“ማኔ፣ ቴቄል፣ ፋሬስ”፡- ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ./መንግሥት ሆይ በሚዛን ተመዝነህ ቀለህ እየተገኘህ ነውና እንግዲህ እንጠይቅህ … ተጠየቅ …?! በተረፈ ወርቁ

September 20th, 2016 ይመይሉ ይመይሉ ያትሙ ያትሙ

ይህን “ማኔ፣ ቴቄል፣ ፋሬስ” የሚለውን ኃይለ ቃል የምናገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ በትንቢተ ዳንኤል መጽሐፍ ክፍል ውስጥ ነው፡፡ የዚህ ጽሕፈት ምክንያትና ትርጓሜ ታሪክ በአጭሩ እንዲህ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆኑት እስራኤላውያን በኃጢአታቸው፣ በክፋታቸውና በዓመፃቸው የተነሳ እግዚአብሔር ተቆጥቷቸው፣ አዝኖባቸው ነበር፡፡ እናም አምላካቸው ጠላቶቻቸውን፣ ወደረኞቻቸውን በላያቸው ላይ አሥነስቶባቸው በጦርነት ድል ኾነው፣ ውርደትንና ሃፍረትን ተከናንበው፣ ከምድራቸው፣ ከአባቶቻቸው ርስት ተነቅለው በባዕድ ምድር ምርኮኛ፣ ግዞተኛና ተንከራታች ሕዝብ ሆነው ነበር፡፡

በግዞት፣ በባዕድ ምድር ከእናት ምድሩ ከኢየሩሳሌም ርቆ፣ በስደት ሀገር ባቢሎን በአሕዛብ ምድር የነበረው የእግዚአብሔር ሰው ነቢዩ ዳንኤል – የአንቺ የይሁዳ ምድር፣ የአባቶቼ ርስት “ኢየሩሳሌም ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ፣ ምላሴም ከትናጋዬ ጋር ይጣበቅ …!” በሚል ሰቀቀንና ናፍቆት፣ የኀዘን እንጉርጉሮ፣ የወገኖቹን ኃጢአት በደላቸውን፤ ፍዳ ሐበሳቸውን ተሸክሞ፣ የሕዝቡን ውርደታቸውንና ሥቃያቸውን፣ መከራና ሰቆቃቸውን፣ ዋይታና ጩኸታቸውን … የአባቶቻቸው አምላክ ያህዌ ከሰማይ በቃ ይልና ወደ ምድራቸው፣ ወደ አባቶቻቸው ርስት ይመልሳቸው ዘንድ በጸሎቱ፣ በእንባው ስለ ሕዝቡ የተማፀነ፣ አብዝቶ የቃተተ፣ የተሟገተ ብርቱ ነቢይ ነበር፡፡ መጽሐፍ እንዲህ እንዲል፡-

“በከለዳውያን መንግሥት ላይ በንገሠ … በአሕሻዊሮስ ልጅ በዳርዮስ በመጀመሪያ ዓመት እኔ ዳንኤል የኢየሩሳሌም መፍረስ የሚፈጸምበትን ሰባውን ዓመት፣ እግዚአብሔር በቃሉ ለነቢዩ ለኤርምያስ የተናገረውን የዓመቱን ቁጥር በመጽሐፍ አስተዋልሁ፡፡ ማቅ ለብሼ በአመድም ላይ ሆኜ ስጾም፣ ለሕዝቤና ለሀገሬ እጸልይና እለምን ዘንድ ፊቴን ወደ ጌታ አምላክ አቀናሁ፡፡” ዳን. ፱፣፩-፲፱፡፡

