ኢትዮጵያዊነትና አርበኝነት (ቅዱስ ሃብት በላቸው ከአድላይድ/ደቡብ አውስትራሊያ)
ስፍራው አዲስ አበባ፣ ዘመኑ 1931 ፋሺሽት ኢጣሊያ አገራችንን በሃይል በተቆጣጠረበት ወቅት ነው። አንድ ቀን የወራሪው ጦር አዛዥ የነበረው ማርሻል ባዶሊዮ ግራዚያኒ ሕዝቡን ለማታለልና ለመስበክ “በንጉሳችሁም ሆነ በኢጣሊያ ዘመን የተሰጣችሁ የክብር ልብስ ካለ ለብሳችሁ፤ የተሸለማችሁት ኒሻን ካለም ይህንኑ አድርጋችሁ ነገ ማለዳ ላይ ታላቁ ቤተ መንግስት እንድትሰበሰቡ!” ሲል አዲስ አበባ ውስጥ በራዲዮና በጥሩምባ ያስለፍፋል።
ይህንኑ ተከትሎም በሕይወት ዘመናቸው ከ21 በላይ ልዩ ልዩ መፅሃፍትን ፅፈው ያሳተሙት ስመ-ጥሩው ኢትዮጵያዊ ሊቅ ብላቴን ጌታ ሕሩይ ወልደ-ስላሴ፣ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ሁለት ሜትር ቁመት በአንድ ሜትር ወርድ አጋጥመውና ጃኖ አጣፍተው በመልበስ፣ በላዩ ላይ ካባ፣ ላንቃና ጎፈር ደርበውና አሸብርቀው የፋሺሽቱ ወራሪ ጦር ያስቀደደለትን ልብስ ደርቦ ከሚግተለተለው የባንዳ መኳንንትና ሰራዊት ጋር እየተጋፉ ሰተት ብለው ከቤተ መንግስቱ ቅጥር ግቢ ይዘልቃሉ። በዚህም የተገረመው መኳንንቱ፣ የኢጣሊያ ሶልዳቶና ባንዳ ሁሉ ትኩር ብሎ ሲያያቸው ቆይቶ፣ ኋላ ላይ ማርሻል ግራዚያኒ አይንም ይገባሉ። በዚህ ድርጊታቸውም የተበሳጨው ግራዚያኒም አስጠርቶ አጠገቡ ያስመጣቸውና በብስጭት “ይህ የለበስከው ጨርቅ ምንድነው!” ሲል ያፈጥባቸዋል። እርሳቸውም ምንም የፍርሃት ስሜት ሳይታይባቸውና ሳይርበተበቱ “ምነው ትናንት የክብር ልብሳችሁን ለብሳችሁ እንድትመጡ አልተባለም እንዴ? … እኔ ያለኝ የክብር ልብስ ይህ ስለሆነ ነው ለብሼ የመጣሁት” ሲሉ በድፍረት እንደመለሱለት ታሪክ ይነግረናል።
አዎን! እኛ ኢትዮጵያውያን ሰንደቅ አላማችን ክብራችን፣ የፍቅርና የአንድነታችን መገለጫችን፣ የነፃነትና የሕብረብሔራዊነታችን ምልክታችን፣ በደስታችንም ሆነ በሃዘናችን ጊዜ ከማንኛውም ነገር በላይ ማጌጫና ማሸብረቂያችን ነው። ሰርግና ምላሻችን`፣ ድግስና ጣጣችን፣ ሃይማኖታዊም ሆኑ ሕዝባዊ በዓላቶቻችን፣ በሰንደቅ አላማችን ተውበው እንደሚደምቁት ሁሉ፣ በኢትዮጵያዊነቱ ጎልቶ የሚታወቅ ሰው የዚህ አለም ጣጣውን ጨርሶ ሲሰናበት አስከሬኑ ወደ መቃብሩ የሚሸኘው በዝችው በሰንደቅ አላማችን ተሸፍኖ ነው። ምንም እንኳን ይቺ የሁላችን መገለጫ የሆነችው ሰንደቅ ዓላማችን በዓዋጅ ብሄራዊ መለያችን ሆና የፀደቀችው በአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ቢሆንም፣ ከዚያ በፊትም የነበሩት ቀደምት ኢትዮጵያውያን አባት እናቶቻችን መለያቸው አድርገው ይጠቀሙባት እንደነበር ታሪክ ይነግረናል። እኔ በበኩሌ ይቺን ከኢትዮጵያዊነታችን ጋር አብራ በልባችን የታተመች ሰንደቅ ዓላማችንን አይደለም፤ ሌላም በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሕብረ ቀለማት የተሰራ ቁሳቁስ አይኔ ሲገባ ነፍሴ በሃሴት ይሞላል። ይህን ስሜት ደግሞ በሚልዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንደሚጋሩኝ አምናለሁ። እስከማውቀው ድረስ በዓለም ላይ የሚኖሩ ጥቁር ሕዝቦች ሳይቀር እንደ ነፃነት ዓርማቸው በመውሰድ በመለያነት የሚመርጧትን ይቺን ክቡሯን ሰንደቅ ዓላማችንን ባደባባይ “ጨርቅ!” ሲል ያንቋሸሸና ያዋረደ ብቸኛው የአገራችን ርዕሰ ብሔር፤ ብሎም ኢትዮጵያዊም መለስ ዜናዊ ብቻ ነው።
