የኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግር፤ የበሔራዊ አጀንዳ እጦት ነው። (ክፍል አንድ) በጥበበ ሣሙኤል ፈረንጅ።

September 22nd, 2016 ይመይሉ ይመይሉ ያትሙ ያትሙ

ኢትዮጵያ ውስጥ የሕዝብ አመጽ ሲነሳ ይህ የመጀመርያው አይደለም። በተደጋጋሚ የተነሱ ሕዝባዊ ቁጣዎች፤ በስርዓቱ ጨካኝ እርምጃ፤ ቢዳፈኑም ሁሌም ውስጥ ለውስጥ እየተንቦገበጉና፤ እየተብላሉ፤ ጊዜና አጋጣሚ ጠብቀው መነሳታቸው አልቀረም። ዛሬም በኦሮምያ፤ በአማራና፤ በቆንሶ የምናየው ይህንኑ ነው። ሕዝቡ በሶቱን በአደባባይ ይገልጻል ውጭ ያለው የሃገር ተቆርቋሪው ዜጋ፤ የወገኖቹን ችግር ከአድማስ እስከድማስ ያስተጋባል። ምንም ህሊና በሌላቸው ግለሰቦችና፤ የወሮበላ ቡድን የሚመራው አገዛዝም፤ ለሁሉ ነገር መልሱ እስራት፤ ድብደባና፤ ግድያ በመሆኑ፤ ሕዝቡን ማሰቃየትና፤ የሃገሪቱን ብርቅዬ ዜጎች ሕይወት መቅጠፉን ቀጥሎበታል። ተው የሚለው ያጣው ይህ ግፈኛ አገዛዝ፤ ላለፉት 25 ዓመታት፤ ይህን የግፍ አገዛዙን ሊቀጥል የቻለው፤ በጥንካሬው ሳይሆን፤ በተቃዋሚው ደካማነት መሆኑ በተደጋጋሚ ቢነገርም፤ መልዕክቱ አድማጭ ያገኘ አይመስልም። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፤ ከአመታት በፊት “ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ” የሚለው መልእክታቸው ዛሬም ወቅታዊና ያልታሰበበት ጥያቄ ነው።

ደግመን ደጋግመን የምናየው ነገር፤ ሃገራችን ያጣቸው፤ በበቂ ሁኔታ ተደራጅቶ፤ ብሔራዊ አጀንዳ ቀርፆ ትግሉን አቅጣጫ የሚያሲዝ የፖለቲካ ሃይል ነው። በጊዜያዊ አጀንዳ፤ በግዚያዊ “ድል” የሰው ሃይልና ገንዘብ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ፤ የብርቅዬ ወጣቶች ሕይወት ሲጠፋ እያየን ነው። በየጥጉ ጮዋሂው በዝቶ፤ አድማጭ ለመጥፋቱ፤ የማህበራዊ ሚድያዎች ምስክር ናቸው። ላለፉት 42 ዓመታት፤ ወያኔ በሃገራችን የተከለውን የመርዝ ችግኝ ለመንቀል ከፍተኛ ትግል ቢደረግና ከፍተኛ መስዋዕትነት ቢከፈልም፤ የትግሬ ብሔርተኝነት፤ የአማራ ብሔርተኝነት፤ የኦሮሞ ብሔረተኝነት፤ ወዘተ፤ ከሁሉም በላይ ደግም ጽንፈኛ አመለካከቶች እያደጉና እያበቡ ሲመጡ አየን እንጂ፤ መስዋዕትነቱ የምንፈልገውን ፍሬ እያፈራ አይደለም። ከዚህም አልፎ በኢትዮጵያዊነት ስም፤ ዘረኝነት በአደባባይ ሲደሰኮር፤ “እረ ተው የሚለው ሰው ቁጥርም” ማነሱን የምንመስክርበት አደገኛ ወቅት ላይ ደረስናል።

የ1966 (በኢትዮጵያ አቆጣጠር) የፈነዳው አብዮት፤ አስተባባሪና መሪ ድርጅት በመጣቱ፤ ወታደራዊ መንግስት፤ ስልጣኑን ዘርፎ ለ17 ዓመታት ሲያስረን፤ ሲደበድበን፤ ሲያሳድደንና ሲገድለን ኖረ። በስንት ውድ ኢትዮጵያውያን ሕይወት መስዋእትነት፤ ፋሽስታዊው ደርግነ በማስወገድ የተገኘው ሕዝባዊ ድልም፤ ብሔራዊ አጀንዳና፤ ኢትዮጵያዊ ራእያ ባጡ ጥቂት ወሮበሎች ተነጥቆ፤ ላለፉት 25 ዓመታት ስንታሰር፤ ስንደበደብ፤ ስንሳደድና፤ ስንገደል ኖረናል፤ አሁንም እየሞትን ነው። ይህ ከታሪክ ባለመማራችን የከፈልነው ከፍተኛ ዋጋ ነው። ዛሬም ትምህርት አልወሰድንም፤ ዛሬም ብሔራዊ አጀንዳ ቀርጾ ሕዝቡን ከዳር እስከዳር የሚያነቃንቅ ሃይል አጥተን፤ በምናያቸው “የአካባቢ ሕዝባዊ አመጾች” እና ንቅናቄዎች እየተኩራራን፤ ‘ወያኔ ሊወድቅ ነው አለቀለት’ እያልን በውሸት እራሳችንን እናሞክሻለን። በእኛው ስህተት ትግሉ ረጅምና መራራ ሆንዋል። ወያኔ ጠንካራ ሆኖ አያውቅም፤ ፈተናችን ጠንካራ ተፎካካሪ አለማግኘቱ ነው። ወደ ኋላ ተመልሼ፤ በተለይ ተቃዋሚው ስለተጎናጸፋቸው ድሎች፤ ስለፈተናውና ስለችግሮቹ ብናገር፤ ስድስት መጽሐፍት ይወጣዋል። ዛሬ ካለው ነገር ልነሳና፤ እየተጓዝን ያለንበትን አቅጣጫ፤ እንዲሁም ስር ነቀል ለውጥ ከፈለግን ምን ማድረግ እንዳለብን ያለችኝን ላካፍል።

