አክሱምና እስልምና በፍቅር ወርቁ
በአክሱማውያን ታሪክ «አልነጃሺ» የተባለ የሰለመ ንጉሥ ነበርን፡- ስለ ነቢዩ መሀመድ፣ የእስልምና ሃይማኖት እና ኢትዮጵያ ግንኙነት ዙሪያ ታሪክ የሚነግረን ሀቅ ምንድን ነው?
በፍቅር ለይኩን፡፡ [befikir12@yahoo.com/fikirbefikir@gmail.com]
ከጥቂት ወራት በፊት የመንግሥታቸውን የሥራ ሂደት ሪፖርት ለማሰማትና ከክቡራን የምክር ቤት አባላት ለሚቀርቡ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት በፓርላማ የተገኙት ክቡር ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ በሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ መስመሩን እየሳተ እየሄደ ስላለውና አንዳንድ በሃይማኖት ሽፋን የአክራሪነትና ጽንፈኝነት እንቅስቅስቃሴ ስለሚያራምዱ ግለሰቦችና ቡድኖች ማስጠንቀቂያና ማሳሰቢያ በሚመስል ንግግራቸው፡- ‹‹እንዲህ ዓይነቱን በሃይማኖት ሽፋን እየተካሄደ ያለውን የአክራሪነትና የጽንፈኝነት እንቅስቃሴ መንግስት ችላ እንደማይለውና በንቃት በመከታተል እርምጃ እንደሚወስድም በግልጽ አስረድተው ነበር፡፡››
ጠቅላይ ሚ/ሩ አክለውም በሀገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት ታሪካዊና ጥንታዊ የሆኑት ሁለቱ ሃይማኖቶች ክርስትና እና እስልምና ለረጅም ዘመናት በሀገራችን ተከባብረውና ተዋደው የኖሩና ይህ ልዩ የታሪክ እውነትም የተቀረው ዓለም እስከ አሁንም ድረስ የሚደነቅበትና በመልካም አርዓያነቱ የሚጠቅሰው መሆኑን አስታውሰው ይህን እውነታ የሚያስረግጥ አንድ ገጠመኛቸውን ለፓርላማው ክቡር አባላት እንዲህ አቅርበው ነበር ክቡር ጠቅላይ ሚ/ር መለስ፡-
በቅርቡ አሉ ጠቅላይ ሚ/ሩ አንድ ከወሎ ክ/ሀገር የገጠር ቀበሌ የመጣ ሰው/ወደጃቸው በዛ ቀበሌ ዝናብ በመጥፋቱ ምክንያት ድርቅ ስላጠቃቸው በቀበሌው ያሉ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኝ ክርስቲያኖች ታቦታቸውን ነቅለው ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ መቁረጣቸውን የሰሙ የእስልምና እምነት ተከታዮችና የዕድሜ ባለጸጋ አባቶች ክርስቲያን ወገኖቻቸውን ይህ ታቦት የእናንተ ብቻ እኮ አይደለም የሁላችንም ነው፡፡ በዚህ ቦታ ለብዙ ዘመን ቆይቷል እናም እባካችሁ ከዚህ ቦታ አትንቀሉት እኛም አላህን እንለማመናለን እናንተም እግዜርን ተማጠኑ በማለት ክርስቲያኖቹ ታቦታቸውን ነቅለው እንዳይሄዱ እንዳገላገሉ ለፓርላማው አባላት ተናገረው ነበር፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚ/ሩ በዚህ ንግግራቸው ሊያስተላልፉ የፈለጉት መልእክት ለብዙዎቻችን ግልጽ ይመስለኛል፡፡ በታሪካችን የቆየውና እንደ ምሳሌ የምንጠቀስበት በሃይማኖቶች መካከል ያለው መከባበርና መቻቻል በዚህ ዘመን እንዴት እየጠፋና ከመስመር እየለቀቀ እንዳለ ያሳሰቡበት መልእክት ይመስለኛል፡፡
