ጠንቅ ይሆናል። አንድ ህብረተሰብ ዕውነተኛ ስልጣኔን እንዳይጎናጸፍ ልዩ ልዩ መሰናክሎችን በመፍጠር አንድ ህዝብ ፍዳውን እያየ እንዲኖር ያደርጋል።

ቀደመ ብዬ ለማሳየት እንደሞከርኩት የሰው ልጅ ከማሰብ ኃይል ጋር የተፈጠረ ነው። የማሰብ ኃይሉ በተለያየ መልክ የሚገለጽ ሲሆን፣ ይህንን በተለያየ መልክ የሚገለጸውን ግን ደግሞ በአንድ አጠቃላይ ውስጣዊ ኃይል የሚገዛውን ሎጂካዊ አስተሳሰብ በመጠቀም የማሰብ ኃይሉን በማዳበር ተፈጥሮን በመለወጥና በማሻሻል መኖሪያ ያደርጋታል። የማሰብ ኃይሉን በመጠቀም የተዘበራረቀውን ሁኔታ በምሁራዊ ኃይል መልክና ስርዓት በመስጠት በአንድ በኩል በሰዎች መሀከል የሚኖረው ግኑኝነት ሚዛናዊነት እንዲኖረው ያደርጋል፣ በሌላ ወገን ደግሞ የተፈጥሮን ህግ በመረዳት በተፈጥሮና በሱ መህከል ሊኖር የሚገባውን መደጋገፍ በመገንዘብ በተፈጥሮ ላይ ብዙም አደጋ ከማድረስ ይቆጠባል። ተፈጥሮን የበለጠ ቅርጽ እየሰጠና እየተንከባከበ ወደ ምድራዊ ገነትነት ይለውጣታል። በዚህ ብቻ ሳይቆጠብ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠርና በማዳበር ስራውን ያቃልላል፤ እንዲያም ሲል በተወሰነ ሰዓት የበለጠ ምርትን ማምረት ይችላል። ይህ ዐይነቱ የማሰብ ኃይል ከዘርና ከቀለም ባሻገር ለሰው ልጅ ሁሉ የተሰጠ ጸጋና ከሰው ልጅ ጋር አብሮ የሚፈጠር ነው። ይሁንና ግን እያንዳንዱ ሰውና ህብረተሰብ ይህንን ተፈጥሮአዊ ጸጋ ለመጠቀም እንዳይችል የሚያግዱት የተወሳሰቡ ህብረተሰብአዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ግኑኝነቶች በየአገሮች ውስጥ አሉ። በአለንበት በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ደግሞ የአንድ ህዝብ የማሰብና የመፍጠር፣ ወይም ደግሞ ያለማሰብና ያለመፍጠር ኃይል ከውጭው ዓለም ጋር ባለን ግኑኝነት የሚወሰን ነው። የየአገሮች ባህሎች፣ ኢኮኖሚዊ ግኑኝነቶና ፖለቲካዊ አወቃቀሮች በጎሎባል ካፒታሊዝም ውስጣዊ ኃይል ስለሚወሰኑ፣ አንድን አገር በተስተካከለና በሳይንሳዊ ዘዴ ለመገንባት እጅግ አስቸጋረ እየሆነ የመጣንበትን ሁኔታ እንመለከታለን። በሌላ አነጋገር በብዙ መልክ የሚገለጸው ግሎባል ካፒታሊዝም የሃሳብ ጥራትን ከማምጣትና የማሰብ ኃይልን ከማዳበር ይልቅ እያዘበራረቀውና የሰውን ልጅ ወደ አልባሌ ተግባርና ወደ አረመኔያዊነት ድርጊት እየመራው እንደሆነ በምድር ላይ የሚታየውን ለተከታተለና ራሱን ለጠየቀ በቀላሉ መልስ ሊያገኝ ይችላል። በተለይም ደግሞ እንደኛ ባለው ምሁራዊ ኃይል እጅግ ደካማ በሆነበት አገርና፣ ሎጂካዊና የተወሳሰበ አስተሳሰብ ቦታ በሌላቸው አገሮች ውስጥ በተወሳሰበ መልክ ከውጭ የሚመጣውን አገርንና ህብረተሰብን አፍራሽ አስተሳሰብ ለመዋጋት እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል። ከዚህም በላይ የዓለም ማህበረሰብ ሁሉ በአንድ ፎርሙላ መመራት አለባቸው እየተባለ በሚሰበክበት ዓለም ውስጥ ውሸትን ከዕውነት፣ የሰይጣኑንመንገድ ከመንፈሳዊው ለመለየት በጣም ያዳግታል።

ከዚህ ስንነሳ የዩኒቨርሳል ህግ ወይም ተፈጥሮአዊ የማሰብ ኃይል ፈሩን ሊለቅ የሚችልበትን ሁኔታ ጠጋ ብለን እንመልከት። ለአንድ ሰው የማሰብ ኃይል መዳከም እንዲያም ሲል በአልባሌ ነገሮች መወጠርና ወደ ጨካኝነት ማምራት ብዙ ምክንያቶችን መስጠት ይቻላል። በተፈጥሮ ውስጥ ከአፈጣጠር ጋር የሚከሰተውን የማሰብ ኃይል ድክመትና በየአገሮች ውስጥ ያለውን የባህል ሁኔታ ወደ ጎን ትተን፣ ሌሎች የንቃተ-ህሊናችንን እንዲያም ሲል የማሰብ ኃይላችንን መዳከም የሚወስኑ ነገሮች ላይ እናተኩር። በመጀመሪያ ደረጃ በተለይም በዘመኑ በብዙ አገሮች የታዩትንና እንደትዝታ የሚወሩትን የጭካኔ እርምጃዎችና የግፍ አስተዳደሮች ለተመለከተ አረመኔያዊነት በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተስፋፋ የመጣውና መንግስታትም የበለጠ ጨቋኝ መሆን የቻሉት ከንቃተ-ህሊናቸው ጋር ሊስተካከል ከማይችል ቲክኖሎጂ፣ የጦር መሳሪያዎችና ቢሮክራሲያዊ አስተዳደሮች ጋር በመተዋወቃቸው ነው። በሌላ አነጋገር በካፒታሊዝም መስፋፋት በየአገሩ እየተንጠባጠበ የገባው ዘመናዊነት በተለይም በከፍተኛ የህብረተሰብ ሂራርኪ ውስጥ የሚገኘውን የሀብረተሰብ ክፍል አረመኔያዊ፣ ሀብት አውዳሚና አገር አፍራሽ እያደረገው እንደመጣ መገንዘብ እንችላለን። ይህም ማለት ዘመናዊነት ጭንቅላትን ብሩህ ከማድረግና ልብንም ርህሩህ አድርጎ ህብረተሰብአዊ ኃላፊነት እንዲሰማ ከማድረግ ይልቅ፣ አንዱ ሌላውን የሚንቅበትና፣ ራሱ ጥሩ ኑሮ እየኖረ ሌላው ደግሞ ተጨማደደና የተዝረከረከ ኑሮ እንዲኖር የሚያደርግበትን ሁኔታ እንመለከታለን። ይህ ዐይነቱ በብዙ አገሮች የሚታየው የጭቆናና ግፍ አስተዳደር በየአገሮች ውስጥ ያለው ህዝብ የማሰብ ኃይሉን እንዳያዳብር አፍኖ በመያዝ ለድህነት ዋናው ምክንያት ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ ፓለቲካዊ ንቃተ-ህሊና፣(Political Consciousness ) ህብረተሰብአዊ ንቃተ-ህሊና፣(Soical Consciousness) አካባቢን የመንከባከብ ንቃተ-ህሊና፣(Ecological Consciousness) ባህላዊ ንቃተ-ህሊና፣(Cultural Consciousness) ታሪካዊ ንቃተ-ህሊና፣(Historical Consciousness)… ወዘተ. እነዚህን የመሳሰሉት ለአንድ ህብረተሰb እንደ ማህበረሰብ ተስማምቶ እንዲኖር የሚያደርጉትና ታሪካዊ ነገሮችን እንዲሰራ የሚያስችሉት በብዙ መልክ የሚገለጹ ዕውቀቶች እንዳይዳብሩና የህብረተሰብ ኖርሞች ሆነው ማንኛውም ዜጋ እንዲከተላቸው ማድረግ አልተቻለም። በዚህም ምክንያት የተነሳ ውንብድና፣ ሸፍጠኝነት፣ በስነ-ስርዓት አለመስራት፣ ፕሪንሲፕል-አልባ መሆን፣ ለዚህም ለዚያም ነገር መስገብገብ፣ አለሁ አለሁ ማለት፣ ስንትና ስንት ወንጀል እየሰሩ አልሰራሁም ማለት፣ ወይም የሰራሁት አንድ ነገር አሳስቶኝ ነው ማለት ህብረተሰባዊ ኖርሞች በመሆን የአንድን ህብረተሰብ የተወላገደ ጉዞ ደንጋጊ መሆን በቁ። ይህ ዐይነቱ ባህርይ በብዙ ያለደጉ አገሮች፣ በተለይም ደግሞ በኛ አገር ጎልቶ የታያና የሚታይ በብዙ መቶ ሺህ ለሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት መጥፋትና ለተፈጥሮ ሀብት መውደም ምክንያት የሆነ ነው። ዛሬ በአገራን ውስጥ ያለውንም አረመኔያዊ አገዛዝ ከዚህ ዐይነቱ ሁኔታ ጋር ማያያዝ ይቻላል። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ባልተስተካከለ የኢኮኖሚ ዕድገትና ከታች ወደ ላይ በጥናት ባልተደራጀ መንግስታዊ አወቃቀር በመጠናከር አንድ ህብረተሰብ ፈሩን እንዲለቅ ሊደረግ ቻለ።
ከዚህ ስንነሳ በመሰረቱ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ ንቃተ-ህሊና መዳበር ሊወሰንና ህዝቡም ያለውን ተፈጥሮአዊ ፖቴንሺያል ሊጠቀምና፣ ጤናማና የሚተሳሰብ ማህብረሰብ ሊገነባ የሚችለው መንግስታዊ አወቃቀርና የፖለቲካው ሁኔታ መልክ ሲይዙ ብቻ ነው። የአሳ መግማት የሚጀምረው ከጭንቅላቱ ነው እንደሚሉት አነጋገር፣ ንቃታ-ህሊናው እጅግ ደካማ የሆነ ወይም ተሟጦ ያለቀ፣ ዓላማው አንድን ማህብረሰብ መገንባትና ህብረተሰብአዊ ስምምነት ሳይሆን ስግብግብነትን የሚያስቀድም፣ በውጭ ኃይል ተማምኖ ከውስጥ የሚነሱ ብሶቶችን ለማፈን እችላለሁ ብሎ የሚገምት ኃይል በታሪክ አጋጣሚ ስልጣንን በሚጨብጥበት ጊዜ አስተሳሰቡና ድርጊቱ ሁሉ ህብረተሰቡን መረበሽ ይሆናል። የአንድ ህዝብ አስተሳሰብ በመፍጠር ላይና የራስን ኑሮ በማሻሻል እንዳያተኩር የሆነ ያልሆነ ተንኮል በማውጠንጠን የሰፊው ህዝብ ጭንቅላት በአልባሌ ነገሮች እንዲጠመድ ያደርጋል። ኑሮው ጭንቀትና ሀዘን ብቻ እንዲህን በማድረግ የራሱን የግዛት ዘመን ለማርዘም የሆነ ያልሆነውን በህግ መልክ ተግባራዊ በማድረግ በአጠቀላይ ሲታይ አንድ ህብረተሰብ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊዳረስ የሚችል ብሄራዊ ሀብት(National Wealth) እንዳይዳብር ያደርጋል። ይህንን ዐይነቱን አንድን ህብረተሰብ ማወላገድ በአገዛዙ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ኢንስቲቱሽኖችና ሽብርተኝነትን የሚፈለፍሉና በተለያየ መልክ የሚዶግሙ የካፒታሊስት አገር የስለላ ድርጅቶችም ዋና ተግባር ነው። በዚህ መልክ በተሰበጣጠረ ግኑኝነት የተነሳ አንድ ህዝብና አንድ አገር ልኡልናቸውን ያጣሉ። በዘለዓለማዊ ትርምስ ውስጥ እንዲኖሩ ይገደዳሉ። ድህነት፣ ተደጋጋሚ ረሀብ፣ በአጠቃላይ ሲታይ አንድ ህዝብ ለህይወቱ የሚያስፈልጉት መሰረታዊ ነገሮች እንዳይሟሉ ማድረግ የተፈጥሮ ህግ ሆነው ስለሚወሰዱ ጠቅላላው ህዝብ በልመናና በመጽዋት እንዲኖር ይገዳድል። በዚህ መልክ የአንድ ህዝብ የመፍጠር ኃይል ይዳፈናል። ንቃት-ህሊናውን ለማዳበር አቅም አይኖረውም። በተመጣጠኑ ምግቦች ዕጥረት በግልጽ የምናየው ሰውነቱ ብቻ ሳይሆን የማሰብ ኃይሉም ይዳከማል።

ለዚህ ዐይነቱ ለብዙዎቻቸን በግልጽ ከማይታየን የተሳሰረና ጭንቅላታችንን አፍኖ ከያዘን ሁኔታ መውጣት የሚቻለው ጠቅላላው ህዝብ የመንፈስ ነፃነት ሲያገኝና፣ እንደልብም መንቀሳቀስ ሲችል ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር የማሰብ ኃይሉን ማዳበር ሲችልና ራሱን ሲያገኝ ብቻ ነው። አንድ ህዝብ የማሰብ ኃይሉን ሲያዳብርና በሁሉም አቅጣጫ በተወሳሰበ መልክ ማሰብ ሲችል ለማንኛውም ጭግር መልስ ማግኘት ይችላል። አዳዲስ ችግር ፈቹ ቴክኖሎጂዎችን ያፈልቃል። ይህ ማለት ምን ማለት ምን ማለት ነው ? ዛሬ በዓለም ላይ የምናያቸውና የምንጠቀምባቸው ቴክኖሎጂዎችና ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የምንሽከረከርባቸው መመላለሺያዎች ከሰማይ ዱብ በለው የወረዱ ሳይሆን በሰው የማሰብ ኃይል የተፈጠሩ ናቸው። በተፈጥሮ ውስጥ ብዙ ተፈጥሮአዊ ነገሮች ቢገኙም እነዚህን አውጥተን በኃይል (Energy)አማካይነት ወደ መጠቀሚያነት መለወጥ የምንችለው በማሰብ ኃይላችን ብቻ ነው። ኃይል በተፈጥሮ ውስጥ ያለ ቢሆንም እሱን አባዝተን ለመሳሪያ መስሪያ መጠቀም የምንችለው እንደዚሁ በማሰብ ኃይላችን ነው። በሌላ ወገን ግን ይህንን የዩኒቨራሳል ህግ ያልተረዳና ለመጠቀም የማይችል አገዛዝም ሆነ ህዝብ እጣው ድህነትና ረሃብ፣ እንዲሁም ኑሮው መዘበራረቅ ይሆናል። እንደ አገራችን ባለ ሁኔታ የአገዛዙ የፖለቲካ ዘይቤ ተንኮል መጠንሰስ በሆነበትና፣ ስልጣን ላይ ለመቆየት ሲባል ብቻ አንዱን ጎሳ ከሌላው ጎሳ ጋር ማጣላት፣ ወይም አንዱን ሃማኖት ከሌላው ጋራ በማጋጨት በከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ አማካይነት ለዘለዓለም ስልጣን ላይ ለመቆየት መሞከር በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ያለን ውስጣዊ ኃይልና የተፈጥሮን ሀብት ያወድማል። በዚህም ምክንያት የተነሳ ጠቅላላው ህበረተሰብ በአልባሌ ነገሮች ስለሚጠመድና ምክንያቱን ሳያውቀው ርስ በርሱ ስለሚነታረክ ተፈጥሮ የሰጠውን ውስጣዊ የማሰብ ኃይሉን እንዳይጠቀምበት ይገደዳል። ይህ ዐይነቱ አካሄድ ኃይል ማወደሚያ ህግ (The Law of Energy Destruction) ይባላል። በሌላ አነጋገር ጠቅላላው የማሰብ ኃይል ህብረተሰብንና የተፈጥሮን ሀብት በማውደም ላይ የሚያተኩር ስለሚሆን ህብረተሰብአዊ ሀብት(National Wealth)እንዳይፈጠር መንገዱን ሁሉ ይዘጋል። አንድ ህዝብ የሰለጠነ ኑሮ እንዳይኖር ያግዳል። ይህ ዐይነቱ የኃይል ውድመት የሰውን የማሰብ ኃይል ድክመት የሚመለከት እንጂ በተፈጥሮ ውስጥ ያለን ኃይል አይደለም። በፊዚክስ ህግ ኃይል(Energy) ሊፈጠርና ሊወድም አይችልም። ተፈጥሮአዊ ኃይል ከአንድ ሁኔታ ወደ ሌላ ሁኔታ የሚለወጥ ብቻ ነው። ይሁንና ግን ኃይልን በስነ፟-ስርዓት ካለመጠቀም የተነሳ መባከን ይፈጠራል። በሌላ አነጋገር እንደዚሁ በተፈጥሮ ውስጥ ያለን ኃይልና ከአንድ ሁኔታ ወደሌላው የሚለወጠውን ኃይሉ ሳይቀንስ ለመጠቀም ከተፈለገ የግዴታ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች መፈጠር አለባቸው። ይህ ዞሮ ዞሮ የሰውን ልጅ የማሰብ ኃይል ሁኔታ ይጠይቃል። በአጠቃላይ ሲታይ ለሰው ልጅ ዕድገትና በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ስምምነትና ሰላም መኖር የዩኒቨርሳል ህግ ወሳኝ ሲሆን፣ የዩኒቨርሳል ህግን መረዳት ደግሞ በተለይም የማንኛውም ለፖለቲካ ስልጣን እታገላለሁ የሚል ግዴታ ነው። ይህንን ህግ ሳይረዳ ስልጣን ላይ የሚወጣ የግዴታ ህብረተሰቡን አንድገና ለአንድ ሺህ ዐመት በጨለማ ዓለም ውስጥ እንዲኖር ያደርገዋል።

