አምባ ገነን መሪዎችና የዕድሜ ልክ ስልጣን በዮሐንስ እ ተመስገን

January 29th, 2011 ይመይሉ ይመይሉ ያትሙ ያትሙ

በቀድሞዋ ዛየርና የዛሬዋ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መሪ ከነበሩት ሞቡቱ ሴሴሴኮ የሰላሳ ሁለት ዓመት ፕሬዚዳንትነት ታሪክ ተነስተን የዛሬዎቹን ለምዝበራ የተፈጠሩ የሀገር መሪዎች ጭካኔ ስግብግብነትና ጨቋኝነት በቱኒዚያ የተነሳውን የህዝብ ዓመጽ ዓይነት ለመቀስቀስ ህዝብን እየገፋው ይገኛል::

ዛሬ በቱኒዚያ የተቀጣጠለው የለውጥ ማዕበል ወደ ግብጽ አልጄርያ ጆርዳንና የመን መዛመቱ ዘራፊዎችንና በህዝብ ጫንቃ ላይ ተንፈራጠው ደሙን የሚመጡትን መሪዎች በጀርባቸው ቀዝቃዛ ላብ ሳይለቅባቸው አልቀረም:: በውጭ ባንኮች ካስቀመጡትና ከዘረፉት የሀገር ሀብት የተረፈውን እንዴት እንደሚያሸሹና ራሳቸውም እንዴት እንደሚያመልጡም እየተዘጋጁ ይመስላል የቱኒዚያን ህዝብና የየአገሮቻቸውን ተቃዋሚዎች በልባቸው እየተራገሙ:: ከቱኒዚያ ቀጥሎ በግብጽ በታየው ህዝባዊ ማዕበል ጀማል ሙባረክ የግብጹ ፕሬዚዳንት ልጅ ባለቤቱንና ሴት ልጁን እንዲሁም አስራ ሰባት የሚሆኑ ሻንጣዎችን ይዞ በልዪ አውሮፕላን ወደ ለንደን አቅንቷል ተብሎ ለተዘገበው ዜና ማረጋገጫ ባይገኝም ቤን አሊን ያየ መወሰድ የሚገባው ጥንቃቄ ነው ማለቱ አይቀርም:: ውሎ ካደሩ ሁኔታዎች በየደቂቃው ይቀየሩና ያለመውጣትና የተቀረውን ዕድሜ ለሰሩት ሃጢያትም በእስር ለመክፈል በሰደፍ እየተገፉ ወደእስር ቤት መውረድ ሊኖር ስለሚችል ለእንደኛ ሀገር ያሉ መሪዎች የምለው ትንሽ እንቅስቃሴ መስቀል አደባባይ አካባቢ በህዝብ ከተጀመረ አራት ኪሎ እስኪደርስ ሳይጠበቅ የቤን አሊንና የጀማልን ፈለግ ቢከተሉ ነፍሳቸውን አትርፈው በውጭ ያስቀመጡትን እየበሉ ሊኖሩ ስለሚችሉ መቀደም እንደሌላባቸው አሳስባለሁ::

ባይታደል ነው እንጂ ጀማል ሙባረክ የሚቀጥለው የግብጽ መሪነትን ካባቱ ለመውረስ እየተዘጋጀ እያለ ነው የቱኒዚያው ሱናሜ የተነሳው:: ለነገሩማ ከ1990ዎቹ ማብቂያ ጀምሮ የነበረው የመሪዎች የለውጥ ፋሽን አመራርን አባት ለልጁ ሀገርንና ህዝብን የሚያክል እንደ ግል ንብረት ሲያወርስ የታየበት አስርተ አመት አልነበር?
ሎረንት ካቢላ የሞቡቱ ተቃዋሚ ሆነው በ1997 የፕሬዘዳንትነቱን በትረ መንግስት ሲጨብጡ በኡጋንዳ ዩኒቨርሲቲ የተማረውን ልጃቸውን ጆሴፍ ካቢላ ወደ ቻይና ልከው ከፍተኛ የወታደራዊ ትምህርት እንዲከታተል ያደርጉና ሲመለስ የሜጀር ጄኔራል ማእረግ ሰጥተው የሀገሪቱ የጦር ሃይሎች ምክትል ኤታ ማዦር ሹም ስልጣንን አስያዙት:: ሎረንት ካቢላ በጃንዋሪ 2001 ከልዩ ጠባቂዎቻቸው በተተኮሰ ሁለት ጥይት ተመተው ህይወታቸው ሲያልፍ ቦታቸውን ሳይውል ሳያድር ልጃቸው ጆሴፍ ካቢላ በሃያ ሰባት አመቱ የሀገር መሪ ተብሎ ተሰየመ:: ይሄው የኮንጎ ወጣት መሪ ዛሬ አንድ አስርተ አመት በስልጣን ላይ አስቆጥሮአል::

