የግብዞች ግብዣና የቀማኞች ይቅርታ፤ ከቀብር መልስ፡ – አለቃ ተክሌ ነኝ። ቫንኩቨር፡ ካናዳ፡

February 24th, 2010 ይመይሉ ይመይሉ ያትሙ ያትሙ

“በቁሜ ያሳደደኝ፡ በሕይወት የገፋኝ፡
ሳልሞት የቀበረኝ፡ ስሞትም ሊገድለኝ
የመውደዱ ጽናት፡ ለቀብር ጋበዘኝ።”

ሊቀ ጳጳስ፡ ብጹእ ወቅዱስ፡ አቡነ ዜና ማርቆስን ብሆን የምቀኘው።

እንባና ሳቅ፡ ሀዘንና ደስታ፡ ሞትና ሕይወት፡ ልጅና አዋቂ

ብዙ ግዜ ደረቅ ነኝ። አይኔ በግድ ነው እንባ የሚያወጣው። ፊቴ ጨካኝም ነው። አንዱ ስደት ያዘጋጀኝ ነገር እናትም ብትሞት ላለማልቀስ ነው። እነሆ ሲያትል ቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክርስቲያን ተገኝቼ፡ የሚረጨውን እንባና የሚነገረውን ምስክርነት በሰማሁ ጊዜ እንደባዬ ወረደ። አላለቅስም። ሳለቅስ ግን ደስ ይለኛል። አይኑን በሶፍት እያበሰ የሚያለቅስ ሰው አልወድም። እንባ ይፍሰስ እንጂ። ይውጣ። ይተንፍስ። እንዴት እንደሚለቀስ እንኩዋን በቅጡ ሳያዩ ያደጉት የሲያትል ኢትዮጵያዊያን ህጻናት “እዬዬ ሲሉ፡ አባ፡ አባቴ፡ አባታችን፡ ወይኔ፡ አረ ጥለሁን አይሂዱ፡ ምነው አባታችን፡ ….” የስምንት አመት ህጻን ልጅ ደግሞ ተነሳች። አማርኛና እንግሊዘኛ እያደባለቀች ነው የምትናገረው፡ “አሁን ማነው መስቀል የሚያሳልመኝ? አባ ልጄ፡ የኔ ልጅ ይሉኝ ነበር። አሁን ማነው ልጄ የሚለኝ? የማንንስ መስቀል እሳለማለሁ? ስትል ሰው ሁሉ በእንባ ፈረሰ። ሁለት ሶስት ሰው ቀብሬያለሁ። ለቅሶ በቅብር ዘመዶች ወይም በቤተሰብ ዙሪያ የተወሰነ ነበር። ሚስት፡ ልጆች፡ ወንድሞች። አብዛኞቻችን ሱፍ ለብሰን፡ ጥቁር መነጽር አለ፤ ጥግ ይዘን መኮፈስ ነበር ልማዳችን። እነሆ፡ ካገሬ በወጣሁ በዘጠኝ አመቴ፡ ዘመድ የሌላቸው አቡነ ዜና ግን የኢትዮጵያውያን ዓለም ሁሉ አለቀሰላቸው። ከአውስትራሊያ፡ እስከ ቫንኩቨር፡ ከለንደን እስከ ሰዊድን፡ ከዲሲ፡ እስከ አትላንታ፡ ከመርቆሬዎስ፡ እስከ መልከ ጸዴቅ፡ ከሚሚ እስከ ማሙሽ ስናዝን ሰነበትን። ኖ ኖ፡ ለራሳችን ነው ያለቀስነው። ምክንያቱም፡ አቡነ ዜና ቤተሰባቸው እኛ ነበርንና።

የሞተን ማድነቅ ይሆን? የአቡነ ዜናን ምን ለየው?

