ቃለ መጠይቅ ከብርቱካን እናት ጋር – አወደ እትም 24
ቃለ መጠይቅ ከወ/ሮ አልማዝ ገብረ እግዚአብሄር ጋር – በደበበ እሸቱ
ይህን ቃለ ምልልስ ለማድረግ ከወ/ሮ አልማዝ ጋር በነበረኝ ቀጠሮ መሰረት ወደ ቤታቸዉ ወደ ፈረንሳይ ኤምባሲ አካባቢ የሄድኩት በቀጠሯችን ሰዓት ነበር። ዋናዉን መንገድ ለቅቄ ወደ መንደሩ ገባ ስል በአካባቢዉ ካለዉ ወፍጮ ቤት አጠገብ ወ/ሮ አልማዝ ቆመዉ ከአንዲት ሴት ጋር ወሬ ቢጤ ይዘዋል።
አጠገባቸዉ ስደርስ መኪናዬን ሳቆም «ግድ የለም እንናተ ሂዱ፣ እኔ እመጠላሁ» አሉ ። ያሉት ከቤታቸዉ ራቅ ብለዉና እየመሸም ስለነበር «መኪና ዉስጥ ገብተዉ አብረን እንሂድ» ብንልም አሻፈረኝ አሉ። እኔም «በጭራሽ አብረን እንሂድ ይግቡ ፣ ለምኑ ነዉ ?» በማለት ጠንከር ስል «አይ ቅቤ ተቀብቼ ነዉ። ደግ አይደለም ብዬ ነዉ። እባካችሁ ሂዱ እደርስባችኋለሁ» ቢሉም አሻፈረኝ ብዬ የግድ አስገብቻቸዉ አብረን ሄድን።
እዉነቱን ለመናገር አንድም የቅቤ ሽታ አልነበረምና «እሜቴ የታል ቅቤዉ ?» አልኳቸዉ። «አናቴ ጠጥቶ ጨርሶት ይሆናል» ብለዉ ወደ ቤት ይዘዉን ገቡ።
ከተም በሩን የከፈተችልን እሳቸዉም ልጄ፣ ብርቱካን እህቴ የምትላት የወንድማቸዉ ልጅ ነበረች። ሰላም ብለናት ስንዘልቅ «ፍልቅልቋ» ሃሌ በረንዳዉ ላይ ከፊሉን ደረጃ ወርዳ ትጠብቃለች። አያቷን ሰላም ብላ እኛንም ሰላም አለችን። ሃሌና እኔም አብሮኝ የሄደዉም የሺዋስ ጋር እንተዋወቃለንና እቅፍ እያደረገች ነዉ ሰላማታ የሰጠችን። ወዲያዉ ወደ ዉስጥ ገባንና አርፍ አልን።
ስለሄድንበት ጉዳይ አስቀድሞ በስልክ ያነጋገርኩዋቸዉና ጉዳዩን የሚያወቁ ቢሆንም ለማረጋገጥ ያህል በድጋሚ «በአሜሪካ ያሉ የብርቱኬ ደጋፊዎች ስለአስተዳደጓ ማወቅ ስለፈለጉ ነዉ ልጠይቅዎት የመጣሁት» ከማለቴ ወዲያዉ መልስ መስጠት ጀመሩ። ደግነቱ ቴፑ ክፍት ስለነብር ያዘልኝ እንጂ ጉድ ልሆን ነብር።
ከወ/ር አላምዝ ጋር ያደረኩትን አጭር ቃለ ምልልስ እንደሚከተለዉ አቀርቤዋለሁ።
ደበበ – ወ/ሮ አልምዝ ብርቱካን መቼ ነዉ የተወለደችዉ ?
