«አንድነት የሚታገለዉ ለኢሕአዴግ የምርጫ አጃቢነት ሚና ለመጫወት አይደለም» አንድነት – ልዩ ዘገባ – ከአወደ ኢትዮጵያ

February 26th, 2009 ይመይሉ ይመይሉ ያትሙ ያትሙ

የካቲት 19 ቀን 2001

የአለም አቀፍና የአገር ዉስጥ ጋዜጠኞች በተገኙበት የአንድነት ፓርቲ ሰፋ ያለ ጋዜጣዊ መግለጫ ዛሬ የካቲት 19 ቀን 2001 ዓ.ም እንደሰጠ ለማወቅ ችለናል። በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በገዢዉ ፓርቲ በማእከልና በክልል ደረጃ ከፍተኛ ወከባና ተጽእኖ እየደረሰበት እንደሆነ የአንድነት ፓርቲ መረጃ ላይ የተመሰረተ ገለጻ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት የዜጎችን የመደራጀትና ሃሳባቸዉን በነጻ የመግለጽ መብትን እንደሚደነግግ፣ የመንግስት አካላትም የአገሪቱ የበላይ ሕግ የሆነዉን ሕገ መንግስቱን የማስከበር ግዴታ እንደነበረባቸዉ በማስታወስ፣ ከድርጅቱ ሊቀመንበር ጀምሮ እስከ ክልል አባላት ድርስ በተለያየ መስክ እየደረሰ ያለዉ ሕገ ወጥ ተግባራት እጅግ በጣም አሳሳቢና አገሪቷን ወደ ከፋ ደረጃ ሊወስድ እንደሚችል የፓርቲዉ አመራር አባላት አስረድተዋል።

በማእከል ደረጀ በገዢዉ ፓርቲ እየተወሰደ ያለዉን ጸረ-ዲሞክራሲያዊ አሰራር ለማሳየት እንደምሳሌነት ከተጠቀሱት ዉስጥ በዋናነት የድርጅቱ ሊቀመንበር ክብርት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የተወሰደዉ ሕገ ወጥና ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ነበር።

ወ/ት ብርቱካን ለሁለት ወራት ሕገ መንግስታዊ መብታቸዉ ተነፍጎ፣ ጉዳያቸዉን ፍርድ ቤት እንዳያቀርቡ ታግደዉና በጨለማ ቤት ዉስጥ እንዲቀመጡ መደረጉ እጅግ እንዳስቆጣቸዉ የገለጹት የአንድነት መሪዎች፣ ገዢዉ ፓርቲ ሕገ መንግስቱን ከመናድ ተቆጥቦ፣ እራሱን ለሕግ እንዲያስገዛና የፓርቲዉን ቆራጥ ሊቀመንብር በአስቸኳይ እንዲፈታ አስገንዝበዋል።

ሌላዉ በማዕክል ለሚቀርበዉ ጸረ-ዲሞርካሲያዉ የገዢዉ ፓርቲ ተግባራት እንደምሳሌ የተጠቀሰዉ በአዲስ አበባ ሊደረግ የታሰበዉ የአንድነት ወጣቶች የኪነጥበብ ምሽትን የተመለከተ ነዉ። የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ስለነበረ በወጣቶች ሊደረግ የታሰበዉ ዝግጅት መተለለፉን ያስታወሱት የአንድነት አመራር አባላት፣ አሁን እንደገና ያንን ዝግጅት ለማድረግ ጠይቀዉ በመንግስት አካላት ሕገ መንግስታዊ መብታቸዉን ተረግጦ እንደተከለከሉ ገልጸዋል።

«ማን ያዉራ የነበረ። ማን ያርዳ የቀበረ» እንደተባለዉ በክልል ደረጀ እየደረሰ ያለዉን ወከባ በተመለከተ ከአራት ክልሎች የመጡ የአንድነት የክልል አመራራ አባላት እርሳቸዉ በጋዜጣዊ መግለጫዉ ወቅት ተገኝተዉ ማብራሪያ በመስጠት ገዢዉ ፓርቲ ምን ያህል የአንድነት ፓርቲ ላይ ጫና እያደረገ እንዳለ አጋልጠዋል።