በዛሬው ጹሑፌ ይሄንኑ በሁለቱ ሃይማኖቶች መካከል ለረጅም ዘመናት የዘለቀውን የመከባበር ባሕል እያጠፉና ወደ ጽንፈኝነትና አክራሪነት እየመሩ ካሉት ምክንያቶች አንዱ በሃይማኖቶች መካከል ያለውንና የነበረውን ታሪክ ከማጣመምና አንዳንዴም ደግሞ ያለ በቂ መረጃ በአፈ ታሪክ የሚነገሩ ትውፊቶችና ታሪኮች በአማኞች መካከል የተጋነነ ስሜትና የተሳሳተ አቋም እየፈጠሩ በሃይማኖቶች መካከል የነበረውን መልካም ግንኙነቶች ሲያሻክሩት እየታዘብን ነው፡፡ ከነዚህም መካከል በብዙዎች የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ እየተነገረና በሰፊው እየተጻፈለት ያለው የአክሱም ንጉስ «አልነጃሺ» እና አክሱማውያንም መስለማቸውንና ከዚህም የተነሳ አንዳንዶች አክሱም ቅዱስ የሙስሊም ከተማ ናት እስከማለት የደረሱበትን አጋጣሚዎችንም እየታዘብን ነው፡፡ እናም እስቲ በዚህና በሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ በትምህርትና በሥራ አጋጣሚ በእጆቼ ከገቡ ታሪካዊ ሰነዶችና መዛግብት በማጣቀስ ጥቂት ነገሮችን ልበል፡፡
በ፳፻ ወርኃ ክረምት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እያለሁ በእስልምና ሃይማኖትና በአክሱማውያን ስረወ መንግሥት መካከል የነበረውን ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ግንኙነት ለማጥናትና በዚህም ላይ ለሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ የሚሆነውን መመርቂያ የጥናት ጹሑፍ ለማዘጋጀት ከአሜሪካ ሜኔሶታ ግዛት ከሚገኝ ዩኒቨርስቲ ከመጣ አንድ ጎልማሳ ምሁር አሜሪካዊ ጋር ወደ ጥንታዊቷና ታሪካዊቷ አክሱም ከተማ ለመስክ የምርምር ጥናት አቅንተን ነበረ፡፡ በቆይታችንም ከአዲግራት ፳፭ ኪ.ሜ ርቀት ከሚገኘው የሙስሊሞች ቤተ አምልኮ ከሆነው «አል ነጃሺ» መስጊድ ተገኝተን ነበር፡፡
በዚሁ የመስክ ጉዞ ቆይታችንም በዛ ከሚገኙ በዕድሜ ባለጸጋ ከሆኑ የእምነቱ አባቶችና ሸህዎች ጋር ለጥቂት ሰዓታት እጅግ ደስ የሚያሰኝ ቆይታን አድርገን ነበር፡፡ እስካሁን ልረሳው ባልቻልኩት በልቤ ጽላት ውስጥ በማይደበዝዝ ቀለም በታተመ እጅግ በሚመስጥ ትህትና፣ ጨዋነትና የኢትዮጵያዊነት እንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ነበር አቀባበል ያደረጉልን እነዚህ የሃይማኖቱ አባቶች፡፡
እነዚህ የዕድሜ ባለጸጋዎች የመጀመሪያዎቹ የነቢዩ መሀመድ ተከታዮች በነቢዩ ምክርና ትዕዛዝ ወደ አክሱም ግዛት እንዴት እንደመጡና በአክሱም ስለተደረገላቸው አቀባበል፣ በዛም እስልምናን ለማሳፋፋት ስላደረጉት እንቅስቃሴና ይህም እንቅስቃሴያቸው በወቅቱ የአክሱምን ንጉሥ እንደ እነዚህ ሰዎች እምነት «አል ነጃሺን» ጭምር ሳይቀር የእስልምናን እምነት በገዛ ፈቃዱ እንዲቀበል እንዳደረጉትና በአክሱም ግዛት የሚኖሩ ሰዎችና አንዳንድ መነኮሳትም ጭምር ሳይቀሩ እስልምናን መቀበላቸውን፣ ስለ እስልምና ሃይማኖትና ኢትዮጵያ ታሪካዊ ግንኙነት ጭምር በአፈ ታሪክ ከአባቶቻቸው የተቀበሉትን ትውፊት ከቅዱስ ቁርአንና እንዲሁም ከአረቡ ምድር ታሪክ አዋቂዎች የታሪክ ሰነድና አፈ ታሪኮች በማጣቀስ ጭምር ያስረዱን በራስ መተማመን ፍጹም የተረጋጋ ስሜት ውስጥ ሆነው ነበር፡፡