ወ/ሮ አልማዝ – ቀኑንማ እንግዲህ እኔ ምን አወቄ። ምልክቱ ግን በጃንሆይ ጊዜ ነዉ። ምልክቱ እሱ ነዉ። እርሳቸዉ ሲወርዱ ነዉ የተወለደችዉ። ከዚያን ሰዓት ጀመሮ በአራት አመቷ የፊደል ትምህርት ገባች። በአምስተኛ አመቷ አንደኛ ክፍል ገባች። ከዚያ አንድም ጊዜ ወደቃ አታወቅም። አንደኛ አንደኛ እየወጣች ፣ እየተሸለመች እና 12ትም ያዉ በፈተናዉ 100 አገኘች ተብሎ ዩኒቨርሲቲ ገባች።
ደበበ – በአምስት አመቷ አንደኛ ክፍል ገባች ብለዉ በስንት አመቷ 8ኛ ክፍል እንደጨረሰች አልነገሩኝም።ወ/ሮ አልማዝ – እንዴ ስምንተኛ ሳትጨርስ 12ኛ አትገባም መቼም።
ደበበ – አላነሱትም ብዬ ነዉ
ወ/ሮ አልማዝ – ጠይቀኝ እመልሳለሁ፡
ደበበ – እስከ ስምንተኛ እንዴት ነበር ትምህርቷ
ወ/ር አልማዝ – ጎበዝ ነበረች እንዳልኩህ በአምስት አመቷ 1ኛ ገባች። በቃ በየክፍሉ አንደኛ አንደኛ እየወጣች እየተሸለመች ጨረሰች። አንድም ጊዜ ወድቃ አታወቅም።
ደበበ – በአካባቢዋስ ጠባይዋ እንዴት ነበር ? ከመንደር ልጆች ጋር ትጣላ ነበር ? ተንኮል ነበራት ?ወ/ሮ አልማዝ – ማን ? ብርቱ ? እሷ እቴ ምን በወጣት ? ከመንደሩ ልጆች ጋር ፍቅር ነበረች። ሁሉም አብረዋት ለማጥናት ነዉ የሚፈልጉት። የመንደሩ ሰዉ ሁሉ በፍቅር ነዉ የሚወዳት። ብርቱ ለፍቅር ነዉ የተፈጠረቸዉ ስልህ !
ደበበ – አስተዳደጓስ እንዴት ነበር ? አባቷስ ምን ነበሩ ?
ወ/ሮ አልማዝ – አባትዋ ወታደር ነበሩ። ብርቱ የተወለደችዉ ጡረታ ከወጡ በኋላ ነዉ። ታዲያ በዳቦ ነዉ ያደገችዉ። እንጀራ እንኳን አትወደም ነበር። በጡረታችን ተንከባከብን ነዉ ያሳደግናት።
ደበበ- ጡረታዉ ስንት ነበር ?ጡረታችን 30 ብር ነበር። በኋላም ተመልሰን ሥራ እንደገና ስንጀመር ደሞዝ ከሁለት ወገን ነበረን።
ደበበ – ታስቸግር ነበር በልብስ በጫማ ምርጫ ?ወ/ሮ አልማዝ- እሷ እቴ በጭራሽ። የምታስቸግረዉ እንጀራ አልበላም ብላ ነዉ። ዳቦ ትላለች። ከዚያ ዉጭ በጭራሽ አስቸጋሪ ጠባይ የላትም። አስቸግራኝም አታወቅም። አሁን ነዉ ችግር የመጣዉ። ከጎሮቤት ጠብ የላት። ፍቅር ብቻ ነበረች ። ከማንም ተጋጭታ አታወቅም። ከሁሉም ጋር ፍቅር ነዉ። 12ኛን ስትጨርስ ወንድሟ ጋር አዋሳ ሄደች። ወዲያዉ የ12ኛ ወጤት ሲመጣ አልፋለች ተብሎ ጥሯት ቶሎ ጥሯት ተባለ። አዲስ አበባ ነዉ የደረሳት ተባለ። መጣታ ገባች። ያወ አምስት አመት ተምራ በጥሩ ዉጤት አልፋ በሕግ ተመረቀች።
ደበበ- ከሚሰብሩት ጋር አብራ ትቀላቀል ነበር?
ወ/ሮ አልማዝ – እኔ እንግዲህ ሰበርኩ ብላኝ አታወቅም። ግን መቼም ….ብቻ ብዙ ጊዜ ጥፋት ቦታ አትገኝም። የአሁኑ ምን እንደሆነ አልወቅም። ጥፋት ነዉ አሉ እነርሱ ። እኔ ግን ጥፋቱ አልታይሽ እያለኝ ግራ እጋባለሁ።
ደበበ – እኔ አሁንም ቢሆን ጥፋት አላይባትም። ወ/ሮ አልማዝ እነርሱ ደግሞ ጥፋት ነው አሉዋ !