ታዲያ ይህ የሀገሩና የሕዝቡ መጥፋት አብዝቶ የሚገደው፣ ሕዝብህ በባዕድ ምድር ያለ መሪና እረኛ የትም ተበትኖ፣ ባዝኖ አይቅር … አቤቱ እባክህ ሕዝብህን አስብ፣ ርስትህንም ባርክ – እያለ ማቅ ለብሶ ትቢያ ነስንሶ፣ በአመድ ላይ ተቀምጦ እግዚአብሔር አምላክ ሕዝቡንና ምድሩን በምሕረትና በቸርነት ይጎበኝ ዘንድ የመከራ እንጀራን እየበላ ሱባኤ የገባ፣ በእንባና በጸሎት ወደ ፈጣሪው ስለ ሕዝቡ አጥብቆ የጸለየ፣ የማለደና የቃተተ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው ነበር ነቢዩ ዳንኤል፡፡ (እዚህች ጋር እግረ መንገዳችንን አንድ ትዝብት አከል ጥያቄ እናንሳ እስቲ … እንደው በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ክቡር የሰው ልጅ በየአደባባዩ በጥይት እየተመታ፣ ደሙ በግፍ ሲፈስ- ምድሪቱ አኬል ዳማ ሆና የኢትዮጵያ እናቶች የፍርድ ያለህ እያሉ እንባቸውን ወደ ሰማይ ሰማያት ሲረጩ፣ ዋይታና ጩኸት በየአቅጣጫው ሲሰማ- ሕዝብም:-
“እነርሱ አዲስ አበባ – ተነጋገሩና፣
ካርታውን ድንበሩን – ጨርሰው ላኩና፣
ወንድምህን ጠላት ነው – ብለው መከሩና፣
ወንድምየው ሞተ – እግዜሩም ተናቀ፣
ና! ውረድ አንተ አምላክ – ወገን ተላለቀ፡፡”

እያለ የኀዘን እንጉርጉሮውን ሲያሰማና ሙሾውን ሲያወርድ የየትኛው የሃይማኖት ተቋም የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች ናቸው እንደ ነቢዩ ዳንኤል ማቅ ለብሰው ትቢያ ነስንሰው ስለ ሕዝብና ስለ አገር ጥፋት ከሕዝባቸው ጋር ሱባዔ የገቡት …?! የትኛዎቹ የሃይማኖት አባቶች ናቸው- መንግሥትን ገሥጸው፣ ሕዝብን በፍቅር ቀርበው አረጋግተው፣ የዕርቀ ሰላም ሥራ የሠሩት … እንደውም አንዳንዶቹ ከሰሞኑን እንደታዘብነው በቲቪ ቀርበው፣ በመንግሥት ሳምባ የሚተነፍሱ “ልማታዊ የሃይማኖት መሪዎች” መሆናቸውን በደንብ አስረገጡልን እንጂ … የሃይማኖት መሪዎቻችንን የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞት መግለጫዎችን ያስታውሷል፤ ያስተውሏል፡፡)

“ንግባዕኬ ኀበ ጥንተ ነገር” እንዲሉ አባቶቻችን ሊቃውንት፣ ወደ ቀደመ ጉዳያችን እንመለስ፡፡ ነቢዩ ዳንኤል ከሕዝቡ ጋር በግዞት በነበረበት ባቢሎን ምድር በአንድ ወቅት ንጉሡ በቤተ መንግሥቱ ታላቅ ግብዣ ላይ መኳንንቱን፣ ታላላቅ ሹማምንቱን፣ ባለሟሎቹንና እቁባቶችን ሰብስቦ እግዚአብሔርን ያሳዘነ ፀያፍና የማይገባ ነገርን ያደርግ ጀመረ፡፡ የዚህን ጊዜ የሰው እጅ ጣቶች በንጉሡ እልፍኝ ግድግዳ ላይ እንዲህ ጻፈች:- “ማኔ፣ ቴቄል፣ ፋሬስ”፤ ንጉሡ ይህን ጽሑፍ ባየ ጊዜ በድንጋጤ ተመታ- ፊቱ ተለወጠበት፣ የወገቡ ጅማት ተፈታ፣ ጉልበቱ ከዳው፣ ብርክ ያዘው፡፡