የሶርያው መሪ የነበሩት ሃፌዝ አል አሳድ ለሰላሳ አመት ፕሬዚዳንት ሆነው ለስልጣን ሲያዘጋጁት የኖሩት የመጀመሪያ ልጃቸው ባሰል አሳድ በመኪና አደጋ ህይወቱ ሲያልፍ ሞታቸው መቅረቡን የተረዱት አሳድ ምንም የፖለቲካ ዝንባሌ የሌለውንና የጥርስ ህክምና ሞያ በእንግሊዝ ሀገር ይከታተል የነበረውን ሁለተኛ ልጃቸውን በሻር አል አሳድን ካለበት በፍጥነት እንዲመለስ አደረጉ:: በሻር የወታደራዊ መኮንኖች ማሰልጠኛ ትምህርት እንዲማር አዘው ሲወጣ በጃንዋሪ 1999 የኮለኔልነት ማዕረግ ሰጥተውት የባአዝ ፓርቲ ሊቀመንበርነት አስመረጡት:፡ ሃፌዝ አል አሳድ በጁን 2000 ዓም ከዚህ አለም በሞት ሲለዩ በሻር አል አሳድ በዘጠና ሰባት ነጥብ ሁለት በመቶ ድምጽ በሰላሳ አራት አመቱ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆኖ ተመረጠ::

ንጉስ ሁሴን ጆርዳንን ለአርባ ስድስት አመታት ከገዙ በኋላ አልጋ ወራሽ ወንድማቸውን ሀሰንን በመጨረሻው ሰአት በህክምና ላይ ከሚገኙበት ከአሜሪካ በልዩ አውሮፕላን ወደ አማን ጆርዳን በርረው በአሜሪካና በእንግሊዝ ትምህርቱን የተከታተተለውን የሰላሳ ሰባት አመቱን የመጀመሪያ ልጃቸውን አብደላን አልጋ ወራሽ አድርገው ሲሞቱ ንጉስ አብደላ ከፌብሯሪ 1999 ጀምሮ ጆርዳንን እየገዙ ይገኛሉ::

የሞሮኮው ንጉስ ሐሰን ለሰላሳ ስምንት አመት ሞሮኮን ከገዙ በኋላ በትረ ስልጣኑን በሰላሳ አመቱ የሜጀር ጄነራልነት ማዕረግ ለተሰጠው ልጃቸው ለልኡል ሞሐመድ አራተኛ በጁላይ 1999 አሳልፈው በሰላሳ አምስት አመቱ ንግስናውን ተቀብሎ ሞሮኮን በመግዛት ላይ ይገኛል::
በዚያው ሰሞን ታድያ እንደ ፋሽን የተያዘው ይህ ስልጣንን ለልጅ የማውረስ አባዜ አሜሪካም ደርሶ የጆርጅ ቡሽ ልጅ ጆርጅ ቡሽ ጁኒየር ስልጣን መውረስን ለአፍሪካና ለአረብ ብቻ ማን ፈቀደለት ያሉ በመምሰል ከቴክሳስ አገረ ገዥነት ተንደርድረው ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት ተወዳደሩ አሸነፉም:: በአእምሮ ብሩህነታቸው ብዙም የማይነገርላቸው ቡሽ በአባታቸው ስምና ሀብት በሪፐብሊካን ድጋፍ በ2000 አም ፕሬዚዳንት ሆነው ለስምንት ረጅም አመታት አሜሪካንን አስተዳድረዋል:: ረጅምነቱም የአሜሪካ ስምንት አመት ከሌላው በርክቶ ሳይሆን ያደረሱት ጥፋት ሰላሳ አመት ከገዙት ሌሎች ጋር የማይተናነስ በመሆኑ ነው::

