ከተገለጡት የተደበቁት ተሻሉ በታረቀኝ ሙጬ

May 15th, 2012 ይመይሉ ይመይሉ ያትሙ ያትሙ

ማሳሰቢያ፤ ይህ ጽሑፍ 4 ገጽ ከሩብ አካባቢ ነው፡፡ ረጂም ጽሑፍ ማንበብ እሚወዱ ብቻ እንዲያነቡት ይመከራል፤ ለስልቹዎች ስላልታሰበ በርዝማኔው ምክንያት አንዳችም ስድብ የማላስተናግድ መሆኔን ከወዲሁ አሳስባለሁ፡፡
መቅድም አንድ

እኛ ኢትዮጵያውያን ቀደም ሲል የነበረው ጨካኙና ሀገር ወዳዱ የደርግና አሁን ያለው አረመኔና ሀገር አፍራሹ የወያኔ መንግሥታት ሲያንሱን ነው፡፡ እየኖርነው ያለነው የሰቆቃና የግፍ ሕይወትም ሲያንሰን ነው፡፡ እንደጨው ዘር በዓለም ዙሪያ በስደት መበተናችን ሲያንሰን ነው፡፡ ከአንድ ምዕተ ዓመት በማይበልጥ ያሳለፍነው ዘመን ውስጥ ኢትዮጵያ መጠጊያቸውና ከደረቁቻ በረሃማ መሬት ማምለጫቸው ወደነበሩ የዐረብ ሀገራት ሴቶችና ወንዶች ልጆቻችን ለግርድናና እሽክርና አስከፊ ሕይወት መዳረጋቸው ሲያንሰን ነው፡፡ ወርቅ ላይ ተቀምጠን በምቀኝነትና የርስ በርስ ቁርቋሶ ተጠምደን፣ በኋላ ቀር ዳፍንታዊ መንጦላዕት ዐይናችንን በመጀቦን ከእምቅድመ ዓለም የሥልጣኔ ማማ ተሸቀንጥረን ወርደን፣ እኛ ያኔ የነበርነው ከእነሱ ያኔ ካልነበሩት የአሁናቸው ግርጌ መቀመጥም አቅቶን በቁማችን እንጦርጦስ መውረዳችን የሚገባን እንጂ የሚያንስብን አይደለንም፡፡ ነባሮቹ ሃይማኖታዊና ባህላዊ መልካም ምግባሮች ድራሻቸው ጠፍቶ ብኩን የሃይማኖት እረኞችና በገሃድ መብታቸውን የሚጠይቁ ግብረ ሶዳማውያን ዜጎች እየበዙልን መምጣታቸው የኩራታችን ፈርጦች በመሆናቸው እሰዬው ነው፡፡ እኛ በርሀብና በርዛት አለንጋዎች እየተገረፍን ጥቂቶችን በደቂቃዎች ውስጥ ከትቢያ አንስተን ሚሊዮነሮች ማድረጋችን ሲያንሰን ነው፡፡ ጭንቅላታቸው በምቀኝት፣ በቅናት፣ በቂም በቀልና በተንኮል የተሞላ እባብ ዜጎችን በሀገር ውስጥም በውጪውም ማፍራታችንና ፖለቲካችንን እንደልብ ተቆጣጥረው እንዲፈነጩበት በግላጭ መተዋችን የዕድገታችን ምልክት በመሆኑ እንደአንድ አኩሪ ገጽታችን ሆኖ በጊነስቡክ መዝገብ ሊሰፍርልን ይገባል፡፡ ለሀገርና ለወገን ከመቆርቆር ይልቅ ለታሪካዊ ጠላቶች ያጎበደደ ትውልድ አፍርቶ ለሥልጣን ማብቃትና በውጤቱም ሀገርንና ሕዝብን አንበጣ የወረረው የሰብል ማሣ ማድረግ ከአንድ ታሪካዊ ሕዝብ የሚጠበቅ በመሆኑ አሁንም ልንኮራ ይገባናል፡፡ ዓለም የናቃቸውን የጎሣና የዘውግ ልዩነቶችን እኛ እንደአዲስ አንስተን እርስ በርስ እየተራኮትን ሌላውን ዓለም በተለይም አውሮፓንና አሜሪካንን እያስቀናን በመሆናችን ደስ ይበለን፡፡ ወዳጆቻችን እነቻይናና አሜሪካም ሃሤትን ያድርጉ፡፡…

መቅድም ሁለት

የዓለም ዕድገትና ሥልጣኔ እንደስከዛሬው ባልተስፋፋበት ቀደም ባለ አንድ ወቅት ነው፡፡ አንድ አሜሪካዊ፣ አንድ ራሺያዊና አንድ ኢትዮጵያዊ እግዚአብሔር ዘንድ ቀርበው ተመሳሳይ ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ ጥያቄው፡- “ሀገሬ መቼ ነው አድጋና በልጽጋ የሕዝቧ የኩራት ምንጭ እምትሆነው?” የሚል ነው፡፡ መጀመሪያ አሜሪካዊው ወደቢሮ ይገባና ይህንኑ ጥያቄ በራሱ ቋንቋ ያቀርባል፡፡ እግዜሩም በጥሞና ካዳመጠ በኋላ እንዲህ ይለዋል፤”የዛሬ ሃምሣ ዓመት ገደማ!” አሜሪካዊው ተደስቶ ይወጣል፡፡ ራሺያዊው ይቀጥላል፡፡ ፈጣሪም “ከመቶ ሃምሳ ዓመት በኋላ!” ይለውና ሩስኪው እንደመከፋት ብሎ ይወጣል፡፡ የኢትዮጵያዊው ተራ ይደርስና ጥያቄውን ሊያቀርብ የቢሮውን በር ከፈት ከማድረጉ የሀበሻው ጥያቄ ምን እንደሆነ አስቀድሞ የገባው እግዚአብሔር ስሜቱን መቆጣጠር አቅቶት እዬዬውን ይለቀዋል – አለውም “ያንተ ሀገር ኢትዮጵያ አድጋ የምትታይበትን ዘመን እኔ ራሴም አልደርስበትም የኔ ልጅ!”

መንስኤ ነገር

አንድ ቅዳሜ…

ከቤተሰብ ጥየቃ መልስ እንደወትሮው ተሰባስበን ምግብ በምንቋደስበት ቦታ አንድ ሰው አልተገኘም፡፡ የሆነ ነገር ቅር ሲለኝ ዙሪያ ገባውን ባይኔ ቃኘሁ፡፡
“ጃክስ?” ስል ጠየቅሁት፡፡
ፋሲል፣ ዶክተር ያዕቆብን በርቀት አመላከተኝ፡፡ ከእስር ግቢያችን ዋና መግቢያ በር አጠገብ ውሃ ልክ ላይ ኩርምት ብሎ ተቀምጧል፡፡ ክርኖቹን ጉልበቱ ላይ አስደግፎ በእጆቹ መዳፎች ጉንጮቹን አንተርሶ አቀርቅሮ መሬት መሬት ያያል፡፡ አቀማመጡ የመከፋት ስሜት ውስጥ እንዳለ ያሳብቃል፡፡

“ምን ሆኗል?”