አንዳንች ክፉ ድንጋጤ የወረደበት ንጉሥ ብልጣሶር የዚህን ጽሑፍ ምስጢር ይፈቱ ዘንድም በአስቸኳይ የከለዳውያንን ጠቢባን ሁሉ ወደ እልፍኙ አስጠራ፡፡ ግና የባቢሎን ጠቢባን የዛን ጽሑፍ ምስጢር፣ ፍቺ ለንጉሡ ሊፈቱለት አልተቻላቸውም ነበር፡፡ የዚህን ጊዜ ነበር የእግዚአብሔር ሰው የሆነውን የዳንኤልን ማስተዋልና ጥበብ ጠንቅቃ የምታውቀው የንጉሡ የብልጣሶር ሚስት ወደ እልፍኙ ዘልቃ፣ ወደ ባለቤቷ ጆሮ ተጠግታ በባቢሎን ምድር ከዳንኤል ውጭ የዚህን ጽሕፈት ምስጢር የሚፈታ ማንም ሌላ ሰው እንደሌለ ሹክ አለችው፡፡ “የሴት ብልሃቱን የጉንዳን ጉልበቱን፤ የሴት ምክር የእሾህ አጥር፡፡” እንዲሉ አበው ንጉሥ ብልጣሶር በሚስቱ ደገኛ የምክር ቃል አማካኝነት የእግዚአብሔር ሰው ዳንኤል ወደ ንጉሡ እልፍኝ በክብር ተጠርቶ ገባ፡፡

ዳንኤልም በዙፋኑ ላይ በመኳንንቱ፣ በሹማምንቱና በእቁባቶቹ ተከቦ በድንጋጤ ግራ ተጋብቶ የተቀመጠውን ንጉሥ ብልጣሶርን እንዲህ አለው፤ “ንጉሥ ሆይ እግዚአብሔር አምላክ ለአባትህ ለናቡከደነፆር ሰፊ መንግሥትንና ግዛትን፣ ክብርንና ግርማን ሰጠው፡፡ እርሱ ግን ልቡ በታበየ፣ በኩራትም ያደርግ ዘንድ መንፈሱ በጠነከረ ጊዜ ከመንግሥቱ ዙፋን ተዋረደ፣ ክብሩም ተለየው፡፡ ከሰው ተለይቶም ተሰደደ፣ ልቡም እንደ አውሬ ልብ ሆነ፣ መኖሪያውም ከምድረ በዳ አህዮች ጋር ነበረ፤ እንደ በሬ ሣር በላ፣ አካሉም በሰማይ ጠል ረሰረሰ፡፡ አንተም ይህን ሁሉ ስታውቅ በአባትህ የክፋት፣ የዓመፃ፣ የትዕቢት መንገድ ሄደሃልና ውርደትህና የዓመፅ ደመወዝህ እነሆ በፊትህ አለ …፡፡

ይህ ጽሕፈትም ስለ ክፉ ሥራህና ስለ መንግሥትህ አሳዛኝ ፍጻሜ እንዲህ ተጽፎአል፡፡ የጽሑፉ ፍቺም እንዲህ ይተረጎማል፡፡ ንጉሥ ሆይ ሺህ ዓመት ንገሥ … በረከትህ ለአንተ ይሁን፣ ለእኔ ያልከውን ሽልማትህንና ክብርህንም ለሌላ ሰው አድርገው፤ የነገሩ፣ የጽሕፈቱ ፍቺ ግን ይህ ነው፤ “ማኔ ማለት፥ እግዚአብሔር መንግሥትህን ቈጠረው ፈጸመውም ማለት ነው፤ ቴቄል ማለት፥ በሚዛን ተመዘንህ፥ ቀልለህም ተገኘህ ማለት ነው፡፡” በማለት የእግዚአብሔር ሰው የሆነው ዳንኤል ለባቢሎን ንጉሥ ለብልጣሶር አሳዛኝ የሆነውን የእርሱንና የመንግሥቱን ፍጻሜውን እንዲህ አረዳው፡፡
“እግዚአብሔር ሲቆጣ በትርን አይቆርጥም፣
ያደርገዋል እንጂ ለወሬ እንዳይጥም፡፡”