የተለመደ ይመስላል። ብዙ ሰው ቀብሬያለሁ። ብዙ ሰውም ሸኝቻለሁ። የብዙ ሰው የህይወት ታሪክ ጽፌ የብዙ ሰውም ታሪክ አንብቤያለሁ። ሰው ሲሞት፡ ቀማኛውም ደገኛውም፡ ቀጣፊውም ሰላቢውም መልካም መልካሙ ብቻ ነው የሚነገርለት። የአባታችን መልካምነት ሲነሳ፡ እንደዚያ ከዚህ በፊት እንደሰማናቸው ታሪክ ይመስለን ይሆናል። አይደለም። “አብረውን በነበሩ ሰዓት አባታችንን እንደ ዋዛ አይተናቸው ነበር” ሲል ይጀምራል በአባታችን ሞት የደነገጠውና ቅስሙ የተሰበረው ኪሩቤል የሳቸውን ገድል መጻፍ ሲጀምር። ሕይወቱ በትንሹም ቢሆን በኣባታችን ያልተነካ ሰው አልነበረም። ጠሕግ ባለሙያው ሼክስፒር ፈይሳ፡ ኦርቶዶክስ እንጂ አማኝ አይደለም። አባታችን ግን ሕይወቱን ነክተውታል። ፍቅራቸውን አይቷል። ነቢይ በህዝቡ ዘንድ አይከበርም አይደል? ሼክስፒርም ባንዳንዶች ዘንድ እንደዚያ ነበር። አባታችን በሕይወት ሳሉ አንድ የህግ ጉዳይ ገጠማቸውና ሰዎች እሳቸው ጋር ሄደው ስለሕግ ባለሙያና ስለሼክስፒር ተነሳ። አንዱ ከመካከል “አይ እሱ ገና ጀማሪ ነው፡ በደንብ ላያውቅም ይችላል” አለ። አባታችን ጣልቃ ገቡ “ታዲያ ምን ችግር አለ? እኛ እናሳድገዋለና። የኛው ልጅ አይደል? እኛ ያላሳደግነውን ማን ያሳድግልናል?” ሌላ ግዜ ደግሞ ሌላ ቀጣፊ ሰው መጣና ላባታችን የባጥ የቆጡን፡ ሀሰተኛ ወሬ ጀመረ። ቀጣፊ ያልነው እኛ ነን። አባታችን አይደሉም። አንዷ ሴት አባታችንን ጎተት አድርጋ “አባ ተዉት እባክዎትን፡ ይሄ ሰው የሚያወራልዎት ሁሉ ሀሰት ነው” አለቻቸው። “አይ እናቴ ይጨርስ ላድምጠው እንጂ። እኔ ካልሰማሁት ማን ይሰማዋል ብለሽ ነው” አሏት። ራሷ ነች የነገረችኝ። የታሪኳ ባለቤት። አባ ሰው አይንቁም። አባ ሰው ሲጠቃም አይወዱም። ለዚህ ነው የኢትዮጵያና የብርቱካን መታሰር የሚያንገበግባቸው።

ሙሉነህ ዮሀንስ ወዳጄ ነው። የቤተክርስቲያንን የአባም ልጅ ነው። እሱና ወዳጆቹ ወደ ቤ/ክርስቲያን ሲማልዱ፡ አባታችን በጆሮው “አረ እናንተ ሰዎች ምነው ይህቺን ሴት አሳስራችሁ ዝም ሆነሳ? እንደው ቢሆንም ባይሆንም ጭጭ እንዲል አታድርጉ እንጂ። ተንቀሳቀሱ። ጠላት አይመቸው።” ያቀረብኩት ቃል በቃል አይደለም። ለኔ እንዲመች አድርጌ ነው። እንደሚመስለኝ ለአባታችን ጠላት ዲያብሎስ ነው። ዲያብሎስ ግን በሰው ይመሰላል። አንዳንድ ግዜ በድርጅትም። ሕወሀት። አባ ባመኑበት ይቆማሉ። አይሸሹም። በሁለት ሺህ አምስትም ይሁን ከዚያ በኋላ ምርጫውን ተከትሎ በኢትዮጵያዊያን ላይ የደረሰውን ሁሉ ፊት ለፊትና ባደባባይ ያወግዛሉ። አንዳንድ የቤተክርስቲያኗ ቀኝ እጆች ራሳቸው ቢያጉረመርሙም እንኩዋን፡ አባታችን ከመርዳት ወደኋላ አይሉም። አላሉምም። በ2007 ጥቅምት መሰለኝ፡ እነ ብርቱካን ሚደቅሳ ሲያትልን ሊጎበኙ ሲመጡ፡ አባታችን በቢሯቸው ተቀብለው ቡራኬና ምክርን ሰጥተዋቸዋል። ሕዝቡም ወጥቶ እንዲቀበላቸው ቀስቅሰዋል። ለጊዜው አይጠቅመንም እንጂ ያ ተቃውሞ ገጥሞት፡ ራሱ ራሱን የቻለ ጣጣም ነበረው።