“ምን እባክህ” አለ ፋሲል “እዚህ ትልቅ እምትለው አንዳንዱ ሰው በድርጊቱ የትንሽ ትንሽ ይሆንብሃል፡፡ ይቀልብሃል፡፡ በተለይ ደግሞ እገሌ…” አለኝ አጠገባችን በሚገኘው ማዕድ ዙሪያ ክብ ሠርተው ከሚመገቡት የቅንጅት አመራሮች መሃል አንዱን በአገጩ እየጠቆመኝ፡፡

“ዛሬ ደግሞ ምን ተከሰተ?”

“ከእርሱ ቤተሰቦች መካከል አንዱ ዛሬ ለዶክተር ያዕቆብ ስጦታ ይዞ መጥቶ ነበርና ሰጠው፡፡ ይሄኔ ‹ተቀበለው!› ብሎ አዘዘ፡፡ ጠያቂው ምንተፍረቱን ‹ይቅርታ፣ ለሌላ ሰው ይዤ የመጣሁትን ስጦታ ነው የሰጠሁህ› ብሎ ከዶክተር ያዕቆብ መልሶ ተቀበለው፡፡ ወዲያው ‹ወስደህ ለዶክተር እከሌ ስጠው!› ብሎ አዘዘው፡፡ ጠያቂውም እንደተባለው አደረገ፡፡”

“ከአንዱ ነጥቆ ለአንዱ?ለምን?” ጥያቄዬ የመገረም ዓይነት ነበር፡፡

“እርሱና ዶክተር ያዕቆብ በሽምግልና ጉዳይ የአመለካከት ልዩነት እንዳላቸው ታውቃለህ አይደል? የአመለካከት ልዩነቱ እስከመኮራረፍ ዘልቋል፡፡ ስለዚህ ከእርሱ አመለካከት ጋር ለተስማማው ለዶር. እከሌ እንዲሰጥ አደረገ፡፡ ጃክ የተናደደውና ያዘነው በዚህ ምክንያት ነው፡፡” አለኝ፡፡

“ ግን የእርሱ ቤተሰብ ለዶር. ያዕቆብ ያመጣው ስጦታ ምን ነበር?”

“የአንገት ሹራብ(scarf)”

በዚያች ቅጽበት አንዳች የሀፍረት ስሜት ወረረኝ፡፡ ተደረገ የተባለው ነገር ስለመደረጉ ‹ከባለቤቱ አፍ› ስሰማ ሀፍረቴ ወደ ሐዘን ተለወጠ፡፡

… ቤተሰብ በመካከላችን የአቋም ልዩነት መከሰቱን አያውቅም፡፡ በርግጥ የአመለካከት ልዩነት የነበረ፣ ያለና የሚኖርም ነው፡፡ የሃሳብ ልዩነት መከሰት እንኳንስ ለአንድ ፖለቲከኛ ለሌላውም የሚገርምና የሚደንቅ አይደለም፡፡ አንድ ሰው በአመለካከት ተለየኝ ብሎ፣ ቅሬታን በቤተሰብ ስጦታ አስታክኮ ማንፀባረቅ፣ ከአንድ ፖለቲከኛ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ …

“አሁን እነዚህ ናቸው ቅንጅትን እሚያህል ፓርቲ ሲመሩ የነበሩት?” እላለሁ በግዴለሽነት ስሜት፡፡ ማንም ቢሰማኝ ግድ አልነበረኝም፡፡ “ብቻ ከእስር ቤት የመውጣት ዕድል ላግኝ እንጂ ይሄን ጉዳቸውን ሳላወጣው አልቀርም፡፡ እነዚህ ሰዎች የፖለቲካ ፓርቲ አይደለም የቤተሰብ ማኀበር መምራት እንደማይችሉ ከመናገር ወደኋላ አልልም፡፡” እላለሁ፡፡ [ወሰን - እንኳን ተሣካልህ!]
ወሰንሰገድ ገ/ኪዳን (2004) የቃሊቲ ምሥጢሮች (ገጽ 127-129፣ መስመር ከራሴ) (harawosen@gmail.com)

“ስብሰባው እንዲህና እንዲያ እያለ አስተያየት የተሰነዘረበትና በ30 ደቂቃ ውስጥ የተጠናቀቀ ቢሆንም እኔን እጅግ በጣም የገረመኝ አንዳችም ጠብ የሚል ቁም ነገር ሳይናገርበት አብዛኛውን ደቂቃ የፈጀው ተስፋዬ ታሪኩ መሆኑ ነው፡፡ በእስር ቤት ሕይወት ውስጥ ካገኘኋቸው ሰዎች መሃል እጅግ በጣም የሚያሳዝንህና የምታዝንለት፣ የሚያበሳጭህና የምትበሳጭበት፣ የምትገረምበትና የምትገረምለት፣ የሚያሣፍርህና የምታፍርለት፣ የሚያስቅህና የምትስቅበት… አንድ ሰው ጥራ ብባል የማስቀድመው ተስፋዬን ነው፡፡” (ዝኒከማሁ፣ ገጽ 104)