መለስ ዜናዊ መሰረታዊው የኢትዮጵያዊነት ጥላቻው መንስዔ እስከዛሬ ለብዙዎቻችን እንቆቅልሽ ሆኖ ያለ ነገር ነው። ስለዚህ ነገር ሲነሳ ብዙ ጊዜ የሚወሳው የቀደሙት አባቶቹ ከጠላት ጋር ወግነው አገራችንን የወጉበት አሳፋሪ ታሪክ ብቻ ነው። ይህ ግለሰብ እንደ አብዛኞቻችን እንኳን በችግር ተወልዶ በችግር ያደገ ሰው እንኳን አይደለም። ይቺ አገር ከማንኛችንም የበለጠ አቅፋና ተንከባክባ አስተምራዋለች፤ አሳድጋዋለች። እርሱ ግን በተቃራኒው የህይወቱን አብዛኛውን ዕድሜ ያሳለፈው ኢትዮጵያዊነትን እና ኢትዮጵያን ለመናድ ሲያሴርና ሲያደባ እንደሆነ የምናውቀውና በገሃድ እያየነው ያለ ሃቅ ነው። ለኤርትራ ከእናት አገሯ ለመገንጥሏ ዋነኛውን ሚና የተጫወተ ፤ አጼ ቴዎድሮስ የተወለዱበትን፣ አጼ ዮሃንስ አንገታቸውን የሰጡለትን የአገራችንን ለም መሬት ቆርሶ ለሱዳን አሳልፎ የሰጠ፤ ኢትዮጵያውያን ገበሬዎችን ከመሬታቸውና ከርስታቸው በማፈናቀል መሬታቸውን ለውጭ አገር ባለሃብቶች በርካሽ ዋጋ በመቸብቸብ በገዛ አገራቸው ለስቃይና ለባርነት የዳረገ ሰው ነው። ይህ ግለሰብ ሌላው ቀርቶ የአገሪቷ ከፍተኛ የስልጣን ወንበር ላይ ከተቀመጠ በኋላ እንኳን አንዱን ዘር በወርቅ ሌላውን በጨርቅ እያስመሰለ የብዙሃንን ስሜት የሚጎዳ ንግግር በማድረግ፤ መላ ኢትዮጵያን በቋንቋ ሸንሽኖ በማካለል አንዱ በሌላው ላይ የሚነሳሳበትና የሚጋጭበት እሳት ከመለኮስ የታቀበበት ጊዜ የለም። ይህ ሁሉ ቢሆንም ታዲያ የአራት ኪሎው ቤተ መንግስት እስኪዘልቅ ድረስ አንገቱ ላይ አጥልቆት ከነበረው የሕወሓት ክታብ ውስጥ ኤርትራን ከኢትዮጵያ የማስገንጠል እቅዱን ከግብ ቢያደርስም፣ ከወሎና ከጎንደር ግዛቶች ቆርሶ ወደ ትግራይ ክልል የጨመራቸውን ለም የእርሻ መሬቶች ይዞ “ትግራይ ትግሪኝ” የተሰኘች አገር የመመስረት ሕልሙን ግን ላለፉት 21 ዓመታት እንኳን ዕውን ማድረግ አልቻለም። ይህም ሊሳካለት ያልቻለው እኛ ኢትይጵያዊያን አንዳችን ከአንዳችን እንደድር የተወሳሰብንና የተሳሰርን በመሆናችን፤ ብሎም በክርስትናም ሆነ በእስልምና ዕምነት ታላቅ ስፍራ የሚሰጣት እናት አገራችን እንዳትፈርስ የብዙሃኑን ፀሎትና ልመና የሚያደምጠው የአምላክ ጥበቃም ስላልተለያት ነው ብዬ አምናለሁ።
ለዚህም ይመስላል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመለስ ዜናዊ የሚመራው ስርዓት በመጠኑ ስልቱን ቀይሮ ለይምሰልም ቢሆን የኢትዮጵያዊነትን ካባ ደርቦ መንቀሳቀስ ጀምሯል። “የሰንደቅ ዓላማ ቀን” ተብሎ በመሰየም መከበር የጀመረው ቀንም ከታወቁ አዳዲስ ማደናገሪያዎቹ አንዱ ነው። ይህ ዕለት ሰንደቅ ዓላማችን የምትከበርበት፣ ብሎም ለዝች ሰንደቅ ዓላማ ክብር ሲሉ ሕይወታቸውን ሳይቀር በጀግንነት አሳልፈው የሰጡ ሕያው ጀግኖቻችን እየተወሱ የሚወደሱበት ሳይሆን፣ በተቃራኒው ሕዝቡ እስከዛሬ ከሚያውቃትና ትክክለኛ መለያው እንደሆነች ከሚያምንባት አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለም ብቻ ካላት ሰንደቅ ዓላማችን ጋር ለዘመናት ያለውን የተሳሰረ ቁርኝት ለመበጠስ ታልመው የተዘጋጁ የሚመስሉ እጅግ አስፈሪና አሳሪ ሕገ-ደንቦች ተዘጋጅቶለት ለተግባራዊነቱ ልዩ እንቅስቃሴ የሚደረግበት ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ወያኔ የለጠፈበት የሰይጣን አምላኪዎች መለያ ምልክት የሆነው ኮከብ ያልተቀመጠበት የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ በሰርግ ስነስርዓት፣ በግለሰቦች ዝግጅት ላይ፣ በሃይማኖታዊም ሆነ በሕዝባዊ በዓላት ላይ ይዞ መገኘት እራሱ ከሶስት ዓመት በላይ በእስር የሚያስቀጣ ታላቅ ወንጀል ሆኖ ተደንግጓል። (“ሰይጣኒዝም” እ.ኤ.