ፍኖት- እድሜ ለቴሌቭዥን ሁሉም ተትረፍርፏል

August 8th, 2011 ይመይሉ ይመይሉ ያትሙ ያትሙ

ሰዎች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በውይይት መልክ ከሚናገሩት ይልቅ ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው ሲንሾካሾኩ ይሰማሉ፣ መንግሥት የማይሰማው ነገር እንደሌለ እየታወቀ ድምጽን ቀንሶ መንሾካሾኩ ድምጽን ላለማባከን ካልሆነ በቀር ጥቅም የለውም፡፡

በዚህ የሰላዩ ብዛት አንድ ለአንድ በሆነበት ጊዜ ተንሾካሾከም ድምጽን ከፍ አድርጎ ተነገረ! መሰማቱ አይቀርም ብለው አንዳንድ አሾክሿኪዎች ሲናገሩ ሰምቼ ነገሩ ግራ ቢገባኝ፣ አንዱን ጓደኛዬን ጠጋ ብዬ በሹክሹክታ ”ለሰማኒያ ሚሊዬን ሕዝብ፤ ሰማኒያ ሚሊየን ሰላይ ተመደበ እንዴ?” አልኩት። “ወይስ ሕዝቡ በተቃውሞና በድጋፍ ጎራ ለሁለት ተከፍሎ ለአርባ ሚሊየን ተቃዋሚ አርባ ሚሊየን ሰላይ ተመደበን ?” ስለው እሱም መለስ አድርጎ፤ “አይ አንተ ድሮ ደርግ እንደወደቀበት እለት መሰለህ እንዴ ? ዛሬማ ሁሉም ተቃዋሚ ሆኗል እኮ፡፡ መንግሥት ደጋፊዎቹን በራሱ እጅ አጥቷል፡፡ ነጋዴውን በግብር እንዲሁም አንዳንድ የንግድ ሥራዎችን በመቀማት፤ ተማሪው ከተመረቀ በኋላ በሥራ እጦት፤ የመንግሥት ሠራተኛውም በመዋጮ አሰልችተውት ሁሉም ተቃዋሚ ሆኗል እኮ !” አለኝ፡፡ ይህን ሁሉ የሚለኝ ግን በሹክሹታ ነው፡፡

እኔም በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያሉ ተማሪዎች አባል በመሆናቸው፣ ከተመረቁ በኋላ ለአባሎቹ አባል ካልሆኑት ቀድመው ሥራ እየተሠጣቸው እንደሆነ ሲያንሾካሹኩ የሰማሁትን ስነግረው፣ እሱም “ድሮ ቀረ” አይለኝ መሠለዎት! “ምነዉ ?” ስለው፣ “አባላቱ ስለበዙ ነዋ!” አለኝ፡፡ “ለሁሉም እድል መስጠት ስላልተቻለ፣ ዛሬ እንደ ብሔራዊ ሎተሪ ሥራ የሚሰጠው፤ በእጣ ነው “ ብሎኝ እርፍ፡፡

እኔ እነዚህ አሾክሿኪዎች የሚሉትን አያጡም ብዬ ትክን አልኩ፡፡ ምክንያቱም ይህ ሁሉ ዳር ዳርታ የመንግሥታችን ውለታ አልባሌ ቦታ ለመጣል ስለሆነ፤ ባለፈው አንድ ሴትዮ የጀርመን ሬዲዮ ስለሀገራችን የገበያ ሁኔታ ቢጠይቃቸው “ሁሉም ሞልቷል፤ መንግሥት ለህዝቡ ዘይትም ሆነ ስኳር በበቂ ሁኔታ እያከፋፈለ ነው፡፡ ምንም ሳይጓደል ለእያንዳንዱ ሰው በአግባቡ እየታደለ ነው” ብለው ይመልሱለታል፡፡ ጋዜጠኛዉ ልማታዊ ጋዜጠኛ እንዳልሆነ ያስታውቃል፡፡ “እንዴት አወቅከው ?” ቢሉ ከአጠያየቁ፤ ልማታዊ ቢሆን ሴትዩዋ የተናገሩት በቂ ነበር፡፡ እሱ ግን “ የት ሱቅ ነው የሚታደለው? ” ብሎ ጠየቃቸው፡፡ እሳቸውም “በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ነዋ!” ብለው እርፍ፡፡