ማጠቃለያ አንድ

እኛ እንዲህ ነን እንግዲህ፡፡ የኞች ከምንላቸው ውስጥም ‹ጥቂቶቹ› እንዲህ መሆናቸው ነው፡፡ ነገራችን ሁሉ “ወጣ ወጣና እንደሸንበቆ ተንከባለለ እንደሙቀጫ!” የሆነብን የተስፋቢሶች ተስፈኞች፡፡ ቢከፍቱ ተልባ፡፡ ሰው መሳይ በሸንጎዎች፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ተዋንያን “ድመት መንኩሣ ዐመሏን አትረሣ” ዓይነት አሣዛኝ ፍጡራን ነን፡፡ ትንሹም ዳቦ ትልቁም ዳቦ ሁሉም ተያይዞ ሊጥ የሆነበት አስገራሚ ዘመን! ማንም አባ ደፋር ከነማይምነትና ያልተሞረደ ዕድፋም ስብዕናው ዘገደው እሚልበት የፖለቲካ ባቡር የሠራን አስደናቂ ሕዝብ – እንደሕዝብ! በግሩም ልብስ የተጀቦኑ አስፈሪና አሣፋሪ ጉዶች፣ በሚያማምሩ ‹አቶ›ን ፋቂ ትምህርታዊና ወታደራዊ ቅጽሎች የተዋጁና በነዚያ አላፊና ብል እሚበላቸው ማዕረጋት በድሀ ወገናቸው ላይ የሚኮፈሱ ማይማን፣ በአንደበተ ርቱዕነት የማይታሙ ሥነ ሕይወታዊ ተፈጥሯቸው እየቆዬ ሲታይ ግን ከመርዛማ ንጥረ ነገር የተዋቀረ አሉቧልተኞች… የተሰገሰጉበት የፖለቲካ ሥሪት ባለቤት የሆንን አሣዛኝ ዜጎች – ኢትዮጵያውያን፡፡ አቤት የገባንት አዘቅት!!
የወሰንሰገድን መጽሐፍ ሳነብ ዕንባ እየተናነቀኝ ነው የጨረስኩት፡፡ በኢትዮጵያዊነቴ እንደዚህ ቅጽበት አፍሬ አላውቅም፡፡ አንዳንዶች በጣም ዘገዬህ እንደምትሉኝ አላጣሁትም፡፡ የኛ ነገር ተከድኖ ይብሰል እንጂ ሁሉን ካወሱት የሚጣል እንጂ የሚነሣ የለውም፡፡ ለዚህም ነው ከአንዱ ማጥና አረንቋ ወጣን ስንል ወደባሰበት ሌላ ማጥና አረንቋ የምንቀረቀረው፡፡ የሾተላዩ ሠይፍ ስለቱ ሊበርድልን ቀርቶ ከቀን ቀን እየተሞረደና ይበልጥ እዬሰላ ቀልቶ ሊፈጀን ነው፡፡ መጨረሻውን ያሳምርልን፡፡
ግንቦት ወር ውስጥ ነው የምንገኘው፡፡ ግንቦት ለኢትዮጵያ ብዙም የምትመች አይደለችም፡፡ ግንቦት 8/81ዓ.ም ኢትዮጵያ ብዙ የለፋችባቸው ከፍተኛና የመስመር መኮንኖች መቻቻልንና ምሕረትን በማያውቀው የወቅቱ አምባገነን መሪ (ባይሞትም ነፍሱን ይማር) መንግሥቱ ኃ/ማርያም በይስሙላ ፍርድና አለፍርድ እንዲጨፈጨፉ ምክንያት ሆነ፡፡ በሁለተኛው ዓመት ግንቦት 20/83 የነዮዲት ጉዲትና የነግራኝ አህመድ የመንፈስ ውልድ የሆነው የምዕራባውያን አሻንጉሊት መንግሥት ‹ኢሕአዴግ›በሚለው የማስመሰያ ስመ ጥምቀት የውጪና የውስጥ መርዛቀባዮቹ ባደረጉለት ሁለገብ ረድኤት ከጫካ ወጥቶ አዲስ አበባ ላይ ተተከለ፡፡ ግንቦት 7/97 የእንቁልልጭ ዴሞክራሲ ብቅ ብሎ አጓጉቶንና የበርካታ ዜጎቻችንን ደም በጭዳነት በከንቱ አፍስሶ ላይመለስ ሄደ፡፡ የዚያ የተረገመ ልዩ ግንቦት ጦስ ጥንቡስ እስካሁን አልለቀን ብሎ ይሄውና ኑሯችንን ክፉኛ አመሰቃቅሎት ካሉት በታች ከሞቱት በላይ ሆነን በመንፈስም በሥጋም እዬተንጠራወዝን እንገኛለን፡፡ ግንቦት ወር በሌላ መልክም ይሄን መሰሉ ገደቢስነቷ ቢፈለግ አይጠፋም፡፡ ለነገሩ የአሁኑን አያድርገውና ሠርግ እንኳን በግንቦት ወር አይደረግም ነበር – ገደቢስ ወር ነው ተብሎ ስለሚታመን፡፡ ለወደፊቱ ግን ኢዮብ የተወለደባትን ዕለት ከቀናት ሁሉ ለይቶ እንደረገማት ሁሉ እኛም ይህችን እርጉምት ወርኃ ግንቦት ለዳግመኛው እንዳናያት ቀናቱን ወደተቀሩቱ ብንበትናት ሳይሻለን አይቀርም፡፡ ምልኪዋ አልበጀንምና፡፡