አ በ1966 በአሜሪካዊው ሃዋርድ አንቶን ሳንዶዘር ሌቪይ ሳንፍራንሲስኮ ላይ የተመሰረተና በምዕራቡ ዓለም ቀላል ቁጥር የሌላቸው ተከታዮች ያፈራ እምነት ሲሆን ወያኔ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ላይ እንዲቀመጥ ያደረገው አርማ ደግሞ፤ ክርስቲያኖች መስቀል፤ ሙስሊሞች ደግሞ ኮኮብና ጨረቃን በመለያነት እንደሚጠቀሙ ሁሉ፤ ሰይጣን አምላኪዎችም ለራሳቸው ያወጡትንና ብቸኛ መለያቸውን ነው ወያኔ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ላይ ያስቀመጠው) አምባ-ገነን የተባለው ደርግ እንኳን በስልጣን ዘመኑ በዝችው በፈረደባት ሰንደቅ ዓላማችን ላይ የራሱን አርማ በማዘጋጀት ለጥፎባት የነበር ቢሆንም “ይህ ዓርማ የሌለበት ሰንደቅ አላማ ከያዛችሁ ወየውላችሁ!” የሚል ማስፈራሪያ ሲወጣው አልሰማንም ነበር። እንዲያውም ከመንግስታዊ ተቋማት ስር ከሚንጠለጠሉት በስተቀር በአብዛኛው ማህበረሰቡ ይጠቀም የነበረው ትክክለኛውንና አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ያለውን ሰንደቅ ዓላማ ብቻ እንደነበር አንዘነጋውም።
ይህ ብቻም አይደለም፣ የወያኔው ስርዓት የኢትዮጵያዊነት መገለጫ የሆኑ ቅርሶቻችንን ለዘመናት ጠብቀው ያቆዩንን የእምነት ተቋማቶቻችንን ለመዝረፍና ለመናድ በየቦታው ባስቀመጣቸው ወኪሎቹ አማካኝነት ሳይታክት ይሰራል። በቅርቡ እጄ ገብቶ ያየሁት “የምሽቱ ፍፃሜ” የተሰኘው የአማርኛ ፊልም ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያለውና መንግስት ወይንም ወንጀል የመከላከልና ሕግ የማስከበር ሃላፊነት ያለበት ፖሊስ ሳይሆን ሕብረተሰቡ በራሱ አነሳሽነት የአገሩን ቅርሶች እየጠበቀና ለዚህም ብዙ መስዋዕትነት እየከፈለ እንደሚገኝ፤ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ሆኖ አግኝቼዋለሁና በዚህ አጋጣሚ ለዚህ ፊልም አዘጋጆች ያለኝን አድናቆትና አክብሮት ሳልገልጽ ማለፉ አግባብ አልመሰለኝም። በፊልሙ ላይ በተገላቢጦሽ የአገራችን የፖሊስ ባለስልጣናት ተደራጅተው ቅርሳችንን ከሚጠብቀው ሰው ቀምተው ለመሸጥ ሲያደቡና ወንጀል ሲፈፅሙ ይታያል።
ወደ ምኖርበት አገር ልውሰዳችሁና የስደት ቤቴ የደቡብ አውስትራሊያዋ ዋና ከተማ አድላይድ በዓለም ላይ ለሰው ልጅ መኖሪያነት ተስማሚ ናቸው ተብለው ደረጃ ከወጣላቸው ከተሞች ከመጀመሪያዎቹ ተርታ የተመደበች ናት። ታዲያ ቀስ በቀስ እየተሸረሸረ መጥቶ አሁን አብዛኛው የአገሪቱ ተወላጅ ምንም አይነት ዕምነት የሌለውና ወደ እምነት ተቋማት መሄድ የማያዘወትር ቢሆንም ቀደምት አውስትራሊያውያን የገነቧቸው በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ግን እስካሁን በከተማው እምብርት ላይ ሳይቀር ቆመው ይታያሉ። ምንም እንኳን እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት እድሜያቸው ከ150 ዓመት ያልበለጠና አንዳንዶቹም ምንም አይነት አገልግሎት የማይሰጥባቸው ቢሆንም እንደ አገሪቱ ቅርስ ተወስደው ባሉበት ሁኔታ እየታደሱ ይቆያሉ እንጂ ባለቤቱ ግለሰብ ቢሆን እንኳን የኔ ነው ብሎ የማፍረስ መብት የለውም። በዚህም የተነሳ ቀድሞ የነበረው ውስጣዊ ይዘቱ ተቀይሮ ከቤተክርስቲያንነት ወደ ምሽት ክበብነት የተቀየረ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን እንዳለ ሁሉ አውቃለሁ።