የአባ ጉዞ፡ የአባ ሕይወት

የዛሬ 72 ዓመት፡ አባ ጎንድር ተወለዱ። ደቆኑ። ቀሰሱ። ግሪክ ተማሩ፡ ከታላቁ ሟቹ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጎርጎሬዎስ (የቀድሞው አባ መዝገቡ) ጋር። ወለጋን በኤጲስ ቆጶስነት ሰበኩ።አምስት መቶ ቤ/ክ ተረክበው፡ አንድ ሺህ አደረሱት በስድስት አመት ውስጥ። አባ ሀያ አንድ አመት በቅስናና በዲቁና፡ ሰላሳ አመት ደግሞ በኤጵስ ቆጶስነትና በሊቀ ጳጳስነት አገለገሉ። አምላክ በአባታችን ብዙ ተአምርና ገድልን ፈጽሟል። በሕይወት በነበሩበት ግዜ፡ አባታችን ውዳሴ ከንቱን ስለማይወዱ ይሄን ሰራሁ፡ ይሄንን አደረግሁ ብለው አይመጻደቁም። የረጅም ግዜ የስራ ጓደኛቸው፡ አቡነ ሉቃስ አውደ ምህረት ላይ ቆመው እያለቀሱ ሲመሰክሩ፡ “አባታችን አንዴ ንቦች ተነሱባቸው። መሀል ምስጋና ላይ ንብ አካባቢውን ወረረው። አባታችን ተጨነቁ። ሕዝቡም ታወከ። አባታችን ጸሎታቸውን ቀጥለው ጨክነው ቅዳሴ ገቡ። ቅዳሴ ሲገቡ፡ በቤተ ክርስቲያኑ ላይ ሲተም የነበረው ንብ እንዳለ ከቤ/መቅደስ ገብቶ መንበሩ ላይ ሰፈረ። አባታችን ንቡን በእጃቸው ወደጎን ገለል እያደረጉ ስጋ ወደሙን ፈትትው ቅዳሴያቸውን ጨርሰው ወጡ። ያ ንብ አንድም ሰው ሳይነድፍ ተነስቶ ወጣ።” በጊዜያዊ ቀብራቸው ዋዜማ በድካም ዝለን እስክንለያይ ድረስ ስለአባታችን የሚሰጠው ምስክርነት ሊያበቃ አልቻለም። የተቀረውን ወደፊት እንቀጥላለን።

የት ይረፉ፡ የት ይቀበሩ? ያልሞተ ሰው አንቀብርም

በቁሜ የቀበረኝ፡ ስሞትም ጋበዘኝ፡ አፈር ላልብስ አለኝ።

ከዚያ፡ አንድ ቀን አባ ሞቱ። አረፉ። በሞቱ ማግስት እኛ ተደናግጠንና አዝነን ሳለ፡ በአባታችን ሕይወት እንቅልፍ አጥተው የሰበቱት አባ አባ ጳውሎስና ተከታዮቻቸው እነሆ እኚህ ጻድቅ ሰው በሞታቸውም እንቅልፍ እንዲነሷቸው አይሹምና እንቀብራለን ብለው ጥያቄ አቀረቡ። (በሀቅና ከምር የአባታችን ወደ አገር ቤት ተወስዶ መቀበርን የሚመኙና የሚደግፉ ይኖራሉና ይሄ ትችት እነሱን አይመለከትም)። እኚህ አባ ጳውሎስ ግን፡ ያኔ ብድግ ብለው “አውግዘናል፤ ገዝተናል” ብለው ማነው አንድ ጸሀፊ ባለፈው ሰሞን “የወፍ ግዝት” ብሎ የሰየመውን ግዝት የገዘቱት፤ እንደገና ድንገት አንድ ሌሊት ብድግ ብለው፡ አስራስምንት አመት ያሰደዷቸውን፡ ሰባት ስምንት አመት ደግሞ የገዘቷቸውን አባት፡ በሞቱ ማግስት፡ ባልተፈረመና በሌላ ወፍ ዘራሽ ደብዳቤ በተጠየቁት መሰረት ባስቸኳይ ስብሰባ ውግዘቱን አነሳን አሉ። እና ኢትዮጵያ ይቀበሩ። ነገሩ እንዲህ ነው። አባ ጳውሎስ፡ አይናቸው ቀብሩንና መቃብሩን ካላየ አያምንም። ያኔ ትዝ ይላችኋል? አይሁዶች፡ ክርስቶስን ሰቀልን ብለው ብቻ አላመኑም። ስለዚህ ይሄ ሰው ደግሞ ተነስቶ ህዝባችንን እንዳያውክ ብለው መቃብሩን በታጣቂዎች ሲጠብቁና ሲያስጠብቁ አደሩ። የአባ ጳውሎስ፡ የቀብር ግብዣ ከአይሁዶች መሰል ስጋት የመነጨ ነው። አቡነ ዜና ማርቆስን አፈር ማልበስና አርቀው መቅበር ይፈልጋሉ። ካለበለዚያ ሞታቸውን አያምኑም። ይሄ ሰው ደግሞ በሞቱም ተአምር ይሰራብኛል ብለው ይፈራሉ። ስለዚህም እዚህ ይምጡና ይቀበሩ አይነት ነገር ነው።