ማጠቃለያ ሁለት

ለሕዝብ ለውጥ ሊያመጡ እሚመስሉ ጅምሮዎች ለምን ይከሽፋሉ? ጥበበ ወርቅዬ የሚባለው ዘፋኝ ይመስለኛል፡- “አሁን ገና ገባኝ” እያለ እሚያቀነቅናት ዘፈን አለችው፡፡ ወጣቶች አርሙኝ፡፡ አዎ፣ አሁን ገና ነው በጣም የገባኝ ለምን እንደሚከሽፉብን፡፡ ወደፖለቲካው እሚገቡ አብዛኞቹ ሰዎች እንደ ልደቱ አያሌው ያሉ በአፋቸው ጤፍ እሚቆሉ ተራ የፖለቲካ ቁማር ቆማሪ ሌቦች፣ አጭበርባሪዎች፣ አስመሳዮች፣ ለሥልጣንና ለዝና ሟቾች፣ የስመጥርነት ምርኮኞች፣ ዋና ዓላማቸውን ሀብትና ገንዘብ ያደረጉ ስግብግቦች፣ በጭቁኖች ሞት ተረማምደው የሁሉም ነገር ጣርያ ላይ ቂብ ማለት እሚፈልጉ የማኪያቬሊ ደቀ መዛሙርት ስለሆኑ ነው፡፡ ለሕዝብ አስባለሁ እሚልና የሕዝብን አመኔታ አግኝቶ በሺዎች ደም የበለፀገ የፖለቲካ ስብዕና ባለቤት የሆነ ሰው በተራ ቅያሜ ተነሳስቶ በስጦታ የመጣን የዘመዱን የ10 ብር ያንገት ሽርጥ (ስካርፍ) ከመጣለት ሰው ቀምቶ ለሌላ አይሰጥም ነበር – ሰው ቢሆን፤ በሺዎች ደም አንቱታን ያገኘ የፖለቲካ ሰው ጎረቤት ሀገር ስደተኞች ጣቢያ ለሚገኙ ልጆቹ አፊዳቪት ወይም የፖለቲካ ጥገኝነት እስኪያገኙለት ድረስ በእስር እንዲቆይ ብሎ የይቅርታ ተብዬውን ፊርማ “እባካችሁ አንፈርም” ብሎ ታሣሪ ጓደኞቹን ባላወከ ነበር፡፡ (የወሰንሰገድን መጽሐፍ ያነቧል) ይህ አድሮ ቃሪያነታችን ነው እንግዲህ ከዚህ መጣጥፍ መግቢያ ጀምሮ በንዴት እያንጨረጨረ እዚህ ድረስ እንድዘልቅ ያደረገኝ፤ እኔም እንዳቅሚቲ እናገራለሁ! ምኑ ሲቀርብኝ? ፒ! “ቂጣ ቢያንቅ በውሃ ይዋጣል፤ ውሃ ቢያንቅ በምን ይዋጣል?” በቅንጅት ስም የስሙ ግነት ሰማየ ሰማያት የደረሰ ሰው እንደሕጻን ሲያደርገውና እንዲያውም ከሕጻንነትም በወረደ እንደለየለት ዕብድና ወፈፌ ገና ባልተገኘ ሥልጣንና ወንበር እንዲህ ከሆነ እኛ እዚህ ግቡ እማንባለው ወፍዘራሾች አንሻልም ትላላችሁ? “የዘገነም አዘነ፤ ያልዘገነም አዘነ” እንደሚባለው ካልሆነ በስተቀር እምንም ውስጥ ሳይገቡ አንጋጥጠው ብቻ በኤሎሄ የሚኖሩ ምሥኪን ዜጎች ከነዚህ ቅሌታም ‹ትላልቅ› ሰዎች በእጅጉ የተከበረ ዋጋ አላቸው ብዬ በሙሉ ልቤ አምናለሁ፡፡ ለነገሩ የሰው ሥራው ከቤቱ ውጪ ነው እሚያድር፡፡ እናም የአንዳንዶቹን አስጸያፊ ተግባር ዱሮውንም እንሰማ ነበር፡፡ ነገር ግን ወላድ በድባብ ትሂድ በውስጡ የነበሩና ሁሉን የታዘቡ እንደወሰንሰገድ ያሉ ደፋር ወጣቶች ጉዳቸውን ዘክዝከው አሳዩን – ዘር ይውጣላቸው፤ ቢስም አይይብንና ፈጣሪ በነሱ ይካሰን ፡፡ እናም የማን ማንነት አሁን ወለል ብሎ ታየን፡፡ በየለውጥ ምዕራፎች የሚመጡ ልጆቻችን ሲያሳፍሩን እንጂ ሲያኮሩን አናይም፡፡ የግንቦት ስምንቶቹ ምሥኪኑ ሕዝብ እየተራበ ዊስኪና ጮማ ሲቆርጡ ቆይተው፣ አንዳንዶቹ በየቤታቸው ስንትና ስንት የጤፍና የዊስኪ ቁልል የተገኘባቸው፣ መንግሥቱ ኃ/ማርያምን የመሰለ ጭራቅ አስቀምጠው ባልተጨበጠ ሥልጣን የተገዳደሉ ሞኞች… ሆነው ተገኙ፡፡ እናም ፈጣሪ እነሱን ባይፈቅድልን ይሆናል አከሸፈው፡፡ የግንቦት ሃያዎቹ በርግጥ ወንበሩን ይዘውታል ግን ያዋጁን በጆሮ ነውና ልለፈው፡፡ የግንቦት ሰባት 97ዓ.ም ደግሞ ቆየት ብለን እንዳየነው እስር ቤት ውስጥ ተቀምጦ እስከመሹዋሹዋም የደረሱ ቂሎች ወይም ዶን ኪሾቶች የሞሉበት፣ ብረት ሲመስሉን ኩበት ሆነው ያገኘናቸው ሰዎችን የታዘብንበትና ምናልባትም ሥልጣኑ በነዚህን መሰል ሰዎች እጅ ቢገባ ኖሮ እንደማንጠቀም አስቦ ይሆናል ፈጣሪ አሳይቶ የነሣን፡፡ ምሥጢሩ ረቂቅ ነው፡፡ …
ልብ ካለን ከእንግዲህ ማንም እንዲያጭበረብረን መፍቀድ የለብንም፡፡ ለወትሮው የሞኝ ብልኀነት አንዴ ነበር የሚያሞኝ – ዛሬ ዛሬ ግን ዕድሜ ልክ ሊሆን የቃጣው ይመስላል፡፡ ለዚህም ነው ሕዝቡ በአሁኑ ወቅት ፀጥ ረጭ ያለው፤ ማንን ይመን? ማንንና እንዴትስ ይጠጋ? ያበራሽን ጠባሳ እሚያክም ሳይገኝ ማን ነው ደፍሮ በእሳት እሚጫወት? ‹እውነተኛው ሙዜ ተገኝቶ ሙሽራዋን ሳያዝላት› እንዴት ተደርጎ ሃይ ሎጋው ይባል? ሙሽሪትስ ስንት ጊዜ ትታለል? ፈረንጅ በዚህ ዓይነቱ አስጨናቂ አጋጣሚ “Let us wait until the cat jumps.” የሚለው ወዶ አይደለም፡፡ እኛም እኮ ‹አትቀደም› ‹ሰኞን አለመሆን ነው› እያልን ነው ብልጥ ለብልጥ ዐይናችንን ስንበለጥጥ ጀምበር ልትጠልቅ የተዳረሰችውና ለተምቾቹም ምቹ ሆነን የቀረነው፡፡ ብናውቅበት በሕግ አምላክ የማለት መብቱ የኛው ነበር፡፡ … የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም፡፡ ከእንግዲህ ምን ሲቀርብን? ያመኑት ፈረስ ሁሉ በደንደስ ሲጥል እያየን? ሀገራችን እንዴቱን ያህል ብትረገም ይሆን ግን የልደቱኣዊ ዋልጌዎች ማምረቻ ፋብሪካ ሆና የቀረችው? ለምንድነው የወላድ መካን የሆነችው? የሰው አባባል ልዋስና ቆንጆዎቹ ወዴት አሉ? ወይንስ ገና አልተወለዱም? በእርግጥ ይህም ዘመን እንደቀደምቱ የመከራ ዘመናት አልፎ ልጆቻችን የእፎይታ ጊዜ ያገኙልን ይሆን? ዕድሜ ሰጥቶን ማየት ብንችል በበኩሌ እንደገና የመፈጠር ያህል እቆጥረዋለሁ፡፡ ሁሉን ነገር ማድረግ የማይሳነው አምላክ ይስማን፡፡