ወደ ሁለተኛው፣ በሰውና በተፈጥሮ መሀከል ሊኖር የሚገባውን ግኑኝነትና መደጋገፍም መረዳት የምንችለው የማሰብ ኃይልን ከፍተኛ ቦታ ስንሰጠው ነው። የሰው ልጅ ተፈጥሮን ይፈልጋታል እንጂ ተፈጥሮ ሰውን አትፈልገውም። ብዙም ሳናስብ(Intutively) የሰው ፍጡርም ሆነ እንስሳ ሁሉንም ነገር ሊያገኙ የሚችሉት ከተፈጥሮ ነው። ለመተንፈስ አየር፣ ለመጠጣትና ለመታጠብም ሆነ ለመቀቀያ ውሃ፣ አፍርን ለማብቀያ ብቻ ሳይሆን ወደ ማሺንነት የምንለውጣቸው ጥሬ- ሀብቶች በሙሉ ከተፈጥሮ ውስጥ የሚገኙ የሰው ልጅ ሳይፈጥራቸው በጸጋ የተሰጡ ናቸው። እነዚህን ግን በስነ-ስርዓት እያወጡና በተፈጥሮ ላይ ሚዛናዊንት እንዳይጓደል መጠቀም የሚቻለው የማሰብ ኃይላችንን ስንጠቀም ብቻ ነው። እንዲያው በጭፍንና በጉልበት እየተመካን በተፈጥሮ ላይ ዘመቻ ብናደርግ ተፈጥሮ ራሷ አንድ ቀን የቂም በቀሏን ትወጣለች። በሌላ አነጋገር ዝም ብለን ዛፍን የምናወድም ከሆነ የግዴታ ለዝናብ እጦት ወይም አለመዝነብ አመቺ ሁኔታ እንፈጥራለን። በተጨማሪም አንድ ቀን ኃይለኛ ዝናብ በሚዘንብበት ጊዜ መሬቱ በዛፍ መቆረጥ በመራቆቱ የተነሳ የመሬቱ ፍሬያማ አካል በጎርፍ በመጠራረግ እንደገና ዘር ዘርቶ ለማብቀል የማይቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል። ከዚህም ባሻገር በየቦታው ለጊዜው ሀብት ለማካበትና በአንድ ጊዜ ቱጃር ሆኖ ለመገኘት ሲባል ከዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር በመስማማትና በመፈራረም በሳይንስ ያልተጠና የማዕድን አወጣጥ በተፈጥሮና በሰው ህይወት ላይ ከፍተኛ አደጋ ያስከትላል። በዚህም ምክንያት የተነሳ አንድ አካባቢ ስለሚመረዝ ቦታዎች ከብት የማይረባባቸው፣ ሰው የማይኖርባቸውና ምንም ነገር የማይበቅልባቸው ይሆናሉ።

ይህ ብቻ ሳይሆን አንድ አገዛዝ በዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው በሚባለው እየተመከረና እየታገዘ ከተፈጥሮና ከህብረተሰብ ህግ ጋር የማይጣጣም የኢኮኖሚ ፖሊሲ አውጥቶ ተግባራዊ የሚያደርግ ከሆነ የግዴታ የሰው የማሰብ ኃይል እንዲዘበራረቅ ያደርጋል። ውስጣዊ ኃይሉ ወደ አንድ አቅጣጫ እንዲያተኩር በማድረግ የመፍጠር ኃይሉ እንዲሟጠጥ ያደርጋል። በዚህም ምክንያት የተነሳ በተፈጥሮ ውስጥ ያለን ሀብት በማሰብ ኃይሉ እየታገዘ ህብረተሰብአዊ ሀብት እንዳይፈጠር ያደርጋል። በአገራችን ምድር ለሃያ አምስት ዐመታት ያህል ተግባራዊ መሆን የጀመረውና በገበያ ኢኮኖሚ ስም የሚካሄደው ፖሊሲ ዋና ዓላማው ህብረተሰብን ማዘበራረቅ ብቻ ሳይሆን፣ እያንዳንዱ ዜጋ የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ ተረድቶ ቆንጆ ቆንጆ ነገሮች እንዳይሰራ የተወጠነ የኢምፔሪያሊስቶች ሴራ ነው። ሁሉ ነገር በገበያ ኢኮኖሚ ዙሪያ አካባቢ የሚሽከረከር ከሆነ የሰው ጭንቅላት ገንዘብ በማግኝት ይጠመዳል። ጠቅላላው የኑሮው ፍልስፍና ገንዘብ ወደ ማግኘት ስለሚለወጥ አብዛኛው ህዝብ ተፈጥሮ የሰጠውን በልዩ ልዩ መልክ የሚገለጽውን የማሰብ ኃይሉን እንዲያጣ ይገደዳል። በመሆነም ከሰብአዊነት ይልቅ አረመኔያዊነት በመስፋፋት አንድ ህዝብ ወደ መበላላት ያመራል። በተለይም ደግሞ እንደዚህ ዐይነት ናላው የዞረ አገዛዝ ስልጣን ላይ ሆኖ የሱም መስገብገብና ድርጊቱ እንደምሳሌ በሚወሰድበት አገር አንድ ህዝብ አቅጣጫውን እንዲስት ይገደዳል። ግብረ-ገብነትና ስነ-ምግባር የህብረተሰቡ መለኪያዎች መሆናቸው ቀርቶ ሀብት ማካበትና በማቴሪያል መሸብረቅ መለኪያዎች ይሆናሉ።

ከዚህ ስንነሳ በወያኔ አገዛዝ በአገራችን ምድር ተግባራዊ የሆኑት የኢኮኖሚም ሆነ የጎሳ ፖለቲካዎች በሙሉ ከፍተኛ የሆነ የሀብት ውድመት እንዲፈጠር ነው ያደረጉት። እያንዳንዱ ዜጋ የማሰብ ኃይሉን በመጠቀም ርስ በርሱ የተሳሰረ ግን ደግሞ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተደገፈ ህብረተሰብአዊ ሀብትና፣ ርስ በርሱ የሚደጋገፍና የሚከባበር ህብረተሰብ እንዳይፈጠርና እንዳይገነባ ነው ያደረገው። በተለይም የብሄረሰብ መብት የሚባለውና በክልል ደረጃ የተዋቀረው የከፋፍለህ ግዛ „ፖለቲካ“ ዋና ዓላማው ይህንን በተለያዩ ጎሳዎች መሀከል ሊኖር የሚችለውን የዕውቀትና የሃሳብ መለዋወጥ፣ እንዲያም ሲል የካፒታልና የሰው ኃይል እንቅስቃሴ እንዳይኖር ያገደ ነው። በመሆኑም ጠቅላላው ህዝብ አንድ ላይ ሆ ብሎ በመነሳት ብሄራዊ ምወይም አገር-አቀፍ በሚባሉ ተግባሮች ላይ እንዳይሰማራ ያገደው እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው። ከተማዎችን እንዳይገነባ፣ በየክልሉ የሰራ ክፍፍል በማዳበር ሰፋ ያለ ገበያ እንዳይገነባ፣ በአጠቃላይ ሲታይ ጠቅላላው ህዝብ እዚያው ቀጭጮ እንዲቀር የሚያደርግ ፖሊሲ ነው ባለፉት ሃያ አምስት ዐመታት ተግባራዊ የሆኑት። በዚህ ዐይነቱ የክልልና የማሰብ ኃይልን የማወደም ዕቅድና ተግባር የወዳጅ አገሮች የሚባሉት እንደ እንግሊዝና አሜሪካ እንዲሁም ሌሎች የምዕራብ አገሮች ተሳትፈውበታል። አገዛዙን በመሳሪያም ሆነ በገንዘብና በተለያዩ የተንኮል ዘዴዎች በማሰልጠንና በመደጎም ጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ በራሱ ተነሳሽነትና ዕውቀት አንድ ጤናማና ሚዛናዊ ያለው ህብረተሰብ እንዳይመሰረትና እንዳይገነባ አድርገውታል። በርዳታ ስም በመግባትና በመሰግሰግ አቅመ-ቢስ አድርገውታል። በዚያው መጠንም አገሪቱ ወደ አስረሽ ምቺው ተለውጣለች። ሰፊውን ህዝብ ቡና አምራች፣ አበባ ተካይ፣ የሸንኮራ አገዳ አብቃይና ስኳር አምራች በማድረግ ለምዕራቡ ዓለም የጥሬ-ሀብት አቀራቢ አድርገውታል። ባጭሩ የባሪያ ስራ እንዲሰራና ዘለዓለሙኑ እንደ ነፃና ኩሩ ዜጋ ሆኖ ራሱን አውቆ እንዳይኖር አግደውታል። ስለሆነም በአገራችን ምድር ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ ሀብት ሊወድም የቻለውና ህዝባችንም የማሰብ ኃይሉን ተጠቅሞ ቆንጆ አገር እንዳይገነባ የተደረገው በዚህ ዐይነቱ የእከክልኝ ልከክልህ፣ በውስጥና በውጭ ኃይሎች መሀከል በተፈጠረው መተሳሰርና መተጋገዝ ነው። ከዚህም አንፃር ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ስልጣንን የተቆናጠጠው የወያኔው አገዛዝ የውጭ ቅምጥ ነው ማለት ይቻላል። ጠቅላላውን የኢትዮጵያን ህዝብም ሆነ የትግሬን ብሄረሰብ የሚወክል አይደለም። በከፍተኛ ደረጃ የተፈጥሮ ሀብትና የሰውን ልጅ የማሰብ ኃይል ያወደመና፣ አካሄዱና ተግባራዊ ያደረጋቸው ፖሊሲዎች በሙሉ ዩኒቨርሳል የሆነውን የሰውና የተፈጥሮ፣ እንዲሁም የህብረተሰብን ህግ የሚጻረሩ እጅግ አደገኛ ድርጊቶች ናቸው ማለት ይቻላል። በ1930ዎቹ ዓመታት የጀርመን ናዚዎች ተግባራዊ ካደረጉት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር እንኳን የቅንጣትም ያህል የሚወዳደር አይደለም። እጅግ በጠባብ ስሜት በመወጠር የሶስት ሺህ ዐመት ታሪካዊ ቅርስ እንዲወደም ያደረገና፣ በተለያዩ መልኮች የሚገለጹ አጸያፊ ድርጊቶች እንዲስፋፉና፣ የአብዛኛው ህዝብ የኑሮ ፍልስፍና እንዲሆን ያደረገ ተፈጥሮአዊ ህግን የሚጻረር ነው። በህብረተሰብአችን ውስጥ የጨአት መቃም መስፋፋት፣ የሴተኛ አዳሪዎች ቤት መስፋፋትና በዝሙት ዓለም ውስጥ መዋኘት፣ የአገሪቱ ሀብት ሊሸከም የማይችለውን ውድ ውድ መጠጦችና አሸብራቂ ዕቃዎች እያመጡ ሀብት ማውደምና ታዳጊውን ትውልድ እንዲባልግ ማድረግ… ወዘተ. እነዚህ ሁሉ የአንድን ህብረተሰብ ጤናማና ሚዛናዊ አገነባብ የሚጻረሩ ናቸው። አንድ ህብረተሰብ ተከታታይነት(Sustainable) እንዳይኖረው የሚያደርጉ ናቸው። የህብረተሰቡ ኑሮ የተዘበራረቀ እንዲሆን በማድረግ ለበሽታ የሚዳርጉት ናቸው። ኃይሉን የሚሟጥጡ ናቸው።

ይሁንና ግን ህዝባችን ብዙ ግፍ እየደረሰበት፣ በምድር ላይ የሚታየው እጅግ የሚዘገንና ህዝባችንም የባሰውኑ በድህነት ዓለም ውስጥ በተወረወረበትና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ በረሀብ አለንጋ በሚገረፍበት አገር ውስጥ አገዛዙና ካድሬዎቹ፣ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ኩሙኒቲው የሚባሉት የአምባገነኖች የጀርባ አጥንት የሚነግሩን በአገራችን ምድር ተዓምር እየተሰራ መሆኑን ነው። ህዝባችንና አገራችን በታሪካችን ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የኢኮኖሚ ዕድገትና ብልጽግና እያዩ ናቸው ነው ብለው የሚነግሩን። ህዝባችን የሚኖረው በአሸበረቁ ቤቶች፣ በጋርተን በተከበቡ ከተማዎች፣ መንደሮችና ከተማዎች በልዩ ዐይነት የትራንስፖርቴሽን መገናኛዎች በመገናኝት ህዝባችን በምድር ላይ የገነት ኑሮን እየኖረ ነው እያሉ ለማሳመን የሚሞክሩት። ምንም ስለኢኮኖሚ ዕድገትና ስለ አገር ግንባታ ምንነት የማይረዱና፣ አንድስ ህብረተሰብ በምን መልክ መደራጀትና መገንባት እንዳለበት ለመገንዘብ የማይፈልጉ እዚህ አውሮፓና አሜሪካ የሚኖሩ የአገዛዙ አቀንቃኞች የሚሉንም ይህንን ነው። አገሪቱ ሌሎች አደጉ የሚባሉ አገሮች ደረጃ ለመድረስ የቀራት ትንሽ ጊዜ ነው እያሉን ነው። ይህንን ዐይነቱን ነገሮችን እየገለበጡ ማየት ከድንቁርናና ከጭንቅላት መዛግ ጋር ማያያዝና ማገናኘት ይቻላል። የግሪክ ፈላስፎች የሚሉት አንድ ግሩም አባባል አለ። ይኸውም ጭንቅላት ከታወረ ዐይን ማየት አይችልም የሚለው ፍልስፍናዊ አባባል ነው። በሌላ አነጋገር ጭንቅላቱ ሰብአዊ በሆነ ትምህርት ያልተዋቀረ ስለሰው ልጅና ስለተፈጥሮ ምንነት ሊረዳ አይችልም። የኑሮ ፍልስፍና ስሌለውም ኑሮው ሁሉ ገንዘብ ከማግኝት የሚያልፍ አይደለም። ስለዚህም ከእንደዚህ ዐይነቱ ጭንቅላታቸው ከታወሩ ሰዎችና ስለ ሰውልጅ ምንነት ከማይረዱ ኢትዮያውያን ምንም የምንጠብቀው ነገር በፍጹም ሊኖር አይችልም። ይህንን ካልኩኝ በኋላ ወደ ተጨባጩ ሁኔታ ልምጣ።

ወያኔ ያልገባውና ሊገባው የማይችለው ነገር !