ከአስር አመታት በኋላ ታድያ በዚህ አመት መጀመሪያ የተቀሰቀሰው የቱኒዚያው ሱናሜ የህዝብ ዓመጽና በቃኝ ባይነት ለልጆቻቸው ለወንድሞቻቸውና ለባለቤቶቻቸው ስልጣን ለማውረስ የተዘጋጁ ካሉ ሞዱ እንዳለፈ ግዜው እንዳልሆነ ማየት የቸገራቸው ካሉ ከቤን አሊ ትምህርት ሊወስዱ ይገባል::
እኒሁ የቱኒዚያ መሪ ሀገር ጥለው ከመኮበለላቸው በፊት በአሜሪካ መንግስት የሚደገፉ ነበሩ:: የቱኒዚያ መሪ ባለቤት ሌይላ (ሌሊቷ) እንደኛዋ አዜብ ጎላ (መስፍን) በህዝብ የተጠላች አረመኔና ስግብግብ የነበረች ሲሆን ለሚቀጥለው የፕሬዚዳንትነት ምርጫ እያዘጋጇት ነበር የሚል ዜና ከወደ ቱኒዚያ ተደምጧል:: መለስም ጤናው እየታወከ ባለበት በአሁኑ ግዜ እንደ ሃፌዝ አልአሳድ ልጁን ከእንግሊዝ አስመጥቶ ወታደራዊ መኮንኖች ማሰልጠኛ ይከታት ይሆን ወይስ እንደ ቱኒዚያው መሪ አዜብን እያዘጋጀ ይሆን? ወደፊት የምንሰማው ጉዳይ ይሆናል::