“ዜና ማርቆስ አልሞተም።” ጳውሎስ ያንን ያውቃል። ቢሞት እንኩዋን መቃብር ፈንቅሎ እንደሚነሳ ያውቃል። ስለዚህም ይምጡ፡ እዚህ በሊቀ ጳጳስ ደረጃ ይቀበሩ አሉ። አንደኛ ነገር፡ የቀረበው የቀብር ግብዣ፡ ያንገት በላይ ነው። ምክንያቱም ርስ በርሱ ይጣረሳል። መጀመሪያ ግብዣው እኚህን ሰው እንደበደለኛና ሀጢያተኛ ያስቀምጣል። ይለጥቅና ጥያቄው ከነሱ ሳይሆን ከልጆቻቸው እንደመጣ ይጠቁማል። ከዚያ ይሁን መቼስ ምን ይደረግ አይነት ነገር ነው። እኚህ አባት ዘወትር እ/ር ኢትዮጵያን ነጻ አውጥቶ ለማየት ይጓጉ ነበር። ኢትዮጵያ ነጻ ካልወጣች ግን፡ የአስከሬናቸው እዚያ ነጻ ካልወጣ አገር መሄድ ምንም አይፈይድም። አስከሬናቸውም ይታሰራል። አባ ጳውሎስ ሞታቸውን አላመኑም። ይሄ አስከሬን ከሞትም በኋላ እንቅፋት እንዲሆን አይሹም። ስለዚህ አርቀው ሊቀብሩት እዚህ ይምጡ አሉ። እንጂ፡ ከጎናቸው ያሉትን ጳጳሳት በር እያሰበሩ ያስደበደቡ ሰው፡ እኚህን አባት በበጎ ሊቀበሩ አይጋብዙም። አባታችን እኛ ውስጥ ይቀበራሉ። እኛንም እለት እለት ያበሩናል። እዚህ በነበሩበት ሰዓት እለት እለት እንደባረኩን፡ አሁንም በየወቅቱ እየሄድን ልናያቸውና ልንጎበኛቸው እንዲሁም በስማቸው እግዚአብሄር ተአምር ሲሰራ ልናይ እንመኛለን። ስለዚህም እዚህ ቴክሳስ፡ ራሳው በሕይወት ሳሉ በባረኩት አምስት ሄክታር ላይ በሚሰራ ገዳም ውስጥ ይቀበራሉ።