የኛ አገሩ ነገር ግን ከዚህ በጣም የተለየ ነው፤ ጩኸቱ የቁራ ጩኸት ሆኖ ቀረ እንጂ ወዳጄና አጋሬ እውቁ የስነ-ፅሁፍ ሰው ፀሃፌ ተውኔት ጋሼ አያልነሕ ሙላት እኔ ያገለገልኩባቸውን ጨምሮ በተለያዩ የነፃ ፕሬስ ልሳኖችም ሆነ መድረኮች ላይ፣ የክብ ቅርጽ ያለውን ጥንታዊ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ-ክርስቲያናትን የሕንፃ ጥበብ እንዳለ ለማሳደግ ከመሞከር ይልቅ፣ በዘመናዊነት ስም ያንን እያፈረሱ በፈረንጆቹ ካቴድራል መልክ እንዲታነፁ ለማድረግ በተጠናከረ መልኩ እየተካሄደ ያለውን ዘመቻ አጥብቆ ሲቃወምና ሲተች እንደነበር አስታውሳለሁ። ይህንን ጉዳይ አሁንም ቢሆን በተለይም የዚያች ቤተክርስቲያን ልጆች ነን የምንልን ሁሉ ሊያሳስበን የሚገባ ታላቅ ጉዳይ ነውና፤ የሃይማኖት አባቶች፣ ለቤተክርስትያኗ ተቆርቋሪ ነን የሚሉ ማሕበራት፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና ምዕመናን ትኩረት ሰጥተው ከወዲሁ ማቆሚያ ለማበጀት በጋራ መንቀሳቀስ የምንችልበት መድረክ ያመቻቹልን ዘንድ አቅሙ ላላቸው ሁሉ በዚህ አጋጣሚ ድምጼን ማሰማት እሻለሁ።
በቅርቡ ከ1ሺህ ዓመት በላይ ያስቆጠረውን የዋልድባን ገዳም አፍርሶ ወደ ሸንኮራ አገዳ እርሻነት ለመቀየር በቅርቡ የተጀመረው እንቅስቃሴም አገሪቷን ቅርስ አልባ ለማድረግ ከተወጠኑት የወያኔ ሰይጣናዊ ተልዕኮዎች አንዱ አድርጌ የምወስደው ነው፡፡ ይህንን እቅድ ጊዜ ሳንሰጥ ተረባርበን ማስቆም ካልቻልን፣ ዛሬ ዋልድባን አፍርሼ ሸንኮራ ካልተከልኩ ሞቼ እገኛለሁ እያለ የሚፎክረው የወያኔው ስርዓት ነገ የቅዱስ ላሊበላ፣ የአክሱም ፅዪን፣ የግሸን ደርበ ከርቤ ማርያምንም ሆነ ሌሎች ጥንታዊና ታሪካዊ ገዳማትንና አድባራትን ደርምሼ ሌላ ነገር አደርጋለሁ ብሎ ላለመነሳቱ ምንም ማስተማመኛ የለንም።
ካነሳሁት ዘንዳ፦ሁላችንም እንደምናውቀው በዘመነ ወያኔ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ይህን አለም ንቀው፣ ዘላለማዊውን ዓለም በመመኘት በገዳም ተወስነው በፀሎት የሚተጉ በርካታ መነኮሳት የተጠለሉባቸው ገዳማትና አድባራት ሆን ተብሎ በሚመስል መልኩ በእሳት ሲጨረጨሩ፣ መነኮሳቱም በየጊዜው ጊዜና ወቅት ጠብቀው በሚነሱ ዘረኞችና አረማውያን ሲጨፈጨፉ አይተናል። ለዚህም በተለያየ ስፍራና ጊዜ ለፈሰሰው የሰማዕታት ደም የዜጎችን ደህንነትና መብት ለማስከበር እራሱ አርቅቆ ባፀደቀው ሕገመንግስት ሃላፊነቱን የተሸከመው የመለስ ዜናዊ ስርዓት፣ ሌላው ቀርቶ ከድርጊቱ ፈፃሚዎች መካከል አንድም ሰው ይዞ ለፍርድ በማቅረብ ቅጣቱን እንዲቀበል ሲያደርግ አላየንም። እንዲያውም ይህን መሰል ተደጋጋሚ ጥቃቶች መንግስት በሚቆጣጠራቸው የመገናኛ ብዙሃን ለሕዝብ እንዳይተላለፉ ስለሚደረግ፤ ቢተላለፉም ሃቁ እጅግ በተዛባ መልኩ መሆኑን ደጋመን ስላላየን እነዚህ የጥፋት ሃይሎች ከጀርባቸው አይዞህ ባይ እና የአረመኔው የመለስ ዜናዊ አስተዳደር ድጋፍ እንዳላቸው እኔን ብቻ ሳይሆን ብዙዎችን ወደ ሃቅ የሚያስጠጋን እውነታ ነው።
የመለስ ዜናዊ ስርዓት በተለይም ተከባብረውና ተቻችለው ለዘመናት በዘለቁት የክርስትናና የእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል ግጭት ለመፍጠር ከመጣር የተቆጠበበት ጊዜ የለም። የከነዚህም ስልቶቹ አንዱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ለጥምቀት በዓል ታቦት የሚያድርበትን የተለመደ ይዞታ፤ ወይንም ፀበል የፈለቀበት ስፍራ መርጦ የእስልምና ዕምነት ተከታዮች በቦታው ላይ መስጊድ ወይም ሌላ ነገር እንዲሰሩበት ፈቃድ መስጠት ነው። ምሳሌ መጥቀስ ካስፈለገ በአዲስ አበባዋ የአየር ጤና ኪዳነ ምሕረትን እና የጎንደሩን የቅዱስ ገብርዔል አብያተ ክርስቲያናት ለጥምቀት በዓል ታቦተ ሕጉ የሚያድርበት ስፍራ ለመስጊድ ግንባታ በመስጠት፤ እንዲሁም የጎንደሩን የቅድስት ድንግል ማርያም ቤተክርስቲያን የታቦት ማደሪያ ስፍራ የእስልምና እምነት ተከታዮች ቁርዓን ማስተማሪያ ት/ቤት እንዲገነቡ አሳልፎ በመሰጠቱ የተነሳ ተቻችሎ ይኖር የነበረው ሕብረተሰም ከመቃቃር አልፎ በተፈጠሩት ግጭቶች የሰው ሕይወት ሁሉ መቀጠፉን አስታውሳለሁ። ይህ ደግሞ እኔ ይህን ፅሁፍ ስጫጭር ያስታወስኩት ስለሆነ እንጂ እንዲህ አይነት ችግር የደረሰባቸው አብያተ ክርስቲያናት ቁጥራቸው በርካታ መሆኑን አንባቢ እንዲገነዘብልኝ እሻለሁ።