ከብዙ አቅጣጫ የሚነሳው ጥያቄ፤ በተለይ የትግራይ ሕዝብ ለምን ዝም አለ የሚል ነው። ለጥያቄው መልስ የሚሰጡት ጥያቄውን ያነሱት ሰዎች በመሆናቸው፤ ለእነሱ ምቹ የሆነው መልስ፤ የትግራይ ሕዝብ “የማይነሳው”፤ ከአገዛዙ ተጠቃሚ ስለሆነ ነው የሚል ነው። ከዚህ ድምዳሜ በመነሳት፤ ይህንኑ አመለካከታቸውን፤ የተቀረው ሕዝብ ላይ ለመጫን፤ ባገኙት አጋጣሚና፤ በተለይም በየማህበራዊ ድህረ ገጾች ላይ ይለጥፋሉ። ሌላው ቀርቶ “በጋዜጠኝነት ሙያቸው አንቱ ተባልን” ብለው የሚገምቱ ግለሰቦች ሳይቀሩ፤ ሳሞራ “ትግሬና ወያኔ አንድ ነው” ብሏልና ከፈለጉ ትግራይን ይዘው ይሂዱ በሚል አሳሳች አመለካከት፤ ወያኔ ወደሚፈልገው አቅጣጫ እንድንሄድ ግፊት ሲያደርጉ፤ ‘ተው እንዲህ አይደለም’ የሚላቸው እንኳን አላየሁም። “ትግሬ ዝም አለ” እያሉ ሳንባቸው እስኪድክም የሚጮሁ ዜጎች ግን፤ አዲስ አበባ ለምን ዝም አለ፤ ወላይታ፤ ጉራጌ፤ሽዋ፤ ወሎ፤ ወዘተ ለምን ዝም አለ ሲሉ አንሰማቸውም። ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንደገለጽኩት፤ የትግራይ ሕዝብ፤ ይህንን ስርአት ለመጣል፤ ከሌላው ሕዝብ የተለየ ምንም ሃላፊነት የለበትም። ወያኔ ለሚፈጽመው በደልና ግፍ ተጠያቂው የወያኔ አመራር፤ አባላቱና ደጋፊዎቹ ናቸው። ሳሞራ “ትግሬና ወያኔ አንድ ነው” ብሏል፤ ስለዚህ ሳሞራ ልክ ነው የሚሉን ሰዎች፤ ብአዴን የአማራን ሕዝብ እወክላለሁ ስላለ፤ ብአዴን የአማራን ሕዝብ ይወክላል ብለው ያምናሉ ወይ ብለን ለመጠየቅም እንገደዳለን። አቶ ተክለሚካኤል አበበ የተባሉ ጽሃፍ “የኛ ነገር፤ ትግሬን መነጠል፤ ሐሳዊ-ኢትዮጵያዊነት ነው” በሚል ርዕስ ባስነበቡት ጽሁፋቸው “ትናንትናና ዛሬ ሕወሀት/ኢህአዴግ፤ ነጋሪት ጎስሞ፤ አዋጅ ነግሮ፤ የኢትዮጵያን ችግር ሁሉ የፈጠረ አማራ ነው ሲል፤ ያንን ስንቃወም የኖርን ሁላ፤ አሁን ደግሞ መልሰን የኢትዮጵያ ችግር ሁሉ ፈጣሪ ትግሬ ነው ስንል፤ ለሕወሀት/ኢህአዴግ የአመታት ዘመቻ እጅ ብቻ ሳይሆን፤ እግርም እየሰጠን ይመስላል፡፡” ያሉት፤ ለሁላችንም የሕሊና ደውል ሊሆን ይገባዋል።