እስካሁን ድረስ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለብዙዎቻችን እንቆቅልሽ የሆነብን ነገር እንዴት አድርጎ የጠቅላላው ኢትዮጵያ የስልጣኔ ምንጭ ከሆነ አካባቢ ብቅ ያሉ ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች በተቀረው ህዝብ ላይ ሳይሆን በራሳቸውም ታሪክና ስልጣኔ ላይ እንደሚዘምቱ ነው። ሁላችንም አምነን የተቀበልነው ነገር ከአክሱም በፊትም ሆነ ከአክሱም ጀምሮ የነበሩት አገዛዞች ለዛሪዪቱ ኢትዮጵያ የስልጣኔ ምንጮች እንደሆኑ ነው። ወያኔዎች ግን ይህንን በመካድና የራሳቸውን ልዩ ዓለም በመፍጠር የተቀረይቱን ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን እያራቆቷትና ምስቅልቅሏን እያሳጧት ነው። ጠቅላላው ህዝብ የበደላቸው ይመስል ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበር በህዝባችንና በአገራችን ላይ ሁለ-ገብ ጦርነት አውጀውብናል። ራሳቸው በልዩ ደሴት ይኖሩ ይመስልና፣ በራሳቸው ጥረት ብቻ ታላቋን ትግራይ ይገነቡ ይመስል ከፍተኛ ዝርፊያ እያደረጉ ነው። የታሪክ ወንጀል እየሰሩ ነው።

ከዚህ ስንነሳ ወደ ሰሜኑ የውልቃይት ጽጌ ሁኔታ ስንመጣ እጅግ የሚያሳዝንም የሚያስቅም ሁኔታ እንመለከታለን። በመጀመሪያ ደረጃ ያ አካባቢ የወልቃይቶች እንደሆነ ራሳቸው አንዳንድ የትግሬ ምሁራንና የገዢው መደብ አባል የነበሩ አረጋግጠውታል። የትግሬ ክፍለ-ሀገር አካል ነው ብሎ ማውራት የተረት ተረት እንደማውራት ይቆጠራል። በሌላ ወገን ግን ወልቃይትና ጸገዴ ብቻ ሳይሆኑ፣ ጤናማ አስተሳሰብ ያለው ጠቅላላው አገራችን በዚያች ምድር የሚኖር ህዝብ ወይም የተለያዩ ብሄረሰቦች ሀብትና አገርም ነች። በተለይም ስለ ስልጣኔና ስለዕድገት፣ እንዲሁም ስለህብረተሰብና ስለ ህብረ-ብሄር ምስረታ፣ እንዲያም ሲል በአንድ ባንዲራ ስር ስለሚተዳደር ህዝብ የሚያወራ ይህ የኔ መሬት ነው፣ ያ ያንተ ነው ብሎ አንዱ ኢትዮጵያዊ በሌላው ላይ ሊዘምትበት አይችልም። በሌላ አነጋገር ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በጠቅላላው ኢትዮጵያ ምድር በመንቀሳቀስ ህጋዊ በሆነ መልክ፣ የአካባቢውን ህዝብ ሳይጋፋ፣ ሊሰራ፣ መሬት ሊከራይና እዚያው በመቀመጥ ቤት ሰርቶ ሀብት ሊያፈራ ይችላል። ፋብሪካዎች በማቋቋምና የስራ መስኮችም በመክፈት ማህበራዊና ህብረተሰብአዊ ግዴታውን ሊወጣ ይችላል። ይህ ጤናማ አካሄድ ለማንኛውም በአንድ አገር ውስጥ ለሚኖር ህዝብ ለዕድገቱ እጅግ አስፈላጊ ነው። ይህ የኔ ክልል ነው አትድረሰብኝ ቢል በራሱ ላይ ነው የሚፈርደው። የዕውቀትና የሀብት መንሸራሸር እንዳይኖር ነው የሚያደርገው። አካባቢው እንዳይለማና ቀሰ በቀስም ህብረተሰብአዊ መተሳሰርና መደጋገፍ እንዳይኖር ነው የሚያደርገው። በአጭሩ የዕድገትና የስልጣኔ ዕንቅፋት በመሆን አንድ ህዝብ ለዝንተ-ዓለሙ በጨለማ ዓለም ውስጥ እንዲኖር ያደርጋል። ከዚህ ስንነሳ በወልቃይት-ጸገዴና በትግሬ ብሄረሰብ መሀከል የረጅም ዐመታት መተሳሰር ያለና፣ በተለይም ከትግሬ እየመጡ እዚያው እየሰሩና ሀብት እያፈሩ መኖር የተለመደ ነገር ነው። ነግሩ መበላሽት የጀመረው ወያኔዎች ትግል ሲጀምሩና ታላቋን ትግሬ እንመሰርታልን ብለው ወደ ድል ካመሩና አዲስ አበባ ላይ ቁጥጥ ማለት ከጀመሩ ወዲህ ነው።

ይህንን ህልማቸውን ዕውን ለማድረግ ስልጣን ከመያዛቸው በፊትም በኋላ ሆነ በወልቃይት ጸገዴ ኗሪ ሰዎች ላይ አሰቃቂ ድርጊቶችን ፈጽመውባቸዋል። የህዝቡ ቁጥር እንዲቀንስ እንደ ቢልጌት ከመሳሰሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጥቁር ህዝብ ቁጥር እንዲቀንስ እጅግ አደገኛ ስራ ከሚሰሩ ከናጠጡ ሀብታሞች ጋር በመመሰጣጠር የአማራው ህዝብ ቁጥር እንዲቀንስ የስትሬላይዜሽን ፕሮግራም ተግባራዊ አድርገዋል። ብዙ ጥናቶችም እንደሚያመለክቱት ወያኔ ስልጣን ከያዘ በኋላ የአማራ ብሄረሰብ ቁጥር ወደ አራት ሚሊዮን ያህል ቀንሷል። ብዙ ለአቅመ አዳም የደረሱ ሴቶች የወር አበባቸውን እንዳያዩና እንዳያረግዙ ተደርገዋል። በተለይም በወንዶች ላይ አስቃቂ ግፍ ተፈጽሞባቸዋል። በጠራራ ጸሀይ የተገደሉት ዘመዶቻቸው ሬሳቸውን ለማንሳት ሲሯሯጡ የለም አሞራ ይብላው በመባል ተከልክለው የሰው ልጅ የአሞራና የጅብ እራት ተደርጓል። ይህ አጉል የጥላቻ ዘመቻ ሳይሆን በግልጽ የተካሄደ ነው። ይህ ድርጊት ፋሺስታዊ ድርጊት ነው። ሌላ ሊባል አይችልም።

ያም ሆነ ይህ፣ ይህ የወያኔ እጅግ አስቃቂ ድርጊትና ታላቋን ትግሬን የመገንባት ህልም ምንድነው የሚያረጋግጠው? በአጭሩ ይህ ድርጊታቸው የሚያረጋግጠው ድንቁርናቸውን ነው። የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ ያልተረዱ መሆናቸውን ነው። በመጀመሪያ ደረጃ፣ አዲስ አበባ ተቀምጦ የኢትዮጵያን ህዝብ ወክላለሁ ብሎ ወደ ውጭ ዕውቂያን ያገኘ አገዛዝ አንድን አካባቢ በመሸንሸን ወይም ቆርጦ በመውሰድ የትግሬ አካል ለማድረግ መሞከር ከማሰብ ኃይል ጉድለት የሚመነጭ እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ በታሪክ ውስጥ አንድ ወጥ የሆነ ብሄረሰብ ስልጣኔንና ዕድገትን ያመጣበትና የመነጠቀበት ሁኔታ በታሪክ ውስጥ ታይቶ አይታወቅም። የስልጣኔን ታሪክ በደንብ ለተከታተለ አገሮች ሊያድጉና የአንድ አገር ህዝብም የመፍጠር ችሎታው ሊዳብር የሚችለው፣ አንደኛው ከሌላው ህዝብ ወይም ብሄረሰብ ጋር ሲጋቡ፣ ሲቀላቀሉና የሃሳብና የባህል ልውውጥ ሲያደርጉ ብቻ ነው። ከማዕከለኛው ምስራቅ አገሮች፣ ሶሪያ፣ ኢራክና ሌሎች የአካባቢው አገሮች ከሁለትና ከሶስት ሺህ ዘመናት በፊት ከተለያዩ አካባቢ የፈለሱ ህዝቦችን በማስተናገድ ነው በዘመኑ ስልጣኔያቸውን የተገናጸፉት። የግብጽ ስልጣኔ የኋላ ኋላ ዕምርታን ሊያገኝ የቻለው በታላቁ አሌክሳንደርና፣ ከሌላ አካባቢ በመጡ ፈላስፎችና ምሁራን አማካይነት ነው። በስድስተኛውና በአምስተኛው ክፍለ-ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት አዮን በምትባለው ደሴት የግሪኩ ስልጣኔ ሲያብብ ከግብጽና ከህንድ በመጡ ዕውቀቶች፣ ነጋዴዎችና የዕደ-ጥበብ ሰዎች አማካይነት ነው። በአውሮፓ ምድር ውስጥም ከአስራአራተኛው ክፈለ-ዘመን ጀምሮ ቀስ በቀስ ስልጣኔ ዕምርታን ማግኘት የቻለው ከተለያዩ አካባቢዎች በመጡ ህዝቦች አማካይነት እዚያ ሲጋቡና ዕውቀታቸውን ሲያዳብሩ ነው። ጀርመንም ወደ ኋላ በቀረችበት በ18ኛውና በ19ኛው ክፍለ-ዘመን የፕረሽያ ነገስታት ወይም ሞናርኪዎች ከሆላንድና ከፈረንሳይ በሃይማኖት ሰበብ የተባረሩ አዋቂዎችን በማስተናገድና ቴክኖሎጂውን ውስጣዊ በማድረግ ነው ከሌሎች እርምጃዎች ጋር ተደምሮ ጀርመን በአንድና በሁለት ትውልድ ለማደግ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ ኢኮኖሚ መገንባት የቻለችው። ሆላንድ ራሷ በ17ኛው ክፍለ-ዘመን፣ እንግሊዝ ደግሞ እንደዚሁ በ18ኛው ክፍለ-ዘመን ከወጭ ዕውቀታቸውን ይዘው በመጡና እዚያው ኗሪ በሆኑ ይሁዲዎችና ሌላ ዘሮች አማካይነት ነው የኢንዱስትሪ አብዮት ባለቤት ለመሆን የበቁት። ዛሬ አሜሪካን ኃያል መንግስት ሆኖ ብቅ ማለት የቻለው ከተለያዩ አገሮች የመጡ ህዝቦችን በማስተናገድ ነው። ይህ ዐይነቱ ህብብረተሰብአዊ ዕድገት በተፈጥሮ ውስጥ ይታያል። ሞኖ ካልቸርድ የሆኑ ሰብሎች በቀላሉ ለተባይ ይጋለጣሉ። ሌላ የሚከላካለቸው የሰብልና የአትክልት ዐይነት ከወደመ የማደግና የመዳበር ኃይላቸው የመነመነ ነው። ለጊዜው በማዳበሪያ ኃይል ምርታማ ቢሆኑም ከጊዜ ብዛት በኋላ ምርታማነታቸው በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ ነው የሚመጣው። በቀላሉ ለተባይም ይጋለጣሉ። በሌላ አነጋገር መቀላቀልና መደጋገፍ የተፈጥሮ ህግና ለዕድገትም በጣም አመቺ ነው። በዚያውም መጠን ውስጣዊ ጥንካሬን ያገኛሉ።

ከዚህ ስንነሳ የወያኔ የአማራን ዘር እያጠፉ የራስን ግዛት ለማስፋፋትና ለማበጥ መሞክር በፍጹም ወደ ዕድገት የሚያመራው አይደለም። ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት የትግሬ ብሄረሰብ ከሌላው ህዝብ ጋር ሲጋባና ሲቀላቀል ብቻ ነው ጤናማ ዕድገትን ሊጎናጸፈ የሚችለው። የወያኔዎች ትልቁ ችግር ከውጭ ኢንዱስትሪ እያንጋጉ በመትከል ዕውነተኛ ዕድገትን የሚጎናጸፉ መስሏቸዋል። በታሪክ ውስጥ እንደተረጋገጠው የቴክኖሎጂ ምጥቀትና በኢንዱስትሪ ማደግ ኢቮሉሺናዊ አካሄዶች ናቸው። በምዕራብ አውሮፓ ውስጥ ከሞላ ጎደል ጤናማና የተስተካከለ ዕድገት ሊመጣ የቻለው የኢንዱስትሪ ዕድገት ከታች ወደ ላይ (Organic Grwoth) በመጓዙ ነው። በሌላ አነጋገር በመጀመሪያ የሚያማምሩ ከተማዎችን በመገንባት፣ ለህዝብ መኖሪያ ቦታዎችን በመስራት፣ የገበያ አዳራሾችንና ሌሎች ህዝቡን ሊሰበስቡና የፈጠራ ችሎታውን ሊያዳብሩ የሚችሉ ነገሮች በመስራት ነው።በመጀመሪያ ደረጃ በዕደ-ጥበብ አማካይነትና(Industrialiazation before Industrialization) በንግድ መዳበር የሀብት ክምችትን በማዳበር ነው ወደ ኢንዱስትሪ አብዮት መሸጋገር የቻሉት። በዚህም ምክንያት የተነሳና በከፍተኛ ደረጃ የህዝብና፣(Social Mobility) የሀብት(Capital) እንቅስቃሴ አማካይነት በቀላሉ ማደግና መበልጸግ ችለዋል። ይኸኛው ነው ጤናማው የካፒታሊዝም ዕድገት። በአንፃሩ ይኸኛውን ጤናማውን የዕድገት ጉዞ ያልተከተሉ እንደ ብራዚል፣ ሜክሲኮና ብዞዎች የአፍሪካ አገሮች ውስጥ መዘበራረቅ የሚታየውና ስርዓት ማጣትና የሀብት መባከን ሊፈጠር የቻለው ተፈጥሮአዊ የሚመስለውን የህብረተሰብ አገነባብና የኢኮኖሚ ዕድገት አካሄድ ባለመከተላቸው ነው። በሌላ አነጋገር በአንድ ወጥ ብሄረሰብና ከላይ ወደ ታች በሚጫን የኢንዱስትሪ ተከላና ጋጋታ ሚዛናዊ ዕድገት ሊመጣ አይችልም። የህዝቡም የመፍጠር ኃይል ውስን ስለሚሆን ቲክኖሎጂያዊ ምጥቀት ሊታይ አይችልም።