በምስራቅ ጎጃም (ደብረ ማርቆስ አካባቢ) የዞኑ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ሉልሰገድ ፣ ፓርቲዉ ካለዉ የገንዘብ እጥረት የተነሳ ሕዝቡ እራሱ ከፍቶ የሚያንቀሳቅሳቸዉ አምስት የአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤቶች ( ራስ አገዝ ቢሮውች) በክልሉ ባላሥልጣናት በጉልበት እንዲዘጉ የተደረገ እንደሆነና የአንድነት አባላት ፓርቲያቸዉን ከመደገፍ እንዲቆጠቡ፣ እንዲሁም እያደረጉት ካለ ዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ቢታቀቡ እንደሚቻል በመናገር ከፍተኛ ማስፈራራትና ዛቻ እየደረሰባቸዉ እንደሆነ አስረድተዋል።

በኦሮሞያ በኢሊባቡር መቱ ነዋሪ የሆኑ አቶ ዳንዔል ወልደገብሬል የሚባሉ የአንድነት አስተባባሪ በተራቸዉ፣ ከዚህ በፊት ለ27 ቀናት ፣ አሁን በቅርቡ ደግሞ ለሳምንት ታስረዉ እንደተፈቱ አስረድተዉ ፣በክልሉ ባለሥልጣናት እየደረሰ ያለዉ ግፍ እየጠነከረ መምጣቱን ገልጸዋል። «እኛ የመጣነዉ በጦር መሳሪያ ተዋግተን ነዉ። ከፈለጋቹህ እናንተም እንደኛዉ አደርጉ። እኛ በሞትንበት እናንተ በቀላሉ በምርጫ ሥልጣን መቼም አትይዙም» እያሉ ለዲሞክራሲና ለሕግ የበላይነት ያላቸዉን ንቀት የክልሉ ባለሥልጣናት እየገለጹ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ዳንዔል፣ ሃያ የሚሆኑ የአንድነት ፓርቲ አባላትን ስም ዝርዝር የያዘን ወረቀት በመቱና አካባቢዉ ለሚኖረዉ ሕዝብ በማሰራጨት «እነዚህ ሰዎችን እንዳትቀበሉ። እንዳትሰሟቸው» የሚል ማሳፈራራትም በሕዝቡ ላይ እየደረሰ እንደሆነና የገዚዉ ፓርቲ የክልል አስተዳዳሪዎች ሕገ ወጥ ተግባራት በመፈጸም ላይ እንዳሉ አጋልጠዋል።

በጎፋ ሳወላ እንደዚሁ ለበርካታ ቀናት ታሰረዉ የነበሩና ከተፈቱ ስድት ቀናቸዉ የሆነ፣ እርሳቸዉም አቶ ዳንዕል የሚባሉ የዞኑ የአንድነት ሃላፊ፣ በአካባቢያቸዉ እየተደረገ ያለዉን ግፍና የፖለቲካ ተጽእኖ በሰፊዉ ያብራሩ ሲሆን፣ ያለ ጥፋታቸዉ ከፍርድ ቤት ወረቀት ሳይመጣ በግፍ እንደታሰሩ የገለጹት አቶ ዳንዔል፣ የክልሉ የአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት ለፍርድ ቤት ክስ አቀርቦ በፍርድ ሂደቱ ጊዜ አሳሪ ፖሊሶቹ ስላልተገኑ ሊፈቱ እንደቻሉም አስረድተዋል።