ለምን ይህ ወይም ያኛው ብሔር/ብሔረሰብ አልተነሳም ከማለታችን በፊት፤ በኦሮምያና በአማራ ክልል የተነሱት ንቅናቄዎች ጥያቄያቸው ምንድ ነው ብለን መጠየቅ ያለብን ይመስለኛል። በአማራ ክልል፤ በወልቃይትና ጠገዴ ማንነት ጥያቄ ዙርያ ንቅናቄ ከመንሳቱ በፊት፤ በኦሮምያ አካባቢ የአዲስ አበባን መስፋፋት አስመልክቶ በተነሳው ተቃውሞ የተጀመረው ንቅናቄ ላይ፤ በዙዎቸ “በተቃዋሚው ጎራ የተሰለፍ ሃይሎች” ጥያቄውን ሲያጣጥሉና “ጠባብነት” ነው፤ የአዲስ አበባ መስፋፋት ምን ችግር አለው ሲሉ አንብበናል፤ ሰምተናል። በ2016 መጀመርያዊች ላይ በአማራ ክልል ንቅናቄው ሲነሳና እያደገ ሲመጣ ነው፤ በኦሮምያና በአማራ ክልል ያለው ንቅናቄ እንደ “የጋራ ትግል” እየተቆጠረ የመጣው። ዛሬ በኮንሶ ያለውንም ንቅናቄ ስናይ፤ ንቅናቄው የተነሳው ከኮንሶ መሬት ጋር በተያያዘ ነው። ይህም በመሆኑም ነው፤ ከነዚህ ከሶስት ክልሎች ውጭ፤ በተቀሩት የኢትዮጵያ ክልሎች ሕዝባዊ ንቅናቄ የማናየው። ብዙዎች፤ በተለይ “ወያኔ አለቀለት” በሚል ስሜት ውስጥ ያሉ ሰዎች ያልጠየቁት እና ያላዩት ነገር፤ የወልቃይትና ጠገዴ ጥያቄ ቢመለስ፤ የትግሉ አቅጣጫ ምን ይሆናል? የኦሮምያ ክልል ጥያቄስ ቢመለስ ትግሉ ወዴት ሊሄድ ይችላል? የሚለውን ነው። ነውጡ በመነሳቱ ብቻ እርካታ አግኝተው፤ ሊመለሱ የሚገባቸውን ጥያቄዎች የዘነጉ በዙዊች ናቸው። ለመሆኑ፤ የወያኔ ጥንካሬውና ድክመቱ ምንድነው? የተቃዋሚውስ ድክመትና ጥንካሬ ምንድነው? ወታደሩ፤ ፖሊሱ፤ አጠቃላይ የፀጥታው መዋቅር በወያኔ ቁጥጥር ስር ሆኖ፤የተቃዋሚው ጎራ፤ ሕዝቡን ከጥግ እስከጥግ ሳያስተባብር፤ ስር ነቀል ለውጥ ሊመጣ ይችላል ወይ? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ካለ፤ መልሱን እስካሁን ያስነበቡን ስዎች ያሉ አይመስለኝም።

ወያኔና ሻዕብያ፤ ከዚያድ ባሬ ከወሰዱት ተመክሮ፤ “አማራ” ላይ ያነጣጠረ ትግል አድርገው ነው “ስኬታማ የሆኑት” እኛም ትግሉን በፀረ “ትግራይ” ላይ ካደረግን “ስኬታማ” እንሆናለን የሚል አመለካከት ካለ፤ ትግሉ፤ ሕዝቡ ወደ ሚፈልገው ትክክለኛ አቅጣጫና፤ የምንፈልገውን ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ስርዓት ለመግንባት ወደሚያስችል መንገድ የሚሄድ አይመስለኝም። ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚደረገውን ትግል ያህል፤ ብሔራው አጀንዳውን “ፀረ ትግራይ” ለማድረግ በትጋት የሚሰሩ ጽንፈኞች ለመኖራቸው ሶሻል ሚድያው በግልጽ ያሳብቃል። “ትግራይ ሁሉ ቆዳው ሲፋቅ ወያኔ ነው” የሚለው ደካማና አደገኛ አመለካከት፤ መለስ ዜናዊ ባንድ ወቅት “የኦሕዴድ አባል ሁሉ ቆዳው ቢፋቅ ኦነግ ነው” ከሚለው እኩይና ደካማ አስተሳሰብ የተለየ አይደለም። ማንም ሕዝብ፤ የትግራይን ሕዝብ ጨምሮ፤ሌላው ሕዝብ ሲጎዳ ደስተኛ ይሆናል ብሎ ማሰብ ሕሊናችን በጠባብነት እንዲዳክር መፍቀድ ነው። ትግሬ ሁሉ አመለካከቱ አንድ ነው ካልን፤ አማራ ሁሉ ኦሮሞ ሁሉ ወዘተ አመለካከቱ አንድ ነው ብለን እናምናለን ማለት ነው፤ ይህን ከተቀበልን ደግሞ ስለነዚሀ ብሔሮችም የሚባለውን መጥፎ ነገር ሁሉ እንቀበላለን ማለት ነው። ይህን ካመንን ደግሞ፤ ‘ነጭ ሁሉ አዋቂና ብልህ ነው፤ ጥቁር ሁሉ ደንቆሮና ወንጀለኛ ነው” የሚለውንም መላ ምት የምንቀበል ልንሆን ነው ማለት ነው። የሰው ልጅ “በዘሩ ያስባል” የሚል አመለካከት የለኝም። በነገሬ ላይ “የትግራይን ሕዝብ” በሌላው ሕዝብ ለማሰጠላትና፤ “እኛና እነሱ” የሚለውን ጎራ ለማስፋፋት፤ የወያኔ አባላት የሚሰሩበት ስትራተጂ ነው። የትግራይ ክልል ተጠቅሟል ወይስ አልተጠቀመም የሚለው ጉንጭ አልፋ ክርክር ከመሆን አያልፍም። በዚህ ጉዳይ ላይ አቶ ፈቃድ ሽዋ ቀና በቅርቡ “የትግራይና የህወሀት የበላይነት ጥያቄ – ዕውነቱ ውሸቱና ማስፈራሪያው” በሚል ርዕስ ባሰነበበን ጽሁፍ በሚገባ ገልጾታል። የትግራይ ክልል ተጠቃሚ ሆንዋል፤ ፋብሪካዎች መከፈታቸው፤ የአግልግሎት ሰጭ እንዱስትሪዎች መስፋፋታቸው፤ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች፤ የዘመናዊ እርሻ መስፋፋት፤ እነዚህ ሁሉ ለትግራይ ክልል የስራ እድል ፈጥረዋል። እነ ኤፈርት፤ እና ትልማ፤ የትግራይን ክልል ለመጥቀም እየሰሩ ነው፤ እነዚህ ድርጅቶች፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ከማንኛውም የንግድ ተቋማት በበለጠ፤ ከባንኮች ገንዘብ የማግኘት እድል አግኝተዋል፤ ያለቀረጥ እቃ ከውጭ ያስገባሉ፤ ተገቢውን ቫትም ሆነ የገቢ ታክስ አይከፍሉም፤ ይሁ ሁሉ ለትግራይ ክልል ትልቅ ጥቅም ነው። የትግራይ ክልል አልተጠቀመም ብዬም አልከራከርም። ግን የትግራይ ሕዝብ ለዚህ ተጠያቂ ነው ወይ? ፋብሪካ ሲከፈት አትክፈቱ ማለት አለበት? መንገድ ሲሰራ አትስሩ ማለት አለበት? ይህንን እያንዳንዱ ሰው ይመልሰው። የትግራይ ክልል ተጠቀመ ማለት፤ ትግሬ ሁሉ ተጠቀመ ማለት እንዳልሆን ይሰመርልኝ፤ ይህ ቢሆን ኖሮ፤ አዲስ አበባ በትግራይ ችግረኞች ተጥለቅልቆ ባላየን ነበር። ይህ ቢሆን ኖሮ መቀሌ “አፓርታይድ” ተብሎ የተሰየመ መንደር ባላስተናገደች።