ስለሆነም አንድን ህዝብ እየጨረሱና መሬትን እየቆረሱ በመውሰድ ታላቋን የትግሬን ሬፑብሊክ እንመሰርታለን፣ ጠንካራ ኢኮኖሚ እንገነባለን፣ በዚህም አማካይነት የተቀረውን የኢትዮጵያ ክፍል የጥሬ-ሀብት አምራችና ላኪ በማድረግ አቀጭጨን እናስቀረዋለን የሚለው ህልም በፍጹም የሚሰራ አይደለም። ከዚህ ባሻጋር የአንድ አገር ዕድገት በኢንዱስትሪ መንጋጋት ብቻ የሚገለጽ አይደለም። የአንድ ህዝብ ዕድገት ሁለንታዊ ነው። በሚያማምሩ ከተማዎችና መንደሮች የሚገለጽ ነው። በቲያትርና በሙዚቃ እንዲሁም በሙዚየሞች የሚታይ ነው። በጋርደኖችና በተለያዩ የመገናኛ ማመላለሻዎች የሚገለጽ ነው። እንደዚህ ዐይነቱ በልዩ ልዩ መልክ የሚገለጸው ስልጣኔ ከአንድ ብሄረ-ሰብ በተውጣጣና ከሌላው ጋር ባልተቀላቀለ በፍጹም ተግባራዊ ሊሆን የሚችል አይደለም። ከዚህ ይልቅ ወደድንም ጠላንም ብዙ ብሄረሰቦችን የሚያሰተናግደውና፣ በተለያዩ ነገሮች የሚገለጸው፣ ግን ደግሞ የተሳሰረው የተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ጥሩና አገር ወዳድ መንግስት ካገኘ ከሃያ እስከ ሃምሳ ዐመት ባለ ጊዜ ውስጥ የተስተካከለ ዕድገትን ሊያመጣ ይችላል። የኦሮሞው፣ የጉራጌው፣ የጎሙ-ጎፋው፣ የወላይታው፣ የከፍቼው፣ የአማራውና የሌሎችም ጤናማ አስተሳሰብ ወደ ዕድገት አቅጣጫ እንዲመጣ ከታቀደና ከተጠና ባጭር ጊዜ ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሁለ-ገብ ዕድገት ሊታይ ይችላል። ይሁንና እነዚህ የተቀሩት የኢትዮጵያ ግዛቶች ለማደግና በአጭር ጊዜ ውስጥ ዕምርታን ለማግኘት ከምዕራብ አውሮፓ የካፒታሊስት አገሮች ቴክኖሎጂን መስረቅና መኮረጅ አለባቸው። ብዙ ነገሮች የተፈጠሩ ስለሆነ ከእንግዲህ ወዲያ ብዙም አዲስ ነገር መፍጠር አንችልም። ጥያቄው ከውጭ የሚመጣውን ቴክኖሎጂ እንዴት አድርገን ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር ማገናኘትና ህዝቡ የራሱ በማድረግ ሊያሻሽላቸው ይችላል? በሚለው ላይ ነው በየጊዜው ምርምር መደረግ ያለበት።

ያም ሆነ ይህ የወያኔዎች ሀብትን መዝረፍና ህዝብን እያፈናቀሉ ለማበጥና ለማደግ፣ እንዲያም ሲል ሌላውን ለመዋጥና አቀጭጮ ለማስቀረጥ መሞክር ገደብ የሌለው ድንቁርና ነው። ሳይንሳዊ አካሄድ አይደለም። የራሱን የትግሬ ህዝብ የሚያቀጭጨውና ዘለዓለሙኑ እየፈራና እየተባ እንዲኖር የሚያደርገው ነው። በራሱ ላይ እንዳይተማመን የሚያደርገው ነው። በሌላ ወገን ደግሞ ተሰርቶ ባልተገኘ ሀብት በመዘባነን ሌላውን የሚንቁበት ሁኔታ ይፈጠራል። ይሁንና ግን በዚህ አካሄዳቸው ወያኔዎች የተቀረውን የዋሁን የትግሬ ብሄረሰብ እየጠቀሙት እየመሰላቸው የመጨረሻ መጨረሻ እርቃኑን እንዲቀር እያደረጉት ነው። ይህ አስተሳሰባቸውና አካሄዳቸው እንዲሁም ኢ-ሰብአዊ ድርጊታቸው በተገለጸላቸውና የበላይነት ስሜት በማይሰማቸው የትግሬ ምሁራን መቆም ያለበት ጉዳይ ነው። ይህ የወያኔዎች አካሄድ በተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ፣ በተለይም በአማራው ላይ ብቻ ያነጣጠረ ሳይሆን በጠቅላላው በጥቁር ህዝብና ስልጣኔው ላይ ያነጣጠረ እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው። ስለሆነም እንደዚህ ዐይነቱ የአንድን ብሄረ-ሰብ የበላይነት ለማጎልመስ የታቀደ ህልም በእንጭጩ መቀጨት አለበት። የዕድገትና የስልጣኔ ፀር ነው። ጠቅላላው ህዝብ እየተሸማቀቀ እንዲኖር የሚያደረገው ነው። ስለሆነም ወያኔ የግዴታ ዲሞክራሲያዊ በሆነና በሰለጠነ አገዛዝ መተካት አለበት።

ኢ-ሳይንሳዊ የፖለቲካ አካሄድ !

በአገራችን የፖለቲካ ትዕይንት ታሪክ ውስጥ ቢያንስ አብዮቱ ከፈነዳበት ጊዜ ጀምሮ ስለ ፖለቲካ ስልት ያለን ግንዛቤ ሳይንሳዊ ያልሆነና ፍልስፍናዊ መሰረት የሌለው ነው። ፖለቲካ የሚባለው ህብረተሰብን የሚያረጋጋ፣ አርቆ-አሳቢ አድርጎን በማሰብ ኃይላችን እንድንፈጥር፣ አስተሳሰባችንን በማሾል የህብረተሰባችንን ሁኔታና በፖለቲካው መስክ የሚታየውን የተጣመመ አካሄድ በተወሳሰበ መልክ በመተንተን እንድንረዳውና መፍትሄም እንድንሻ የሚያደርገን ሳይሆን፣ የስልጣን መወጣጫና የራስን ጥቅም ማሳደጃ ሆኖ ነው የተገነዘብነውና ይህንንም እንደስልት የተጠቅምንበት። ከዚህም በላይ ፖለቲካ ህብረተሰብአዊ ፕሮጀክትን ለማካሄድ የሚጠቅም መሳሪያና፣ በህብረተሰብ ውስጥ የሚከሰቱ ቅራኔዎችን በሳይንስ እየተነተኑ መፍቻ መስጫ መሳሪያ እንዳልሆነ ነው ሁላችንም እንድነረዳው የተደረገው። በዚህም ምክንያት የተነሳ ፖለቲካ የሚባለው በስሜታዊነት የታመቀ፣ የራሳቸው አጀንዳ ያላቸው ግለሰቦች እነሱን የሚመስል ስልጣንን ብቻ የሚመኝ አድርባይ እየፈለጉ በቡድን የሚደራጁበትና፣ አንዱን በማራቅ ሌላውን በማስጠጋት አንድን አገርና መንግስትን የግላቸው ሀብት አድርገው በመቁጠር በነሱ የተወላገደ አስተሳሰብ የማይስማማውን ሁሉ የሚወነጅሉበትና የሚያርቁበት መሳሪያ ሆኖ ነው የተወሰደው። ይህ ዐይነቱ የፖለቲካ አመለካከት ግንዛቤ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ በየካቲቱ አብዮት ዘመን እንደታየው የዲሞክራሲንና የማርክሲዝምን አርማ አንግቦ ዲሞክራሲ ያለገደብ እያለ የሚጮኸው ሁሉ ጠብመንጃ አንስቶ ወንድሙን የሚገድልበትና የሚያሳድድበት መሳሪያ ለመሆን በቃ። ፖለቲካ ሳይንስና ህይወት ያለው፣ ህዝብን የሚያቀራርብና ለስራ የሚያዘጋጅና ህብረተሰቡንም በየረድፉ አደራጅቶ ታሪክን ለመስራት የሚጠቅም መሳሪያና በየጊዜው እየተሻሻለ በየወቅቱ የሚከሰቱ ችግሮችን መፍቻ ዘዴ ከመሆን ይልቅ አንድን አገር ወደ ጦርነት አውድማነት መለወጫ መሳሪያ ሆነ። አብዮቱ ተቀለበሰ ከተባለና የብዙ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ህይወት ከጠፋ ከሰለሳ ዐመታት በኋላም አሁንም ቢሆን የፖለቲካ ግንዛቢያችን ይህንን ያህልም የተለወጠ አይመስለኝም። ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ምሁራዊነትን ያካተተ፣ የአንድን የህብረተሰብ ታሪክ በደንብ ያገናዘበና የዕድገቱንም ውጣ ወረድነት በደንብ ለመተርጎም የሚያስችል፣ ፍልስፋናዊና ሳይንሳዊ ዕውቀትን ምርኩዝ ያደረገ ለመሆኑ ብዙዎቻችን ጭንቅላት ውስጥ በፍጹም የለም። ከዚህም በላይ ለፖለቲካ እታገላለሁ የሚል ግለሰብም ሆነ ቡድን የግዴታ መንፈሳዊ ነፃነትን መቀዳጀትና፣ ከማንኛውም ለአንድ ህብረተሰብ ዕድገት ጠንቅ ከሆኑ ዕቡይ ተግባሮች መላቀቅን እንደሚጠይቅ እስከዚህም ድረስ ግልጽ አይደለም። በመሰረቱ ዕውነተኛ የፖለቲካ ሰው ስነ-ምግባራዊና ግብረ-ገባዊ ነው። ለአንድ ቡድን ወይም ብሄረሰብ ያደላ ሳይሆን ግዴታውና ኃላፊነቱን የአንድን ህዝብና የአገርን ደህንነት መጠበቅ ነው። ታሪክን ለመሰራት የሚችልና ለዚህም ለሰፊው ህዝብና ለተከታዮቹ ብቃት ያለው አመራር የሚሰጥ መሆን አለበት። ወደ አገራችን ስንመጣ እነዚህ መሰረተ-ሃስቦች በፍጹም የተጤኑና ከሰውነት ጋር የተዋሃዱ አይደሉም።

የዚህ ሁሉ ችግር ምንድነው ? በህብረተሰብአችን ታሪክ ውስጥ የህዝብን ችግር ስልጣን በመያዝ አማካይነት እንፈታለን ተብሎ ትግል ሲጀመር ከመጀመሪያውኑ ከታች ወደ ላይ መጠናት ያለባቸውን ነገሮች፣ ማለትም ፍልስፍና፣ ሳይንስና የቲዎሪ ዘዴዎች ላይ ለመረባረብ ገቱና ዘዴው የለንም። እነዚህም ነገሮች እንደ ቅድመ-ሁኔታዎች መወሰድ ያለባቸውና በጭንቅላትም ውስጥ መቋጠር እንዳለባቸው ግንዛቤ የሚያደርግ የለም። ከዚህም በላይ ተነጻጻሪ ጥናት(Comparative studies) በሚባለው በህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ የተለያዩ ህብረተሰቦችን ለማወዳደር የሚያስችል የቲዎሪና የኢምፔሪካል ጥናት ላይ ትኩረት ለመስጠት አለመፈላገችን ከመጀመሪያውኑ ለፖለቲካ የሚደረገውን ትግል የተኮላሸ አድርጎታል። እንዲዚህ ዐይነቱ የተቻኮለና መሰረት የሌለው የፖለቲካ ትግል ዘዴ የግዴታ የሸፍጠኝነትን ስልት ለሚያስቀድሙ በሩን ይከፍትላቸዋል። ከመጀመሪያውኑ ሰፋና ጠለቅ ያለ ዲሞክራሲያዊ ውይይት ስለሚዳፈን፣ የፖለቲካ ድርጅትን ለመመስረት የሚታገሉ ግለሰቦች የግዴታ ለማዳመጥና ለመደማመጥ ለማይፈልግ ካድሬያዊ ፖለቲካ መንገዱን ሁሉ ያመቻቻሉ። በዚህም ምክንያት የተነሳ ታሪክ መስሪያና የስልጣኔ መንገድ ቀዳጅ የሆነው በሳይንስ ላይ የተመሰረተው ፖለቲካ ወደ ቡድናዊነትና መፋጠጫ መድረክ በመለወጥ፣ በርዕዮተ-ዓለም ዙሪያ የሚደረግና የሚካሄድ ትግል ያስመስለዋል። በመሰረቱ ግን ያለፈውን ሃምሳ ዐመት ያህል የሚጠጋውን የፖለቲካ ትግል ታሪካችንን ለተመለከተ ፊዩዳላዊና ጠባብ አስተሳሰብን ያዘለ ነው። በርዕይ ደረጃ አንድን ህብረተሰብ ለመገንባትና መረጋጋት እንዲፈጠር የሚያስችለው ይኸኛው የፖለቲካ አመለካከት ነው በሚለው ላይ አይደለም ትግሉና ክርክሩ ያተኮረውና ይካሄድ የነበረው። እኔ እስከማውቀው ድረስ የግራ ፖለቲካንም ሆነ፣ ባለፉት ሃያ አምስት ዐመታት በሊበራል ርዕዮተ-ዓለምና በነጻ ገበያ ስም የተካሄደውን ትግል ስመለከት ትግሉ በቲዎሪ፣ በሳይንስና በፍልስፍና ላይ ያተኮረና የተመረኮዘ አይደለም። በመሆኑም ይሁ ሁኔታ የግዴታ አድማሳችንን በማጥበብ በድፍረትና በራስ በመተማመን በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ትግል ማካሄድ እንዳንችል አድርጎናል። ያለፈውን አስርና አስራአምስት ዐመት የፖለቲካ ትግላችንን ስንመለከት በዚህ ዐይነቱ አካሄዳችን ብዙም ስለ ስልጣኔም ሆነ ስለህብረተሰብ ግንባታ ለማይነግሩንና ለመተንተን ለማይችሉ ግለሰቦች በሩ ተከፍቷል። ከፖለቲካዊ ክርክርና ውይይት ይልቅ የራሳቸውን የበላይነት ለማስፈን ለሚፈልጉ ግለሰቦች አመቺ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል። በተለይም የግንቦት ሰባቱ ምርጫ ውጤት ሊከሽፍና ህዝባችንም አስራአንድ ዐመት ያህል የግፍ ጽዋን እንዲቀምስና እንዲሰቃይ የተደረገው ይኸኛውን በግለሰቦች ዙሪያ የሚካሄደውን የትግል ፈሊጥ በመከተላችን ነው።

ከዚህ መጠን ብሎ ስለቀረበው ስለፖለቲካ ያለን ግንዛቤ ስንነሳ የወያኔን የተጣመመ ፖለቲካ አካሄድና ህዝብን ማከረባበቻ መሳሪያ አድርጎ መቁጠር መገንዘቡ ከባድ አይሆንም። ወያኔ የትግሬዎች ድርጅት ስለሆነ ነው ይህንን ዐይነቱን የማከረባበት ፖለቲካ ሊያካሂድ የቻለው ከሚለው ቀላል አስተሳሰብ መነሳቱና መደምደሚያ ላይ መድረሱ ለችግራችን መፍትሄ ሊሆን አይችልም። ይህ ዐይነቱ አካሄድ የራሳችንን ድክመት ከመሸፈኑም ባሻገር የአገራችንና የህብረተሰብአችንን አወቃቀርና፣ እንዲሁም የፖለቲካ ባህል እንዳንረዳው ያግደናል። በሌላ ወገን ደግሞ የድርጅቱን ታሪክ ለተመለከተና፣ የኋላ ኋላ ወደ ማፊያነት መለወጥ የግዴታ የመጣበትን ብሄረሰብ ተገን እንዲያደርገው አድርግታል። ይሁንና ግን እስከተወሰነ ደረጃ ድረሰም ቢሆን የህብረተሰብ መሰረቱን(Social Base) ለማስፋት እንደጣረና፣ በተለይም ተጨቆኑ የሚባሉትንና ለሆዳቸው ያደሩትን በመሰብሰብና በጥቅም በመግዛት የተወሰነ ሌጂቲሜሲ ለማግኘት እንደቻለ የማይታበል ሀቅ ነው። ይህ ባይሆን ኑሮ ሃያ አምስት ዓመት ያህል ስልጣን ላይ ለመቆየት ባልቻለ ነበር። ከዚህም በላይ ኢትዮጵያን ለማዳከምና አቅመ-ቢስ አድርጎ ለማቆየት የሚፈልጉ ኢምፔሪያሊስት ኃይሎችን ተገን በማድረግ ዓለምአቀፋዊ ዕውቅናን በማግኘት እነሱ የሚፈልጉትን ፕሮጀክት እንዲሰራላቸው ዕድል አገኙ። ወደ ሶሻል መሰረቱ ስንመጣ ወያኔ ሁለት አካሄድን የመረጠ ይመስላል። በአንድ በኩል ከዚህም ሆነ ከዚያኛው ብሄረሰብ የተውጣጡ ግለሰቦችንና፣ በአብዮቱ ዘመን የዚኸኛው ወይም ያዚያኛው የፖለቲካ ድርጅት አባል የነበሩ ግለሰቦችን ሲያቅፍ፣ በሌላ ወገን ደግሞ በማፊያ ስራ የተሰማራና በተለይም በራሳቸው ጥረት በማደግ ላይ የሚገኙ ግለሶቦችን በማስፈራራት፣ ውዝፍ ቀረጥ አልከፈላችሁም በማለት ወደ እስር ቤት ውስጥ መክተትና ሀብታቸውን መንጠቅ፣ አንዳንዶችን ደግሞ በመግደልና ይህንን የፖለቲካ ስልቱ በማድረግ እስካሁን ድረስ ቆይቷል። ይህንን ዐይነቱን ማፊያዊ ፖለቲካውን የሚከተለው ያልተማሩና ያለተገለጸላቸውን ትግሬዎችን በመጠቀም ነው።