መቼም አንዳንድ ሰው ተመስገንን አያውቅ ሆኖ ነው እንጂ መንግሥታችን ቴሌቪዥን እና ሬዲዮ ባይኖረው ኖሮ በምን ያከፋፍል ነበር? ይልቅስ እሱን አያሳጣኝ ማለት አይሻልም ?

እንዲሁ አንድ ወዳጄ በሹክሹክታ አንድ ነገር ነገረኝ። የመንግሥት ካድሬዎች ሁሉ መንግሥት እየሰራው ስለአለው ነገር በቂ መረጃ እንዲኖራችሁ ቴሌቪዥን ማየት አለባችሁ የሚል ግዴታ ቢጤ በስብሰባ ሲነገራቸዉ አንዱ እጁን አውጥቶ “እኔ ማታ ማታ ሁል ጊዜ ቴሌቪዥን ስለማይ ምስጋና እንጂ ትእዛዝ አያስፈልገኝም”
ይላል፡፡ አንዱ ከጎኑ የተቀመጠ ሰው “ምን ተገኝቶ ነው ሁልጊዜ ማታ ማታ ቴሌቪዥን የምታየው ?” ብሎ ቢጠይቀው “ቀን ከሱቅ ያጣሁት ዘይትና ስኳር ማታ ማታ በቴሌቪዥን ስለሚታደል እርሱን በአካል ባጣውም በአይኔ ስለማየው ነው” አይል መሰለዎት፡፡

“ሰው መቼም ተመስገን አያውቅም፡፡ ይህን ላደረገዉ መንግሥታችንና ህዝቡ በቀን ከየሱቁ ያጣውን ዘይት ካለበት ፈልገው በካሜራቸው ቀርፀው እያንዳንዱ ቴሌቪዥን ያለውና ለማየት ዕድል ያለው ሰው ሁሉ እንዲመለከተው ያደረጉ ታማኝና ልማታዊ ጋዜጠኞችስ ቢሆኑ መመስገን ይገባቸው ነበር “ አለኝ፡፡

ታዲያ እንዲህ የተባረከ ሰው እኔንም አስደሰተኝ፡፡ ምክንያቱም የመንግሥታችንንና የልማታዊ ጋዜጠኞችን ውለታ አለአግባብ የትም ከሚጥሉት ይልቅ በዚህ ሰው አነጋገር አንጄቴ ቅቤ ጠጣ፡፡ በእንዲህ በእንዲህ ያሉ ነገራት አንጄቴ ቅቤ ባይጠጣ ኖሮ፣ ቅቤ ገዝቶ ለመጠቀም ይቅርና ዘይቱ እንኳን ተወዶ የለ! ድሮስ ድሀ በህልሙ ቅቤ ባይጠጣ የሆድ ድርቀት ይገድለው ነበር ይባል የለ፤ ለህልም ምስጋና ይግባውና፡፡

እነዚህ አሾክሿኪዎች ሌሎች ወሬዎችን እያወሩ ነዉ። መቼም አሾክሿኪ የሚያንሾካሹከው አያጣም አይደል? ሰሞኑን ደግሞ ነጋዴው በራሱ ጅራፍ እራሱን ገረፈ እያሉ ማንሾካሾክ ይዘዋል፡፡ ለዛሬው ወሬ እንዳላበዛበዎት ይቆየንና ሳንምንት አጫውትዎታለሁ፡፡ ቸር ይግጠመን፡፡

የፍኖት የመጀምሪያዉ እትም ጋዜጣን በሙሉ በፒ.ዲ.ዔፍ ለማንበበ ከዚህ ይጫኑ

አስተያየት መስጫው ተዘግቷል።