ቀጣዩ ጥያቄ የትግራይ ክልል ከሌላው ክልል በተሻለ መልኩ ነጻነት አለው ወይ? ሕዝቡስ በሰላም ወጥቶ የመግባት እድሉ ከሌላው ክልል የተሻለ ነው ወይ? የሚል ነው። በእኔ እምነት ለዚህ መልሱ የተሻለ አይደለም የሚል ነው። እንደውም የትግራይ ክልል ከሌላው በበለጠ መብቱ የተረገጠና፤ ነፃነቱን የተነፈገ ለመሆኑ ብዙ መረጃዎች አሉ። ሌላው ቀርቶ ትግራይ ውስጥ የግል ጋዜጦች እንኳን አይገቡም። በትግራይ ውስጥ ምንም ዓይነት ተቃዋሚ እንዲንቀሳቀስ አይፈቀድለትም። በግንቦት 1991 (አውሮፓ አቆጣጠር) ወያኔ በትረ መንግስቱን ሲጨብጥ፤ ሃገር ውስጥ “በሕጋዊ መንገድ” ለመንቀሳቀስ ከገቡት ድርጅቶች መካከል፤ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ህብረት (ኢዲህ) አንዱ ነበር። ለዑል መንገሻ በትግራይ ሕዝብ የተወደዱና የተከበሩ በመሆናቸው፤ ትግራይ ክልል በዙ ደጋፊ አፍርተው ነበር፤ ይህ ያሰደነገጠው ወያኔ በርካታ የኢዲህን አባላት በማሰር፤ በማፈን፤ ንብረት በማቃጠል፤ የድርጅቱን ደብዛ ከትግራይ እንዲጠፋ አድርጓል። በርካታ ሕብረ ብሔር ድርጅቶች ትግራይ ውስጥ ለመንቀሳቀስ ባደረጉት ሙከራ፤ በስርዓቱ ያጋጠማቸውን ችግር በተደጋጋሚ መግለጫ አውጥተውበታል። ዛሬም አረና ትግራይ የተባለው ድርጅት ምን አይነት ማነቆ ውስጥ እንዳለ የምንሰማውና የምናየው ነው። ትግሬዎች ወያኔ ላይ ስላላቸው ተቃውሞ ሲነሳ፤ የማይነሳው፤ የትግራይ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትሕዴን) ስለሚባለው ድርጅት ነው። ይህ ድርጅት ከግንቦት ሰባት ጋር ግንባር ፈጥሮ ወያኔን እየታገለ እንደሆነ በቻ ሳይሆን፤ ወያኔን በትጥቅ ትግል ከሚፋለሙት በብዛትም በትጥቅም የበለጠ መሆኑን በተደጋጋሚ ተገልጽዋል፤ ታድያ የእነዚህ የትግሬ ታጋዮች መስዋእትነት አይቆጠርም? ሞላ አስገዶም የተባለው የድርጅቱ መሪ ለወያኔ እጁን ሲሰጥ፤ “ዘር ከልጓም ይስባል” ተብሎ ሲተች፤ በእኔ እምነት፤ ከሞላ የበለጠ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ ጉዳት ያደረሰውና አሁንም በማደርሰ ላይ ያለው ሰለሞን ተካልኝ የተባለ ሙዚቀኛ፤ በዘር ልጓሙ እንዴት አልተመዘነም? ዛሬ ወያኔን የሚደግፍ ሁሉ ትግሬ ብቻ ነው ካልን፤ እነ አባዱላ፤ እነ ተፈራ ዋልዋ፤ እነ ሙክታር፤ ወዘተ በምን የዘር ሂሳብ ነው የሚሰሉት?