በወዲቲ ወላይታ ዞን ተወካይ ባደረጉት ገለጻ የአንድነት አባላት አንድ ጽ/ቤት ተከራይተዉ ይንቀሳቀሱ በነበረበት ወቅት፣ የክልሉ ባለሥልጣናት ከቢሮ አስወጥተዉ ቤቱን በሌላ ቁልፍ ቆልፈዉባቸዉ እንደሄዱ ያስረዱ ሲሆነ አባላቱ ግን ተስፋ ሳይቆርጡ እንደገና ሌላ ጽ/ቤት እንደነበረ ገልጸዋል። ነገር ግን ሁለተኛ ቢሮዋቸዉ ዉስጥ ሳሉ ወደ 16 የሚሆኑ የገዢዉ ፓርቲ የክልሉ ባለሥልጣናት በጉልበት የኢትዮጵያን ባንዲራ አወርደዉ፣ ሰንደቁንም ነቅለዉ ለሁለተኛ ጊዜ ቢሮዋቸዉን ሊዘጉት እንደቻሉ የሳወላ የአንድነት ተወካይ ይፋ አደርገዋል።

ይህ በማእከልም ሆነ በክልል ደረጃ በአንድነት ፓርቲ እየደረሰ ያለዉ ጫናና ወከባ እጅግ እንዳሳሰባቸዉ የገለጹት የአንድነት አመራር አባላት ገዢዉ ፓርቲ ሕዝቡን ተስፋ አስቆርጦ፣ ራስ ምታት የሆነበትን የሰላማዊ ትግልን ለማጥፋት እየሞከረ እንደሆነ፣ ድርጅቱ ግን በሕዝብ ከመተማመንና ከሰላምዊ ትግል ዉይጭ ሌላ አማራጭ ስለሌለዉ፣ በከተማ፣ በገጠር፣ በአገር ዉስጥና ከአገር ዉጭ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል፣ ህዝብ ደግሞ የማታ ማታ አሸናፊ እንደሚሆን ሙሉ እምነት እንዳላቸዉ አስረድተዋል።

በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት በርካታ ጥያቄዎች ተነስተዉ በበቂ ሁኔታ ምላሽ የተሰጣቸዉ እንደሆነ ለማወቅ ችለናል። ከተጠየቁት ጥያቄዎች አንዱ ምርጫን የተመለከተ ሲሆን የአንድነት ፓርቲ በምርጫ የሚያምን ፓርቲ እንደሆነና ለምርጫ እንደሚዘጋጅ ያስረዱት የአመራር አባላቱ ምርጫዉ ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ከሆነ እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።

አሁን እያየነዉ ያለ አፈናና ወከባ ካልቆመ፣ ነጻና ፍታህዊ ምርጫ ይኖር ዘንድ የሚረዱ ተቋማት ካልተሻሻሉ የአንድነት ፓርቲ የምርጫዉ ተካፋይ እንደማይሆን ከወዲሁ ያስገነዘቡት የአመራር አባላቱ «አንድነት የሚታገለዉ ለኢሕአዴግ የምርጫ አጃቢነት ሚና ለመጫወት አይደለም። ነገር ግን በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ስርዓት እንዲገነባ እንጂ» ሲሉ ምርጫዉን በተመለከተ አንድነት ያለዉን ቁርጥ ያለ አቋም አስቀምጠዋል።

የአንድነት ፓርቲ ያወጣዉን ሙሉ መግለጫም አያይዘን አቅርበናል።

መግለጫውን ከዚህ በታች ያንብቡ!


ከአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አነድነት) የተሠጠ መግለጫ
መንግሥት ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን
እያስከበረና እያስከበረ አይደለም!