የውጭውን ዓለም ድጋፍ ለማግኘት ሲል ደግሞ አውቆም ሆነ ሳያውቅ ድህነትን ፈልፋይ የሆነውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን በቀመበልና ተግባራዊ በማድረግ ዕውነተኛ የሊበራል የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አራማጅ ሆኖ ቀረበ። በዚህም ምክንያት የተነሳ እስካሁን ድረሰ ቢያንስ ወደ 40 $ ቢሊዮን የሚቆጠር ዕርዳታ በማግኘትና ራሱን በማደለብ ስልጣኑን ለማጠናከር ቻለ። ከዚህ ስንነሳ በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ተንታኞች ወያኔ ብቻውን እንደቆመና ካለውጭ ዕርዳታ እዚህ ለመድረስ እንደቻለ የሚሰጠው ትንታኔ ኢ-ሳይንሳዊ ብቻ ሳይሆን በጣም አደገኛም ነው። የውጭ ኃይሎች ለአንድ ደካማ አገር ዕርዳታ የሚሰጡት በእርግጥም የዚያ አገር መንግስት እነሱ የሚፈልጉትን ፖለቲካ፣ በተለይም ደግሞ የትርምስና የጦር ፖለቲካ እስካካሄደ ድረስ ብቻ ነው። የውጭ ኃይሎች በተለይም እንደ አሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የመሳሰሉት የአገራችንን በሳይንስና በቴክኖሎጂ ዳብሮ የተረጋጋና የተከበረች አገር እንዲገነባ አይፈልጉም። በራሱ የሚተማመን አገር ወዳድ ዜጋና ባህሉን ዕምርታ እየሰጠ የሚጓዝ ትውልድ የነሱ ጠላት እንደመሆኑ መጠን እንደዚህ ዐይነቱ ትውልድ ስልጣን ላይ እንዲመጣ በፍጹም አይፈልጉም። በመሆኑም አሁንም በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን የሚቀርበው „እሮሮ አሜሪካ ጊዜው ሳያመልጥህ ቶሎ ብለህ የህዝባችን ወዳጅ ሁን“ የሚለው አቤቱታ እጅግ አደገኛና ትጥቅ አስፈቺ ነው። ህዝባችን የዲሞክራሲንና የነጻነት እንዲያም ሲል የስልጣኔን ብርሃን እንዳያይ ከመጀመሪያውኑ በሩን እንደመዝጋት የሚያስቆጥር አደገና አካሄድና ትጥቅ አስፈቺ ነው። አደገኛ የሆነ በፖዘቲቭ ሳይንስ ላይ የተመሰረተ የድህነቱንና የጨለማውን ዘመን የሚያራዝም ነው። ከዚህም በላይ የአገራችን የሶስት ሺህ ዐመት ታሪክና በተደጋጋሚ ሊወሩ የመጡ የውጭ ኃይሎችን በጀግና ልጆቿ አማካይነት መክታ የመለሰችውን አገርና የጀግና ልጆቿን ታሪክ እንደማንቋሸሽ ይቆጠራል። ለኢትዮጵያ ህዝብ ያዘኑ ይመስል በየጊዜው እንደዚህ ዐይነት የእሮሮ ድምጽ ማሰማትና ደብዳቤ መጻፍ ከዓለም ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ የተለያዩ የአሜሪካ አገዛዞች በታሪካቸው ውስጥ ዕውነተኛ ሰብአዊነትን ያሳዩበትና እሴትም(Values) አላቸው የሚያስብላቸው ታሪክ የላቸውም። የዛሬይቱ አሜሪካ ታላቅ ሆኖ ብቅ ማለት የቻለው በመጀመሪያ ደረጃ 17 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢንዲያኖችን ከጨፈጨፈ በኋላ ነው። ከዚያም በኋላ ጥቁር አሜሪካንን በፕላንቴሼን ኢኮኖሚ ላይ በማሰማራትና በመበዝበዝ ነው የካፒታል ክምችትን በማዳበር በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረት ዕድገትን ለመጎናጸፍ የቻለው። እስከ 1960ዎቹ አጋማሽ ድረስ ጥቁር አሜሪካውያን እንደ ነጩ በዕኩልነት የማይታዩ አልነበሩም። ይህ ሁኔታ በመሰረቱ አሁንም ቢሆን ስር ሰዶ ያለ ነው። ብዙ ጥቁር አሜሪካውያን ተነጥለው የሚኖሩና ከነጩ ጋር ሲወዳደር ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲዎች ገብቶ የመማር ዕድላቸው በጣም የመነመነ ነው። በተጨማሪም ባልተመጣጠነ የምግብ ዐይነትና በድህነት የተነሳ በብዛት በተለያዩ የስልጣኔ በሽታዎች በሚባሉት የሚሰቃየው ጥቁር አሜሪካዊ ነው። ከዚህ ስንነሳ የአሜሪካንን አገዛዝ እሴት(Values) ያለው አገዛዝ አድርጎ ማቅረብ የጥቁርን ህዝብ መስደብ ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ደረጃ ታሪክንም ማጣመም ነው።

ሌላው ቢቀር ቢያንስ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ያለውን ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ ሁኔታ በምንመረምርበት ጊዜ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በምንም ዐይነት ዲሞክራሲና ብልጽግናን በሶሰተኛው ዓለም አገሮች፣ በተለይም በአፍሪቃ፣ በላቲንና እንዲሁም በማዕከለኛው አሜሪካ እንዲሰፍንና፣ እነዚህ አገሮች ራሳቸውን እንዲችሉ ያደረገበት ጊዜ የለም። በእነዚህ አገሮች ውስጥ ሁሉ የተካሄዱት የመንግስት ግልበጣዎችና በኮሙኒዝም ስም እየተሳበበ ለዲሞክራሲና ለዕድገት የታጋሉ ግለሰቦች እንዲታረዱ፣ ወደ እስርቤት እንዲወረወሩና እንዲሰቃዩ፣ የተረፈው ደግሞ ወደ ውጭ አገር እንዲሰደድ የተደረገው በአሜሪካን ኢምፔረያሊዝም ዕውቅ ፖሊሲና ድጋፍ ነው። እስካሁን ድረስም አብዛዎቹ የላቲንና የማዕከለኛው አሜሪካ አገሮች በብዙ ሺህ ድሮች በተሳሰሩ ችግሮች የሚሰቃዩት ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በተዘረጋው አገሮችን ከማዳከም የሚሊታሪ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ የአሜሪካን ስትራቴጂ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ አሜሪካና የተቀሩት የምዕራብ አውሮፓ አገሮች እነሱ ብቻ በተቀረው የዓለም ህዝብ ላይ የበላይነትን ይዘው ለመቆየት ሲሉ በሊበራሊዝምና በነጻ ገበያ ስም በአገሮች ላይ ጭነት በማድረግ፣ አልቀበለም ያሏቸውን ደግሞ ተቃዋሚ የሚሏቸውን ቡድኖችንና ግለሰቦችን በገንዘብ፣ በሃሳብና በጦር መሳሪያ በመደገፍ በአንድ አገር ውስጥ በወንድማማቾች መሀከል ጦርነት እንዲካሄድና ደም እንዲፈስ ያደርጋሉ። ዋናው ስትራቲጄያቸውም በተለይም ጥንታዊ የታሪክ አገሮችን፣ እንደ ኢራክ ሊቢያና ሶሪያ የመሳሰሉትን አዳክሞና አገሮችን በጎሳ ነጣጥሎ ትናንሽ አገሮች እንዲፈጠሩ ማድረግ ነው። ከዚህም በላይ በዩጎዝላቢያ ላይ የተካሄደው ጣልቃ ገብነትና በኋላም የይጎዝላቢያ መበታተን፣ በቅርቡ ደግሞ ዩክሬይንና የተቀሩትን የባልቲክ አገሮችን አሳቦና ተገን አድርጎ ራሺያን መክበብና ወደ ጦርነት ውስጥ እንድትገባ ማድረግ ዋናው የአሜሪካን፣ የእንግሊዝና የተቀረው የምዕራብ አውሮፓ አደገኛ ፖለቲካ ነው። በመሆኑም አሜሪካን ለኢትዮጵያውያን የተለየ ሊሆን አይችልም። ብዙ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡትና ካለብዙ ጭንቀትም መገንዘብ እንሚቻለው እስከየካቲቱ አብዮት ድረስና፣ በኋላም አሜሪካ ኢትዮጵያ እንድትዳከምና ቀጭጫ እንድትቀር ያላደረገው ሙከራ ይህ ነው አይባልም። ኢትዮጵያችንም በትናንሽ አገሮች እንድትሰነጣጠቅ የማያደርገው ጥረት ይህ ነው አይባልም። በአሜሪካ አማካይነት ነው „ኢትዮጵያ ዘመናዊነትን ለመጎናጸፍ የቻለችው፣ እኛም የስኮላርሺፕ ዕድል ለማግኘት የቻልነው“ የሚለው አባባል ዘመናዊነት(modernization)ማለት ምን ማለት እንደሆነ ካለመገንዘብ የተነሳ የሚነፍስ አደገኛና አሳሳች አባባል ነው። ዘመናዊነት በሚለው ዙሪያ የተደረገውን ሰፊ የቲዎሪ ትንተናና ኢምፔሪካል ምርምር ለተመለከተ ከ1945 ዓመት በኋላ በአገራችንም ሆነ በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የተካሄደው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዝብርቅርቅነትን ያመጣና አዲስ ህብረተስብአዊ ግኑኝነትን የፈጠረ ነው። ይህንን ዐይነቱን ዘመናዊነት ለመረዳት ደግሞ፣ በቀላሉ የኛንና የብዙ የሶስተኛውን ዓለም አገሮች ከካፒታሊስት አገሮችና፣ በኋላ ደግሞ ከጃፓንና ከደቡብ ኮሪያ ጋር በማወዳደር ውስጣዊ ድክመቱን መረዳት ይችላል። ይህንን በሚመለከት አሁን ለንባብ ባወጣሁት አዲስ መጽሐፌ ላይ በሰፊው ስላተትኩ መጽሐፉን መመልከቱ ከሞላ ጎደል ጥሩ ግንዛቤ ሊሰጠን ይችላል። በዚያው መጠንም አገራችንና የተቀሩት የአፍሪቃ አገሮች መከተል ያለባቸውን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲ መረዳት ይቻላል።

ያም ሆነ ይህ ይህንን ትተን ወደ ውስጡ ፖለቲካ ስንመጣ አንድ አገዛዝ ለረጅም ጊዜ ስልጣን ላይ ለመቆየት ከፈለገ በህብረተሰቡ ውስጥ አሉ የሚባሉትን ቅራኔዎች በማባባስና አርቲፎሻል ነገሮችን በመፍጠር ለዘለዓለም ስልጣን ላይ ለመቆየት አይችልም። የግዴታ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ከተፈለገ በምድር ላይ የሚታዩትን ችግሮች፣ ማለትም ድህነትንና ረሃብን፣ በመሰረቱ መሰረታዊ ፍላጎቶች(Basic Needs) በመባል የሚታወቁትን ለመፍታት መቻል አለበት። በዚህ ብቻ ሳይረካ አገሩ የተረጋጋች እንድትሆንና፣ ዘላቂነት ያለው ስላም እንዲስፍን ከፈለገ ሰፋ ያለ የስልጣኔ ፕሮጀክት መዘርጋት አለበት። በዚህ መልክና በሚፈጠረው ህብረተሰብአዊ መተሳሰርና ጥንካሬ አንድ አገዛዝ ህዝባዊ ተቀባዊነትን በማግኘት እንደ አለኝታ ይታያል። የብልጣ ብልጡ ወያኔ ተልዕኮውና ህልሙ ግን ይህ አይደለም። አገሪቱን በሁሉም አቅጣጫ ማዳከምና ከውስጥ ህብረተሰብአዊ ቅራኔዎች እንዲፋፋሙ በማድረግ እራሱን አጎልምሶ ታላቋን ትግሬ መገንባት ነው። ሞኙ ህዝባችን ይህንን እጅግ አደገኛና የጥቁር ህዝብ ጠላት የሆነውን ፕሮጀክቱን ዝም ብሎ መመልከት አለበት። ይህንን ዐይነቱን የህዝብ ጠላት የሆነውን አደገኛና በቀላሉ ሊቀረፍ የማይችለውን ተግባር ወያኔዎችና ግብረ አበሮቻቸው ፖለቲካ ይሉናል።