ከዛም ባሻገር ከመጀመሪያዎቹ ወደ አክሱም ከመጡት የእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል የነቢዩ ሙሀመድ ልጅ የሆነቸው ሩቂያ፣ ባለቤቷ በኋላም ሦስተኛ ካሊፋ የሆነው ኡስማን አቡበከር፣ ጃፋር አቡጣሊብና የሌሎችንም የመጀመሪያዎቹ ስደተኞች በአክሱም በሰላም መቆየታቸውንና ከእነዚህም ስደተኞች መካከል አስራ አምስት የሚሆኑት በዚሁ በአልነጃሺ መስጊድ ቅጥር መቀበራቸውን የሚያረጋግጥ መካነ መቃብራቸውንም በእነዚህ የእምነቱ አባቶችና ዕድሜ ባለጸጎች ልብን ከሚመስጥ ትረካቸው ጋር ለመጎብኘት ችለን ነበር፡፡ እነዚህ የእምነቱ አባቶች በገለጻቸው መጨረሻም በነቢዩ መሀመድም ሆነ ከእርሱ በኋላ በተነሱ የእስልምና ታላላቅ አባቶች ዘንድ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በሙስሊም ሃይማኖት አማኞችና በአረቡ ዓለም ያላቸውን ታላቅ ተቀባይነት፣ መፈራትና ክብር የነገሩን ታላቅ በሆነ ሀበሻዊ ኩራትና ደስታ ውስጥ ሆነው ነው፡፡
ለሰዓታት ባደረግነው ቆይታችን ይህ አሜሪካዊ ተመራማሪ ለመመረቂያ ጹሑፉና ለምርምር ጥናቱ የሚጠቅሙትን መረጃዎች በድምጽ በምስልና በጹሑፍ ከከከተበ በኋላ በሰጡን ሰፊ መረጃዎችና ትንታኔዎች ላይ ሞቅ ያለ ውይይትና ክርክር እያደረግን ወደ ጥንታዊቷ አክሱም ከተማ ተመለስን፡፡ ጉዞአችን እጅግ አስደሳችና ውጤታማ በመሆኑ በወቅቱ የተሰማን ስሜት እጅግ ልዩ ነበር፡፡ እስቲ የጉዞአችንን ማስታወሻ ትረካ በዚሁ ልግታውና አንድ ጥያቄ እናንሳ፡-
ለመሆኑ አክሱማውያን/ኢትዮጵያውያን ከእስልምና ሃይማኖት ጋር የነበራቸው ታሪካዊም ሆነ ሃይማኖታዊ ግንኙነት አንዳንዶች እንደሚሉት የአክሱምን ንጉሥና አክሱማውያን ከክርስትና ወደ እስልምና እስኪያፈልስ ድረስ ጉልበት ነበረውን? ስለ ‹‹አልነጃሺ›› እና ስለ አክሱማውያን መስለም የሚተረከው ታሪክ ምን ያህል እውነት ነው? የታሪክ ድርሳናትና መዛግብት እንዲሁም በዚህ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ የሆነ ጥናትና ምርምር ያደረጉ ምሁራንስ ምን ይላሉ፣ ምንስ ጻፉ…፡፡
በእርግጥስ በኢትዮጵያውያኑ፣ በምዕራባውያኑና በአርብ ሀገራት የታሪክ ተማራማሪዎች፣ ሊቃውንትና ጸሐፍት የታሪክ ድርሳናት ዘንድ በእርግጥ የአክሱም ንጉሥና አክሱማውያን ስለመስለማቸው ነው የሚነግሩን ወይስ በተቃራኒው፡፡ በእኛስ ዘመን «ኢትዮጵያ ክርስቲያናዊ ደሴት» የሚለው የቆየው ብሂልና አገላለጽ በአንዳንድ ሙስሊሞች ዘንድ ለምን ቅር ከማሰኘት አልፎ ከቃላት ውርጅብኝ ወደ ቁጣና ወደ ግጭት እና ጥቃት ለመሻገር እንዲበቃ ያደረገው የዘመናችን ጽንፈኞችና አክራሪዎች «የአልነጃሺ ሰልሟል» እና «አክሱም የመጀመሪያዋ የእስልምና እምብርት ከተማ ናት» መፈክርና ተጨባጭ ማስረጃ የሌለው ትረካ ከሃይማኖቱ ባለፈ ግብ ያደረገውና የተቀመመበት ታሪካዊ መነሻና ዳራው ውሉ ከየት እስከ የት ሊመዘዝ ይችላል፡፡ በአንዳንድ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ከመካ፣ ከመዲናና ከሶሪያዋ ደማስቆ ቀጥሎ አክሱም አራተኛዋ የእስልምና ቅዱስ ከተማ ተደርጋ መጠቀሷስ ውስጠ-መልእክቱ ምንድን ነው፡፡