እንዲሉ አበው – የንጉሥ ብልጣሶር መንግሥት ፍፃሜው ያማረ አልሆነምና፣ በዛው ሌሊት በጠላቶቹ ተይዞ፣ በግፍ ተገደለ። መንግሥቱና ግዛቱም ለሁለት ተከፍሎ ለሜዶንና ለፋርስ ነገሥታት ተላልፎ ተሰጠበት፡፡ ታሪኩን በዚሁ ልግታውና ወደ ዋናው የዚህ መጣጥፌ ጭብጥ ልለፍ፡፡
ዛሬም ኢሕአዴግ/መንግሥት የቆመበት የታሪክ ጫፍና መስቀለኛ መንገድ ይህን ከላይ ያነሣሁትን ታሪክ የሚያጎላ መስሎ ቢሰማኝ ይህን አሳዛኝ ታሪክ እና “ማኔ፣ ቴቄል፣ ፋሬስ” የሚለውን የመጽሐፍ ኃይለ-ቃል የዛሬው መጣጥፌ አርዕስትና መግቢያ፣ መንደርደሪያ ይሆነኝ ዘንድ መረጥኩት፡፡ ሮማዊው የሕግ ሰው፣ ፈላስፋና የታሪክ ሊቅ የሆነው ሲስሮ፣ “ከታሪክ ለመማር የማይወዱ ሁሉ ታሪክን ለመድገም የተፈረደባቸው ናቸው፡፡” እንዲል፤ ከዘውዱና ከወታደራዊው የደርግ ሥርዓት አሳዛኝ ውድቀት ለመማር የፈለገ የማይመስለው ኢሕአዴግም ሌላ የጥፋት፣ የውርደት ታሪክ በራሱና በአገሪቱ ላይ ለመድገም በተጠንቀቅ የቆመ፣ የተፈረደበት ነው የሚመስለው፡፡

ዛሬ አርፍዶም ቢሆን ኢሕአዴግ/መንግሥት በመልካም አስተዳደር እጦት፣ የሕዝብ አገልጋይነት ቅን መንፈስ መራቆት ድርቅ ክፉኛ ተመትቼ እየተንገላታሁ ነው፣ ሙሰኝነት የሥርዓቱ/የመንግሥቴ አደጋ ሆኖ ከፊት ለፊቴ እንደ ዘንዶ ሊውጠኝ አፉን ከፍቶብኛል፣ የባለ ሥልጣናቶቼ ኪራይ ሰብሳቢነት ዓይን ያወጣ ሌብነት/የጠራራ ፀሐይ ዝርፊያ በአፍጢሜ ሊደፋኝ ደርሷል፣ የመበስበስና ዝቅጠት አደጋው ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍቶብኛል፣ ትምክህተኝነትና ጠባብነት እንደ አብሾ አናታቸው ላይ የወጣባቸው መንገዴን ሁሉ በእሾህ አጥረውና ዳጥና ጨለማ አድርገውት ግራ አጋብተውኛል፤

እስከ አንገቴ ያጠለቀኝ የሕዝብ የፍትሕ ያለ ጥያቄና ብሶት፣ ዋይታና ሮሮ ጎርፍ ሆኖ ጠራርጎኝ ከመወሰዴ በፊትም “በጥልቀት መታደስ/መለወጥ” አለብኝ በሚል ከጓዳ እስከ እልፍኝ ድረስ ተጠራርቶ በየክልሉ አፈርሳታ ተቀምጧል፤ እንግዲህ ወዶም ይሁን ተገዶ በሚዛን ላይ የወጣው ኢሕአዴግ ወይ ተመዝኖ ያልፋል አሊያም ደግሞ እንደ ገለባ ቀሎና ተቃሎ – “ማኔ፣ ቴቄል፣ ፋሬስ” ተብሎ በእግዚአብሔር ፍርድ – እንደ ትቢያ ተራግፎ፣ በሕዝብ ቁጣ ነፋስ ተገፍቶ በታሪክ ማህፀን ውስጥ ተጠቅልሎ አልፎ በጸጸት በነበር እናወሳው ይሆናል፡፡ መቼም ኢሕአዴግ መንግሥተ-ሥላሴ አይደለምና ለዘላለም አይኖርም፤ ሊኖርም አይችልም፡፡ ሀገርና ሕዝብ ግን ሁሌም ይኖራሉ፡፡ ኢሕአዴግ/መንግሥት ሆይ እንግዲህ የታሪክ እውነታው ይኼና ይኼው ብቻ ነው፡፡