ዛሬ የቱኒዚያው ሰደድ ተቀጣጥሎ ግብጽ ሲደርስ ሰላሳ አመታቸውን በአራተኛ የግብጽ ፕሬዚዳንትነት ያስቆጠሩት ሆስኒ ሙባረክ የአርባ ስድስቱን አመት ልጃቸውን ጀማል ሙባረክን ለውርስ እያዘጋጁት እንደነበርና ጀማልም በአባቱ ስልጣን መውደድ እንዳዘነ ግብጾች የሚያወሩት ቀልድ ብጤ አላቸው:: የዛሬ አስር አመት በነ ንጉስ ሞሃመድ አራተኛ በነ በሻር አልአሳድ በነ ንጉስ አብደላ ግዜ እድሜአችንም አንድ አካባቢ በነበረበት ስልጣን ለልጅ ማውረስ ቄንጥ በነበረበት ግዜ ሳያወርሰኝ እስከ አሁን በመቆየቴና የማገኘውም ስላልመሰለኝ አዝኜአለሁ ብሎ ለየመኑ ፕሬዚዳንት አሊ አብደላ ልጅ ለአህመድ ሲያጫውተው ተወው እባክህ የኛን አባቶች ነገር:: ስም ብቻ ነው የተረፈን ብሎ መለሰለት አሉ ብለው ይቀልዳሉ::
በስልጣን ላይ ለሰላሳ ሁለት አመት የቆዩት የየመኑ መሪ አሊ አብደላ ሳላህ ሰሞኑን በተደረገው የህዝብ ተቃውሞ ላይ በቴሌቪዥን ለህዝባቸው ማረጋጊያ ያደረጉት ንግግር ልጄን አህመድን ለፕሬዚዳንትነት እያዘጋጀ ነው ብለው የሚያወሩት ህዝቡን ቅደም ብለው በየስርቻው የተደበቁ ሽብርተኛ ተቃዋሚዎች ናቸው በማለት ቢገልጹም ህዝቡ አንተም ልጅህም የቀድሞ የቱኒዚያው መሪ በሄደበት እንድትሄዱ ነው ሰልፍ የወጣነው ብሎ ሰልፉን አፋፍሞታል:
የሳዑዲው ንጉስና የሊቢያው የዕድሜ ልክ መሪዎችም የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም ይህን መሰል ስርአት አልበኝነት ህዝብንና ሀገርን ይጎዳል ሲሉ ተደመጡ እንጂ ካለነሱ በስተቀር ሀገሮቻቸው መሪ የማይኖረው ነው ብለው ራሳቸውን አሳምነው የተቀመጡትን አምባ ገነኖች የሰላማዊ ሰልፈኛው የተቃዋሚው መብትና ጥያቄአቸው ይታይ አላሉም::
ይህን የህዝብ አመጽ ሰደድ ያየው የወያኔ መሪም እሳቱ ወደርሱ እንዳይደርስ ዙሪያውን ውሃ በማርከፍከፍ ላይ ይገኛል:: በብልጠቱና በተንኮሉ የቆዳውን ቀለም እንደ እስስት እየለዋወጠ የሃያ አመት ዕድሜውን በማራዘም ላይ ያለው የመለስ አስተዳደር ሰሞኑን የዋጋ ቁጥጥር ብሎ በነጋዴዎች ላይ የጀመረውን ዘመቻ በማጠናከር ለሰራተኛው ህዝብ ደሞዝ ጭማሪ አደርጋለሁ በማለት ሽር ጉዱን ተያይዞት በአንድ ጆሮው የህዝቡን የልብ ትርታ ሲያዳምጥ በሌላው የግብጽንና የሌሎችን ህዝባዊ አመጽ በአንክሮ እየተከታተለ ነው::
ሙባረክ እንዳይወድቅም ጸሎት እያደረሰ ቤን አሊንም እየረገመ በኦባማ ንግግርም እየተበሳጨ አራት ኪሎ በሚገኘው መኖርያው የግብጽን ተቃዋሚ ሰልፈኛና የፖሊስ እንቅስቃሴ በ ቴሌቪዥን እያየ ማስታወሻው ላይ እየጻፈ ይገኛል:: ምናልባትም ታክቲክና ስትራቴጂ ይሆናል የሚያጠናው ማን ያውቃል ወደፊት የሚፈጠረውን?

በአሜሪካ የሚመራው የምዕራቡ ዓለም አስተዳደርስ? ይህን ሁሉ የህዝብ ንብረት ዘራፊ መሪ ተብዬ ሲደግፉና በገንዘብ ሲረዱ ቆይተው ገንዘብ በመቶ ሚሊዮኖችና በቢሊዮን ዶላር በየአመቱ ሲያፈሱላቸው የኖሩትን መሪዎች ሃይላቸው በተመናመነ ህዝብ በተነሳባቸው ሰአት የህዝብን ድምጽ አክብሩ ማለቱን ተያይዘውታል:: አሸናፊ የሚወዱት የምዕራባውያኑ ሀገሮች መሪዎች ድሮ መባል የነበረበትን አስተያየት ከመሸ እያጎረፉ ነው:: በተለይም የአሜሪካው መሪ ፕሬዚዳንት ኦባማ ለቱኒዚያ አሁን ደግሞ ለግብጽ ህዝብ ድምጽ መከበር መግለጫ በመስጠት የህዝብ ወገናዊነታቸውን ሊያሳዩ እየሞከሩ ነው::

የነገ ሰው ብሎን የተቀጣጠለው የህዝብ ዓመጽ ማቆሚያው የት እንዴትና መቼ እንደሆነ ያሳየን::
በቸር ይግጠመን::
ዮሐንስ እ ተመስገን