ደበበ – እነርሱ ባሉት ሳይሆን እንደ እዉነቱ ።
ወ/ሮ አልማዝ- እንደ እዉነቱማ ብርቱ ጥፋት ያሉት ነገር አታወቅም። አላደገችበትም። አልኖረችበትም። አይተዋወቁም።
ደበበ – አሁንም አላጠፋችም። ጥፋት የለባትም።
ወ/ሮ አልማዝ ጥፋት ነዉ ብለዉ አይደል ወህኒ ያገቡብኝ።
ደበበ – የጉልባት ጉዳይ ነዉ እርሱ
ወ/ሮ አልማዝ – መቼ አሉ ? ጥፋት ነዉ ነዉ የሚሉት።
ደበበ – የለም ጥፋት አይደለም። ለሕዝብ ታማኝ መሆን፣ ለሕዝብ መቆም፣ የሕዝብ መብት ለማስከበር መታገል ቃልን መጠበቅ ምኑ ነዉ ጥፋቱ ?
ወ/ሮ አልማዝ – እስቲ እንግዲህ ይሁን ። እግዚአብሄርን ነዉ የምንለምነዉ። የርሱ ድርሻ ነዉ ከእንግዲህ ወዲያ – የሱ ጉዳይ ነዉ።
ደበበ- ትምህርትስ ከጨረሰች በኋላ
ወ/ሮ አልማዝ – የየካ ክፍለ ከተማ ዳኛ ሆነች በኮንትራት
ደበበ- እንዴት ነበረ ከሕዝብ ጋር ከባለጉዳይ ጋር የነበራት ስም ?
ወ/ሮ አልማዝ – በፍቅር ነበር የሚያነሷት። ይነግሩኝ ነበር። ለሰዉ ታዝናለች ይሏት ነበር። በኋላም ደግሞ ዳኝነቱን ትታ ጠበቃም ስትሆን ጥሩ ስም ነበራት። ለቸገረዉ በነጻ ትቆማለች። የቻላችሁትን ክፈሉ ትላላች። ደግ ነች። ሌሎች ጠበቆች ታዲያ ያንን ሲሰሙ ይበሳጩ ነበር። አበላሸሽብን እያሉ ይወቅሷት ነበር። እርሷ ደግሞ የተቸገሩ ጠበቃ ይጡ ወይ ትል ነበር።
ደበበ- አንድ ጊዜ ዳኛ እያለች የአቶ ስዬ አብርሃን የዋስ መብት ፈቅዳ ነበርና ያን ጊዜ ሰዉ ምን አለ ?
ወ/ሮ አልማዝ- ዉጭ ነበርኩኝ ያን እለት። ተመልሼ ቤት ስመጣ ቤት ሰዉ ብቻ ነበር። ምንድን ነዉ ስል እንዲህ እንዲህ ሆነ አሉ።
ደበበ – ምንድን ነዉ እንዲህ እንዲህ?
ወ/ሮ አልማዝ – «ለብዙ ጊዜ አለአግባብ ዋስ ተከልክለዉ የነበሩትን ስዬ የሚባሉትን (የነሱ ጓደኛ ነዉ አሉ) የዋስ መብታቸዉን ፈቀደችላቸዉ። የሕግን የበላይነት አረጋገጠች። ለሕግና ለደንቡ እንጂ ለማንም ብላ እንደማትፈርድ አሳየች።» ብለዉ ደስ ብሏቸዉ እግዚአብሄር ከአይን ያዉጣልሽ አሉኝ። ወዲያዉ ከሥራ ወጣሁኝ አለች። ደነገጥኩኝ። ምን እንሆናለን እያልኩ ሃሳብ ያዘኝ።
ደበበ-ወጥታስ?
ወ/ሮ አልማዝ – ጥብቅና ገባች። ከዚያ በኋላ ነዉ ይህን ቤት የሰራነዉ። የበፊቱን አፍርሰን ይህን ሰራን። ጥብቅና ከገባች በኋላ። አሮጌ አፍርሰን አዲስ ስንሰራ መቀመጫ አጣን።
ደበበ-ወደ ፖለቲካ ከገባችስ በኋላ ?
