ለማሸነፍ በልጦ መገኘት – ከዳኛቸው ቢያድግልኝ

February 26th, 2009 ይመይሉ ይመይሉ ያትሙ ያትሙ

ታሪኩ አባዳማ የሞተ ፈረስ መደብደብ ወንዝ አያሻግርም በሚል ርዕስ ቀልብ የሚስብና እጥር ምጥን ያለ ጽሁፍ አስነብበውናል። (ካላነበቡ በኒህ አድራሻዎች ያንብቡ http://ethiomedia.com/aurora/flogging_a_dead_horse.pdf ወይም http://www.abugidainfo.com/amharic/wp-content/uploads/2009/02/deadhorse2.pdf) ጭብጡ ግባችንን አውቀን ወደዚያ የሚወስደን መንገድን መጀመር እንጂ ያሰብንበት እንዳንደርስ ያደረጉንን ምክንያቶች አገዝፈን የሞተ ፖለቲካ ሰልስትና ተዝካር እያወጣን እኝኝ ብንል የትም አንደርስም መሰለኝ። በተለያየ ወቅት መንግስት መጣል ዋና አላማ እየሆነ ብዙዎች ከወደቁ በሁዋላ በሚወድቀው መንግስት ምትክ የሚመጣው ምን እንደሆን ሳናውቀው እንደ ዱብ እዳ የራበው ጅብ ከጠገበው ስልጣን ሲወስድ ቆይቷል። በዚህ ዑደት ውስጥ አንዴ ከተበላው አንዴ ከሚበላው ስንወግን ወይ ዳር ቆመን በላተኞች ስንመለከት የኖርን ነን። ለዚህም ነበር በአንድ ጽሁፌ ውስጥ እስከ አሁን የሄድንበት መንገድ ካሰብንበት ካላደረሰን ጓዳ ጎድጓዳችንን መፈተሽና የመንገድ ለውጥ ማምጣት የግድ ነው ያልኩት። ይህን እንድጽፍ ያበረታታኝ ደግሞ ይኸው ከላይ የጠቀስኩት ጽሁፍ ነውና ታሪኩ አባዳማን ላመሰግን እወዳለሁ። በእርግጥም ቀና ብሎ አይሞግትምና የሞተ መኮነን ጀግናና አዋቂ አያደርግም ለድልም አያበቃም።
ለማሸነፍ በልጦ መገኝት ነው!! ሌላ ምንም ቀመር የለውም ማሸነፍ የፈለገ ተወዳዳሪውን በልጦ መገኘት አለበት። የተሸናፊ አሸናፊ የለውም ያ ምናልባት የሚሰራው ለጽድቅ ብቻ ይሆን ይሆናል:: እርሱም ቢሆን ፈጣሪ የሰጠውን አእምሮና ጉልበት መጠቀም ካልቻለና ሕዝቡን ከሰቀቀንና ከሰቆቃ ማውጣት ካላወቀበት መክሊቱን እንደጣለ አደራ በላ ተቆጥሮ ምህረት ላይደረግለት ይችላል። ይህን ትንተና ለቀሳውስቱ ልተውና የምድር የምድሩን የሃሳቤን ልምጣበት።

በሰላማዊ መንገድ በምርጫ ኢትዮጵያውያን ወያኔን እንደማይፈልጉ በግልጽ አሰቀምጠዋል። እንኳን በሩቅ ያሉት የወያኔ ቤተዘመዶችም ጭምር ምናልባት ሚስትና ልጆች ሳይቀሩ አላማረባችሁም ተዉት ያሉአቸው እስኪመስል ድረስ ድምጽ ተሰጥቶ ነበር። ወያኔ በዚህ አይነት የአማረ የስልጣን ዑደት ውስጥ ለመግባት አልተዘጋጀም። እኛም ስልጣኑን ለመረከብ አልተዘጋጀንም ነበር። ምክንያቱም ወያኔ በሚበልጠን ይበልጠን ነበርና። አብላጫው ሕዝብ ወያኔን የሚቃወም ከሆነ ለተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች አንድ ትልቅ ስራ ተቃሎላቸዋል። የከበደው ነገር ይህን ትልቅ እምቅ ኃይል ወደ ውጤት ሊወስድ የሚችል የድርጅት አቅም ማጣት ይመስላል።