በእኔ እምነት ትልቁ ችግር ብሔራዊ አጀንዳ አለመኖሩና ሕዝቡን በብሔራዊ አጀንዳ ስር እንዲነሳ አለማድረጉ ነው። ከጥቂት ጊዜያት በፊት፤ የአዲስ አበባን ህንጻ ያንቀጠቀጠው የሙስሊሙ ማህበረሰብ የት ገባ? ተገቢ ጥያቄ ይመስለኛል። ችግራችን፤ አፈንጫችን ሲመታ ዓይናችን አለማልቀሱ ብቻ ሳይሆን፤ ልባችን አለመድማቱም ጭምር ነው። ከ 1993 እሰክ 1996 (አውሮፓ አቆጣጠር) በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ ሬድዮ ላይ እሰራ በነበረበት ጊዜ፤ በዋሽንግተን አካባቢ የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ አባላትን የማነጋገር እድል አጋጥሞኝ ነበር። በወቅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የስብአዊ መብት ጥሰት የነበረበት ወቅት ነበር፤ እነዚህን መሪዎች በዚህ ጉዳይ ላይ አቋም እንዲወስዱ ስንጠይቅ፤ የሚነግሩን ገለልተኛ እንደሆኑ ነበር። እንዳውም አንዳንዶቹ፤ ከወያኔ ጋር በቁርኝት ይሰሩ ነበር። የሙስሊሙ ማህበረሰብ እንደ አንድ ማህበረሰብ የተነቃነቀው፤ ወያኔ በቀጥታ በሙስሊሙ ሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ በመግባት በፈጸመው ወንጀል ነው። ይህን የማነሳው ጣት ለመጠቆም አይደለም፤ ዛሬም ተመሳሳይ ነገር ስለማይ ነው። አንዱ ሲነካ ሌላው እንዲነሳ፤ የአንዱ ጉዳት የእኔም ጉዳት ነው እንድንል፤ የሚያስተባብር ሃይል የለንም። በግንቦት 1997 የአዲስ አበባ ነጋዴዎች አድማ አድርገው በነበረበት ጊዜ (በወቅቱ አዲስ አበባ ነበርኩ)፤ እኔና ጓደኞቼ ባለታክሲዎቹም እንዲያድሙ ለማስተባበር ስንሞከር፤ የሰጡን መልስ፤ “እኛ ስናድም ማን አገዘን?” የሚል ነበር። ያኔ የነበረው “የብሔራዊ አጀንዳ እጦት” ዛሬም ድረስ መቀጠሉ፤ ‘ለዚህ ተግባር ብቃት ያላቸው የተቃዋሞ መሪዎች አሉ ወይ’ ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል። ትልቁ ችግር፤ የአማራው ጥቃት፤ የኦሮሞ ጥቃት፤ የክርስቲያኑ መጠቃት፤ የሙስሊሙ መጠቃት ሆኖ እንዲሰማን የሰራነው ስራ የለም። ሁሉም “ለየእራሱ” ነው የሚጮኸው። የኦሮም ብሔራዊ ኮንግረስና ሰማያዊ ፓርቲ አብረን መስራት ጀምረን ካሉ ወራቶች አልፈዋል። ዛሬ ግን መግለጫ ከመስጠት ባሻገር የፈየዱት ነገር ምን እንደሆነ ለእኔ ግልጽ አይደለም። ውጭ የምንገኘውም፤ ያለውን ሕዝባዊ ንቅናቄ ብሔራዊ መልክ እንዲይዝ፤ ሃገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን በሃሳብም ይሁን በገንዘብ ለማገዝ በቂ እርዳታ እያደረግን አይደለም። እንዲተባበሩም ለማድረግ፤ መጀመርያ እኛ እራሳችን እዚህ መተባበር አለብን። እዚህም ቢሆን ላለፉት 25 ዓመታት በዲፕሎማሲው በኩል ምንም ስራ አልሰራንም ማለት ይቻላል። ያለንን የፖለቲካ ካፒታል ልንመነዝረውና ጥቅም ላይ ልናውለው አልቻልንም። ብዙ ጊዜ ችግራችን፤ ከሃገር ፍቅር የበለጠ፤ የድርጅትና የቡድን ፍቅር ማየሉ ይመስለኛል። ዛሬም “ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ” ማለት ግድ ይላል። በተሰባበረ አጀንዳ ወጣቱ አይለቅ፤ ብሔራዊ አጀንዳ ሊኖረን ይገባል፤ ዘረኝነት ከየትም አቅጣጫ ይምጣ ሊወገዝ ይገባል። “ጥሩ አማራ የሞተ አማራ ብቻ ነው” የሚለው የመከነ ወያኔያዊ አስተሳሰብ አደገኛና በታኝ ነው ብለን ካመንን “ጥሩ ትግሬ የሞተ ትግሬ ብቻ ነው” የሚለውን የመከነና የደከመ አስተሳሰብ ባንድ ድምጽ ልናወግዝ ይገባል። እንዲህ ዓይነት የተሳሳቱና ከፋፋይ አስተሳሰቦች፤ ትግሉ በሔራዊ አቅጣጫ እንዳይዝ የሚያደርጉና፤ ሃገራችንን ከፍተኛ አደጋ ላይ የሚጥል ነው። በዙ ጊዜያችንን የምናባክነው፤ ሃገር ውስጥ ያለውን ሕዝባዊ ንቅናቄ በማራገብ ነው። አስትዋጾአችን ከዚህ የተሻለ መሆን አለበት፤ ትግሉ ብሔራዊ አቅጣጫ እንዲይዝ፤ ብሔራዊ አጀንዳና እስትራቴጂ ለመቀየስ መስራት ይኖርብናል። አለዚያ፤ ልክ እንደ 2005 ምርጫና ነውጥ፤ ወያኔ ትግሉን ለጊዜውም ቢሆን ሊያዳፍነው ይችላል። ይህ ሁላችንንም እንቅልፍ ሊነሳ የሚገባ ነገር ነው። በቅርቡ በወያኔ፤ ጎንደር ውስጥ የታፈነችው ወጣት እንዳለችው፤ “እነሱ ሃገር ለማጥፋት ሌት ተቀን እየሰሩ፤ እኛ ሃገር ለማዳን ሌት ተቀን መስራት እንዴት ያቅተናል?”