መንግሥት ያወጣውን ሕገ-መንግሥት የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት አለበት። ይህንን ኃላፊነቱን ግን በሚገባ እየተወጣ አይደለም። በዚህም ምክንያት የዜጎች መሠረታዊ መብቶች እየተጣሱ ነው።

አነድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ በሕጉ መሠረት ተመዝግቦና የምስክር ወረቀት ተሰጥቶት በሀገር አቀፍ ደረጃ በይፋ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ ነው። ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ቤቶችን ለመክፈት ወደ ክልሎች በአደረጋቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ የተሰጠውን የእውቅና የምስክር ወረቀት ተብብርን ከሚጠይቅ የፓርቲው ደብዳቤ ጋር ለሚመለከታቸው የክልል አካላት ሁሉ አቅርበናል። እያቀረብንም ነው። ሆኖም በተለያየ ደረጃ የሚገኙ አንዳንድ የክልል የመንግሥት ባለሥልጣናት ከምርጫ ቦርድ ለተሰጠው የምስክር ወረቀትም ሆነ ከፓርቲያችን ለተጻፈው የትብብር ደብዳቤ ዋጋ ባለመስጠት ቢሮዎቻችንን በመዝጋት፤ አባሎቻችንን በማሰርና በማስፈራራት ውሎቻቸውን እንዲያፈርሱ ተጽእኖ በማድረግ ዘርፈ ብዙ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን እየፈጸሙ ነው። ይህንንም በማድረጋቸው የፓርቲያችን የመደራጀትና በነጻነት የመንቀሳቀስ ሕገ-መንግሥታዊ መብት እየተጣሰ ነው። ለአብነት ያህል ብቻ፦

በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክላዊ መንግሥት በሳውላ ከተማ አመራሮችን ማሠር፤ በቦዲቲ (በወላይታ ዞን) ጽ/ቤታችንን መዝጋትን፤

በኦሮሚያ ክልል በሀገረ ማሪያም የጽ/ቤቱን ማንዲራ ወስዶ ማበላሸት እንዲሁም በመቱ የጽ/ቤቱን ተጠሪ ለሁለተኛ ጊዜ ማሠርን፤

በአማራ ክልል የደብረ-ማርቆስና ሌሎች ወረዳዎች ጽ/ቤቶች መዝጋትና አመራሮችን ማሠር መጥቀስ ይቻላል።

የድርጅታችን የወጣቶች ጉዳይ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ንዑስ ኮሚቴ አባላትና ደጋፊዎቻቸው የሚሳተፉበት የሥነ-ጽሁፍ ምሽት አዘጋጅተው ጥር 18 ቀን 2001 ዓ.ም. የሚያካሂድ መሆኑን በአዲስ አበባ አስተዳደር ለሚመለከተው አካል በጽሑፍ አሳወቀ። የሚመለከተው ክፍል “በወቅቱ የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ የሚካሄድበት በመሆኑ ፕሮገራማችሁን ከስብሰባው በኋላ ብታካሂዱ” የሚል ሃሳብ በጽሑፍ ስለአስተላለፈልን ሃሳቡን በመቀበልና በማክበር ፕሮግራማችንን አስተላለፍን። ከመሪዎቹ ስብሰባ በኋላ ቀደም ሲል ያቀድነውን ፕሮግራም የካቲት 10 ቀን 2001 ዓ.ም. እንደምናካሂድ የማሰወቂያ ደብዳቤ ቀደም ሲል ለተጠቀሰው የአዲስ አበባ አስተዳደር ክፍል ጥር 29 ቀን 2001 ዓ.ም. አስገባን። ነገር ግን እስከአሁን ድረስ ተገቢው መልስ አልተሰጠንም። ለምን እንዳልተሰጠን ስንጠይቅ የተሰጠን መልስ “የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ውሳኔ አልሰጡበትም” የሚል ነው። በሕጉ መሠረት የማሳወቂያው ሰነድ ከገባ በኋላ በ 12 ሰዓት ውስጥ መልስ ካልተሰጠ የመሳወቂያው ማመልከቻው ተቀባይነት እንዳገኘ ተቆጥሮ የታቀደው ፕሮግራም ሊከናወን ይችላል።