በተለይ ለወጣቶች፡-

ከእኛ ከ‹ትላልቆች› ተማሩ፡፡ ካቆየንላችሁ የምቀኝነትና የትንሽነት ስብዕና በአፋጣኝ ውጡ፡፡ በዛሬ ዘመን ትልቅ እሚባል ሰው ማግኘት ከባድ እየሆነና እናንተም በአርአያነት እምትከተሉት ሰው እየጠፋ በመሆኑ የቀድሞዎቹን መልካም ሰዎች አብነት ከመጻሕፍት እያነበባችሁ ራሳችሁን አንጹ፡፡ እርግጥ ነው አሁንም ቢሆን መጠናቸው አንሶ በማኀበረሰቡ ውስጥ ሊፈጥሩት እሚችሉት አወንታዊ ተፅዕኖ ጎልቶ ሊወጣ ባለመቻሉ እንጂ እንደነዶክተር ኃይሉ አርአያና ዶክተር ዳኛቸው አሰፋን የመሳሰሉ እውነተኛ የሀገር ተቆርቋሪ ምሁራን በውስጥም በውጪም አሉን – ጨርሶ አይበድልም፡፡ (የወሰንሰገድን መጽሐፍ ያነቧል) በዛሬ ዘመን የምታዩትን ትልቅ ሰው የዕድሜ በረከቱን እንጂ ተግባሩን እምብዝም አትመኙ፡፡ ከሁሉም ከሁሉም መልካም መጻሕፍትን እየመረጣችሁ አንብቡ፡፡ በመጻሕፍት ራሳችሁን አሳድጉ፤ ብዙዎቻችሁን ስታዘብ ሕይወታችሁ ሩጫ የበዛበት ከመሆኑ አንጻር ሰፋ ያለ ነገርን በጥልቀት ከማንበብ የራቃችሁ ትመስሉኛላችሁ፡፡ ያንዳንዶቻችሁን የቋንቋ አጠቃቀም ስታዘብ ደግሞ ብዙ ማንበብ እንደሚኖርባችሁ እየተረዳሁ መጥቻለሁ፡፡ ይህን ስል ተስፋ ሰጪ ወጣት ምሁራን ዜጎች መኖራችሁን ዘንግቼው አይደለም፤ ነገር ግን ገና ብዙ እንደሚቀረን ይሰማኛል፡፡ ያለ ነገር ወዴትም አይሄድምና ባለን ነገር ከመኮፈስ ይልቅ ለመጨመር መጣር የትልቅ ስብዕና ዓይነተኛ ምልክት ነው፡፡ የንባብ ትሩፋት እውነተኛ ማንነትን ያስገኛልና ጓደኛችሁ መጽሐፍ ይሁን፡፡ በመሠረቱ ዘመናዊ ባህል ጥሩ ነው፤ ዘመናዊ መሆንም ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን በዘመናዊነት ስም በነፈሰው ንፋስ ሁሉ አትወሰዱ፡፡ ሀገራችሁ ያለ ተረካቢ እንዳትቀር እኛን ታላላቆቻችሁን- ዕድሜችንን በከንቱ ያሳለፍነውን የትውልድ እርጉማንን ሳትመለከቱ በንባብና በሕይወት ገጠመኝ በምታዳብሩት ዕውቀትና ግንዛቤ የጥበብ ሰዎች ሁኑ፡፡ ሁሉም ያልፋል፡፡ ነገር ግን የሚያልፈው በአዲሱ ሲተካ መጪው የእናንተ እንዲሆን ጥረት ማድረግ ይኖርባችኋል፡፡ አለበለዚያ አሮጌ መጥፎ ነገር በአዲስ መጥፎ ነገር ሊተካ እንደሚችልም መረዳት ይኖርባችኋል፡፡ ዘመኑ የኀብስተ መና ሣይሆን የጥረትና የልፋት መሆኑን ልብ በሉ፡፡ በዛፍ ላይ የሚገኝን ጣፋጭ ፍሬ ሌላ ሰው አውርዶ እንዲያጎርሳችሁ ከጠበቃችሁ ሞኝነት ነው፡፡ አውራጅ እንኳን ቢኖር በእናንተና በዛፉ መካከል ያለው ርቀት የምትጠብቁትን ያህል ፍሬ እንድትጎርሱ ላያደርግ ይችላልና ሁልጊዜ ተራራው ወደእናንተ እንዲመጣ ከመጠበቅ ይልቅ እናንተም ወደተራራው እንደትሄዱ ዘመኑ ያስገድዳችኋል፡፡ ከእኛ የምትማሩት መልካም ነገር እምብዝም ያለ አይመስለኝም፡፡ እኛ ባስቀመጡን እማንገኝና በዘመናችን የሰይጣን መሣሪያ ወደ መሆን ያዘነበልን ምግባረ ጥፉዎች ነበርንና የተውንላችሁ ቅርስ እምብዝም የለም፡፡ የምንሸከመው ትልቁ የትምህርት ደረጃ ሰውን በከንቱና አለሥራው በሃሜት ከመቦጨቅና ከመጥላት እንደአፍላ ጎረምሣም ሰው እስኪታዘበን ድረስ ፀያፍ የዱርዬ ስድብ ከመወራወር አላዳነንም፡፡ ‹ተምሮ ላፈር› ማለት ይህን ዓይነቱን በቁሙ ‹መሃራ ለነፍሰ ገብሩ…› እሚያስብል ምሁር ተብዬ የሀገር ሸክም ነበር፡፡ ምክንያቱም ላይጠቀምበት ብዙ የሀገር ገንዘብና የራሱን ዕድሜ አለመላው ፈጅቷልና፡፡ ሲመረቅ የለበሰው ጥቁር ካባና መነሳነስም የሀዘን ጅማሮውን እንጂ ሀገሩንና ሕዝቡን ለመጥቀም ቃለ መሃላ መግባቱን በጭራሽ አያመለክትም፡፡ የምሁራን ደናቁርት የተሸከመች ብቸኛዋ ሀገር ኢትዮጵያችን መሆንዋን ተገንዝባችሁ አዳዲስና ለሀገርና ለወገን ተቆርቋሪ ምሁራን ለመሆን ጣሩ፤ በእውነቱ ከወጣቱ ብዙ ይጠበቃል፡፡ ከገንዘብ አምልኮትም ባፋጣኝ ውጡ፡፡ ገንዘብ ወገንን ያስከዳል፤ሀገርን ያሸጣል፤ሃይማኖትን ያስክዳል፤ የኀሊናን ሚዛንም ያናጋል፡፡ እነመለስም ሆኑ ከነሱ በፊት የነበሩት መሪዎች ባብዛኛው እነዚህ በመሳሰሉ ችግሮች የተጠቁና የሀገር ስሜታቸውን የራስ ወዳድነት ብል የበላው ነበሩ፡፡… በተለይ በህክምናው ዘርፍ የተሰማራችሁ ባለሙያዎች ምሥኪን ወገናችሁን በቀናነትና በትጋት ማገልገል እንድትችሉ፣ አንዳንዶቻችሁም በፍቅረ ንዋይ ተማርካችሁ ከተዘፈቃችሁበት ጠርዝ የለቀቀ የገንዘብ አሰባሰብና ኢሥነ ምግባራዊ የሆነ የህክምና አሰጣጥ እንድትወጡ …እግዚአብሔር ይርዳችሁ፡፡

አስተያየት ካለዎ፤ tmuchie95@gmail.com

  1. grumnew
    | #1

    what kind of curse has come upon us? what should we really do to undo the sorcery spelled upon us for centuries? Oh, God bless Ethiopia! ya solomon tekalign ‘hulum zero zero’ blo yezefenew tikikl neber rasum bemechereshaw zero hono arefew enji.

  2. MELKAMU
    | #2

    ስርየት መጥቶ ኢትዮጵያ ዳግም እንድታንሰራራ ዳግም ህዳሴ እንዲመጣ ከተፈለገ እንደ ፀሃፊው አይነት(ከአንጀት ከሆነ) እራሱን ወደ ውስጥ በጥሞና የሚመለከት ምሁራዊና አጠቃላይ ማህበረሰባዊ መፀፀትና ንስሃ መግባት ግድ የሚልበት ታሪካዊ ወቅት ላይ ነን፡፡ከዚህ በፊትም ለመናገር ሞክሬያለሁኝ ይህ አይነት እራስን እንደ ዜጋ እንደ ህዝብ እንደ ሀገር ወደ ውስጥ መመልከት(በተለይም የምሁራኖቻችን መፀፀትና ንስሃ መግባት) ከሌለና ዛሬም በጥራዝ-ነጠቅ ፖለቲካዊ እይታ አምባገነን ዲሞክራት እያልን እንደ በቀቀን የምናላዝን ከሆነ እውነተኛ ስርየትና ህዳሴ በኢትዮጵያ ውስጥ ከቶውንም እውን ሊሆን አይችልም፡፡በፖለቲካው ውስጥም ሆነ ከፖለቲካው ውጪ ያለነውን የኢትዮጵያውያን ምሁራን ምሁራዊ ድንቁርና እንደሚከተለው ባጭሩ ላስቀምጥ፡፡