ከዚህ ሁሉ የታሪክ ሽሚያ ወይም ዝርፊያና ሃይማኖትን ማስፋፋት ዘመቻ ባሻገር በሀገራችን በሁለቱ ሃይማኖቶች ዘንድ በአንጻሩም ቢሆን ለዘመናት የቆየው ተከባብሮና ተዋዶ እስከ ጋብቻ መጣመር ድረስ የዘለቀውና ለተቀረው ዓለም ሁሉ ምሳሌ እስከመሆን የዘለቀው በሰላም የመኖር ባሕል በእኛ ዘመን በተዛባ ታሪክና በጓዳው ውስጥ ተረት ተረት/አፈ ታሪክ በተወለደ የአክራሪነትና የጽንፈኝነት መንፈስ እንዴት እንዲህ ያለው አደጋ ሊጋረጥበትና እንዲህ ዓይነቱ አጣብቂኝ ውስጥ ሊገባ ቻለ፡፡ ከዚሁ ሁሉ ሁነቶች ጀርባና ስለ ‹‹አል ነጃሺ›› አክሱምና አክሱማውያን ከእስልምና ሃይማኖት ጋር የነበራቸውስ ግንኙነት ምን ድረስ ነው በሚሉት ጉዳዮች ላይ የታሪክ መዛግብትና ሰነዶች ምን ይላሉ የሚለውን በጣም በአጭሩ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በዓለማችን ተወዳዳሪና አቻ ካልተገኘለት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጀምሮ በእስልምና ሃይማኖት መጽሐፍ ቅዱስ ቁርአን፣ ዓለማችን አሁን ለደረሰችበት ስልጣኔና እድገት ትልቁን ድርሻ በሚሰውዱት በግሪካውያኑ ታላላቅ የጥበብ፣ የፍልስፍና እና የታሪክ መጻሕፍት ውስጥ ስሟ ተደጋግሞ በአድናቆት የተጠቀሰ በመካከለኛው ክፍለ ዘመንም ለአውሮፓውያን አሳሾችና ተጘዦች የልብ ትርታ ሆና የቆየችና «የታላቁ የቅዱስ ዮሐንስ ክርስቲያን ሀገር» በመባል ትልቅ ስምና ዝናን ያተረፈች ሀገር መሆኗን በርካታ አሳሾችና የታሪክ ድርሳናት የመሰከሩላት ሀገር ናት፡፡
ከዚህም ባሻገር በጥበብ ፍቅር አቅሏን ለሳተችው በቅዱስ ወንጌል በጌታችን አንደበት ‹‹የጥበብን ሀሰሳ ረጅም ጉዞዋ›› በአድናቆት የተተረከላት የንግሥተ ሳባ ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ፤ ይህች ንግሥታችንም በሩቅ ሆና በሰለሞን የጥበብ ዝና መንፈስዋ ሸፍቶባት ይህን ታላቅ ጥበብ በጆሮዋ ሰምታ በዓይኗ አይታ ለማረጋገጥ ከምድር ዳርቻ እስከ ዛሬ ድርስም ሆነ ወደፊትም አንድ ሴት ለአንድ ወንድ ልሰጠው ከምትችለው ስጦታ ወደር ያልተገኘለትና እንደ ሁለቱ እንግሊዛውያን የታሪክ ምሁራንና ጸሐፍት ኖርማን ፐርን እና ቨርኖን ባርሎው Quest for Sheba በተባለው መጽሐፋቸው በአድናቆት እንደገለጹት፡-
በንጉሡ በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ሲተመን ከሃያ አምስት ሚሊዮን ፓውንድ በላይ የሚገመት ስጦታን ይዛ፣ (ይህ የስጦታ መጠን ስንሰማ ዛሬ በድህነት ቀንበር ስር ወድቀን በቀን ሦስቴ እንዃን እንደ ነገሩ በልቶ ለማደር የመጽዋቾችን በር ነጋ አልነጋም ብለን ደጅ ለመጥናት ለተገደደን ኢትዮጵያውያን ወይ ነዶ… እንዲህ ካለው የታሪክ ሰገነት ተሸንቀጥረን