ሆኖም በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ሁለት ችግሮች አሉ። አንደኛው ችግር በ12 ሰዓት ውስጥ ከሚመለከተው አካል መልስ ካልተሰጠ ማመልከቻው ተቀባይነት እንዳገኘ ተቆጥሮ የታቀደውን ፕሮግራም ለማካሄድ ቢሞከር ፖሊስ በቦታው ተገኝቶ “ፈቃድ የላችሁም” በማለት ፕሮገራሙ እንዳይካሄድ ያግዳል። በዚህ መብት ለማስከበር በሚፈጠር ክርክር አላስፈላጊ ግጭት ሊፈጠርና ጉዳት ሊደርስ ይችላል።

በሌላ በኩል የመስብሰበያ አዳራሽ የሚያከራዩ ድርጅቶች ከሚመለከተው የመንግሥት አካል የመሰብሰቢያ “ፈቃድ” ካላመጣችሁ አናከራይም ይላሉ። ለምን ተብለው ሲጠየቁ “ፈቃድ ለሌለው ድርጅት እንዳናከራይ መመሪያ ተሰጥቶናል ይላሉ። መመሪያው ከማን እንደተሰጣቸው፤ በምን መልክ እንደተሰጣቸውና መቼ እንደተሰጣቸው ሲጠየቁ ግን ለመናገር ፈቃደኞች አይደሉም። በዚህ መሀል የታቀደ ጠቃሚ ፕሮግራም ሳይካሄድ ይቀራል። በዚህ መሀል አንድ በሕግ የተቋቋመ የፖለቲካ ድርጅት ለአባላቱና ለደጋፊዎቹ ጠቃሚ ፕሮግራም የማካሄድ መብቱ በአስተዳደራዊ ስልት ይጣሳል። ይህ ድረጊት የሕግ ጥሰትና የአስተዳደር ድክመት ብቻ አይደልም። ከበስተኋላው የአንድነትን እንቅስቃሴ ለመገደብና ከሕዝብ ጋር የመገናኘት እድሉን ለማጥበብ ታቅዶ የሚከናወን የፐለቲካ ተግባር ነው።

የአንድነት ለዴሞከራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ሊቀመንበር ወ/ት ብርቲካን ሚደቅሣ ዳግም መታሰርም በሕግ ጥሰት የታጀበ ነው። እዚህ ላይ አነድ ነገር ግልጽ መሆን አለበት። የኸውም በተደጋጋሚ እንደተገለጸው አንድነት ሕግ የጣሰ ሰው በሕግ መጠየቅ የለበትም የሚል አቋም የለውም። የአንድነት አቋም ግን በህግ የመጠየቅ ሂደቱ ራሱ ሕግን የተከተለ መሆን አለበት የሚል ነው። ከዚህም አቋም በመነሳት ይህች አገር የምትተዳደረው በሕግ ከሆነ የወ/ት ብርቱካን ለዳግም እስራት መዳረግ ሕግን የተከተለ አይደልም የሚል ጽኑ እምነት አለው።

ወ/ት ብርቱካን በመጨረሻ የጽሑፍ ቃላቸው የኢትዮጵያ ሕዝብንና መንግሥትን ይቅርታ ጠይቀዋል። ስለዚህ ይቅርታ አልጠየቁም በሚል ቀደም ሲል የተሰጠ ይቅርታ ያለበቂ ምክንያት ሊነሳ አይገባም። መነሳት ካለበት ደግሞ አነሳሱ ሥርዓት አለው። ይህም ሥርዓት በአዋጅ ቁጥር 395/1996 ተደንግጓል። ወ/ት ብርቱካን ለእስር የተዳረጉበት ሂደት በዚህ አዋጅ ውስጥ የሰፈሩ ድንጋጌዎችን ይጥሳል። ለምሳሌ የአዋጁ አንቀጽ 1 እና 2 ይህን ይደግፋሉ።