ከዚህ የታሪክ እውነታ ባሻገር ግን … እስቲ በዚህ የጭንቅ፣ የጣር ቀን ወዶም ይሁን ፈቅዶ፣ አሊያም ባጋጠመው ተግዳሮት፣ ብርቱ ፈተና ማጣፊያው አጥሮት ሳይወድ በግድ ራሴን እገመግማለሁ፣ በጥልቀት አያለሁ፣ እፈትሻለሁ ብሎ ወደ ሚዛን ላይ ተገፍቶ የወጣውን የትናንትናውን የበረሃ ፋኖ የዛሬውን የኢሕአዴግ መንግሥት ታሪኩን፣ ገድሉን ከዛሬው የትግሉ ፍሬ ጋር እያነፃፀርን በጥቂቱ፣ በጣም በጥቂቱ እናየው፣ እንፈትሸው ዘንድ ወደድኹ፡፡

ያን ወርቃማ የወጣትነት አንዳንዶቹም ገና አፍላ የልጅነት ዘመናቸውን ምንም ነገር ሳይጓጓቸው – የእናት፣ የአባት፣ የቤተሰብ፣ የወዳጅ ዘመድ … ናፍቆትና ትዝታ ወደ ኋላ ሳይጎትታቸው ከሞቀ ቤታቸው፣ ከእናቶቻቸው ጉያና ነገ የተሻለ ኑሮንና ሕይወትን ከሚያመቻችላቸው ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ወጥተውና ርቀው ወርቃማ የወጣትነት ዘመናቸውን ለበረሃ የገበሩ- የበረሃው እዋይና ንዳድ … ፈጽሞ ሳይበግራቸው፣ ረሃቡና ጥሙን ታግሰው፣ አንጀታቸውን በዝናር መቀነት ጥብቅ አድርገው አስረው፣ ከጠኔ ጋር ታግለው፣ አንጀታቸው በረሃብ የተነሳ ክፉኛ ታጥፎ፣ በውሃ ጥም ጉሮሮአቸው እየተሰነጠቀ … የልጅነት ወዛቸው በፀሐይ ሐሩር ገርጥቶ፣ የወጣትነት ውበታቸው እንዲያ ከስሎና እንደ ምድጃ ጠቁሮ፣ ከሰውነት ተራ ወጥተው ብርቱ ሥቃይን ያሳለፉ እኒያ የትናንትናው የድሃው ገበሬ ልጆች፣ የጭቁኑን ወገናቸውን ተስፋውን፣ የነገ ሕልሙን ተሸክመው ረጅሙን ተራራ በጽናት የወጡ፣ ተራራን ያንቀጠቀጡ፣ ተራራን ያናወጡ ትውልዶች፣ ከእሳት የወጡ ትንታጎች፣ ፋኖዎች፤

ከላይ ሳያቋርጡ የእሳት አሎሎን ከሚያዘንቡ የጦር ጀቶችና አውሮፕላኖች፣ በምድር ላንቃቸውን ከፍተው ሳያባሩ የሞት መቅሰፍትን ከሚተፉ ከባድ የጦር መሣሪያዎች ፊት አንዳንች ፍርሃት ሳይበግራቸው፣ በታላቅ ጀግንነትና ወኔ ሞትን፣ ፍርሃትን ተቋቋመው ስለ ፍትሕ የተሟገቱ፤ በሞት ጣር ሸለቆ፣ አስፈሪ የጨለማ ፅልመት ውስጥ አልፈው፤ ከደሃው፣ ከጭቁኑ ገበሬ ጋር የበላውን በልተው፣ ረሃቡን ተርበው፣ ጥማቱን ተጠምተው፣ የመኝታ መደቡን ተጋርተው፣ በማጀቱና በጎታው ውስጥ ውለውና አድረው፣ ሀገርን ያህል – ኢትዮጵያን ያህል ትልቅ ምስጢር በልባቸው ቋጥረው – በምድር ልብ፣ በዋሻና በሸለቆ ውስጥ ለሕዝብ፣ ስለ ሕዝብ ከሕዝብ ጋር በአንድነት ቁመው፣ መክረውና ዘክረው፤