እኛ ኢትዮጵያውያን ከቀድሞ ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ ከመጣው ታሪካችን እንደምንረዳው በሌላው ዓለም ባልተለመደ መልኩ፣ ክርስቲያኖቹ አብያተ ክርስቲያናት ሲገነቡ ባካባቢው የሚኖሩ ሙስሊሞች ድጋፍ እንደሚያደርጉት ሁሉ ሙስሊሞቹም መስጊድ ሲያንፁም የክርስቲያኖቹ ድጋፍ አይለያቸውም። የቅርብ ጊዜውን እንደምሳሌ ብጠቅስ እንኳን አርሲ ውስጥ ሻርካ በተሰኘው አካባቢ የታነፀውና ግንቦት 21 ቀን 1998 ዓ.ም ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የቅድስት ስላሴ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ሲሰራ የአካባቢው የገበሬ ማሕበር ሊቀመንበር በሆኑት የእስልምና እምነት ተከታዮ አቶ ማማ ሁሴን በራሳቸው አነሳሽነት የአካባቢውን ሙስሊሞች በማስተባበር ገንዘብ ከማሰባሰባቸውም በተጨማሪ፣ ይህንን ቤተክርስቲያን ለማሰራት በተቋቋመው ኮሚቴ ውስጥም እርሳቸውን ጨምሮ ስድስቱ ሰዎች የእስልምና ዕምነት ተከታዮች ነበሩ። በዚህ ብቻ ሳይሆን ትክክለኛው ኢትዮጵያዊነት፣ ዘር፣ ሃይማኖት፣ የማይገድበውና በእውነተኛ ፍቅር ላይ ብቻ ተመስርቶ የተገነባ ሕያውና ዘላለማዊ ሃውልት መሆኑን ደግሞ ከሰሞኑ የካናዳ/ቶሮንቶው ኢትዮጵያዊ አባት ሃጂ ሞሃመድ ሰኢድ አጥንት የሚያለመልም ንግግር ያስተዋልን ይመስለኛል።
በተለያየ ወቅት አገራችንን በድፍረት ለወረረው ለኢጣሊያ ጦር ወግነው አገራቸውንና ወገናቸውን ከወጉት ዋነኛ ባንዳዎች ዘር የሚመዘዝ የዘር ሃረግ ያለው መለስ ዜናዊ ለአገራቸው አንድነትና ድንበር መከበር አኩሪ መስዋዕትነት ከፍለው ላለፉ ሰማዕታት በሚዘጋጁ ስነ-ስርዓቶችና የድል በዓሎች ላይ ባለመገኘት አስፈላጊውን ክብር በመንፈግ ይታወቃል። እንደ አዲስ እንዲቀረጽ ባደረገው የትምህርት ፖሊሲ መሰረትም ታትመው የሚወጡት የመማሪያ መፅሃፍት ላይ ለአገራቸው ሲሉ አኩሪ መስዋዕትነት ከፍለው ያለፉ ዘላለማዊ ጀግኖቻችን የህይወት ታሪክ እንዳይሰፍርበት አድርጎ ትውልዱ ስለቀደምት አባት እናቶቹ ተጋድሎ ያለው ግንዛቤ አናሳ እንዲሆን ይሞክራል። ሌላው ቀርቶ የመቶ ብር ኖት ላይ የነበረው የአርበኛ ምስል እንዲነሳ በማድረግ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ለከፈሉት መስዋዕትነት ያለውን ንቀትና የጥላቻ ስሜት በግልጽ እያሳየ ያለ ሰው ነው። የዘመነ- ደርግ ልጅ ነኝና ገና የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ መፃሃፍቶቻችን ላይ የነበሩት የነሌ/ኮል አብዲሳ አጋ እና መሰል ጀግኖች ገድል እስከዛሬ ድረስ በውስጤ ታትመው የቀሩ ብቻ ሳይሆኑ ኢትዮጵያዊነት በምንም ነገር የማይለወጥ ክብር ያለው የማንነት መገለጫ መሆኑን የተረዳሁባቸው፤ ብሎም ዛሬም በባዕድ አገር በሌሎች ሕዝቦች መካከል ሆኜ በኩራት አንገቴን ቀና አድርጌ ለመራመድ ያስቻሉኝ የሞራል መጠገኛዬ ናቸው።