ወ/ት ብርቱካን እንደገና የታሰሩበትን ጉዳይ በተመለከተ በጽሑፍ የተሰጣቸው ሠነድ የለም። እስካሁንም የደረሳቸው ሠነድ የለም። ለእድሜ ልክ እስራት መዳረግ ቀላል ጉዳይ ባለመሆኑ ለታሪክ መመዝገብም ስለአለበት የጽሁፍ ሠነድ መኖርን ግድ ይላል። ይቅርታው የተሰጠው ለምን እንደተሰጠ በሚገልጽ ጽሁፍ ነውና ሲነሳም ለምን እንደተነሳ የሚገልጽ ጽሑፍ መሆን አለበት። በሌላ በኩል ይቅር ተባዩ ይቅርታው ለምን እንደሚነሳ በጽሑፍ ከደረሰው በኋላ የአዋጁ አንቀጽ 17 ንዑስ አንቀጽ 2 ከሃያ ቀን ያልበለጠ ጊዜ ይሰጠዋል ይላል። ወ/ት ብርቱካን ይህ መብታቸው አልተከበረላቸውም። ሙሉ ይቅርታ ተደርጎለት ከነሙሉ መብቱ ከእስር የተፈታ ሠላማዊ ዜጋ ያለፍርድ ትእዛዝ እንደማይያዝና ለእስር እንደማዳረግም ሕጉ ይደነግጋል። ወ/ት ብርቱካን ወደ ወህኒ የተወሰዱበት ሁኔታ ግን ከጎዳና ላይ ሰብአዊ መብታቸውን በሚነካ ሁኔታና የመያዣ ትእዛዝ በጽሑፍ ሳይደርሳቸው ነው።

ስለዚህ ቢያንስ በእነዚህ በተጠቀሱት የሕግ ጥሰቶች ምክንያት ቀደም ሲል የተሰጠው ይቅርታ የፀና ሆኖ ወ/ት ብርቱካን ከእስር እንዲፈቱ እንጠይቃለን።
በወ/ት ብርቱካን ጉዳይ ላይ ጠ/ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎች ባለሥልጣኖች በመንግሥት ሚዲያዎች ወደ አንድ ጎን ያጋደለ “ማብራሪያ” ሲሰጡ አስተውለናል። የመንግሥት ሚዲያ የጋራ መሆኑ ታምኖበት እኛም እድሉ ቢሰጠን ለማብራራት፤ ለመከራከር ዝግጁ መሆናችን በዚህ አጋጣሚ ጥሪ እናደርጋለን።

በአሁኑ ጊዜ የማዕከልም ሆነ የክልል ባለሥልጣናት ሕግን በመጣስ የሚያሳዩት ድፍረትና ማንአለብኝነት በዚህች ሀገር የሕግ የበላይነት አለመከበሩን በግል ያሳያል። ምንግሥት በማዕከልም ሆነ በክልል ባለሥልጣናቱ አማካይነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ማንገድ የአንድነትን እንቅስቃሴ ለመገደብ የተቀነባበረ ዘመቻ የሚያካሂድበት ምክንያት ግልጽ ነው።

የ2002 ሀገር አቀፍ ምርጫ እየመጣ ነው። ገዢው ፓርቲ አንድነትንም ሆነ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አዳክሞ ብቸኛ ጠንካራ ፓርቲ ሆኖ ለመውጣትና በምርጫው አሸንፎ የሥልጣን ዘመኑን እንደተለመደው ለማራዘም የፈልጋል የሚል እምነት አለን። ይህንን ግቡን ለማሳካትም የፈለገውን እርምጃ ለመውሰድ ሕግ እንደማይገታው እስካሁን ድረስ የወሰዳቸው የዲሞክራሲና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ማስረጃዎች ናቸው።