ወያኔዎች ከተሸነፉ ሰንበትበት ብለዋል። ሽንፈታቸውን ግን ገና አልተቀበሉትም። የጎጠኛው ስርአትን ስጋ የሚያላውሰው ነፍስ እስኪነጠቅ ድረስ ግን ሲንፈራገጡ በእግራቸው ሊራገጡበት፣ በጥፍራቸው ሊቧጥጡበት በጥርሳቸውም ሊናከሱበት ይችላሉ። የፕሮፓጋንዳና የቅስቀሳ ልሳናቸው ከተያዘ ከረምረም ብሏል። ቢቆጡ አያስፈራም፣ ቢጣሩ አይሰማም፣ ቢለማመጡ አንጀት አያራራም። ግን ግን መርዘኛው ስርአት ገና አልሞተም።

ወያኔዎችን ለማሸነፍ በልጦ መገኘት የሚለውን አርእስት የመረጥኩት በልጠን በተገኘን ቁጥር በድል መመለሳችንን ለማመልከት በመሻትና በሚቀሩን ጉዞዎች ላይ ልንበረታታ ያስፈልገናል ለማለት ብቻ ነው። ተመሳሳይ ዓላማ ያለን ሰዎች ለአፍታ እንኳን አንድ ላይ ስንቆም ወያኔዎች ሽብር በሽብር እንደሚሆኑ ተመልክተናል። አብረን መክረም ባለመቻላችን ግን ተመልሰን እዚያው እየተገኝን የሌላቸውን ጉልበት እየቸርናቸው እንገኛለን።

አንዳንዶቻችን በደረቅ ጥላቻ እየተሞላን አስረግጠን ወያኔን ለመታገል አቅም ያንሰናል። አገር ማፍረሳቸውን ብቻ ሳይሆን አገር እንዴት ልንገነባ እንደምንችል መንገዱን ልናውቅ ይገባል። የኢኮኖሚ ቀውሱ ያስከተለውን ችግር አማርረን ወያኔ ከመጥላት በላይ በምን መንገድ በድል
ንወጣ እንደምንችል ለይተን ማወቅና መፍትሄውም ምን እንደሆነ መመርመርና መምከር ያስፈልገናል። ያኔ ከማሸንፋችንም በላይ ብልጽግናን የሚያመጣውን መንገድ ልናውቅ እንችላለን። ያለበለዚያ ነገ ወደ ስልጣን የሚመጡትን እንኳ ተጠያቂ ለማድረግ ወይም በሚመርጡት መንገድ መሄዱ ትክክል ነው ወይስ አደገኛ ብለን ለመመርመር አቅም ያንሰናል። ይህን ልብ ባለማለትም ነው የችግር አዙሪት ውስጥ ደጋግመን የምንመላለሰው።

የመርዝ ፕሮፓጋንዳ ሲረጩ ለመመከት የማርከሻ ፕሮፓጋንዳ ያስፈልጋል። ለማሸነፍ ግን ራቁት የሚያስቆማቸውና እንቅልፍ የሚነሳቸው አይነት የቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳ ስራ ሊሰራ ይገባዋል። ያኔ መጥፎው አስተዳደር ወደ መቃብሩ ይጠጋል። እነርሱ ለአፍታ የውጭ ዜጋ ካገኙ በአማራው መንግስት (የነርሱ አጠራር ነበር) የእርጉዝ ሴት ሆድ እየተቀደደ ወንድ ወንዱ እንደሚገደል አልቅሰው ይናገሩ ነበር። ዛሬ እነርሱ የሚያደርጉትን ያለ ለቅሶ ተናግሮ ማሳመን ይቻላል። ይህን የምናደርግ ግን ጥቂት ነን። ይህ የፖለቲካ እውቀት የማይሻ የሀገር ፍቅር ብቻ የሚበቃው ስራ ነው። እነርሱ ከፍተኛ ገንዘብ እያፈሰሱ የተማረከ ወታደር ሰብስበው በየጎጡ ሸንሽነው እንደ አጋሰሰ የሚነዱትንና መንገድ የሚመራቸውን ሲያደራጁ እኛ ወያኔን ትተው የሚመጡትን እንኳ በአግባቡ ልንጠቀምባቸው አልቻልንም። ይልቁንም እያስፈራራናቸው እዚያው የወያኔ ጉያ ብትቀመጡ ይሻላችኋል አይነት አታካች ቅስቀሳ እንቀሰቅሳለን። በዚህም ምክንያት የሚሰራውን ግፍ እየተመለከቱ አንጀታቸው እያረረ መውጫ ቀዳዳ አጥተው የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም አይነት ግፍ እንዲፈጽሙ የሚገደዱ እንዲበዙ እያመቻቸን ነው። በጊዜያቸው ፈንጭተውብን አሁን እየተለሳለሱ ያሉትን አቅፈን እየያዝን ትንሽም ብትሆን የፖለቲካ ትርፍ የሚያስገኙትን ማብጠልጠል ብልህነት የጎደለው ጀግንነት ይሆናል። እነርሱ ሊጠልፉበት የገመዱትን የተንኮል ገመድ እኛ ወደ ጅራፍነት ለውጠን ብንገርፋቸው እንጂ ገመዱን ራቅ አድርገን ብንጥል ትርፋችን ብዙ አይሆንም።