ወ/ሮ አልማዝ – የፖለቲካን ነገር እኔ አልወቅም። እንዲህ ያለ ነገር ጋር አትሂጅብኝም እላለሁ።
ደበበ – እርሷስ ምን አልችዎት ?
ወ/ሮ አልማዝ – ማን ? ብርቱ ? እርሷ ስቃ ዝም ነዉ። እንዲህ ነዉ እንዲያ ነዉ አትልም።
ደበበ – አሁንስ ቃሊቲ ይሄዳሉ። ይጠይቋታል። ሃሌም ትሄዳለች ?
ወ/ሮ አልማዝ – እሁድ አልደርስ እያለኝ እጠብቀዋለሁ። ለኔ ሲሆን ደግሞ ቅዳሜና እሑድ ይርቃል። በፊት ሳይታሰብ ነብር የሚደርሰዉ። አሁን ይጎተታል።
ደበበ -ብርቱኬ ስሜቷ እንዴት ነዉ ? አሁን እናንተን ስታይ ሃሌን ስታይ እንዴት ነዉ ስሜቷ ?
ወ/ሮ አልማዝ – እኛ እንዴት ሆና ይሆን ብለን እንጨነቃለን። እርሷ ደህና ነች። ጎበዝ ጠንካራ ነች። የተገላቢጦሽ እኛን አይዟቹህ ትለናለች። እኔንም ሃሌንም እህቷንም ታጫወታለች። ታበረታታለች።
ደበበ – ሃሌ – ብርቱ ምን ትልሻለች ?
ሃሌ – እንዴት ነሽ ? አይዞሽ እመጣለሁ ትለኛለች። እንዴት ነሽ ስትለኝ ደህና ነኝ እላለሁ።
ደበበ – አባቷ ስለብርቱ ምን ይሉ ነበር ?
ወ/ሮ አልማዝ – አይ አይ እንኩዋንም ይህን አላዩ። አለማየታቸዉ እግዚአሄር ቢወዳቸዉ ነዉ። ችግሯን አይወዱም። ማንም ሲነካት አይፈልጉም። እንኳን ያላዩ ።
ደበበ – ይሄ አሁን የምንነጋገረዉ ዉጭ ያሉ ደጋፊዎች ጠይቀህ ላክልን ስላሉኝ ነዉ። ለነርሱ ምን የሚሏቸዉ ነገር አለ።
ወ/ሮ አልማዝ – በርቱልኝ ነዉ የምላቸዉ። «ከእግዚብሄር ጋር በርቱልኝ። ለምታደርጉት ነገር ሁሉ አመሰግናለሁ። እግዚአብሄር ከኔም ከናንተም ጋር ይሁን። እግዚአብሄር ከመላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ይሁን።» ነዉ የምለዉ። አመሰግናቹሃለሁ በብዙዉ በልልኝ።
ደበበ – ዉጪ ባሉት ደጋፊዎቻችንና በራሴም ስም በአንድነትም ስም ከልብ አመስግናለሁ።



one day u will be free soon, not only u but also all ethiopians could have great chance free from opressor as a result of ur strong devoted for ur people.
wow , oh my lord help for Birtukan ,her mom and all inocent ethiopian people. in this time she supposed to help and support her mom and her beatuful daughter instead of nasty prison or whatever .
እናመሰግናለን አቶ ደበበ
ምነው በምስል አላቀረብህልንም? ለደህንነታቸው ታስቦ ከሆነ መልካም::
Get up everybody. Let’s get out of this mess. Prayer is the only way out. God bless Ethiopia
ጋሽ ደቤ መጠይቕን አጠር ያደረግካት ለምን እንደሆነ ይገባናል በእህታችን ህይወት አይነት ውስጥ ስላለፍኩኝ ይሁን አላውቅም ውስጤ አለቀሰ አላህ ሁሉንም አዋቂና ተመልካች ስለሆነ ሀሌ እና አያትዋም የሚደሰቱበትን ቀን ቅርብ እንዲያደርግላቸው (ዱዓ)ጸሎት አያደረግኩ ነው ::
ደቤ ስለ ሀሌ አባት ግን ያልከን ነገር የለም ለምን?
ሰላም እንሁን!