ስለጊዜያዊ ቀብራቸው፡ ማረፊያቸው።

የሲያትሉ ጊዜያዊ ቀብራቸው ነገር፡ አይነሳ። የኛ ሰው ሁሉ እዚያ ነበር። እዚህ ጋር ነገር ልደባልቅ። ዘወር ስል ኦሮምኟ እሰማለሁ። ትግሪኛም አደምጣለሁ። ሁለቱንም ቋንቋዎች ስሰማ ለምን እንደሆነ አላውቅም እደነግጣለሁ። የከተማው ሊመዚን ሁሉ እዚያ ነበር። ኮረብታው በሰው ግጥግጥ ብሎ ሞልቶ ይታያል። ፕሮቴስታንቶች ነበሩ። እስልምና እምነት ተከታዮችም እንደዚያው። አንድ ቀን እራት ያበሉት የፕሮቴስታን እምነት ተከታዮች መሆናቸው ተነግሮኛል። አባ የሁሉም ወዳጅ ናቸው። ነበሩም። የሲያትልን ህዝብና የቀብር ስነ ስርአት አስተባባሪ ኮሚቴዎቹን ሳላደንቅ አላልፍም። ህዝቡን በማስተናበርና ስርአት ጠብቆ እንዲጓዝ በማድረግ ረገድ ያሳዩት ስራ የሚደነቅ ነው። አንበሶች። ትግሉንም እንደናንተ የሚያስተባብሩ ሰዎች ያስፈልጉናል። ትንሽ ያልተመቸኝ ነገር፡ ይሄ አስከሬን እንደ ኤግዚቢሽን የማሳየት ባህል ነው። የኛ ባህል ስለመሆኑ እንጃ። እኔ አልተመቸኝም። ጊዜ ይፈጃል። በርግጥ ባባታችን ግዜ ብዙ ሰው አላወከም እንጂ፡ ከዚህ በፊት በነበርኩባቸው ቀብሮች ቤተሰብ ካልነካሁ፡ ካልዳበስኩ እያለ ያስቸግር ነበር። የፈረንጅ ባህል ሁሉ መልካምና ልንወርሰው የሚገባ ነው ማለት አይደለም። አንዳንዱ፡ አይጠቅመንም። ይሄንን አልወደድኩትም።
ጳጳሳቱንም ሳላደንቅ አላልፍም። ከያሉበት ተጠራርተው መጥተው ሀዘን ተቀምጠው ለህዝቡ መመሪያና ቡራኬ ሲሰጡ ሰንብተዋል። ሌሎች አንበሶች። ይሁን እንጂ በጳጳሳቱ ረገድ ብዙ የሚቀር ስራ ያለ ይመስለኛል። አንደኛ ነገር፡ ጳጳሳቱ በንዲህ ያለው የሀዘን ሰዓትም ይሁን፡ ዘወትር፡ አገር ቤት ስልጣንና መንበር ያላግባብ ይዞ የሚያሰድደንን ባላንጣ በየመገናኛ ብዙሀኑ፡ የሚዋጋ፡ በትምህርትና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም የዳበረ እውቀት ያላቸው ወጣቶችን ማሰልፍ አለባቸው። እንደተመለከትኩት ከሆነ፡ አባቶች ለባህላዊና ለሀይማኖታዊ ቡራኬ እንጂ፤ ጸሎትና ምህላ ብቻ ሰይሆን ተንኮልና ብልጠትም ለሚያስፈልገው የዘመናችን ሀይማኖታዊና ፖለቲካዊ ግብግብ የተሰናዱ አይመስሉም። ስለዚህም፤ ይሄንን የአባታችንን ሞት፡ ህዝብን ለማሰለፍ፡ አገርን ለማዳን፡ ጠላትን ለማስደንገጥ፡ ፖለቲከኞቻችንን ለማሳሰብ መጠቀም የምንችልበት ጥሩ አጋጣሚ ሆኖ ሳለ፡ በሲኖዶሱ በኩል የወጡ መግለጫዎችና ንግግሮች ውሱንና ፈራ ተባ የሚሉ ናቸው። የአባታችን የቀበር ስነ ስርአት፡ የሕይወት ምስክርነትና ተያያዥ ሂደቶች በሙሉ ዘመኑ ባፈራቸው መገናኛ ብዙሀን ለህዝብ በቀጥታ መቅረብ ነበረባቸው። ሁለተኛ አባቶች፡ የስደታችን ምክንያት የሆነውን ስርአት ከማውገዝና ህዝቡም ነጻነት ታጋዮችን እንዲያግዝ ከመምከር ወደኋላ ማለት የለባቸውም። መቼም አባቶች ይሄ ስደት የሚወዱትና የሚጣፍጣቸው አይመስለኝም። ለምሳሌ፡ በቀብር ስነ ስርአቱ ወቅት ሁሉ፡ በጣም ውሱን ከሆኑ ቅጽቦች በስተቀር፡ ዛሬ ኢትዮጵያም ትሁን ቤተክርስቲያናችን በጠላትናና በአገር በቀል ጽኝ ገዢ ስር ስለመውደቋና መማቀቋ የተገለጸ ነገር የለም። ብዙ ይቀራል።