 1. Milui
  | #1

  Samuel:

  I agree with your questions. … I was exactly asking my friend the questions you raised, especially the immaturity of the solidarity between Oromo and Amhara. Thank you for writing on this. Unfortunately, your conclusions seem to be devoid of the realty on the ground. … You are saying tell Ethiopians to hail Ethiopia not Ogaden, Oromo, Tigre, Sidama, Konso, Amhara, Gurage, Wolaita etc. You are writing from the US. I understand why you have a blind spot. Do you think your conclusion is a liability or and asset? I feel like your conclusion is a liability to current struggle underway. Please write more with an in-depth reading on the existing situation. You are now too shallow!

 2. ዶዶ
  | #2

  ከዚህ በፊት ይህ ሰው እኔ ኤርትራዊ ነኝ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም እያለ ሲያስካካ ነበር. አሁን ደግሞ የወያኔ ደጋፊ ሆኖ ብቅ ብሎአል

 3. Tibebe Samuel Ferenji
  | #3

  Dear Milui: I am somebody who strongly believe in the ideal of “Ethiopianism” and Ethiopia. My father is ethnic Oromo, whose father fought aginst the Italian invasion. There has never been a conflict between his Oromo ethnicity and “Ethiopinism”. Ethnocentrism is something I can’t comprehend. There reason could be I am from mixed ethnicity and have lived all my life seeing individuals as individuals instead of their ethnic background. There are millions of people with mixed ethnicity; in what “ethnic basket” are you going to put these Ethiopians? Unfortunately, some of those who advocate for ethnic politics are also from mixed ethnicity, or they are married to other members of ethnic group other than “their own”. For example, Jawar Mohamed has indicated that his mother is ethnic Amhara; Abo Abiyu Geleta’s wife is ethnic Amhara and so on. Some of my friends who advocate “only for Oromos” have either ethnic Amhara father or mother. If advocating for the ideal of Ethiopianism where the rights of all Ethiopians, regardless of their ethnicity is respected makes me Shallow, then I am guilty. I have done in depth reading in the danger of ethnic politics; and I have written a book about it titled “ዘረኝነትና ኢትዮጵያን የማዳን ፈተና”. Advocating for “Ethiopianism” is not debunking or dismissing any one ethnic groups concern. As far as I am concerned there is no conflict between being an Oromo and Ethiopian, Amhara and Ethiopian, Tigrean and Ethiopian, Ogaden and Ethiopia, etc. It has been a while since I left Ethiopia, but I was back in 1996 and stayed there for 11 months, and I was also back in 2006 and stayed there for about 10 months. Fortunately, in my line of business, I deal with newly arrival Ethiopians to the US every day; these are Ethiopians from all walks of lives, and share their views with me. I am also a “political junky” who digest every news and articles written about Ethiopia. My point in this article is that we need a national agenda that addresses everyone’s question and concern. I completely disagree with your assertion about “the immaturity of the solidarity between Oromo and Amhara”. There may have been a rift between the “Amhara” and Oromo elites in some quarter of our society; but there has never been any evidence to suggest that there has been any rift or conflict between the Amhara and the Oromo people. In 2006-2207, I spent most of my time in “Oromia region”, and I can tell you with certainty that the majority of Oromos that I encountered do not support ethnic politics. Ethiopia belongs to all ethnic groups in her territories. As you have indicated, I live in the US, and I have lived among, the Asians, Latinos, Africans, Europeans, blacks, whites, yellows, reds, etc. We came from divers continents and continue to live in one nation. I am not an American citizen but my right is protected as any American. This is the kind of Ethiopia I want; Ethiopia, united, with her beautiful diversity, where everyone’s right is protected and where justice for all is prevailed. If that makes me shallow; I respectfully accept “your complement”. If you think “ethnic politics is the answer, then let us have a real debate and avoid name calling. Thank you for taking the time to read the article and comment.

 4. አባ ቆያስ
  | #4

  ብሄራዊ አጀንዳ እንዳይኖር እንቅፋት ከሆኑት ነገሮች አንዱና ዋነኛው በዘርና በዘረኝነት መካከል ያለውን ልዩነት በትክክል ያለመረዳት ወይም ለመረዳት ያለመፈልግ ችግር መስሎኛል.

 5. ሰላም ለኩሉኩሙ
  | #5

  ወንድም ጥበበ፡
  ችግሩን በሚገባ አስቀምጠኸዋል። በትክክል አንዳስቀመጥከው ብሄራዊ አጀንዳ ባለመኖሩ የሚካሄደው የሕዝብ እንቅስቃሴ አንደ 1966 የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው። የሚያስጋው ግን በብሔራዊ አጀንዳዎች ዙሪያ ለማሰባሰብ የሚችል ሃይል አስካሁን ድረስ አለመፈጠሩ ነው። እንዲት ነው የሚፈታው የሚለው የወቅቱ የጋራ ጥያቄ ይመስለኛል።

 6. Lesson to learn
  | #6

  ጥበቡ ሳሙኤል ፈረንጅ
  ለአንተም ለተክሌም ሆነ ተመሳሳይ ሀሳብ ላላችሁ ሁሉ ማወቅና መርሳት የሌላባችሁ መሰራታዊ ጉዳዮች አሉ
  1. ያለፉትን ሁለት መንግስታት አወዳደቅ ብንመክለት
  የኢትዮ ሕዝብ ሲያምጽ በስልጣን ላይ ባለው መንግትስና በደጋፊዎቹ ላይ ነው
  ደርግና ወታደሩ አብሮ ወደቂ የጃንሆይ መንግስትና የፊውዳሉ ስርአት ደጋፊዎች አብሮ ወድቀዋል
  ስለዚህም ወያኔም ይወድቃል የትግራይ የበላይነት አብሮ ያክትማል ቻሉት!!!