… አዎን እነዛ ፋኖ ብላቴናዎች፣ ታላላቅ ነን በሚሉት ዘንድ እጅግ የተናቁ፣ በብዙዎች ዘንድ አንዳንች ክብርና ሥፍራ የተነፈጋቸው፣ አብዝተው ስድብንና ንቀትን የጠገቡ ታናናሽ የሕዝብ ልጆች ባልፀና ጉልበታቸው፣ ባልጠነከረ ጫንቃቸው … ግን ደግሞ ከብረት በጠነከረ ወኔያቸው፣ ተራራን ባፈለሰ ፅናታቸው እንደ መርግ የከበደውን ያን ሁሉ የመከራ ውርጅብኝ ተሸክመውና ታግሰው፣ ስለ ጭቁኑ ወገናቸው ያላቸው ታላቅ ፍቅርና መቆርቆር – ኃይልና ጉልበት ሆኗቸው የሕዝባቸውን ቀራኒዮ በጽናት፣ በትዕግሥት የወጡ ባለ ድሎች፤ ባለ ገድሎች፡፡ ለፍትሕና ለዲሞክራሲ፣ ለነፃነት፣ ለሰው ልጆች መብትና እኩልነት ሲሉ በየበረሃው የወደቁ የታጋይ ጓዶቻቸውን የደም ቃል ኪዳንና የወገናቸውን ፅኑ፣ ታላቅ አደራ በልባቸው ጽላት ተሸክመው ረጅሙን ተራራ የወጡ የሕዝብ ባለ አደራዎች፤
ስለ ፍትሕ፣ ስለ ጭቁኖች መብትና እኩልነት፣ ስለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት … ገና ከማለዳው ‹‹ዱር ቤቴ›› ብለው ፋኖነትን ምርጫ ያደረጉና አብዝተው ስለ ጭቁኑ ወገናቸው የጮኹ፣ የቃተቱ … ላባቸውን፣ ደማቸውንና እንባቸውን በአንድነት ቀላቅለው ሳይሰስቱ ለሕዝባቸው ጥቅም የገበሩ- የድሃው ገበሬ የአብራኩ ክፋዮች፣ በእሳት የተፈተኑ፤ ታሪካቸውን፣ ገድላቸውን በደም የጻፉ፣ የሕዝብ ልጆች ትናንትና ነበሩን፣ ዛሬም አሉን …፡፡ ታሪካችንን ስንመረምር ድኅነትንና ኋላ ቀርነትን ለማጥፋት፣ ፍትሕና ዲሞክራሲን ለማስፈን በሚል ዓላማ ስር በየአቅጣጫው ተሰልፎ ከፍተኛ የሕይወት መሥዋዕትነትን የከፈለው የተማሪው፣ የገበሬው፣ የሀገሪቱ ምሁራንና ሕዝብ ቁጥር የትየለሌ ነው፡፡

ይህ መሥዋዕትነትና ታላቅ ገድል፣ ይህን አኩሪ ታሪክ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ኢትዮጵያ ጫፍ ያሉ ሕዝቦች ስለ ነፃነትና ፍትሕ፣ ስለ ሰው ልጆች እኩልነት፣ መብትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፈን ላባቸውንና ደማቸውን የገበሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በጋራ የሚጋሩት የሕዝብ ልጆች ሁሉ ታሪክና ገድል ነው እንጂ ከአንዳንድ የኢሕአዴግ አንጋፋ ታጋዮች ዘንድ በነጋ ጠባ እንደምንሰማው ሌላውን በጠላትነትና በፀረ ሕዝብነት ፈርጀው ብቻቸውን የሚኩራሩበት የእነርሱና የእነርሱ የብቻው የሆነ ታሪክ ወይም ገድል እንዳይደለ፣ እንዳልሆነም በቅን መንፈስ ለዛሬዎቹ ልባቸው በኩራት ለታበየባቸው የኢሕአዴግ ታጋዮችና ሹማምንት ልንነግራቸው እንወዳለን፣ እንደፍራለንም፡፡