    1ኛ)ቤተሰቦቹ እናቱና አባቱ ሂድ ጓዳ ግባ እያሉ ‘አምባገነን’ በሆነ አካሄድ እያሸማቀቁና እየገላመጡት (ባህላችንና ሃይማኖታችን የሚፈቅደው ተገቢ የልጅ ቅጣትና ተግሳፅ ጥሩነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ) ያሳደጉት ኢትዮጵያዊ ምሁር ሁሉ በዘመኑ አቅማቸው በፈቀደ ያስተማሩትና ያስተዳድሩት የነበሩት ንጉስ አፄ ኃይለስላሴ አገዛዝ ለምን በአንድ ጀንበር ዲሞክራት አይደለም ብሎ ዲሞክራሲ በአንድ ጀንበር እንዲመጣ በቀን ቅዠትና ስሜታዊነት ማስተዋል የጎደለው አመፀኛና ሃኬተኛ መሆኑና ነባራዊው ሁኔታ ከሚፈቅደው ከተገቢው አካሄድ ባፈነገጠ መንገድ ያለአግባብ ሌባ ሌባ ውሻ ውሻ እያለ ንጉሱንም እያበሻቀጠ መሳደቡና መገልበጡ አሁን ለመጣብን አደጋና መቅሰፍት አንዱ ምክንያት ነው፡፡ሀገር በዘመኑ ባለው በዲሞክራሲ ተረት ተረት ብቻ አልተመሰረተም እንደዚሁም አልተመራም እንዲያውም ከዚህ ይልቅ በቤተሰባዊ ስሜት ቢመሰረትና ቢተዳደር እንዴት መልካም እንደሆነ አልተረዳንም እንጂ፡፡ብዙዎች ኢትዮጵያውያን ምሁራንና ፖለቲከኞች ዲሞክራሲ በሚለው የምእራቡ አለም መጤ የፋሽን ቃል ከልክ በላይ ተጠምደዋል እንደዚሁም በዚህ አስተሳሰብ የቅዠት አለም ውስጥ ነው ያሉት፡፡በዚህ የተነሳም የሀገርና የህዝብን ስር የሰደደና የተስፋፋ የዘመናት ችግር በምርጫ ዲሞክራሲ ተረት ተረት ብቻ መፍታት እንደሚቻል በማሰብ ላለፉት 40 ዓመታት ያህል ሀገርንና ህዝብን ከፍተኛ ቀውስና ትርምስ ውስጥ ነው የከተተው፡፡ይህ ምሁራዊ ማህበረሰብ የወጣበትን ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ የቆየ ስነ-ልቦና ወግ ባህል ሃይማኖት ታሪክ ወዘተ በቅጡ ያላገናዘበ አካሄድ በመከተል ነው በጥራዝ ነጠቅ እይታ ሲያራምድ የኖረው፡፡ከነባራዊው እውነታ ባፈነገጠ ያልዘሩትን ለማጨድ መሞከር ወይንም መጠበቅ ተገቢ አይደለም፡፡ውድ ፖለቲከኞቻችንና ምሁራኖቻችን ሆይ ስለ ዲሞክራሲ በጥራዝ ነጠቅነት ስናስብ ብዙ እርቀት ሳንሄድ በቅርቡ በዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ሽፋን ጋዳፊን በዚያ አይነት ገልብጦና አጥፍቶ በሊቢያ የተከሰተውን ዳግም ዘመናዊ ቅኝ-ግዛትና ቀውስ ልብ ብለን እናስተውል፡፡
    ይህ ኢትዮጵያዊ ምሁራዊ ማህበረሰብ ቢያንስ የጥንት አምባገነን የሚባሉት ንጉሳዊ አገዛዞች ሲታገሉት የነበረውን የባእዳን ሃይሎች መስፋፋትና ቅኝ-ግዛት ዛሬ በዲሞክራሲ ሽፋን በረቀቀና በተቀነባበረ መንገድ እየተዘፈቀበት ነው ያለው፡፡ስለዚህም ይህ የዘመናችን ኢትዮጵያዊ ምሁራዊ ማህበረሰብ ልብ የማይገዛና ምሁራዊ ድንቁርና የሚያጠቃው ነው ለማለት እደፍራለሁኝ፡፡ታዲያ እነዴት ብሎ ነው ይህ ዘመነኛ ምሁራዊ ማህበረሰብ የሀገሩን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውነትን ህልውናና ደህንነት ዛሬ ለማስጠበቅና ለማስቀጠል እያቃተው እየተንገዳገደና እርስ በርሱ ባለመግባባትና ባለመተማመን እየተናከሰ ያለ ሆኖ ሳለ እንደነ አፄ ምኒልክ ያሉትን የአውሮፓን ተስፋፊ ጭምር በዲፕሎማሲም ሆነ በሃይል ያንበረከኩና የኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውነትን ዋና መሰረት የጣሉ የታሪክ ፋና ወጊዎችን አምባገነን እያለ ለማውገዝና በእነሱ ላይ አፉን ለመክፈት የሞራል ብቃት የሚኖረው?በእውነቱ በዘመነ ወያኔ ያለውን የኢትዮጵያን የኢትዮጰያዊነትን የኢትዮጵያውያንን አጠቃላይ ሁኔታ ሳስብ አንዳንድ ጊዜ ሲወራ እንደምንሰማው እውነትም ኢትዮጵያ “ሰው አይብቀልብሽ : ወንድ አይብቀልብሽ” ተብላ የተረገመች ነው የሚመስለው፡፡የኢትዮጵያውያንንም ምሁራኖችና ፖለቲከኞች ሳስብ ይህ ነገር ትዝ እያለኝ እውነት እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ውድ ፀሃፊ ሆይ ዛሬ እኛ ኢትዮጵያውያን አጠቃላይ የትውልድ ዝቅጠትና ቀውስ ውስጥ(Generational Systemic Crisis) ውስጥ ነው ያለነው፡፡ምናልባት ብዙዎቻችን ዛሬ በዘመነ ግሎባል ካፒታሊዝም በገንዘብ ኃይል(በእርዳታም በብድርም በዝርፊያና በሙስና) ብቻ እንደ ሸቀጥ ከውጪ እያግበሰበስን ባሰገባናቸውና በየአደባባዩና በየመንገዱ በምናያቸው ዘመን አመጣሽ አርተፊሻል ብልጭልጭ ነገሮች የተነሳ ብዙዎቻችን ይህ እውነታ ላይገለጥልን ይችል ይሆናል፡፡እውነታው ግን አጠቃላይ የትውልድ ዝቅጠትና ቀውስ ውስጥ(Generational Systemic Crisis) ውስጥ መሆናችን ነው፡፡እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ዛሬም ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን ምሁራኖቻችንና ፖለቲከኞቻችን ችግሩ የአምባገነንነት ወይንም የተራ የምርጫ ዲሞክራሲ እጦት እንደሆነ እያላዘኑብን ነው፡፡የሚገርመው ግን ለእነሱ በምርጫ ዲሞክራሲ ዙሪያ በሚያቀነቅን የፓርቲ ፖለቲካ ሰበብ በየሆቴሎችና በየስብሰባ አዳራሾች የሚወራው ዲስኩርና በዚህም ስም የሚወረወረው ገንዘብ ከእነሱ የድግስ ሆያ ሁዬ ግርግርና ፌሽታ ባለፈ ለተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ብዙም የሚፈይድ አለመሆኑ ነው፡፡
    2ኛ)ሌላው ኢትዮጵያ ዛሬ በዘመናዊ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ውስጥ ነው፡፡ባእዳን ሃይሎች ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛት ለመግዛት ለዘመናት ሲጥሩ የነበረ ቢሆንም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ግን ሳይሳላላቸው እንደቀረ የሚታወቅ ነገር ነው፡፡ነገር ግን “ያገሩን ሰርዶ ባገሩ በሬ” እንዲሉ መለስ/ወያኔ እና ኢሳያስ/ሻእብያ የሚባለውን ቅጥረኛና ባንዳ ከሃዲ ሃይልን በረቀቀና በተቀነባበረ መንገድ በመጠቀም እነሆ ዛሬ በአድዋ ድልና በሌላም ምክንያት ለዘመናት ጥርስ ሲነክሱባት የቆዩት ባእዳን ሃይሎች ዛሬ ህልማቸው በመለስ/ወያኔ እና ኢሳያስ/ሻእብያ እውን እየሆነላቸው ነው፡፡ከዚህ በመነጨም ንጉሱን ፊውዳል ደርግን አምባገነን ጨፍጫፊ ወዘተ እያለ ሲያወግዝ የነበረ ኢትዮጵያዊ ምሁርና ፖለቲከኛ ሁሉ ከንጉሱና ከደርግ ውድቀት በኋላ ከደደቢት በረሃ ዲሞክራሲና ዳቦ ይመጣል ብሎ በተስፋ ከመጠበቅ በዘለለ ኢትዮጵያ ወደፊት ምን አይነት ነገር እንደሚጠብቃት አርቆ ማስተዋል አልቻለም ነበር፡፡የኢትዮጵያ አጠቃላይ ህልውናና ደህንነት ጉዳይ በውስጥ አገዛዞች ዲሞክራሲያዊነትና አምባገነንት ላይ ብቻ የሚያነጣጥር ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን መልካም ከማይመኙ ከውጪ ከባእዳን ሃይሎች ፈተና ጋር ጭምር የተቆራኘ እንደሆነ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ምሁርና ፖለቲከኛ ፈፅሞ ለመረዳት አልቻለም፡፡ከዚህ በመነጨም መለስ/ወያኔ ስልጣንን ሀ ብሎ ሲቆናጠጥ ኤርትራን ገንጥሎ አስገንጥሎ ኢትዮጵያን የባህር በር አልባ አድርጎ የመጣ እኩይ ቅጥረኛ ሃይል መሆኑ እየታወቀ ከዚህ ሃይል ዲሞክራሲንና ስልጣንን ከምርጫ ኮሮጆ መጠበቅ ከእባብ እንቁላል እርግብ እንደመጠበቅ ማለት ነው፡፡