 1. በርታ
  | #1

  ምርጥ ጽሕፍ

 2. በለው!
  | #2

  ሰሞኑን “ሀገር ፍቅር ሬዲዮ “የዋሽንግተን ዲሲ ተከታታይ “የህገ መንግስት ትረካ በጋዜጠኛ ጸሐይዬ እንደፍቅር እስከመቃብር ሲተረክ ነበር
  መቼም ፈስ ያለበት ዝላይ አይችልም:: የዚህ የሕገ መንግስት ትረካ ከማሳቁም ሌላ ምንም ቁምነገር አልነበረውም ማናቸውም ዜጋ በ 15
  የኢትዮጵያ ብር ገዝቶ ማንበብ ይችላል ግለሰቡም ከንባቡ በቀር የሰጡት ማብራሪያና የጠቀሱት አንቀጽ በጭራሽም አልተገናኘላቸውም::
  ይሀን ያስጠቀሰኝ ሰሞኑን የህዝብ አመጽ በጎረፈባቸው ሀገሮች በከፊል ሲሳካላቸው በከፊል ትግሉ ቀጥሏል እንግዲህ ይህ በዝምታ የተዋጠው
  የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳይነሳ የሚደረግ ማስፈራሪያ ከዋጋ ማስተካከል እስከ ደሞዝ ጭማሪ ያለው ሩጫ በጣም አስገራሚ ነው::
  ጠ/ሚ እንዳሉት”የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን ድምጹን የሰጠን የተሻለ ሥራ እንድንሰራ በማሳሰቢያ ነው”ብለዋል የቃል አመራረጡ ጥሩ ነው
  እኔ እንደገባኝ ግን “በማስጠንቀቂያ”ለማለት እንደሆነ ነው::1997 የታየው ማዕበል ቢደገም ይህ “ሕገ መንግስቱንና ሕገ መንግስታዊ
  ሥርዓቱን በአመጽ ለመናድ “የሚለው ቧልት በሕዝብ ሬዲዮ ህገመንግስትን መተረኩ የሚያዋጣ መስሎ አልታየኝም ለማለት ነው::
  ህዝባዊ ጥያቄ ሰላማዊ ሰልፍና የአስተዳደር ለውጥ የሕዝብ ቁጣ እንኳንም የእሳት አደጋ ዉሃ,አስለቃሽ ጭስ,የሰዓት እላፊ ገደብ የወጣው
  የወታደር ታንክ እንኳን ለሰልፈኛው ማገልገሉ ሰራዊቱ ለሕዝቡ የቆመ ከሕዝብ አብራክ የወጣ እንጂ በዘርና በጎሳ በቋንቋ ተለይቶ ለሆዱ አለማደሩን የኢትዮጵያ ሠራዊትም ትምህርት ሊሆነው ይገባል ::ሕገ መንግስት የሕዝብ መተዳደሪያ ማገልገያ እንጂ ማስፈራሪያ “ሳማ” እንዳልሆነ ዘመነኞችና አፈ ቀላጤዎች በአንክሮት ይረዱ በለው!በቸር ይግጠመን ከሀገረ ካናዳ

 3. ግሩም
  | #3

  አረ እኛም አገር ትግባ አሜሪካ ለነ ወይዘሮ ቀዳማዊት ብልሹ ትንገርልን መውጣት እንካን አይውጡ ከጠፉማ የልባችን እሳት በማን ላይ ይብረድ ቃሊቲ ገብተው ወይም ደደቢት መፈረድ አለባቸው ወዴት መውጣት

 4. ባክቡክ
  | #4

  በዚህም ሆነ በዚያ በሃገራችን ለውጥ የመመጣቱ ጉዳይ አይቀሬ ነው:ያም ቢሆን የለውጡ ተዋናዪች እኛ ኢትዪፕያውያን በጥምረት የምናካሂደው ትግል እንጂ ምእራባውያንማ ወደ ነፈሰበት የሚነፍሱ እስትንፋሶች መሆናቸው ይታወቃል:;