በመሰረቱ ይህ ዐይነቱ የፖለቲካ ግንዛቤና አካሄድ አንዳንድ የድሮ ድርጅቱ አባል ከሆኑት እንደሚሰማው ከሆነ፣ ድርጅቱ አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ በመሆኑ ነው ይህንን የፖለቲካ አካሄድ እንዲመርጥ የተገደገደው የሚለው አመለካከት ኢ-ሳይንሳዊ አቀራረብ ነው። ሁለቱንም መሰረተ- ሃሳቦች ነጣጥለን በምንተነትንበት ጊዜ ሁሉቱም ፅንሰ-ሃሳቦች የሚሰጡን የተለያየ ትርጉም አለ። በመጀመሪያ ደረጃ አብዮት የሚባለው ጽንሰ-ሃሳብ ጤናማ አስተሳሰብ ያለውና ስር-ነቀል እርምጃን የሚያካትት ነው። በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ በአንድ አገዛዝ የሚገለጽና ተግባራዊ የሚሆን ለዕድገት ጠንቅ የሆነ ህብረተሰብአዊና ፓለቲካዊ ግኑኝነት ባለበት ጊዜ የጥገና ለውጥ የማይቻል ከሆነ የግዴታ አብዮታዊ እርምጃ የሚያስፈልግበት ጊዜ አለ። ይህ ዐይነቱ አብዮት የግዴታ ከማርክሲዝም ጋር መያያዝ የለበትም። ማርክሲዝም እንደፍልስፍናና የፓለቲካ መመሪያ ሆኖ ከመፈጠሩ ወይንም ብቁ ከማለቱ በፊት ከሁለትና ከሶስት መቶ ዓመታት በፊት የከበርቴው አብዮት ተካሂዷል። በዚህም መሰረት ነው የፊዩዳሉ ስርዓት ሊገረሰስና ለከበርቴያዊ፣ እንዲያም ሲል ለኢንዱስትሪ አብዮት መሰረት መጣል የተጀመረው። በሌላ ወገን ደግሞ በኢንዱስትሪ አብዮት የተነሳ ህብረተሰብአዊ መመሰቃቀል ሲመጣና ድህነት ሲከሰት፣ እንዲሁም የአካባቢ መቆሸሽ ህዝቡን መኖሪያ ሲያሳጣው ማርክስና ተከታዮቹ ብቻ ሳይሆኑ ሮማንቲኮች የሚባሉ ምሁሮችም ለህብረተሰብአዊ ለውጥ ታግለዋል። ትግላቸው ግን ደም መፋሰስን የሚጋብዝ ሳይሆን በሰብአዊነት መርሆች ላይ የተመረኮዘ እንደነበር በበቂው ተመዝግቧል። ዲሞክራሲ የሚባለው ጽንሰ-ሃሳብ ደግሞ የማያሻማ ትርጉም አለው። ሌላ ትርጉም ካልተሰጠው በሰተቀር ህዝብን የሚያካትትና የህዝብን ጥያቄ መመለሻ መሳሪያ ነው። በሌላ አነጋገር ለጥቂት ኤሊት ነን ባዮች የሚሰጥ ጽንሰ-ሃሳብና መሳሪያ አይደለም። በአገራችን ካልሆነ በስተቀር በታሪክ ውስጥ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚባል ነገር የለም። ይሁንና ግን በብዙ የቀድሞ ሶሻሊስት አገሮች በማዕከል ደረጃ ያልተፍታታ ዲሞክራሲያዊ ሴንትራሊዝም የሚሉት አነጋገር ነበር። ይህ ዐይነቱ ዲሞክራሲያዊ ሴንትራሊዝም አገራችን ውስጥ አለ ከሚባለው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም። በጊዜው የዲሞክራሲ ሴንትራሊዝም ሰፍኖባቸዋል በሚባሉት የቀድሞ የሶሻሊስት አገሮች ውስጥ የነበረውን የህዝቡን ኑሮ ስንመለከት አብዛኛው ህዝብ ስራ የነበረውና በህይወቱም እርግጠኝነት የሚሰማው ነበር። ድህነት የሚባል ነገር አይታወቅም ነበር። በውጭ ፖለቲካቸውም እንደኛው እንደ ዛሬው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ተቀጢያዎች አልነበሩም። ከሞላ ጎደል ራሳቸውን የቻሉ ነበሩ። የተጨባጩ ሶሻሊዝም(Real Socialism) ችግር ቀስ በቀስ እያለ ስርዓቱን ለማደስ ወይም ጥገናዊ ለውጥ ለመውሰድ አለመቻሉ ነው። ሁሉም ነገር በማዕከል ደረጃና ዕቅድ ይካሄድ ስለነበር ለግለሰብ ፈጠራ አመቺ ሁኔታን ሊያዘጋጅ አልቻለም። ከፖለቲካ ኢኮኖሚ ህግ አንጻር የማርክስን ዳስ ካፒታል ላነበበ፣ የኢኮኖሚ ዕድገቱ አካሄድ ቀስ በቀስ እያለ ከዝቅተኛ ወደ ከፈተኛ ደረጃ የሚሸጋገርን የኢኮኖሚ አካሄድ የተከተለ አይደለም። ሌላው የሶሻሊዝም ድክመት ልክ እንደካፒታሊስት አገሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀብትን በመዝረፍ የተገነባና ሌሎች አገሮችን የጥሬ-ሀብት አምራቾች አድርጎ ለማስቀረት የቻለ ባለመሆኑ የመጨረሻ መጨረሻ ስርዓቱ ሊከሽፍ ችሏል። ይህ ማለት ግን አንዱ አገር ሌላውን ካልበዘበዘ ሊያድግ አይችልም ማለቴ አይደለም። ተጨባጩን የካፒታሊዝምን ዓለምአቀፋዊ የሀብት ክምችትና የብዝበዛ ዘዴ ለማሳየት ብቻ ነው። ይሁንና ግን በጊዜው የሶሻሊዝም ርዕዮተ-ዓለም መስፋፋትና ተግባራዊም መሆን ከካፒታሊዝም ውስጣዊ ቅራኔ ጋር የተያያዘና የአንደኛውና የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወጤት ነው ማለት ይቻላል። በጊዜው ግዴታዊ አካሄድ ነበር። በመሆኑም ሶሻሊዝም ወደ ናሺናሊዝምነት በመለወጥ ሶቭየትህብረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከእርሻ (Agrarian) ኢኮኖሚ በኢንዱስትሪ ላይ ወደ ተመሰረተ ኢኮኖሚ መሸጋገር ችላለች። ኃያል መንግስትም ለመሆን በቅታ ነበር። በጦርነት የፈራረሰውን ከተማዎቿን እንደገና መልሳ ለመገንባት ችላለች። ይህንን ሁሉ ያደረገችው በራሷ ጥረትና እንደ አሜሪካ ዕውቀትንና ሀብትን ከሌሎች አገሮች በመውሰድ አይደለም። ከዚህ ስንነሳ ስለ አብዮታዊ ዲሞክራሲና በቀድሞ የሶሻሊስት አገሮች የነበረውን ስርዓት መለያየት አለብን። እንዲያው በጥላቻ ላይ ተመርኩዘን የምናደርገው ዘመቻ በሰፊው እንዳናስብ ብቻ ሳይሆን፣ አማራጭ መንገዶችንንም እንዳንፈልግ ከመጀመሪያውኑ መንገዱን ይዘጋብናል።

ያም ሆነ ይህ ወደ ወያኔው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ስንመጣ በምንም ዐይነት ለውጥን ሊያመጣ የቻለና የሚያስችል አይደለም። ለስርዓት ለውጥም የሚያመች አይደለም። የዚህ ዐይነቱ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ፍልስፍና፣ ሳይንስና ቲዎሪ ምን እንደሚመስል የሚታወቅ ነገር የለም። በመሰረቱ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የፍልስፍና መሰረቱ ማርክሲዝምና የሶሻሊዝም ቲዎሪ መሆን ነበረባቸው። የወያኔ አገዛዝ ግን ከማርክሲዝም ጋር የተሰናበተው በመጀመሪያ ደረጃ ጫካ ውሰጥ ሆኖ ሰው መግደል ሲጀምር ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ስልጣን ከጨበጠ በኋላ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረ ወዲህ ነው። ስለሆነም ይህ የተምታታ ፖሊሲው ለዘመናዊ ፊዩዳሊዝም መንገዱን የከፈተና፣ በዓለም አቀፍ ደራጃ ደግሞ የባሰውኑ ቀጭጨን እንድንቀር የሚያደርገን የስራ-ክፍፍል ውስጥ ነው የከተተን። አዲስ ዐይነት የሴንተር-ፔሪፌሪ(Center-Peripheri) ግኑኝነት ተግባራዊ ያደረገ „አብዮታዊ ዲሞክራሲ“ ነው ተግባራዊ የሆነው። ስለሆነም የስትራክቸራል አድጀስትሜንትን ፕሮግራም ወይም የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲን የተቀበለና ተግባራዊ የሚያደርግ አገዛዝ ለመሰረታዊ ወይም ለአብዮታዊ ለውጥ ዝግጁ አይደለም። እንደሚታወቀው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዋና ዓላማው በየአገሮች ውስጥ አዲስ ዐይነት የሶሻልና የፖለቲካ ግኑኝነት(Social and Political Relationship) በመፍጠር አገዛዞችን በዓለም አቀፍ የአገዛዝ ሂራርኪ ውስጥ በማካተት ህዝቦችን ማሸትና ማድኸየት ነው። ለዚህ ደግሞ ናኦሚ ክላይን(Naomi Klein) The Shock Doctrine በሚለው ግሩም መጽሀፏ ውስጥ እንዳሳየቸው የገበያ ኢኮኖሚ ብለው በሚጠሩት የሞኔተሪ ፖሊሲ የጠቅላላውን ህዝብ ጭንቅላት ሙሉ በሙሉ ማጠብ ነው። በሌላ አነጋገር፣ በዚህ ዐይነቱ የሾክ ዶክትሪን ቲዎሪ አማካይነት የአንድ አገር ህዝብ ጭንቅላት ከድሮ አስተሳሰቡ እንዲላቀቅ መደረግ አለበት። ጭንቅላቱ ተበጥብጦ ሲጣራ የዚያን ጊዜ የገበያ ኢኮኖሚን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ ይጀምራል። ሙያው ሁሉ ገንዘብን ማሳደድ ይሆናል። ናኦሚ ክላይን የብዙ አገሮችን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሁኔታ ኢምፔሪካል በሆነ ዘዴ ከመረመረች በኋላ የደረሰችበት ውጤት ይህ ዐይነቱ ሾክ ዶክትሪን በብዙ አገሮች ኢኮኖሚያዊ ብልጽግናንና የማህበራዊ ሁኔታን መሻሻል ሳይሆን ያመጣው፣ በከፍተኛ ደረጃ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ድቀትን ነው ያስከተለው። ለዚህም ነው አጥፊው ካፒታሊዝም(Disaster Capitalism) ብላ የጠራችው። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አምባገነናዊ አገዛዝን በማጠናከር ሁኔታው እየተበላሸ ሲሄድ ደግሞ ወደ ፋሺስታዊ ስርዓት እንዲሸጋገር ማድረግ ነው። ለዚህ ደግሞ በአገዛዙና በህብረተሰቡ ውስጥ ያለው በጣም ዝቅተኛ የፖለቲካ ንቃተ-ህሊና በጣም አመቺ ነው። ስለሆነም ሴኪዩሪቲውን በአዲስ መልክ ማደራጀትና ማጠናከር፣ ልዩ አፋኛና አነጣጥሮ የሚተኩስ ቡድን ልክ ናዚዎች ያደራጁት ዐይነት ኤስ ኤስ(SS) የሚመስል ፋሺሽታዊ የጦር ኃይል በማደራጀት የተዘረጋውን ስርዓት ይቀናቀኑኛል የሚላቸውን ሁሉ እያነጣጠሩ መግደል ነው።

የመሰለውን አነጣጥሮ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን የሚገድለውን ፋሺስታዊ አጋዚ የሚባለውን የጦር ኃይል ሲአይኤ(C.I.A) ሲያሰለጥነው፣ የፌዴራል ፖሊስ የሚባለውን አስፈሪ ኃይል ደግሞ እንግሊዝ ናት ያስታጠቅችውና ያሰለጠነችው። በተጨማሪም ኢትዮጵያ የሲአይኤ መመላለሻ ቤት ስትሆን፣ በውጭ ጉዳይ ምኒስቴርና በጸጥታ ኃይል ውስጥ እንግሊዞችና ሌሎች የምዕራብ አውሮፓ ሰዎች ተስግስገውበታል። ከዚህ በላይ የሃይማኖት ሰባኪዎችና የዕርዳታ ሰጪዎች በመምሰል በአገሪቱ ውስጥ በመሰማራት የአማራው ብሄረሰብ ዝቅ አድርጎህ ይመለከትሃል በማለት ህዝባችን ርስ በርሱ እንዲበላላና የማያልቅ ጦርነት ውስጥ እንዲገባ የጥላቻ መርዛቸውን እየረጩ ነው። እንግዲህ እነዚህ የወዳጅ አገሮች የሚባሉት ናቸው የወያኔ የጀርባ አጥንት በመሆን ህዝባችን ርስ በርሱ እንዲተላለቅና አገራችንም በዘለዓለም ትርምስ ውስጥ እንድትኖር የሚያደርጉት። ይህ ዐይነቱ የፍርሃትና የጦርነት ፖለቲካ ደግሞ በአሜሪካን አገርም በግልጽ የሚታይ ነው። ፖሊሱን ወደ ወታደርነት በመቀየርና አነጣጥሮ የሚተኩስ ጠብመንጃ ይዞ እንዲዘዋወር በማድረግ፣ አደጋ ሊያደርሱብኝ ነው የሚላቸውን ለጋ ወጣቶች ሁሉ ሳይቀር ምክንያት እየፈለገ እያነጣጠረ እንዲተኩስ ፈቃድ ተስጥቶታል። ስለሆነም ህዝቡ በፍርሃት ዓለም ውስጥ እንዲኖር ተገዷል። በዚህ መልክ በ1960ዎችና በ1970ዎቹ ዓ.ም በላቲን አሜሪካንና በሴንትራል አሜሪካ አገሮች ፋሺስታዊ አገዛዞች በመስፋፋት በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ምሁራንና የዋህ ህዝቦችን ገድለዋል፣ የተቀረውን ደግሞ በየስርቤቱ ጥለዋል። ይህ ዐይነቱ የመንግስታት መኪናዎች አደረጃጀት ዘዴ ፣ በአንድ በኩል በየአገሮች ውስጥ የተፈጠረውን ልዩ ዐይነት ህብረተሰብአዊ ግኑኝነት መጠበቅ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ አገዛዞችን ፍጥጫ ውስጥ በመክተት በጎረቤት አገሮች መሀከል ጦርነት ለመቀስቀስና ህዝብን ለመጨረስ ነው። በዚህ መልክ የየአገሩ መንግስታት በመፈራራት የማያቋርጥ ወይም በቀላሉ መፍትሄ የማይገኝለት ጦርነት ውስጥ ይገባሉ። በዚያው መጠንም እነዚህ አገሮች በኢንዱስትሪ አገሮች የሚሰሩት የጦር መሳሪያዎች ማራገፊያ ወይም ገበያ ይሆናሉ። ይህ የካፒታሊዝም ውስጣዊ ህግ ነው። ካፒታሊዝምና ጦርነት የተያያዙ ናቸውና።

ከዚህ ዐይነቱ የእከክልኝ ልከክልህ ፖለቲካና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተዘረጋውን የአገዛዝ ሂራርኪ ስንረዳ ነው የወያኔንም የውስጥ ፖለቲካ መገንዘብ የምንችለው። ይህንን የተወሳሰበና በሺህ ድሮች ተሳስሮ ለስልጣኔና ለዕውነተኛ ዲሞክራሲ እንቅፋት የሆነውን ስርዓትና ከውጭ ኃይሎች ጋር ያለውን መተሳሰር ካልተረዳን ስለ እኩልነትና ስለ ዲሞክራሲ ማውራት በፍጹም አንችልም። ስለዚህም የነገሮችን መተሳሰር መመልከት አለብን። ከዚህ ስንነሳ ካለፉት አስራአንድ ወራት ጀምሮ፣ በተለይም ካለፉት አራት ሳምንታት ጀምሮ ወያኔ በህዝባችን ላይ የሚያደርሰው ግድያና ማሰቃየት ከበስተጀርባው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም አለበት። በተለይም ደግሞ የጎሳው ፖለቲካ ስላልሰራና በሃይማኖት መተላለቅም ስላልተከሰተ የምዕራቡ ዓለም በጣም ተደናግጧል። አገራችንን የመበታተኑና በዘለዓለማዊ ጦርነት ውስጥ ዘፍቃ እንድትቀር የታሰበውና የታቀደው ስትራቴጂ ስላልሰራ አገዛዙ አነጣጥሮ በመተኮስ እርምጃው እንዲገፋበት የአረንጓዴ መብራት ተስጥቶታል። ስለዚህም ነው እስከዛሬ ድረስ እንደዚያ በአገራችን ምድር ብዙ ደም እየፈሰሰ የምዕራቡ ሚዲያ ምንም ነገር የማይጽፈውና የማያሰማው። ሁኔታው እንደሶሪያ እስኪሆን ድረስ ነው እነ አሜሪካና የተቀረው የምዕራቡ ዓለም የሚጠባበቁት። በመሆኑም ከብዙ የዋህና ተማርን ከሚሉ ኢትዮጵያውያን የሚቀርበው እሮሮና የይድረሱልን ጩኸት ቦታና ትርጉም የለውም። ይህ ዐይነቱ የይድረሱልኝ እሮሮና ከአሜሪካን ሆኖ ተጠባባቂ መንግስት መመስረት አለብን እያሉ መጮህ ህይወቱን በተሰዋውና በየቀኑ በሚሰዋው ህዝባችን ላይ እንደማላገጥ ይቆጠራል። ከዚህ ዐይነቱ ጭንቅት ለመውጣት የግዴታ በራሳችንና በህዝባችን ላይ መተማመን አለብን። ራሳችንንም ነፃ ማውጣት የምንችለውና ጠንካራ አገር መገንባት የምንችለው በአሜሪካን በመታገዝ ሳይሆን በራሳችን ጥረት ብቻ ነው።