መቼስ “የኢሕአዴግን ፖሊሲ እስከደገፈ ድረስ መሃይምም ቢሆን እንሾመዋለን” ብሎ በድፍረት የነገረን መለስ ዜናዊ በመንግስታዊ ተቋማትና ድርጅቶች ውስጥ ብቻ ሳይሆን፣ በሲቪክ ተቋማት ውስጥም ጥቅሙን የሚያስከብሩለት ወኪሎቹን በሃላፊነት ማስቀመጡ የተለመደ ነው። ከነዚህም የይምሰል ሹመኞች መካከል ከ1928 -1933 ዓ.ም ከፋሺሽት ኢጣሊያ ወራሪ ጦር ጋር ተፋልመው ጠላትን ድል በማድረግ ባባረሩ አርበኞች በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት የተመሰረተው “የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር” ፕሬዚዳንት አስታጥቄ አባተ (ሊቀ ትጉሃን) ይገኝበታል። ይህ ግለሰብ በአርበኞች ስም በየአደባባዮ የወያኔን ፖሊሲና እቅድ ደግፎ ከማቅራራትና ከማላዘን በተጨማሪ በፕ/ር ኤፍሬም የሚመራውና ወያኔ ያደራጀው “የአገር ሽማግሌዎች” አባል በመሆን በየጊዜው የሚሰተውን ተልዕኮ ለማስፈፀም የሚዳክር አጭበርባሪ ነው። ያለፈውን እንተወውና ይኸው ግለሰብ ከቀናት በፊት የድል በዓል ሲከበር (ሚያዝያ 27 ቀን) ከመሰል አሻንጉሊቱ አባዱላ ገመዳ ጋር ተገኝቶ ባደረገው ንግግር “… “ድሉን ያገኘነው ታሪካዊ መስዋዕትነት ከፍለን ነው!” በማለት ባልዋለበት ውሎ ለመመፃደቅ መሞከሩን ከአንድ የወያኔ ልሳን ላይ እንዳነበብኩ የዚህ ሰውዬ እንዲህ ይሉኝታ እንኳን እያጣ መምጣት ዛሬ ስለርሱ የማውቀውን እውነታ እንድተነፍስ አስገድዶኛል።
አስታጥቄ አባተ ትውልዱም ሆነ እድገቱ ጎንደር ነው። ይህ ግለሰብ ከ1928 ዓ.ም እስከ 1933 ዓ.ም በዘለቀውና 71 ዓመታት ባስቆጠረው ቀደምት አባት እናቶቻችን የፋሺሽቱን ጦር በዱር በገደሉ እያሳደዱ አኩሪ ገድል በፈፀሙበት የአርበኝነት ዘመን ተገኝቶ የድርሻውን መወጣት አይደለም፣ በዚያን ጊዜ ያልተወለደና እድሜውም ለዚያ የማያበቃው ትንሽና ተራ ሰው ነው። ይህንን ደግሞ በቀላሉ ሰውዬውን በአካል የሚያውቀውም ሰው የሚመሰክረው ሃቅ ነው።
መጀመሪያ ከጎንደር ወደ አዲስ አበባ ስራ ፍለጋ የመጣው አቶ አስታጥቄ አባተ ዛሬ ባማረ መኪና የሚንፈላሰስባትን የሸገርን ህይወት “ሃ!” ብሎ የጀመረው የደብረ ፅጌ ቅዱስ ኡራዔል ቤተክርስቲያን አቅራቢያ ይኖሩ በነበሩትና ባካባቢው ታዋቂ በሆኑት “ወ/ሮ የሺወርቅ” የተሰኙ እናት (የአባታቸው ስም ተዘነጋኝ) በዘበኝነት ቀጥረውትና አስተግጠውት ነበር። ሆኖም በዚህ መልኩ ብዙም ሳይቆይ ቀልጣፋው አስታጥቄ መጀመሪያ የከፍተኛ 15 ቀበሌ 36 አብዮት ጠባቂ፣ ከዚያም ቀስ ብሎ የፍርድ ሸንጎ፤ እንዲሁም የአካባቢው የዘመቻ ጥምር ኮሚቴ እና ጎርፍ አስወጋጅ ኮሚቴ ውስጥ ተሹሞ ደርግን አገልግሏል። በዚህ ጊዜም “መስፍን” ተብሎ ለሚጠራና ጥቁር ኣንበሳ ሆስፒታል ውስጥ በአስተዳደር ስራ ተሰማርቶ ያገለግል ለነበረ ሰው ያለአግባብ በአካባቢው የቤት መስሪያ ቦታ እንዲሰጠው በማድረጉ ሰውዬው ይህንን እንደ ውለታ በመቁጠር የሚሰራበት ሆስፒታል ውስጥ በምግብ (ወጥ) ቤት ሰራተኝነት እንዲቀጠር አደረገው። በዚህ መልኩ ኑሮውን እያደላደለ የመጣው አስታጥቄ ጠቅላላ ቤተሰቡን ከጎንደር በማምጣት ኑሮውን አዲስ አበባ ላይ ዳግም መመስረት ብቻ ሳይሆን፤ ወያኔ ለስልጣን እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ቀስ በቀስ ባለቤቱን የሸዋ ክ/ሓገር ጤና ቢሮ (አሁን ኦሮሚያ ቢሮ) ጽዳት ሰራተኛነት፤ አንድ ወንድ ልጁን በሞተረኛነት (ፖስተኛ)፣ ሴት ልጁን ደግሞ ቦርቸሌ ውስጥ ካርድ ክፍል ውስጥ ማስቀጠር ችሏል። ይህ ብቻ ሳይሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ እርሱም ቢሆን በዚሁ ግለሰብ አማካኝነት ከሚንስ ቤት ሰራተኛነት የሸዋ ክ/ሓገር ጤና ቢሮ የግምጃ ቤት ሰራተኝነት ዕድገት ማግኘት ችሎ ነበር። በወቅቱም ከተለያዩ ሰዎች ጋር በመሳጠር የመንግስት ንብረቶችን እያወጡ በመሸጥ ለግል ጥቅሙ ያውል እንደነበር በወቅቱ በቅርበት የሚያውቁት ሰዎች ሲናገሩ ማድመጤን አስታውሳለሁ። የለመደ እጅ አያርፍምና ይህን ፅሁፍ በማዘጋጅበት ወቅትም ይህ ግለሰብ ከአጋሮቹ ጋር በመሆን የአርበኞች ማሕበሩን ገንዘብና ንብረት እየመዘበረ እንደሆነ በመግለጽ የማህበሩን ም/ሊቀመንበር ጨምሮ ሌሎች አባላት ጩኸታቸውን ማሰማት መጀመራቸውን ከቀናት በፊት ሰምቻለሁ።