 5. ሰም የለሊው
  | #5

  ትሩ ገንዛቢ ነው

 6. ዮሃንስ
  | #6

  ውድ አንባቢዎች! የእድሜ ቁጥር ማስተካከያ አለኝ “….ጆሴፍ ካቢላ በሃያ ሰባት አመቱ የሀገር መሪ ተብሎ ተሰየመ የሚለው” በሃያ ዘጠኝ አመቱ ተብሎ ይነበብልኝ ከይቅርታ ጋር::
  አመሰግናለሁ::

 7. በለው!
  | #7

  አቶ ዮሐንስ ያቀረቡት ጥያቄ ወ/ሮ አዜብ መስፍን(ጎላ)የስልጣን ተተኪ ይሆኑ ይሆን? ያሉት መልካም ጥያቄ ግለሰቧ ምን ይላሉ?
  መቼም አንድ ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝብ ቤተ መሞከሪያ ሆኗል ባሕሉም ቋንቋውም ሕጉም ሃይማኖቱም ልብሱም የተውሶ ከሆነ ሰነበተ!
  ሚሊኒየም ተብሎ ጭፋሮ ከተጀመረ በሗላ የተከተለው (first lady)ቀዳማዊት እመቤት እየተባለ መደናቆር ነበር ለመሆኑ ትክክለኛ ትርጓሜ ነበረው? ምን አልባት “የመጀመሪያይቱ ሴት ከሆነ እመብርሃን “መሆናቸው ነበር::የመጀመሪያይቱም ሴት ንግስት እንዳይባልም ታሪክ ሰርተው ያለፉ ንግስቶችም ነበሩ:: መቼም ትንሽ ሥጋ እንደመርፌ ትወጋ ሆነና ወልቃይት ጠገዴ መወለዳቸው ቋንቋው የገባቸው ወ/ሮ አዜብ ጎላ በቃለ መጠይቃቸው ሲያስረዱ…” ቀዳማዊት እመቤት ማለት የአቶ መልስ ሚስት ለማለት ነው እኔ ግን ታጋይ አዜብ ተብዬ ብጠራ እወዳለሁ” ብለው ነበር ::ይህ የሚያስረዳው ቀጣይቷ የሀገሪትቷ ጠ/ሚኒስትር እኔ ስለምሆን ሥልጣኑን የማገኘው እንደሌሎች ሴቶች በፓርቲ ታቅፌ በሕዝብ ምርጫ አሽንፌ ወይም ከባሌ በውርስ በቀዳማዊ እመቤትነቴ ሳይሆን በታጋይነቴ ብቻ ነው ባሌም በታጋይነቱ እንኳን ኢትዮጵያን አፍሪካን መወከል በቅቶ የለምን? ስለዚህ ቀዳማዊ እመቤትነቴ ይቅርብኝ እንጀራዬን ይዘጋዋል ማለታቸው ነበር::እንግዲህ “ትራንስፎርሜሽኑም”ወይ ስር ነቀል ለውጥ ነው ወይም (power Transfer)የለየት ትርጓሜ የለውም ዘመነኞቹም ዲያስቦራዎች ሀገራቸውም ለመስራት ገብተው ዛሬም ዲያስቦራ ተብለው ይጠራሉ በሰሞኑም ዲስኩራቸው ሲደመጡ
  “ለጨረቃ አልመን ኮከብ እንመታለን ባቡሩ ከምንቀሳቀሱ በፊት ቶሎ ተሳፈሩ ይላሉ”ነገሩ ባልከፋ ግን ይቺ ባቡር መድረሻዋ የት ይሆን? ሰሞኑን እንቁላል ዋጋዋ ሁለት ብር ለምን ሆነ ቢባል “ለእናቷ ዶሮ ተመን ባለውጣቱ ተናዳ ነው አሉ እናቴም በሕገ ደንቡ የዋጋ ተመን ካልወጣላት ህጉ ያዳላል የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብቴ ይጠበቅ”ስትል ከሕዝቡ ቀድማ ድማጿን ማሰማቷ አይገርምም?
  ንቃ በለው!በቸር ይግጠመን

አስተያየት መስጫው ተዘግቷል።