በሌላ ወገን ግን ወያኔ አሁንም የሚከተለው የግድያና የአፈና ፖለቲካው ውድቀቱን የሚያፋጥነው ነው። በተለይም በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የጎንደርና የጎጃም ህዝብ ቆርጦ መነሳቱ በጣም ያስደነገጠው ወያኔ በጠቅላይ ምኒስተርነቱ አማካይነት ይህ ዐይነቱን ከጭቆናና ከዘረፋ ለመውጣት የሚደረገውን የጦር እንቅስቃሴ ከውጭ ወረራ ጋር ለማያያዝ ነው የሞክረው። በአቶ ኃይለማርያም አባባል፣ የኢትዮጵያን ሀብት ለመዝረፍ ጠላት በየጊዜው ወረራ እንዳደረገባትና፣ አሁንም እንዳልተኛ ነግረውናል። አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ግን የሚነግሩን የተገላቢጦሹን ነው። በብዙ መቶ የሚቆጠር ጋሻ መሬት ለውጭ ከበርቴዎች በመሰረቱ ዘራፊዎች አከራይቶ የአገር ሀብት እንዲበዘበዝና ተራው ገበሬ ከመሬቱ እንዲፈናቀል፣ እምቢ ያለውን ደግሞ የሚገድለው ወያኔ ነው። የጎንደር፣ የጎጃም፣ የኦሮሞና የጋምቤላ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚታገሉት በመሬታችን ላይ ከአበባ ይልቅ ለምግብ የሚሆን እህል እንትከልበት፤ ከመሬታችን አታፈናቅሉን እያሉ ነው። በተጨማሪም አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ስለ ዕድገት ያላቸው አስተሳሰብ የተጣመመ ነው። አንድ ሰው መዋያው ያማረ ቤተ-መንግስትና ጋርተን ውስጥ የሚዘዋወርና የሚበላውም ምግብ የተለየ ከሆነ ስለሌላው ማሰብ አይችልም። ስለዚህም አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝና የካቢኔት ሹማምንቶቻቸውን የምንመክረው ሌላው የአገሪቱ ክፍሎች ጋ ሳይሄዱ እዚያው አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ መርካቶ ቢዘዋወሩና አንድ ሁለት ቀን እዚያ ቢያድሩ ስለ ዕድገት ያላቸውን አስተሳሰብ ሊለውጡ ይችሉ ይሆናል። የምንመክራቸውም ሼራተን በመሄድና በመመገብ ሳይሆን፣ ወይም የተወሰነ አካባቢ በመዘዋወር ሳይሆን ስለ ዕድገት መናገር የሚቻለው በየቦታው በእግር በመዘዋወር የህዝባችንን አኗኗር ሁኔታ በመቃኘት ነው። እንደምናየው አብዛኛው ህዝባችን እንደ አይጥ እየተሽሎከለከ በቆርቆርና በተሰባበረ የእንጨት ቤት ውስጥ የሚኖር ነው። ከዚህም በላይ አገሪቱ የቆሻሻ መጣያ የሆነችና ወደፊት በቀላሉ ይህንን ሪሳይክል ለማድረግ የማይቻልበት ሁነታ ተፈጥሯል። ይህ የሚያሳየን ምንድነው ፟? አንድ አገዛዝ የተፈጥሮን ህግ ሳይረዳ በራሱ ስሜትና በማፊያ መልክ በተደራጀው የዓለም-አቀፍ ኮሙኒቲ በሚባለው የወጣና የሚደገፍ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ካደረገ የአንድን አገር የሰውና የተፈጥሮን ሀብት ያወድማል። አዳዲስ ቲክኖሎጂዎችን ሊፈጥር አይችልም። በዚህም የተነሳ ከህዝብ ቁጥር ማደግ ጋር የሚያያዝ ምርታማነትን ሊታይ አይችልም፤ ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ሀብትም አይፈጠርም። ዛሬ በአገራችን ምድር ያለውን የኢኮኖሚ ሁኔታ አስመልክቶ አንደ የገዢው መደብ አቀንቃኝ የሆነች ከአውስትራሊያ ለሚተላለፈው የአማርኛ ፕሮግራም አዘጋጅ ለቀረበላት ቃለ-መጠይቅ የሰጠችው መልስ የሚያስቅ ነው። የህዝቡ ጥያቄ(Demand) ስለአደገ ነው የኢኮኖሚ ችግር የሚታየው የሚለው ግራ የሚያጋባ ነው። በመሰረቱ በአለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በአገራችን ምድር አገሪቱን ሊያዳርስ የሚችል በመንግስትና በኢንስቲቱሽን የተደገፈ ብሄራዊ ሀብትን ሊፈጥር የሚችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ አልተካሄደም። የስኳርና የኮካኮላ እንዲሁም የቢራ ፋብሪካ በየቦታው በመትከልና በማምረት የአንድን ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎት ማሟላት አይቻልም። በሁለተኛ ደረጃ፣ አንደ ከአገዛዙ ጋር የተቆራኘ እንደ ኢፈርት የመሳሰለ ድርጅትና አላሙዲ የሚባል ተልዕኮው ምን እንደሆነ የማይታወቅና ስለ ኢኪኖሚ ህግ መሰረታዊ ዕውቀት የሌለው ሰው ሁሉንም ነገር በሚቆጣጠሩበት አገር ውስጥ ስለ ዕውነተኛ ዕድገትና ሰለ ህዝብ ጥያቄ ማደግ ማውራት በፍጹም አይቻልም። በሶስተኛ ደረጃ፣ የግል ባለሀብቶች በየቦታው እየተንቀሳቀሱ ኢንቬስት እንዳያደርጉ መዓት እንቅፋቶች በተደቀነበት አገር ውስጥ የስራ መስክ መክፈትና የተለያዩ የምርት ዐይነቶችን ማምረት አይቻልም። ይህም ማለት በአንድ አገር ውስጥ መንግስት ብቻውን የአንድን ህዝብ ፍላጎት ሊያሟላ አይችልም። ቴክኖሎጂያዊ ምጥቀትና ሰፋ ያለ የመዋዕለ-ነዋይ እንቅስቃሴ ሊታይ የሚችለው ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ ያለ የግለሰቦች ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ሲኖር ብቻ ነው። በሌላ ወገን ግን መንግስትና ድርጅቱ ማፊያዊ በሆነ መልክ የሚንቀሳቀሱትን ግለሰቦች ምክንያት እየፈጠሩ ገበያውን ለቀው እንዲወጡ ያደርጓቸዋል። አንዳንዶች ደግሞ በወያኔ የማፊያ ሰዎች ይገደላሉ። ታዲያ በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ እንዲት አድርጎ ኢኮኖሚውን ማሳደግና በየጊዜው እያደገ የሚሄደውን የህዝብ ግላጎትና ጥያቄ ማሟላት ይቻላል ?

ያም ሆነ ይህ በየቦታው መፋፋም የጀመረውን ሰላማዊና ራስን ወደ መከላከል የተለወጠውን የህዝብ እንቅስቃሴ ወያኔ ለመፍታት የሚፈልገው የባሰዉኑ በጠብመንጃ ኃይል ብቻ ነው። በየጊዜው አረመኔያዊነቱን እያረጋገጠና ህፃናትንና እናቶችን ሳይቀር በጠራራ ፀሀይ በመግደል እንቅስቃሴዉን የሚገታ መስሎታል። በዚህ መልክ የሚያካሄደው የጭፍን ፖለቲካው የባሰውኑ ኃይሉን እየበታተነበትና፣ ለትግሬዎች ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፣ እንዲሁም እናቶቻችንና አባቶቻችን አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እየከተታቸው መጥቷል። በተለይም ቶሎ ብለው አገዛዙን ማግለል የማይችሉና ሰፊው ወንድማቸው ጎን ቆመው ለዲሞክራሲና ለነፃነት ለመታገል የማይችሉ ከሆነ በተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ እንዲጠሉ ይደረጋሉ። ስለዚህም በአስቸኳይ ከሰፊው ህዝብ ጎን መቆማቸውን ማሳወቅ አለባቸው። የወያኔ አገርን የመበታተንና ኢትዮጵያን አዳክሞ ታላቋን ትግሬ የመገንባት ህልምና ፕሮጀክት ያከተመለት መሆኑን ማንኛውም ወጣት እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ትግሬዎች መረዳት አለባችው። አንድ ህዝብ ታሪክ ሊሰራ የሚችለው በመነጣጠልና በመናቆር ሳይሆን፣ በመሰባሰብና፣ ኃይሉን በማጠንከርና አንዱ ከሌላው በመማር የተረዳዳና ለጋራ ዓላማ የተነሳሳ እንደሆነ ብቻ ነው። በመሆኑም የፖለቲካን ሰፊና ገንቢ ትርጉም መረዳት የጊዜው አንገብጋቢ መሰረተ-ሃሳብ ይሆናል። ለአዲሲቱና ለዲምክራሲያዊቱ ኢትዮጵያ መገንባት የሁላችንንም ተሳትፎ ስለሚጠይቅ፣ ይህንን ከፋፋይና ህብረተሰቡን አዳክሞ የውጭ ኃይሎች ተገዢ የሚያደርገንን አገዛዝ በጋራ ትግል መጣል አለብን። ወያኔ የራሱ ጦር አልበቃ ብሎት ከውጭ ጦር በማስመጣት በህዝባችን ላይ መዝመቱ ማንኛውንም የፖለቲካ ውይይት መንገድ ዘግቶታል። ይህ አገዛዝ ስልጣን ወይም ሞት ብሎ ቆርጦ የተነሳ ስለሆነና፣ በዚህም የሚገፋበት በመሆኑ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ይህን አገዛዝ ይቅርታ እንዲጠይቅና ወደ ህዝብ እንዲመለስ የሚያደርገው ጥሪ እጅግ አሳሳችና አደገኛ ነው። ይህ ዐይነቱ አቀራረብ በአንደ በኩል በአገዛዙና በኢምፔሪያሊስት ኃይሎች የተቀነባበረብንን ልዩ ሴራ በቅጡ ካለመገንዘብ የሚሰነዘር ኢ-ፖለቲካዊ አባባል ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ የህዝባችንን ዕውነተኛ የነፃነትና የስልጣኔ ጥም ለመረዳት ካለመቻል የሚቀርብ አስፈላጊ ያልሆነ ጩኸት ነው።

ከኛ የሚጠበቀው !

እኛ እዚህም ሆነ እዚያ ሆነን ጩኸታችንን የምናሰማ ኢትዮጵያውያን በአገራችን ምድር ሰላም፣ መረጋጋት፣ ዲሞክራሲና ነፃነት እንዲሁም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ብልጽግና እንዲመጣ ከፈለግን ከሁለት ነገሮች አንዱን መምረጥ ያለብን ይመስለኛል። ለብዙዎቻቸን እስካሁን ግልጽ ያልሆነና ከጥንት ጀምሮ ፈላስፋዎችን ሲያከራከር የነበረው ሁለት የዕድገት ፈለገ አለ። አንደኛው እነሶክረተስና ፕላቶን የፈጠሩትና የመንፈስን የበላይነት ያስቀደመው መንገድ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ በሚታዩና በሚጨበጡ ነገሮች ላይ ያተኮረው ዕውቀትን የመፍጠሩ ጉዳይ ነው። ይህ ዐይነቱ አካሄድ በተለይም ከአስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በአንድ በኩል በነላይብኒዝ የሚወከለውና የእነ ፕላቶንን ፍልስፍና መሰረት ያደረገው የስልጣኔ መንገድ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በእንግሊዞች ኤምፕሪሲስቶች የሚሰተጋባው ከሶፊስቶች የተወሰደው ዕውቀትን የማፍለቅ ዘዴ ወይም ፖዚቲቭ ሳይንስ በመባል የሚታወቀውና፣ አንድን ተቀባይነት ያገኘን ስርዓትና አገዛዝ፣ እንዲሁም ከዚህ የፈለቁትን መመሪያዎች ሳይመረምሩ እንዳለ መቀበል ነው በሚለው መሀከል የተካሄደውን የጦፈ ክርክር ነው። በጊዜው እነላይብኒዝ ይከራከሩና ተከታዮቻቸውን ያስጠነቅቁ የነበረው ማንኛውም አገር የእንግሊዝ ፈላስፋዎችን መንገድ የምትከተልና፣ ፖሊሲዎች በሙሉ በዚህ መሰረት የሚወጡ ከሆነ መጪው የዓለም ህዝብ ዘለዓለሙኑ በጦርነትና በድህነት ውስጥ ዘፍቆ ፍዳውን እንደሚያይ ነው። ይህ አመለካከት በኋላ በመጡት በእነ ካንትና ሺለር፣ በኋላም በእነ ሄገል በመስፋፋት፣ የአንድ አገር ዕድገት የግዴታ በአርቆ አስተዋይነትና በከፍተኛ ንቃተ-ህሊና(Self-Consciousness) ላይ መመርኮዝ እንዳለበትና፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከሌሎች ህብረተሰብአዊና ማህበራዊ እንዲሁም ባህላዊ ዕድገት ተነጥሎ መታየት እንደሌለበት አስተምረዋል። በእነሱ አመለካከት አንድ ነገር ከሌላው ጋር የተያያዘ ስለሆነ፣ በአንድ አካባቢ የሚሰራ ስህተት የግዴታ በሌላው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል። በሌላ አነጋገር አንድ አገዛዝና አገር የተሳሰተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚከተሉ ከሆነ የመጨረሻ መጨረሻ ጠቅላላዉን ሁኔታ ያዘበራርቃሉ። የአገራችንን ሁኔታ ለሚመለከተው ይህንን መረዳቱ ከባድ አይሆንም። ለዚህ ነው በአገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም-አቀፍ ደረጃ ሚዛናዊነት እየጠፋና ጥቂቶች እየደለቡና፣ ሲጠግቡ ደግሞ ወደ ጦርነት የሚያዘነብሉት። ይህንን ለማመልከት ሲል ነው ውድ ወንድማችን ዳዊት አለማየሁ „ሚዛንሽ ተዛባ አንቺ ዓለም“ እያለ ግሩም በሆነ መልክ የሚዘፍነው። ስለዚህ ይህ ሙዚቃና ታች ከዚህ ጽሁፍ ጋር የተያያዙት የድህረ-ገጽ አድራሻዎች ብዙ መልዕክቶችን ያስተላልፉልናል። የዓለምን የመዘበራረቅ ሂደት በትንሹም ቢሆን ጠጋ ብለን እንመልከት።