አንድነት በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፤ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እውን እንዲሆንና የሕግ የበላይነት እንዲከበር ሠላማዊ ትግሉን አጠናክሮ ቀጥሏል። ይቀጥላልም። በመንግሥት በኩል ግን ከላይ እንዳብራራነው ሕግን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነቱን እየተወጣ ባለመሆኑ ይህንኑ ግዙፍ ኃላፊነቱን በተሟላ ሁኔታ እንዲወጣ አበክረን እንጠይቃለን።


አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
የካቲት 19 ቀን 2001 ዓ.ም
አዲስ አበባ

 1. ዓቢይ
  | #1

  ቁርጥን በጊዜ ማወቅና ማሳወቅንም የመሰለ ነገር የለም. ቁርጥን ማወቅ ጊዜ መፍጀት አልነበረበትም.
  ቡርቱካንን ያለ ምክንያት ያሰረ ወያኔ,ከቁልቁለቱ ላይ የሚያግደው ነገር የለም.እቅጩን ለህዝብ አሳውቆት ግሉን በሌላ መልክ መጀመሩ አማራጭ የለውም.እንደጨነቀው ዱቄት ከነፋስ መጠጋቱ ምበፍጹም አያዋጣም. እነመለስን ለማወቅ ጊዜ ሊፈጅብን አይገባም.በጊዜ ራሳችሁን እወቁ…

 2. እንግዳ
  | #2

  አንድነት ፓርቲ ከወዲሁ የኢህአዲግን ለፍትሐዊ ምርጫ ያለውን ዝግጁነት ማረጋገጥ አለበት:: አሁን ያለንበት ዓለም በሕገ ወጥና በተጭበረበረ ምርጫ የሚመጡ መንግስታትን የማይቀበልና የሚያወግዝ እንደሆነ ኢሕአዲግ ጠንቅቆ ያውቃል:: ስለዚህ ለይስሙላም ቢሆን ምርጫ ማካሄዱ አይቀርም:: ወያኔ ግን በአደባባይ ያለ እኔ ኢትዮጵያን ማንም አይመራም ሲል እንደነበረ ይታወቃል:: ሕዝብ ደግሞ በነጻነት የመምረጥ ዕድል ከተሰጠው ኢሕአዲግ አንድም ድምፅ እንደማያገኝ ያውቃል:: ስለዚህ በምርጫ እንሳተፋለን የሚሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አስተማማኝ የሆነ የምርጫ ሁኔታዎች መመቻቸቱን ከወዲሁ ማረጋገጥ ይገባቸዋል:: ካልሆን ግን እንዲሁ የወያኔ አምባገነን አገዛዝ አዳማቂ ከመሆን አያልፉም:: ፍትሐዊና ትክክለኛ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል የሚባለው ደግሞ ማንም በሕዝብ ያልተመረጠ አካል ግልፅ በሆነና ራሱን በወንጀል ካላጨማለቀ በስተቀር ምርጫውን የማያጭበረብርበት ሁኔታ ሲመቻች ብቻ ነው:: በዚህ በኩል የ1997 ምርጫ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል:: የወያኔ የዲሞክራሲ ካባ የተገፈፈው: መጠነኛም ቢሆን ለትክክለኛ ምርጫ የሚሆኑ ሁኔታዎች ተፈጥረው ሰለነበር ነው:: ይህንን ምርጫ ለማጭበርበር ወያኔ ከፍተኛ የሆነ ውርደትና ቅሌት ውስጥ ገብትዋል: ብዙ ወንጀል ፈፅሞአል: ለዲሞክራሲ ቆሜአለሁ የሚለውንም ውሸት በግልፅ እንዲታወቅ ሆኖአል::

  ስለዚህ ተቃዋሚዎች ከወዲሁ የፍትሀዊ ምርጫ ሁኔታዎች መኖራቸውን የሚያረጋግጥ ሁኔታ እንዲኖር ያሚያስችል ዋስትና ፍጠሩ: ካልሆነም በግልፅ እንደማትሳተፉ አሳውቁ::

አስተያየት መስጫው ተዘግቷል።