አብዮት ጠባቂው አስታጥቄ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ሊቀመንበር ተብሎ የሹመት መና ሲወርድለት ምንም አይነት ማዕረግ የሌለው ሰው መሆኑ ደግሞ እዚያ ቦታ ላይ ቀድሞ ከተቀመጡት ስመጥር አርበኞች ጋር የሚለየውና የሚያሳንሰው ሆኖ ተገኘ። ስለዚህም በአባ ጳውሎስ ጋሻ ጃግሬ ታደሰ ውቤ አማካኝነት ስሙ ሌጣውን እንዳይጠራ በሚል ባልዋለበት “ሊቀ ትጉሃን” ተብሎ የቤተክሕነት ማዕረግና ካባ ሊደረብለት በቅቷል። ይህ ቤተክርስቲያንን በትጋት ላገለገለ ሰው ሊሰጠው የሚገባው የማዕረግ ስም፣ ያለቦታው በየደረሰበትና በዋለበት መድረክ ሁሉ ወያኔን ከማወደስና ከማሞገስ በቀር ሌላ ስራ ለሌለው ተራ አሻንጉሊት በዚህ መልኩ መሰጠቱ በእጅጉ የሚያሳዝንና የሚያስኮንን ድርጊት ነው።
እናት አገራችንን ከፍተኛ መስዋዕትነት በመክፈል ጠብቀው ያቆዩልንና፣ ይህም የጀግንነት ውሏቸው የተመሰከረላቸው በርካታ በሕይወት ያሉ አባት እናቶቻችን በወር 150 ብር ያልበለጠ ደሞዝ (አበል) እየተወረወረላቸው ተገፍተው እድሜና ችግር እያንገላታቸው ሳለ፣ እንዲህ አይነቱ ምንም አይነት ሚና የሌለው ተራ አብዮት ጠባቂ እነ ደጃዝማች ኪዳኔ ወልደመድሕንን የመሰሉ ስመጥርና ታላላቅ ጀግኖች ይመሩት የነበረ ማህበር ላይ ያለአግባብ ተሹሞ መቀመጡ የሚያቃጥልና የሚያንገበግብ ብቻ ሳይሆን የነዚህን የቀደምት ጀግኖች አባት እናቶቻችንንም ተጋድሎ የሚያራክስና የሚያንኳስስ አሳፋሪ ነገር ነው።
ለመሆኑ እኛስ የዘመናችን አርበኞቻችንን ያለ አግባብ እስር ቤት ተጥለው አበሳቸውን እያዩና እየተሰቃዮ እያየን በሰላም ተኝተን የምናድረው እስከመቼ ይሆን? ዓለም እንኳን ከእነዚህ ሰዎች አንዳንዶቹን ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት አርበኞች እንጂ አሸባሪዎች አይደሉም ብሎ ከመመስከርና እንዲፈቱ ከመጮህ አልፎ፤ እውቁን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን፤ እንዲሁም የምንኮራባት እሕታችንን ጋዜጠኛና መምሕርት ርዕዮት አለሙን ለከፍተኛ ሽልማት ሲመርጣቸው እኛ የጉዳዩ ባለቤቶች ዝምታችን እስከመቼ ድረስ ነው? ሌላው ቢቀር እነዚህ ሰዎች አብዛኞቹ የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች ናቸውና ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለእውነት በመቆማቸው እስር ቤት ሲጣሉ ከራሳቸው አልፎ በቤተሰቦቻቸው ላይ ብዙ ችግር ሊደርስ እንደሚችል ተገዝበን አቅሙ ያለን ሰዎች በያለንበት ተደራጅተን ከቤተሰቦቻቸው ጎን ለመቆም እንዴት ይሳነን? ባጠቃላይ ለዚህ ብቻ ሳይሆን ስርዓቱ በአገራችንና በወገኖቻችን ላይ እያደረሰ ያለው በደል ይህ ነው ተብሎ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አልሆነምና በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የምንኖር ኢትዮጵያውያን ይህንን ስርዓት ለማስወገድ ለሚደረገው ሁለንተናዊ ትግል የበኩላችንን ድጋፍና ጥረት ለማድረግ በቁርጠኝነት መነሳት ይኖርብናል እላለሁ።
አበቃሁ!