በተለይም ከአስራስምንተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የእንግሊዙ መንገድ ባሸናፊነት ከወጣ ጀምሮ ቀስ በቀስ ብዙ አገሮች ሳያውቁት ይህንን መንገድ በመከተል የየአገሮቻቸው፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሚሊታሪ ፖሊሲ መመሪያ በማድረግ ህዝብን መቆጣጠሪያ ዘዴ አደረጉት። በጊዜው የእንግሊዝ ኤምፕሪሲስቶች የሰብአዊነት አመለካከት ያላቸውን አዋቂዎችን ካሸነፉ በኋላ ነፃ ገበያና ነፃ ንግድ የሚለውን በማወጅ፣ በዚያው መጠንም እንዴት አድርገው ዓለምን ለመቆጣጠር የሚችሉበትን ዘዴዎች ቀሰ በቀስ ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ። ይህ አካሄድ የመጀመሪያው የተጣመመው የግሎባላይዜሽን መሰረት ነው። ከዚህ በመነሳት ነው ቀሰ በቀስ የቅኝ-አገዛዝ ፖሊሲ አገሮችን የማዳከም ስትራቴጂ የተቀየሰውና ተግባራዊም የሆነው። በውጥኑ መሰረት አብዛኛዎች የአፍሪቃ አገሮች የጥሬ-ሀብት አምራችና አቅራቢ በመሆን እዚያው ቀጭጨው መቅረት አለባቸው። እንደ ህብረተሰብና እንደ አገር በሁሉም አቅጣጫ ማደግና መበልጸግ የለባቸውም። በተለይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በአሸናፊነት ከወጣ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ይህ መንገድ የበለጠውን በመርቀቅና እየተወሳሰበ በመምጣት የብዙ አገሮች መመሪያ ሆነ። ብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች በዘመናዊነት ስም ዕውነተኛ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ሳያደርጉ፣ በዚያው መጠንም የየመንግስት መኪናዎቻቸውን በአሜሪካ የጦር አደረጃጀት ስልት ማዘጋጀት ተገደዱ። ጠቅላላው የሲቪል ቢሮክራሲው በሙሉ በዚህ ዐይነቱ የፖዘቲቭ ሳይንስ መመሪያ በመሰልጠኑ በዓለምአቀፍ ደረጃ በተዘረጋው የሚሊታሪ-ኢንዱስትሪ ኮምፕሌክስ ውስጥ በመዋሃድ በየአገሮች ውስጥ ሚዛናዊነት ያለውና ከተፈጥሮና ከህዝብ ፍላጎት ጋር እየተመጣጠነ የሚሄድ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዳይሆን አገደው። በተለይም እ.አ በ1944 ዓ.ም እነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና(IMF) የዓለም ባንክ(World Bank) ከተቋቋሙ ጀምሮ ዋናው ተግባራቸው በተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት በየአገሮች ውስጥ የተዛባ ዕድገት የሚመስል ነገር ማምጣትና፣ በዚያውም መጠንም ድህነትን መፈልፈል ነው። ይህ ዐይነቱ የፖሊሲ አወቃቀር በየጊዜው ስሙን በመለዋወጥና በየአገሮች ውስጥ ተግባራዊ በመሆን የብዙ አገሮች ኢኮኖሚዎችና ማህበረሰቦች እንዲዘበራረቁ ሆኑ። ቀስ በቀስም ማህበራዊ ቀውሱ ጥልቀት በማግኘት፣ እ.አ ከ1989 ዓ.ም በኋላ የተፈጠረውን አዲስ ክስተት ተገንና ሽፋን በማድረግ የየአገዛዞች ዋናው ተግባር አሸባሪዎችን መዋጋት ነው በሚል የአብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች መንግስታት ዋናው ተግባር ወደ ጦርነት በማድላት የመንግስታቶቻቸውን መኪና የባሰውኑ ሚሊታራይዝ በማድረግና የየአገሮቻቸውን ሀብት በመምጠጥ በፍጥጫ ዓለም ውስጥ እንዲወድቁ ተገደዱ። በአስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን እነላይብኒዝና፣ የኋላ ኋላም ተከታዮቻቸው ሌሎች የጀርመን ፈላስፎች ያሰጠነቀቁት የነበረው ሁኔታ ዕውን በመሆን፣ ይህ ዐይነቱ መንግስታዊ አወቃቀርና ከዚህ የሚወጣው ፖሊሲ ለአንደኛውና ለሁለተኛው ዓለም ጦርነት ምክንያት ሆነ። የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ፍጻሜ ካገኘና አሜሪካንም የበላይነትን ከተቀዳጀ በኋላ ጦርነት ወደ ሶስተኛው ዓለም አገሮች በመሸጋገር ብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች በጦርነት ዓለም ውስጥ እንዲዘፍቁ ተገደዱ። ከቬትናም እስከ አንጎላና ሞዛምቢክ ድረስ በ60ኛውና በሰባኛው ዓ.ም ይካሄዱ የነበሩት ጦርነቶችና ለብዙ መቶ ሺህ ህዝቦች ማለቅ ምክንያት የሆኑት ዋናው ቀስቃሺዎች አሜሪካንና ተካታዮቻቸው ናቸው። እነዚህ በወንድማማቾች የተካሄዱት ጦርነቶች በሙሉ በመሰረቱ የውክልና ጦርነቶች(Proxy War) ናቸው። ዛሬ ወያኔ በአገራችን ምድር ላይ የሚያካሄደው ጦርነት የውክልና ጦርነት ነው። ካለበቂ ምክንያት በወንድማማቾች መሀከል የሚካሄድ ጦርነት ነው። እነ ሻቢያም ነፃ ወጣን እስካሉ ድረስ ጀምሮ ያካሂዱ የነበረው ጦርነት በውጭ ኃይሎች የታገዘና በማቴሪያልና በገንዘብ የሚደገፍ ለብዙ መቶ ሺህ ኢትዮጵያውያን-ኤርትራውያን እልቂት ምክንያት የሆነ ጦርነት ነው። የኦሮሞ ነፃ አውጭ ነኝ የሚባለው ድርጅትና ራሳቸውም የግራ ኃይሎች ነን ይሉ የነበሩት ሳያውቁት ያካሂዱ የነበረው ጦርነት በመሰረቱ የውክልና ጦርነት ነበር። ኃይልን የሚበታትን፣ ሀብትን የሚጨርስና የድህነቱን ዘመን የሚያረዝመው ነው። በመሰረቱ በአንድ አገር ውስጥ በአንድ ህዝብ መሀከል በብሄረሰብና በርዕዮተ-ዓለም ስም አሳቦ ወይም ስልጣን ላይ ለመውጣት በማለት የማያስፈልግ ጦርነት ማካሄድ ይቅርታ የማይደረግለት ነው። የታሪክ ወንጀል እንደመስራት ይቆጠራል። ግሎባላይዜሽንና ነፃ ገበያ አማራጭ የሌላቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ናቸው ተብለው መሰበክ ከተጀመሩበት ከ90ዎቹ ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአንድ በኩል የዎል ስትሪት(Wall Street) ተዋንያንና በዓለም አቀፍ ኢንስቲቱሽኖች ውስጥ ሲሰሩ የነበሩና እንደሎሚ ልጣች ተመጥጠው ያለቁ ኤክስፐርቶችን እየላኩብን በቀጥታ የኢኮኖሚ ጦርነት አውጀውብናል። በተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ደሃ ሆነን እንድንቀር ለማንም የማይታይና ማንም ሊረዳው የማይችል የረቀቀ ጦርነት አውጀውብናል። ከዚህም በላይ አሸባሪዎች የሚባሉትን በየቦታው እንድ አሸን እንዲፈልቁ በማድረግ ጦርነት አውጀውብናል፤ ለአለመረጋጋት ምክንያት ሆነዋል። ይሁንና የአሸባሪዎች ዋናው አማካሪ፣ መሳሪያ አቀባይና ገንዘብ አቅራቢዎች ደግሞ የአሜሪካን የስለላ ድርጅትና በዘይት ዶላር የናጠጡ የአረብ አገሮች ናቸው። አልሻባብ የሲአይኤና የወያኔ ውልድ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ በአሸባሪነት ስም የሚካሄዱት ግድያዎች በሙሉ ከዘጠና በመቶ በላይ በስለላ ድርጅቶች የሚካሄዱ ናቸው። ለዚህ ደግሞ እንደ ሃርፕ የመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀምና የወጣቱን ጭንቅላት በማዞር ነው።

ይህ ማለት ማለት ነው? እኛ የዛሬውን አገዛዝ የምንታገልና ነፃነት እንዲመጣ የምንፈልግ ኃይሎች ሁሉ ከሁለት አንደኛውን መንገድ መምረጥ አለብን። ከመንፈሳዊውና ከሰይጣኑ መንገድ። በዝህቦች መሀከል ስምምነት እንዲመጣ፣ እያንዳንዱ ዜጋም የማሰብ ችሎታውን በማዳበር አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር የሰለጠነች አገር እንዲገነባ ከተፈለገ የግዴታ የመንፈሳዊዉን መንገድ መምረጥ አለብን። ወጣቱ ቄስ ዳነኤል እንደሚያስተምረን ወደ ገነት ለመግባት ከፈልግህ የሰይጣኑን መንገድ መምረጥ የለብህም። የግዴታ ቅዱሳዊውንና የገነቱን መንገድ ስትመርጥ ብቻ ነው ወደ ገነት መግባት የምትችለው። በዩኒቨርሳል ህግ ወይም በተፈጥሮ ህግም መሰረት ዋናና ተቀዳሚው ተግባር የአስተሳሰብ አንድነት(Unity of Thought) ማዳበር ነው። የአስተሳሰብ አንድነትና ጥራት ሲኖር የስልጣኔው መንገድ ብሩህ ይሆናል። የአስተሳሰብ ጥራት ሲኖረን እርስ በራሳችን መናቆሩን እንተወዋለን። ሁለተኛው የዩኒቨርሳል ህግ መመሪያ በተናጠል አንድ ግብ መድረስ አይቻልም። በአንድ ጣት ምንም መስራት አይቻልም። በሁለት ጣቶች እርሳስ ማንሳት ይቻላል። በአምስት ጣቶችና በሁለት እጆች ብዙ ነገሮች መስራት ይቻላል። ብዙ ሰዎች ስንሆን ደግሞ ተራራንም ማንቀሳቀስ እንችላለን። ስለሆነም አንድ ጠንካራና ስላም እንዲሁም ብልጽግና የሚሰፍንባት አገር ለመገንባት ከፈለግን የግዴታ ኃይላችንን መስብሰብ አለብን። ሁሉም ታጋይ ነኝ እያለ በየቦታው ለመታየት የሚፈልግ ከሆነና፣ እዚህና እዚያ የፖለቲካ ፓርቲ የሚሉትን ፈሊጥ የሚመሰርት ከሆነ አንድ ጠንካራ አገር መገንባትና ሰላምን ማምጣት በፍጹም አይቻልም። ሶስተኛውና እጅግ አስፈልጊው የዩኒቭርሳል ህግ የግዴታ በራስና በራስ ህዝብ መተማመንን ይፈልጋል። ለዚህ ደግሞ የመንፈስ ነፃነት እንዲሰማ ያስፈልጋል። ከዚህ ስንነሳ የውጭ ተጠሪ የሆነና በውጭ ኃይል የሚተማመን ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል አገዛዝ በምንም ዐይነት ዕውነተኛ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ስልጣኔና ዕድገትን አያመጣም። በአራተኛ ደረጃ፣ ሌላው የዩኒቨርስ ህግ አንዱ ለሌላው ማሰብና ርስ ብርስ መረዳዳት አለበት። በተለይም መጦሪያ የሌላቸውንና በየቦታው የወደቁትን ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን፣ እንዲሁም እናቶቻችንና አባቶቻችንን መደገፍ ካልቻልንና መጠለያ ካልሰጠናቸው ስለ አገርና ዕድገት ማውራት በፍጹም አንችልም። በአምስተኛ ደረጃ፣ ሌላው የዩኒቨርስ ህግ የሚለን በአንድ አገር ውስጥ የተለያየ ብሄረሰብና አስተሳሰብ፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ የምግብ ዐይነቶችና ባህሎች መኖራቸው ተፈጥሮአዊ ናቸው። ተፈጥሮ ራሷ በልዩ ልዩ ነገሮች የምትገለጽ ነች። ሰውነታችንም ራሱ እዚያው በዚያው አንድም ብዙም ነው። ስለዚህም በአገራችን የተለያዩ ብሄረሰቦች መኖራቸው የውበታችን መግለጫዎች ናቸው እንጂ የመጠላላትና የመቀናናት ምክንያት ሊሆኑ አይገባቸውም። ጥያቄው እንዲዚህ ዐይነቱን ነገሮች በምን ዐይነት ፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲ ልንፈታቸው እንችላለን በሚለው ላይ ነው መነጋገር ያለብን። ስለሆነም ሁሉም ህዝብ ከዘርና ከሃይማኖት ባሻገር መረዳዳት አለብን። በመረዳዳትና በመከባበር ብቻ ነው ጤናማና ተከታታይነት ያለው አገር መገንባት የምንችለው።
የለም እኛ በአሜሪካን ትምህርት ነው የሰለጠን ነው፣ የአሜሪካን እሴትም ትክክለኛው ነው ብለን ይህንን የሙጥኝ ብለን የምንይዝ ከሆነ ያለመረጋጋቱንና የፀረ-ስልጣኔውን መንገድ መረጥን ማለት ነው። የሰይጣኑንና የመበታተኑን መንገድ ፈለግን ማለት ነው። ከዚህ ስንነሳ ወያኔን ለማስወገድ የሚደረገው ትግል ከዚህ ዐይነቱ የአስተሳሰብ ክልል ውጭ ሊታይ አይችልም። በሌላ አነጋገር በአገራችን ምድር ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ከተፈለገ፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የዚያች አገር ዜጋ መሆኑን እንዲረዳና ሙሉ ነፃነቱን እንዲቀዳጅ ከተፈለገ ነገሩ ወያኔን በማስወገድ ብቻ የሚያቆም መሆን የለበትም። በኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ በአጭሩ በአገር ግንባታና በሚሊታሪ ፍልስፍና ዙሪያ የምናካሄደው የጦፈለት ክርክር ወደ ፊት ይጠብቀናል። ዛሬ በሰሜንም ሆነ በደቡብ ከወያኔ ጋር የሚጋፈጠውና የነፃነት ያለህ እያለ የሚጮኸው ህዝባችን የሃሳብ ጥራትን ይጠብቃል። ከወያኔ ከተላቀቀ በኋላ በአስቸኳይ ጊዜያዊ ችግሩን እየቀረፍንለት ሰፊውን የአገር ግንባታ ተግባራዊ እንድናደርግ ከኛ ይጠብቃል። የመጨረሻ መጨረሻ ዕውነተኛ ነፃነቱ በተጨባጭ ነገሮችም የሚመነዘር መሆን አለበት። አዳዲስ ከተማዎችንና መንደሮችን መገንባት፣ ሀብትንና የሰው ኃይልን ለማንቀሳቀስ በየቦታው ኢንስቲቱሽኖችን ማቋቋም፣ በህዝብ ዘንድ ያለን ገንዘብ ለማንቀሳቀስና ምርታማ በሆነ ነገር ላይ ለማዋል የባንኩን ስይስተም በአዲስ መልክ ማደራጀት፣ የምግብን ችግር ለመቅረፍና በምግብ ራሳችንን ለመቻል የመሬትን ጉዳይ በአዲስ መልክ ለመፍታት መቻል፣ በተለይም ልዩ ልዩ የሰብልና የእህል ዐይነቶች ሊዘሩና ሊበቅሉ የሚችሉበትን ሁኔታ ማጥናትና በአስቸኳይ ተግባራዊ ማድረግ፣ በንጹህ ውሃ እጦት ለሚሰቃየው ህዝባችን በአካባቢውና ከረጅም ጊዜ አንጻር ደግሞ ቤት ውስጥ የመጠጥ፣ የመቀቀያና የማጠቢያ ውሃ የሚያገኝበትን ዘዴ ማጥናት፣ በተለይም የቤትን አሰራር በአዲስ መልክ በመቀየስ በማዕከለኛው ዘመን ይኖር ይመስል ለሚሰቃየው ህዝባችን አዲስ የአኗኗር ስልትን እንዲለምድ… ወዘተ. በነዚህና በአያሌ የአገር ግንባታ ነገሮች ላይ መረባረብ አለብን። ይህንን የህዝባችንን ህልምና ፍላጎት ዕውን ማድረግ የምንችለው ዓለምንና እያንዳንዱን አገር ከሚያጠፋው የሰይጣን ርዕዮተ-ዓለም የተላቀቅን እንደሆን ብቻ ነው። ለዚህ የተቀደሰ ተግባር ቀን ሌሊት መስራት አለብን። ብርታቱንና ጽናቱን ይሰጠን ዘንድ ራሳችንን በራሳችን ማግኘት አለብን። ሁሉም ነገር በጭንቅላታችን ውስጥ ስላለ ህዝባችን የተመኘውን ስለምና ዕድገት ተግባራዊ ለማድረግ ምንም የሚቸግረን ነገር የለም።ሁሉም ነገር አለን፣ ነገር ግን እንዳናስብና እንዳንሰራ ታግደናል !!
ፈቃዱ በቀለ
fekadubekele@gmx.de

http://www.ethiopia.org/index.php?lang=en

አስተያየት መስጫው ተዘግቷል።