    እኔ ብዙዎች ምርጫ 97 ን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ዲሞክራሲን በሚመለከት እንዳመለጠን አንድ ትልቅ የታሪክ አጋጣሚ መቁጠራችን በባእዳን ሃሎችና በመለስ/ወያኔ እና ኢሳያስ/ሻእብያ ቀድሞውኑ ለዚህች ሀገር በረቀቀና በተቀነባበረ መንገድ የታቀደላትን የጥፋትና የመበታተን አደጋ አርቆ ካላሰበ ሰው የሚጠበቅ እይታ ነው፡፡ስለዚህም ልብ የምንገዛና አርቀን የምናስተውል ከሆነ ምርጫ 97 እንዲያውም ስለ ዲሞክራሲ መልካም እድል ማምለጥ ሳይሆን መረዳት ያለብን የዚህን ተቃራኒ ኢትዮጵያ ምን አይነት እኩይ የሆነ ሃይልና አገዛዝ ውስጥ እንደገባች ቆም ብለን ልንረዳበት የተከሰተ የታሪክ አጋጣሚ ነበር፡፡መለስ ከ97 ምርጫ ክስተት በኋላ ከስህተታችን ተምረናል ሲሉን እንዴት ነው የተረዳናቸው እረ?ይህንን ክስተት በምን አይነት ምሁራዊ ድንቁርና ነው እየተረጎምንና እየተረዳን ያለነው? ታዋቂው ኢትዮጵያዊ ሳይንቲስትና ኢንጂነር ቅጣው እጅጉ አንድ ወቅት የተናገሩት ግን በእርገጥ ኢትዮጵያ ሰው አጥታም ፈፅሞ እንዳላጣች የሚያመላክት ነበር፡፡አዎ በእርግጥ አምባገነን ዲሞክራሲ የሚል የተለመደ የፖለቲከኛ የአፍ መፍቻ ቃል ዘወትር ካፋቸው የማይለይና ይህንንም እንደበቀቀን የሚዘምሩ የተለመዱ ብልጣብልጥና ሸፍጠኛ ጥራዝ-ነጠቅ ፖለቲከኞች ሞልተውናል የጠፋው ግን እንደዚህ እንደ ቅጣው እጅጉ አይነት እውነተኛና አስተዋይ ሰው ነው እንጂ፡፡ታዲያ ምን ብለው ነበር እኝህ ታላቅ ሰው?
    1ኛ)ኢትዮጵያ ለቅኝ ግዛትና ተስፋፊዎች አልበገረም በማለቷና ማንነቷን በማስጠበቅና ለሌሎችም አርአያ በመሆኗ የተነሳ ባእዳን ተስፋፊ ሃይሎች ለዘመናት ጥርስ እንደነከሱባትና ይህንንም ለመበቀል የታሪክ አጋጣሚን እንደሚጠብቁ፡፡
    2ኛ)መለስ የተባለውን ቅጥረኛ ሰው በትክክል እንዳልተረዳነውና በዚህ የተነሳም ለሚመጣብን መከራና ቀውስ ሁሉ በዋናነት ችግሩ የእኛ እንጂ የመለስ አለመሆኑን፡፡እባብ እባብነቱን ወይንም ጊንጥ ጊንጥነቱን ስለማይቀይር እንዳንጎዳ መጠንቀቅ የራሳችን ፋንታ ነው አይነት አባባል ነው፡፡
    3ኛ)በየባእዳን ሀገሮች ኢምባሲዎች እንደ ቁራ ለተቃውሞ መጮህ ምንም የሚቀይረው የረባ ነገር ሊፈይድ እንደማችልና ዘለቄታዊ መፍትሄውም ባለጌን ባለጌ ብሎ ከራስ ላይ ማውረድ ብቻ መሆኑን አስረግጥው ተናግረው ነበር፡፡
    እንግዲህ ይህንን ከላይ ያለውን 3 መሰረታዊ እውነታ አለመረዳትና ከመለስ/ወያኔ ዲሞክራሲና ዳቦ መጠበቅ ምሁራዊ ድንቁርና ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ ይህንን እንደ ኢንጂነር ቅጣው እጅጉ አርቆ መረዳት ደግሞ ከምሁርነትም በላይ በራሱ ነቢይነት ነው፡፡ታዲያ ከዚህ እውነታ ጋር በተያያዘ የፖለቲካውን ምህዳር በሞኖፖል በተቆጣጠሩት በአብዛኞቹ ጥራዝ-ነጠቅ ፖለቲከኞቻችን ምሁራዊ ድንቁርናና አደርባይነትና በዚህም የተነሳ እየተፈጠረ ባለው ጥፋትና አደጋ በአንድ በኩል ሳዝን በሌላ በኩል ደግሞ በእንደነ ኢንጂነር ቅጣው እጅጉ ዶ/ር ፈቃዱ በቀለና ሌሎችም አይነቶች ደግሞ እፅናናለሁኝ፡፡ስለዚህም እውነተኛ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ወይንም ህዳሴ ሊመጣበት ከሚችለው ወሳኝ ነገር መካከል ደግሞ እኔንም ጨምሮ የኢትዮጵያዊ ምሁራዊ ማህበረሰብ ድንቁርና ሲቆምና ይህም ማህበረሰብ ወደ ውስጥ እራሱን በመመልከት ተገቢውን ምርመራ አድርጎ ለሰራው ምሁራዊ ስህተትና ጥፋት በመፀፀት ንስሃ ገብቶ ስርየት ሲመጣ ብቻ ነው፡፡በአለማዊውም ሆነ በመለኮታዊ ፍርድ እንኳን ለጥፋት የሚሰጥ ፍርድ እንደ ግለሰቡ ንቃተ-ህሊና ደረጃና ህገ-ልቦናን መሰረት ያደረገ ጭምር ነው፡፡ይህ ብቻም አይደለም በእርግጥ ፊደል ያልቆጠረውም ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብም ጭምር እንደ ምሁሩ ሁሉ እርሱም እንደ ንቃተ-ህሊናው ደረጃ በየደረጃው የጥፋቱና የውድቀቱ ተባባሪ ነውና እንደ የደረጃው ከታሪክ ተጠያቂነት ከቶ የሚያመልጥ ሊሆን አይችልም፡፡በራቸውን በቅጡ ሳይዘጉ ሰውን ሌባ ይላሉ እንዳለው ሌባ የራሳችንን የቤት ስራ እንደ ህዝብ እንደ ዜጋ በቅጡ ካልሰራንና ሃላፊነታችንንም በቅጡ ካልተወጣን እንደ መለስ/ወያኔ አይነት ሀይሎችን ብቻ ዘወትር መውቀስና ተጠያቂ ማድረግ ብቻውን በህሊናችን በትውልዱ በታሪክና በፈጣሪ ፊት በሃላፊነት ከመጠየቅ አያድነንም፡፡
    ስለዚህም ከአንጀት ከሆነ የፀሃፊው አይነት ምሁራዊ መፀፀትና ንስሃ መግባት የሚያሳየው አሁን እያደረግነው ባለው እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ አንድ ትልቅ እርምጃ እንደሆነ ነው፡፡እውነቴን ነው የምላችሁ ኢትዮጵያ ውስጥ የጠፋው አሁን ይህ አይነት አካሄድ ነው፡፡ይህንን ስል ግን መለስ/ወያኔን የመታገሉን ዋና አንገብጋቢ አጀንዳ በመርሳት አይደለም፡፡ነገር ግን ይህ በራሱ የዚህ አንገብጋቢ ትግል ዋና አካል ጭምር ነው፡፡የመለስ/ወያኔን ነገር አውርተነው አውርተነው ከቶ የሚያልቅ አይደለም፡፡አሁን ወደራሳችን ተመልሰን ይህ እስኪሆን ድረስ እንዴት እጃችንን አጣጥፈን ተቀመጥን ወደሚለውና ይህንን አደጋና ቀውስ ለመቀልበስ ምን እናድርግ በሚለው ላይ መሆን ነው ያለበት፡፡ይህ እራስን ወደ ውስጥ የመመልከት እይታና አላማ ባለፈው ነገር በከንቱ ለመወቃቀስም አይደለም እንዲያውም ንስሃ በመግባትና በመፀፀት እራስን ለማደስና አዲስ ጉልበትና ሃይል ለማግኘት እጅግ ጠቃሚ ስለሆነ ጭምር ነው፡፡በስተመጨረሻ ለፀኃፊው አድናቆቴን ልገልጽ እፈልጋለሁኝ፡፡
    እግዚአብሄር የኢትዮጵያዊነት ፀጋችንን ክብራችንን ተስፋችንን ፍቅራችንን መተማመናችንን መግባባታችንን ዳግም ይመልስልን!!!
    እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይጠብቅ ይባርክ!!!