ለግል አስተያየት efjakhb@yahoo.com



የወያኔን በደል ከሞላ ጎደል የማያውቅ ያለ አይመስለኝም ሆኖም ግን ስለተናገርን ብቻ አይወርድም በመጀመሪያ አንድ ነገር በግልጽ መታወቅ ያለበት እነሱ እስከቻሉት ድረስ ለመግዛት ወስነዋል በምርጫ ደሞ እንደማይሆን ህጻን ልጅ የሚያውቀው ጉዳይ ነው ታዲያ ያለው አማራጭ ምንደነው ? አገራችን ሰፊ ነው እንደአባቶቻችን ጊዜ በዱር በገደል መፋለም ካልቻልን ወያኔን ማስገደድ አይቻልም ግዴታ የተደራጀ ጦር መኖር የለበትም በተለያየ ግንባር በየቦታው በተበታተነ አነስተኛ ወታደር ማስጨነቅ ይቻላል እንደ ለገሰ ወጊ ,,,ወያኔ ለምንድነው ለገሰን ለማጥፋት ያለ የሌለ ገንዘብ እና ፕሮፖጋንዳ ሲፈጅ የነበረው ? የሚገባቸው ያመንገድ ብቻ ስለሆነና ከዛ ውጭ ስልጣን ለማስረከብ ዝግጁ ስላልሆኑ ነው ያለበለዚያ ይሄ በጥላቻ የታጨቀ ቡድን የመከራ ቀናችንን እንዳረዘመው ይኖራል
ስለ ወያነ ብዙ ቢነገር ትርጉም የሎውም. ለወያነ መታገል ግን የሀሳብና የድርጊቶች ሀብረት ያስፈልጋል. ወርያ በዛ ስራግን የለም
ወያኔና ሻዕብያ የኣንድ ብር ሁለት ገጽ መሆናቸው ኣታውቁም እንዴ?
ኢሰያስ ወደ በረሃ ሲወጣ ዋና ይስራ-መደቡ ካውንተር ሪቮሉሽን ለማክሄድ እንጂ ለኤርትራ ህዝብ ኣስቦ ኣይደለም። መለስም እንደዚሁ ተቀጥሮ ነው ለበረሃ የተላከ። ወያኔን ደግሞ በሻዕብያ ሰልጥኖ በመልክ ይቀያአር ኣንጂ ብይዞታ ኣንድ የስራ መደብ ያለው ሌባ ቡድን ነው።
ታድያ ከወያኔና ሻዕብያ (ከመለስና ኢሰያስ የኢትዮጵያ ህዝብ ይሁን የኤርትራ ህዝብ ምን ይጠብቃል?
ኣነዚ የሲ.ኣይ.ኤ.ና የሞሳድ ቅጥረኞት ኣገርን ለነጮች ለማስረከብ ብቻ ነው ስራቸው።
ስለዚ የነ ሃጸይ ተድሮስን የነ ራስ ወልደሚካኤል ሰለሞን ጅግንነት ብኣሁኑ ወቅት መነሳት ኣለበት።
ለነዚህ ቅጥረኞች በጥይት ኣንጂ በወሬ ልናሸንፋቸ ኣንችልም!። ኣገራችን ወይም ሞት! ብለን ያ የሙሴ በትር በእጃችን ይዘን እንደ የበረሃ እባብ ጭንቅላታቸውን እንዲፈነዳ ማድረግ ብቻ ነው። ሊላ ኣማራጭ የለም ።
ከዚህ የባሰ ምን ልያድርጕን ነው? ሃይማኖታችን ተደፍሮ መሬታችን ለባእድ እየተሸጠ፣
የመንፈስና መንነታችን ምልክትን ኵራት የሆነ ታቦታችን (ጽላተ-ሙሴ The Ark of covonance .or The Holy Ark; The Holy Grail) ነጮች እንዲዘምቱት መለስና ኢሰያስ ፈቃድ ሰጥትዋቸዋል። ገና እየፍለጉት ናቸው። የባህሪዳርና የዙቅዋላ ገዳማት ሲደፈሩ…የኤርትራ ፓትሪያርክ በኢሰያስ ሲታሰሩ…ከዚህ የባሰ ቀውስ ምን ይምጣ ?
ወያኔና ሻዕብያ ዓላማ የምባል የላቸውም!…እንደ ሪሞት ኮንትሮል የሚሰሩ እቃዎች ናቸው። ብሲ.ኣይ.ኤ. እና በሞሳድ ኣንዲሁም በኤም ኢ 6 ተነድተው ይምንቀሳቀሱ ሪሞት-ራዲካሎች ናቸው። ህፍረት ኣያውቁም ህይወታቸው ገንዘብ ብቻ ነው…የህዝብና የኣገር ክብርና ኵራት ኣያውቁም።
“በዓለም ላይ የሚኖሩ ጥቁር ሕዝቦች ሳይቀር እንደ ነፃነት ዓርማቸው በመውሰድ በመለያነት የሚመርጧትን ይቺን ክቡሯን ሰንደቅ ዓላማችንን ባደባባይ “ጨርቅ!” ሲል ያንቋሸሸና ያዋረደ ብቸኛው የአገራችን ርዕሰ ብሔር፤ ብሎም ኢትዮጵያዊም መለስ ዜናዊ ብቻ ነው።”