ሌሎች አስተያየቶች፡ ቢከፋችሁም እናገረዋለሁ።

ደግሞ ሲኖዶሱ ጎንደር በዝቶበታል። ከጎንደር ምንም ችግር የለብኝም። እንደውም የወደፊት ሚስቴ አንድም ጎንደሬ ወይም ኤርትራዊ ትመስለኛለች። ከዚህ ቀደም ፈራ ተባ እያልኩ እንዳነሳሁት ግን በዚህ የሸዋ-ወሎ-ጎጃም-እና-ሌሎችም አካባቢ ተወላጆች ስብጥር ማነስ ምክንያት የተከፉ ሰዎች አምርረው ሲናገሩ ሰምቻለሁ። እንደውም አንዱ በዚህ በውጭ ላለው ህጋዊ ሲኖዶስ መዳከም ዋና ምክንያት ወይንም ባንዳንድ ቦታዎች ለሕወሀት አብያተ ክርስቲያናት መጠናከር ዋና ምክንያት ይሄ የሸዋና ጎንደር ሽኩቻ ነው የሚል መደምደሚያ ካንድ የሸዋ ካህን ሰምቻለሁ። ያንን ሀሳብ፡ እኔም በተወሰነ መልኩ እጋራዋለሁ። አባቴ ሸዋ ስለሆነ ነው መሰለኝ እኔንም ትንሽ ከንክኖኛል ይሄ ነገር። ሲኖዶሱ ውስጥ፡ ትንሽ ወሎና ሸዋ፡ ወረድ ብሎም አርሲና ባሌም ደብለቅ ማድረግ ያስፈልጋል። ጎጃምን አልዘለልኩትም። በዚህ ረገድ ሕወሀት ሳይበልጠን አልቀረም። በዚህ አነጋገሬ ብዙ ሰዎች ልትናደዱብኝ እንደምትችሉ አምናለሁ። ግን ሁሌም ቢሆን ሰዎችን የሚያስደስት ነገር ብቻ በመናገር መወሰን የለብንም። መቼም፡ አማራ ትግሬ ኦሮሞ፡ ሀመር፡ ሶማሌ አፋር፡ ምናምን የሚለውን የፌደራሊዝም አሰላለፍ ለምንጠላና ለምንሸሽ ሰዎች፡ እንደ አማራጭ የምናቀርበውን ትግራይ፡ ወለጋ፡ ሸዋ፡ ሀረር ምናምን የሚል የመልክአ ምድር አወቃቀር በተቋሞቻችን ውስጥ ሁሉ፡ ፍትሀዊ ውክልና ልንሰጠው ይገባል። ሲኖዶሳችን ይሄ ይጎድለዋል። ሲኖዶሳችን ይሄንንና ሌሎችንም አገራዊ ስራዎች የሚሰራ ብልጥና ስልጡን የህዝብ ግንኙነት ያስፈልገዋል።

ለዚህ ሁሉ ግን፡ በአባታችን ስም የሚሰራውን ገዳም አጧጡፈን በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ ብንሰራ፡ ሀይማኖታዊውን ብቻ ሳይሆን፡ ሀገራዊውን ችግራችንንም የሚፈታ ትውልድ የምናስተምርበት ተቋም ሊሆን ይችላል።

አለቃ ተክሌ ነኝ። ቫንኩቨር፡ ካናዳ፡ የካቲት፡ 2002/2010

 1. ተራራው
  | #1

  ፖለቲካ ከኃይማኖት አታገናነው አንድነት እንዲህ ነው ጅል

 2. Dillu
  | #2

  Good Job, Tekle.

  The biggest problems in the Sindos are

  1. Lack of diversity and control of all sits by people from one region
  2. Lack of competence of those in the position
  3. The big tension between the Gondar and Shewa elders

  How come one group who denouce aba paulos and TPLF for racism, do the same thing in thier group?

  I think this a good time to resructure the Sindos with capable and diversified people.

  Thank you, again for rasing this point.