  3. ምንትዋብ
    | #3

    በአሁኑ ጊዜ ይሄ የሚወራ አይደለም የሥራ ፈት ወሬ ይመስላል

  4. Hello
    | #4

    Dear Tarekegn

    If you have reached to this general conclusion with one book, I advise you to revise your educational background which you advised others to improve. There were many journalists and politicians in prison, I guess over 100. Only Sisay and Wosen have so far wrote their experience. There are other journalists who have not yet written their experience. Above all we expect a book from Dr Hailu Araya. We need writers to tell us about Wosen himself. If we believe rumors, Wosen himself was one of the prisoners who had a lot of personal and psychological problems, who is a born accuser and with inferority complex in addition to his psychosis. That accusation also needs to be investigated. Dr Yakob needs also to tell us about his experience. He has recently released a book about Assab, and hope can say something about Kaliti. Dr Berhanu , prof Mesfin etc must write too. I think we expect over 100 books from kaliti prisoners to have a balanced conclusion. Let’s urge others to write books. For me by all benchmarks Kaliti prisoners were by far better than the woyanes. There could be some spoilers, but don’t forget that Kaliti had produced people like Sisay Agena, Dereje H/wold, Fasil Yenealem, Eskinder Nega, Dawit Kebede,Dr Hailu Araya, Andualem Arage, Dr Berhanu Nega,Muluneh Eyoel, Bertukan Midekesa, Sekalem Fasil, and many many more. Where do you place the contribution of these people who have given themselves for freedom?
    I am very much curious to know about Kaliti, and Wosen’s book may help us to know some, but not enough.

  5. Tewabech
    | #5

    what do you mean mintwab?no.3 above.

  6. Hello
    | #6

    Dear Tarekegn

    If you have reached to this general conclusion with one book, I advise you to revise your educational background which you advised others to improve. There were many journalists and politicians in prison, I guess over 100. Only Sisay and Wosen have so far written their experience. There are other journalists who have not yet written their experience. Above all we expect a book from Dr Hailu Araya. We need writers to tell us about Wosen himself. If we believe rumors, Wosen himself was one of the prisoners who had a lot of personal and psychological problems, who is a born accuser and with inferority complex in addition to his psychosis. That accusation also needs to be investigated. Dr Yakob needs also to tell us about his experience. He has recently released a book about Assab, and hope can say something about Kaliti. Dr Berhanu , prof Mesfin etc must write too. I think we expect over 100 books from kaliti prisoners to have a balanced conclusion. Let’s urge others to write books. For me by all benchmarks Kaliti prisoners were by far better than the woyanes. There could be some spoilers, but don’t forget that Kaliti had produced people like Sisay Agena, Dereje H/wold, Fasil Yenealem, Eskinder Nega, Dawit Kebede,Dr Hailu Araya, Andualem Arage, Dr Berhanu Nega,Muluneh Eyoel, Bertukan Midekesa, Sekalem Fasil, and many many more. Where do you place the contribution of these people who have given themselves for freedom?
    I am very much curious to know about Kaliti, and Wosen’s book may help us to know some, but not enough.

  7. Lucy in America
    | #7

    Tarekegn muche is another kidetu ayalew. Is this so important for the poor ethiopia’s people? alubaletegna ena hodamoch ye ethiopia andinet telatoch nachew. tarekegn muche lebe kaleh ena yetateketew suri yewonde kehone wode gonder gebeth EPPF tekelakele woyim arefeh tekemet. why do not you publisha book instead of posting so trash back bitting?

  8. ግዛቸው
    | #8

    ውይዘሮ/ወይዘሪት ምንትዋብ ምንድንው እሚሉት? ስራፈትስ እራስዎት ኖት:: ይህን ግሩም የብሶትአችንን መግልጫ ጦማር እንድይት የስራአጥ ውርየ ይመስላል ይባላለ? ነውር አይደለም? እየተስተዋለ እንጂ!የህዝብ ተቆርቁዋሪ እንድናጣ ነው ጥረቱ? ለማንኛውም ይታሰብበት::

አስተያየት መስጫው ተዘግቷል።