  2. ያለፉትን ሁለት መንግስታት መሪነት ብንመለከት የአንድነት መንፈስ እንዲኖረን ሰርተዋል እንጂ የዘር መለዮ የመንግስት ፓሊሲ አርገው አልተነሱም
  ያ ማለት ግን ስህተቶች አልተሰሩም አየድለም ግን ሁለቱም መንግስቶች በብዙሃን መገናኞቻቸው የኦሮሞ ይሁን የትግራይ ሕዝብ የማዋረድ ስድብ እንደመሳሪያ አርጎ ሲጠቀሙ አልታየም አለ ካላችሁ አምጡት
  ስለዚህም ወያኔ ዘረኛ ነው የትግራይ ሕዝብ ከሌላው እንደተለየ ሕዝብ ለማድርግ ጥራል
  የወያኔና የደጋፊዎቹ ፓሊሲ እንጂ ሕዝብ በትግራይ ሕዝብ ላይ የትኛውን የብዙሃን መገናኛ ተጠቅሞ በዘራቸው ሲሰድባቸው ታውቃላችሁ
  የትግራይ እንደሌላው ህዝብ ሰርቶ መብላት አለበት እንጂ ከወገኑ አፍ በዝርፍያ በተነጠቀ ሃብት መኖር ትክክል አለመሆኑን ምስተማር አለብን እንጂ ዘራፍ አልተካሄደም ለትግራይ ክልል ከሌላው በላይ በጀት አልተመደበም ካልን በመረጃ እንነጋገር

  3. የትግል ጥሪ ለትግራይ ወገናችን መደረጉ ወገናዊነታቸው ማረጋገጥ ስለሆነ ለምን ተሳተፉ ተባሉ ማለት ስህተት ነው
  4. ትግሬን ሕዝብ ተለይቶ እንዲይታይ ያደረገው ወያኔ ስርዓት እንጂ ተቃዋሚው አይደለምና ተቃዋሚውን ከመክሰስ ታረሙ
  ወያኔ እንዳይወድቅና የስራውን ሃጢአት እንዳይታወስ የምፈልጉ ካላችሁ ታረሙ
  5. ያለፉትን ሁለት መንግስት ታሪካው አመጣጣቸው ከወያኔ ጋር ብንመለክት ሁለቱም መንግስት የአገር ውስጥ ድጋፍ አግኝተው እንጂ በውጭ ሃይል እገዛ ስልጣን አልወጡም እንደወያኔ በእንግሊዝና አሜርካ ድጋፍ መጥተው አገሩን ለባእዳን አላሰልፉም

  ደርግ የወታደሩና የሰራተኛው ድጋፍ አግኞቶ የመጣ ነው ወታደሩም ከአማራው ከትግራይ ከኦሮሞ ከሌሎችም አባል ነበሩበት ነበር
  ወያኔ ትግራይ ተወላጅ ብቻ ነው የሚወክለው

  የጃንሆይ መንግስት ከሽዋው ዘር መነሻነው ቢመጣም ታሪካዊ አመጣጠን መመልክት ያስፍለጋል የፊውዳሉን ስርአት ርሳቸው የፈጠሩት አይደልም የጎጃም ንጉስ ተካታዮች ነበሩ የትግራይ ንጉስ ዘሮችን ተከትሎ የሚያምጹ ነበሩ ስለዚህም የጎሳው ችግር ታሪካዊ ምክንያት ነበረው እንጂ ጃንሆይ የፈጠሩት አይደለም

  እውነት እንነጋገር ከተባለ የሸዋው ክፍል ወይም የጎሻም ክፍል ከሌላው የተለየ የልማት ፕሮግራም አላገኙም
  አለ ካላችሁ አውጡት

  ወያነ ዘረኛው ነው ክትግራይ በስተቀር ሌላው ይውደም ብሎ ነው የሚንቀሳቀሰው

  የጃንሆይንም መንግስት ከደርግም የበለጠ ሰርተዋል የሚያሰኘው ኢሮፕውያን አፍሪካን በመዳፉቸው ባረገበት ዘመን ይመሩ የነበሩ መሪ ነበሩ አገሪታን ክነሱ መዳፍ በማውጣት ትልቅ አመራር ሰጠተዋል ያም ሆኖ በሸዋ ክልል ከሌላው ክልል የበለጠ የልማት ፕሮግራሞች አለነበሩም በሃቅ እንነጋገር ከተባል

  ስለዚህም ወያኔ ዘረኝነትና ክትግራይ ሕዝብ ብቻ ድጋፍ አግኝቶ በመውጣቱና በውጭ ሃይሎች ድጋፍ ብቻ ሕልውናው የተመሰረተ በመሆኑ በይብልጥም የወያኔ መንግስት ግልጽ ፓሊሲ አውጥቶ ገንዝብ ሐብት ከሌላው ክፍል ዘርፎ ትግራይ ብቻ ሊያለማ በመነሳቱ ሕዝብ የትግራይ ተወላጅ የሆኑት ተባባሩ ብሎ ጠይቆአል
  ዘረኛው ወያኔ እንጂ ተቃዋሚው ሕዝብ አይደልም!!!!