የቀድሞው የሕወሓት አንጋፋ ታጋይ ሜ/ጄ አበበ ተ/ሃይማኖት/ጆቤ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ እንዳሉት፣ “ከ25 ዓመት በፊት በተገኘው የትጥቅ ትግል ድል አድራጊነት ታሪክ አልያም መንፈስ እየተኩራሩና እየተኮፈሱ መኖር አይቻልም። አንዳንድ ወገኖች፣ የትግሉ ድል ሕዝቦች በጋራ ያመጡት መሆኑን ክደው (የትግራይ ሕዝብ ከፍተኛ መሥዋዕትነት የከፈለ መሆኑ ሳይዘነጋ) ‘እኛ ያመጣንላችሁ ነጻነት ነው፤’ በማለት ሲኮፈሱ …” በማለት ያነሡት መከራከሪያ፣ የወቀሳ ሐሳብ ከላይ ያነሣሁትን ሐሳቤን የሚያጠናክርልኝ ይመስለኛል፡፡ ይህን የታሪክ እውነታ ከፍ ስናደርገው፣ ስናልቀው ደግሞ፡-

ለሦስት ሺህ ዘመናት የሚልቅ የሥርዓተ መንግሥት/State Formation የረጅም ዘመናት ታሪክ ያላትንና በበርካታ ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበረሰባዊ … ወዘተ- ውስብስብ የታሪክ ሂደቶችና ለውጦች ውስጥ ያለፈችን ታላቅ አገር- ኢሕአዴግ ዛሬ ደርሶ ትናንትና እንዳልነበረችና ዛሬ በእርሱ ትግልና ተጋድሎ ሕያው የሆነች ነገም ኢሕአዴግ ከሌለ ዕጣ ፈንታዋ የሚከፋ ሞቷም ሆነ ትንሣኤዋ በእርሱ እጅ ብቻ እንዳለ በመቁጠር – የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ “አልፋና ኦሜጋ” እርሱና እርሱ ብቻ እንደሆነ የማሰብ አባዜ፣ ታሪክን የመቀራምትና የመጠቅለል ሩጫ፣ ከልክ ያለፈ ኩራት/over dose pride ፈጽሞ ጤነኛ አካሄድ አይመስለኝም፡፡

ይህ ሕዝብ/ኢትዮጵያውያን እኮ የረጅም ዘመናት የነፃነት ተጋድሎ አኩሪ ታሪክ ያለውና ይህ ታሪኩ፣ ባህሉና ቅርሱ – ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ፣ ከአውሮፓ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ፣ ጃማይካና ካሪቢያ ድረስ ተሻግሮ እልፍ የነፃነት ፋኖዎችን መንፈስና ወኔ የቀሰቀሰ፣ በጥቁር ሕዝቦች ላይ የተጫነን የቅኝ ግዛትን አስከፊ የጭቆና ቀምበርን የሰበረና የነፃነት ቀንዲልን የለኮሰ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ከጉራዕና ጉንደት እስከ መተማ፣ ከደባርቅ እስከ መቅደላ፣ ከዶጋሊ፣ አምባላጌ፣ መቀሌና ዐድዋ እስከ ማይጨው … ወዘተ ለነጻነታቸው፣ ለሉዓላዊነታቸው ያደረጉት ተጋድሎ- ለአፍሪካ አሜሪካውያኖቹ የጥቁሮች መብት ታጋዮች ለእነ ማርከስ ጋርቬይ፣ ማልኮሜክስ፣ ለዶ/ር ማርቲን ሉተር ለፓን አፍሪካኒስቶቹ – ለኬንያው የነጻነት አባት ጆሜ ኬንያታ፣ ለጋናው ለዶ/ር ክዋሜ ንኩርማ፣ ለደቡብ አፍሪካው የነጻነት፣ የፀረ አፓርታይድ ታጋይና አርበኛ ለኔልሰን ሮሂላላ ማንዴላ … ወዘተ የወኔ ስንቅ የኾነ፣ የአፍሪካና የመላው ጥቁር ሕዝቦች ኩራት የኾነ የአኩሪ ታሪክ ባለቤት ታላቅ ሕዝብ መሆኑን- ኢሕአዴግ/መንግሥት ፈጽሞ፤ ፈጽሞ ሊዘነጋ አይገባውም፡፡ ይቀጥላል፡፡
ሰላም!!

አስተያየት መስጫው ተዘግቷል።