ከመሰረታዊ እውቀት ይልቅ አሉባልታን አብዝተን የምንወድ ከሆነና ዛሬ ላይ ቆመው ነገን ማየት በተሳናቸው የእድሜ ልክ ተቃዋሚዎች መድረኮች ከተጣበቡ እልፍ ማለት አይቻለንም። ነጻነትን፣ ፍትህንና ብልጽግናን በወኪል ማግኘት የምንሻ ከበረከትን ነጭ ባንዲራ እንዳውለበለበ ምርኮኛ ነን። ስለዚህ የሞከሩትን ስንኮንን እኛስ ከመውቀስ ባሻገር ምን ፈየድን በማለት ራስን ቀድሞ መጠየቁ ተገቢ ነው። ለወቀሳ ከመነሳታችሁ በፊት የሰራችሁትን ገድል ተናገሩ የሚባል ቢሆን ዝምታ የሚሰፍን ይመስለኛል።

ለማጠቃለል ያህል በተለያዩ የእውቀት ዘርፎች ራሳችንን አስታጥቀን ከስሜታዊነት ይልቅ በአስተዋይነት ወዳጅ የምናበዛና የተፎካካሪዎቻችንን የእውቀት መካንነት የምናሳይ መሆን አለብን። በቅስቀሳውና በፕሮፓጋንዳው መስክ ደግሞ የአየር ሞገዱን እየሰነጣጠቀ የተቀናቃኙን ጎራ ፍርክስክሱን የሚያወጣ ስራም ያለመታከት ሊሰራ ይገባዋል። ታሪካዊው የኦባማ አሸናፊነት መሰረቱ ሕዝቡ ነበር። በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በሚከሰክሱ ባለሀብቶች ሳይሆን አንድና አምስት ዶላር መስጠት የሚችሉቱ ነበሩ የኦባማን የምርጫ ጊዜ ወጪ ተወዳዳሪ የሌለው እንዲሆን ማድረግ የቻሉት። ወያኔዎች ይህን በጊዜያቸው ሰርተውታል። የነርሱ አባላት ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ አንጻር ሲታይ ትንሽ ነው። ይህ የሀገሩ ጉዳይ እርር ድብን የሚያደርገው ወገን ግን ለዚህ ጉዳይ ምን ያህል ለጋስ ነው? ብለን የየራሳችንን ብንገመግም ባዶአቸውን የሚውተረተሩ የሰዎች ስብስብ በመሆናቸው የእውቀት አቅም ሳያንሳቸው ተሽመድምደው የሚቀሩ ተቋማት ሊበዙ የቻሉበትን ምክንያት መረዳት ያስችለናል። ስለዚህ ይህን የመከራ ጊዜ ማሳጠር እንችል ዘንድ በእውቀት ለመታነጽ እየተማማርን፣ በፕሮፓጋንዳው ለመብለጥ የመረጃ ምንጮቻችንን እያጠናከርን እንደልብ ለመንቀሳቀስ የገንዘብ አቅማችንን በማጎልበት ከአለችን ማዋጣት ብቻ ሳይሆን ፈጠራ በተሞላው መንገድ ገንዘብ ማሰባሰብ መቻልን ካወቅንበትና በልጠንም ከተገኘን ማሸነፋችን እርግጥ ነው። ስለዚህ እንደ ታሪኩ አባዳማ አባባል ወንዙን ለመሻገር የሞተ ፈረስ ከመደብደብ ይልቅ ብርቱ ፈረሶችን መግራቱ ይበጀናል።

እግዚአብሄር ይርዳን!!