  6. ወያኔ ለሰራው የትግራይ ሕዝብ ተጠያቂ ያለ የለም የተባለው ልማቱ የትግራይን የበላይነት ለማምጣት ብቻ ሁላችንም እንድንደሀይ የሚሰራ ደባና ወንጀል በመሁኑ ይቁም በቃ በቃ ነው
  7. ብሔራዊ አጀንዳ አለ የለም ብሎ በተቃዋሚው ላይ ማሳብብ ወያኔ አጀንዳ ማራማድ ገጽታ ነው
  አምራው ከኦሮሞው እስላም ክርስትያኑ በህብረት ተቃውሞክ ማሳመታ ከጀመሩ ቆይቶአል ትግላቸውም የብሄራዊ አጀንዳው አንድ ገጹ ነው ብሐራዊ አጀንዳ እንዳይኖር የሚሰራውኮ ወያኔ እንጂ ተቃዋሚኮ አይደለም የብሄራዊ አጀንዳ መኖሩ ከወያነ በስተቀር የሚጠላ የለም በተጨማሪም ለምሳሌ ግንቦት ሰባትና አርበኞች ግንባር ብሄራዊ አጀንዳ እንዲኖር የበኩላቸውን እያስተባበሩ ነውና ለምን በዚህ ተሳታፊ አትሆኑም
  8. ወያኔ አስገድዶ በዘር እንድንደራጅ አድርጎ እንጂ ሰው በፈቃዱ አይደልም
  እንካንስ ሰውን ዶሮ የወላይታ ሽሮው የሽሬ ብሎ ያደራጀው ወያኔው ነው
  ስለዚህም ወያኔ እስካል ሕዝብ ወዶ ሳይሆን በግል በክልሉ ተደራጅተዋል ያንን አሁን ተቃዋሚ እይሰበረው ነውና ብሄራዊ አጀንዳው እየታየ ነው ነጻነት እየመጣ ነው

  አባዱላ ምናምን የምትላቸው ምርኮኞችና ግልሰቦች ሲሁኑ አሁን ያምጸው ከዳር እስክዳር ሕዝብ ነውና ስጋ ቁጠር ቢሉት ጣፊያ እንደሚባለው ነው

  ትግራይ ሕዝብ ወገናችን ነው የትግራይ ሕዝብ የበላይነትን ግን አንቀበለም
  ሁላችንም በእኩልነት በመክባበር እንኑር ነው ትግሉ!!!!!

 7. ዳንግላ
  | #7

  በጣም አሳሳቢ ጥንቃቄ ! ህውሃት ኢንፍራ ስትራክቸሮቺን እያፈራረስ ነው ስልጣን የያዘው :: የውጭ አገር ኢንቨስትሜንት ኦብዠክቶቺን ቁጥር አንድ ጥበቃ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው ::ህውሃት ራሱ ነው የአኢኮኖሚ ተቋማትን የሚያቃጥለው : ያኢትዮጵያ ህዝቦች የሚታገሉት ከህውሃት ጋር ብች ነው :: አላማቸውም ይህ ብች ነው :: ከኢኮኖሚ ተቋም ጋር አይደለም : የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ሊያደርገው አያስበውም :: እንዲህ አይነት ጸያፍ ባህል የለዉም :: አሁን በዎያኔ ጊዜ እንዴት ይህ ነገር ተከሰተ ? የታዎቀ ነው ህውሃት የኢኮኖሚ ተቋማትን ማዉደም የሱ የስለጠነበት ሙያው ነው :: የሚቃዎሙትን ለማስዎንጀል የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም ::

 8. ሥብኃት
  | #8

  ኣዲስ የሚዎጣ ፊልም ..ምናልባት በቅርቡ ዎይም ትንሽ ቆየት ብሎ ህዉሃት እና ግብረ አበሮቹ ተቃዋሚ ውስጥ ስለ አሉ አንድ አንድ የኪነ ጥበብ ግለ ሰቦች ላይ character assasination የሚያደርግ መናኛ ካሪካቱር ፊልም ለመስራት ያን ሰገራ ነፍሳቸዉን ለማስታዎክ ተዘጋጅተዋል . ለዚህ ነገር መቆጨት አይስፈልግም ራስን ከፍ አርጎ ማስቀመጥ ነው . እነሱ በቀረቡኝ ቁጥር የኔን ከፍታ አያለሁ

 9. በላይ ዳኜው
  | #9

  አቶ ሳሙኢል በትክክል አስቀምጠህዋል እንዲያውጥሎብን ነው እንጅ ኢትይጵያዊያን ይህ የዚህ ዘር ያየዛ ዘር ይሚል የአይምሮ ድህነት ከገጠመን 25 አመት አለፈንና መመልስ አቃተን ዛሬ ሰው ጎንደር ተወልዶ አማረኛ ዘፈን መስማት አትችልም ተብሎ ሲገደል ከዚህ የበለጠ የሚያም ምንም ነገር የለም ድርጅት ቢኖር ኑሮማ ስንት ስራ በተሰራ ግን ምድረ ተለጣፊ ነው የተሰበሰበው የኢትዮጵያን የመከራ ቀን ለማሳጠር ማንም ሰው በሰውነቱ ብቻ ለ እውነት መታገል አለበት:

አስተያየት መስጫው ተዘግቷል።