 3. እውነት
  | #3

  ጸሃፊ ሁሉ ምን ነው ቀና ልብ በሰጠው
  አባታችን ማረፋቸው የሚያሳዝን ቢሆንም ውግዘቱ አንስተናል እና አገራቸው መጥተው ይቀበሩ ያሉትም ቢሆን ያን ያህል ባይወቅሱ ምን አለበት.በክርስቶስ ክርስትያን የተባልነው እንደ ክርስትያን ብናስብ ምን አለበት. ይቅር መባሉ ምን መጥፎ ነገር አለው ወይስ የሰው ባህርያችን ደጉም መትፎውም ስለማይቀበልልን ነው?አባታችን እኮ በስጋ ቢሞቱም በነፍስ ዘላለማዊ ናቸው. ውግዘቱም ለስጋ ሳይሆን ለነፍስ ነው. ስለዚህ ጻሃፊዎች ሁሉ ውግዘቱ መነሳቱ እንደ የይምሰል መቁጠራቸው የክርስትናን ህይወት በደንብ አለማወቃቸውን ያሳያል. ዘላለማዊት ነፍስ እንጂ አላቂ የሆነች ስጋ አትገዘትም. ስጋ እስር ቤት ትገባለች እንጂ አትገዘትም.አባቶች ግዝቱን አንስተናል መባሉ የዚህን ምስጢር ስለየሚያውቁ ነው. ባላወቅነው ሁሉ መጻፍ ስለ ቻልን ብቻ ባንፈርድ ጥሩ ይመስለኛል. አለቃ ተክለም አለቃ መባሉ ስሙ እንጂ ዕውቀቱ ያላቸው አልመሰለኝም.ወይም ለበተክርስትያኒቱ አንድነት ተጨንቀ ሳይሆን የሰፋውን እንዳይጠባቸው ነው መሰለኝ.
  ያም ሆነ ይህ አምላካችን በምህረቱ ይጎብኘን. ለአባታችንም በነአብርሃም አጠገብ ይኑርልን.

 4. እውነት
  | #4

  ምነው አለቃ ተክለ
  “በቁሜ ያሳደደኝ፡ በሕይወት የገፋኝ፡
  ሳልሞት የቀበረኝ፡ ስሞትም ሊገድለኝ
  የመውደዱ ጽናት፡ ለቀብር ጋበዘኝ።”
  ግጥሙ በት ይመታል የፖለቲካ ይዘት ባይኖረውና የክርስትናን ህይወት በአግባቡ በማወቅ ቢሆን ኖሮ. እኔ አሜሪካ ከመጣሁኝ 5ዓመት ሞላኝ ውግዘቱ የተላለፈው ከ2 ዓመት በፊት “ሰባት ስምንት አመት ደግሞ የገዘቷቸውን አባት” ከየት መጣ? ወይስ የርስዎ ቆጣሪ ዳብል ዳብል ወይም ትሪፕል ነው የሚቆጥረው? ብዕራቹ ለበተክርስቲያን አንድነት ተጠቀሙበት.

 5. ዕልልታ
  | #5

  አለቃ ተክለ ገና አሁን ተፎገሩ የእስካሁኑ ጽሑፎችህ አድናቂ ነበርኩ ያሁኑ ግን መላቅጡ የጠፋ ሆነብኝ:: ፖለቲካና ሃይማኖት ተደበላለቁበት:: የክርስቶስ የይቅር ባይነት መንፈስ ተፋቀ መስቀል ላይ ያወጀው ዘላለማዊ ይቅርታ ተሰረዘ እና እባክህ ይህን ዓይነት ስሜታዊነት ተው:: አንተ ፖለቲካው ላይ ነው የሚያምርብህ:: ሃይማኖት ውስጥ ገብተህ አታደፍርስ:: ሃይማኖትና ስሜታዊነት አብሮ አይሄድም:: በተረፈው እግዚአብሐር ያግዝህ ልቦና ይስጥህ::