ከዳኛቸው ቢያድግልኝ

biyadegelgne@hotmail.com

 1. ሕሊና
  | #1

  ዳኛቸው ጥሩ ብለዋል

  አናንዳንዶቻችን ድምጻችንን ከፍ አድርገን ወያነን ስላወገዝን ብቻ በትንፋሳችን ጥንካረ መለስን ከበተመንግስት ገፍትረን የምናስወጣው የሚመስለን አለን:: ይሀ ድግሞ ረጋ ብሎ ክማሰብና እውነተኛ ለውጥ ሊያመጣ ከሚችለው ተግባራዊ እንቅስቃሰ ብዙ ወደ ሁዋላ እየጎተተን ይገኛል:: ለዚህም ይመስለኛል አንዳንድ ለኢትዮጵያ ነጻነት ሲባለ ወያነ መፍርስ አለበት በማለት ቀን ከለሊት የሚጮሁ ጠንካራ ኢትዮጵያውያኖች ወያነን ጥለው በመውጣት ሊያዳክሙት የሚችሉትን ሰዎች “አንደ ወያነ ሁለ ወያነ” በማለት ወደተቃዋሚው ጎራ እንዳይቀላድሉ የሚያከላክሉት:: ይህ ደገሞ የወያነን እድመ ለማራዘም ከምንም በላይ አስተዋጸኦ ማድረግ ነው::አቶ ሰየንና በርካታ ዝርዝሩን የማናውቀውን የወያነን ጉድ ያወጣውን ጋዘጥኛ “ጥላችሁትም ሆነ ተገፍታችሁ የወጣችሁበትን አጥፊ ድርጅት አብረን እናዳክም” በማልት በጋራ ከመስራት ይልቅ “ወያነ ከስልጣን የወረድ ለት ለፍርድ እናቀርባችሁዋልን እንሰቅላችሁዋልን” በማለት በባዶ መዳ ዛቻ በማብዛት ሊያገዙን የሚችሉትን በርካታ ሰዎች የምናርቀው:: እግዘር ብልጠቱን ሰጥቶን ዋናው ትኩረታችን ወያነን በትክክለኛ መንግስት የምንልወጥበትን ቀን ያቅርበው እላለሁ::

 2. አቢይ፡ኢትዮጵያዊ
  | #2

  )))))))))))))የመረረ:ትግል((((((((((((((
  “መለስ?”
  ወይስ፣
  በእነ”መለስ?”
  የኢትዮጵያ፡ጠላት?
  ማ’ነው፡የገደላት?
  በጁ፡ነው፡በሌላ?
  የሰው፡ደም፡የበላ?
  እያልን፡ስናወራ፤
  ነገር፡ስናጣራ፤
  በፖለቲካ፡ቃል፤
  እንካ፡ስንባባል።
  ሺህ፡መላ፡ስንመታ፤
  ሕዝቡ፡እንዳይረታ።
  ሺህ፡ማውራት፡አይበቃም?
  ዛሬም፡አንነቃም?
  አሥራ፡ስምንት፡አመት?
  አይበቃም፡መሟገት?
  ይልቅ፣«ኣቦ፡ተስፋይ»
  የተሻለ፡እንድናይ፤
  ይሄን፡ያንን፡ሳንል፤
  ችቦው፡እናቀጣጥል፡፡
  የሕዝብ፡አመፅ፡ግሞ፤
  ዛሬ፡ተፍገምግሞ።
  በተግባር፡ሲበስል፤
  በወላዲት፡ሲምል፤
  ይፈጃል፡ለብልቦ፣
  ዶግ-አመድ፡ያደርጋል፤
  ግፍ፡ይጠራርጋል።
  እየፋመ፡ሲግል፤
  የመረረ፡ትግል።

አስተያየት መስጫው ተዘግቷል።