 6. ገጣሚ ጸዳለ ሞገስ(ጸዲ)
  | #6

  ታሪኩን በጥንቃቄ ሳነበው ቆየሁና እንዲያው ስጠረጥር ልቤ ነገር ስለገባው ጻፍኩኝ እንጂ በዻዻሶቹ መካከል የተፈጠረውን ግጭት ስሰማ
  አንድ የማስጠንቀቂያ ደወል ነው ለእኔ የሆነልኝ ይህም የዘመኑ ፍጻሜ መድረሱን!!!!……..
  እኛም ፈራጅነትን ማን እንደሰጠን ባናውቅም መፍረድ እንጂ ማስተዋል አልቻልንም::
  “እግዚአብሔር በተቀደሰው መቅደሱ ነውና ምድር ሁሉ በፊቱ ዝም ትበል” ይላል ቅዱሱ መጽሐፍ እንደገናም አሁን አሁን በየትኛውም የቤተክርስትያን ምዕመን እየታየ ያለው አባቶችን መዝለፍ ነው ለሁሉም እንደስራው የሚከፍል እርሱ በሰማይ እያለ የፈራጅነትን ምላስ
  ማን ሰጠን?? “የእግዚአብሔር ክብር ነገርን መሰወር የነገስታት ክብር ነገርን መመርመር ነው”ይላልና እርሱ የሰወረውን ማን ገላጭ
  አደረገን??………
  ደግሞም “ራሳችንን ብንመረምር ባልተፈረደብን” ስለሚል ሁሉ ራሱን ይመርምር የቱጋ እንዳለ ይወቅ ይሔንን አድርጎት ከሆነ ይቀጥል!!
  እነኚህ ሁሉ የዘመኑ ፍጻሜ ምልክቶች ናቸው::
  እግዚአብሔር በአንድነት ከነውር ይጠብቀን አሜን::አንድነትን እንደግፋለን::

 7. ፌይሳ
  | #7

  Dear Aleka; I like your style of writting Amharic essay.Moreover, I admire your political maturity in relation to religion. You remind me of our people back home who after just participating in church and mosque religious ceremonies, go out fighting for their democratic rights against their oppressive tairant government.It is universal trueth that religion and politics have one common pricple that is equality of human beings and justice. So many religious leaders have sacrificed and died by bullet of capitalists in Latin American counties while fight for democracy, equality and justice of the poor working people of those counties. In our society, particularly, those so called religious leaders, have been preaching to us that participating in politics is ‘SIN’. I hope those like of you who knows our relion, our society and what politics is about, will do a lot, and alot work teaching the relation between polics and religion so that all Ethiopian will participate in transforming our society to a democratic one. s

 8. ታዛቢ ከዚችው ከኛ ሀገር
  | #8

  በአለቃ ተክሊ ተከታታይ ጽሁፍ በጣም ተማርኪ ነበር አሁን ግን መነሻው እና መድረሻው ስለጠፋብኝ ከምን እንድምጀምር ባላውቅም ከላይ ስለጹ አባታችን ዚና እረፍት ከተረኩ መልካም ፍሪ ያለው ምክር ሰጥተዋል ግን ወደመጨረሻው አካባቢ ምን ለማለት እንደፈለጉ ባላውቅም ምነው ጎንደር ብቻ ይላሉ?/ ከዚያም ወደፊት የማገባት ሚስት አንድም ጎንደሪ አለያም ኢርትራ?? ከዚያ ደግሞ አባቲ መንዚ ስለሆነ ነው መሰለኝ ይከነክነኛል ይላሎ እጅግ ያሳዘነኝ ነገር ቢኖር የአለቅነት ማረግ ያለው አንድ ሰው አባቶቹን አለማወቅ ብቻ ሳይሆን በሲኖዶስ ውስጥ እነማን አሉ ብሎ በጥናት የተደገፈ ጽሁፍ ነበር ማዉጣት የነበረበት ካልሆነ ግን አመለካከቱ ወይም አስተያየቱ ምሎ ነው ብሎ ለመቀበል ይከብዳል: እግዚኢብሒር ሀገራችንን ኢትዮጵያን ይባርካት;;አሚን አሚን

 9. Sileshi
  | #9

  Terraw, Ewunet and Elilta

  Instead of commenting unimportant stuff on this young well-educated and truth teller, Tekle, you better look at the Sinodos closely. The Sinodos is just made of people who hailed from the same Mender and totally inefficient. While the majority of people hate Aba Palos and try to be with the exile Sinodos, they are not doing anything except show up.

  If the church has to be reserected the Sinodos should be representative of the whole chiristians in the country and it should work lots of works actively.

  I never saw Tekle physically but I read what he writes. He is a truth teller and wants Ethiopia grow and he works hard fo that.

  We like you Tekle. Keep up what you are doing.

  Sileshi

አስተያየት መስጫው ተዘግቷል።