ነው ለዚህ የበቃነው አያሰኝም ትላለችሁ አንባቢዎቼ) በሺህ ግመሎችና የጋማ ከብቶች የተጫኑ ውድ የሆኑ ማዕድናትን አስጭና የተጓዘች የጥበብ ምርኮኛ ንግሥት የሳባ ሀገር ኢትዮጵያ የዓለማችን የእግዚአብሔር ምስጢር ምድር እንደሆነች በብዙዎች የተጻፈላትና የሚደመሙባት ሀገር ናት፡፡ ይህች እናት ሀገራችን ኢትዮጵያ ገና ብዙ የአርኪዮሎጂና የታሪክ ምርምር ጥናት የሚያስፈልጋት ባለ ብዙ ምስጢርና ባለ ብዙ ኅብር ባለታሪክ ምድር ናት፡፡
ሀገረ ኢትዮጵያ እስከዛሬም ድረስ ዓለም ምስጢርና እንቆቅልሽ የሆነበት የቃል ኪዳኑ ታቦት የሚገኘው በእኔ ምድር ነው ኢትዮጵያውያንም የዚህ ታላቅ የእግዚአብሔር ምስጢር ጠባቂና ባለአደራ ናቸው የምትል ብቸኛዋ የዓለማችን ሀገር ናት፡፡ ከዚህም የተነሳ የብዙዎችን ጎብኚዎች አሳሾችና ታሪክ ተመራማሪዎች ቀልብ የሳበች ሀገር ለመሆን በቅታለች፡፡ በአንድ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የሆነ የሽያጥ ጣራን ለመቆናጠጥ የበቃው በእንግሊዛዊው ግራሃም ሀንኩክ የተጻፈው The Sign and the Seal የተባለው መጽሐፍ ኢትዮጵያን ከጥንት ጀምሮ በመንፈሳዊ ኩራት ስለሚናገሩለት ስለእዚሁ ስለ ቃል ኪዳኑ ታቦት ሀሰሳ/ፍለጋ የተጻፈ ክርስቲያኑን ዓለም በሰፊው ያነጋገረ መጽሐፍ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
አስገራሚው ገጠመኝ ደግሞ ኢትዮጵያ ከዓለማችን ሀገራት በተለየ መልኩ በመካከለኛው ምስራቅ ለተገኙት ለሦስቱ ታላላቅ ሃይማኖቶች ለአይሁድ፣ ለክርስትና እና እስልምና ቀዳሚ ማእክል መሆኗ ነው፡፡ ይህን እውነት የመካከለኛው ምስራቅና የዐረብ ሀገራት እውቅ የታሪክ ተመራማሪ፣ የእስልምና ሃይማኖት ምሁር፣ የእስራኤልና የአረቡ ዓለም/የፍልስጤም ግጭት ታሪክ ከፍተኛ ተንታኝና በአንድ ወቅትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ መምህሬ የነበሩት አሁን በሕይወት የሌሉት በአንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ Department of History and Heritage Management ባልደረባ የነበሩት ፕሮፌሰር ሁሴን አህመድ Aksum in Muslim Historical Traditions በሚል ጥናታዊ ጹሑፋቸው አክሱምን ሁለቱን የመካከለኛው ምስራቅ ሃይማኖቶች በሰላም ያስተናገደች ከተማ መሆኗን ሲገልጹ፡-
Aksum possesses the unique distinction of being at once the cradle of both Christianity and Islam in Ethiopia, and perhaps represents perhaps the earliest example of a geographical setting favorable for a peaceful encounter and harmonious coexistence between two great monotheistic religions: Christianity and Islam.
በተጨማሪም ፕሮፌሰር ሁሴን አህመድ al-Tiraz al-Manqush fi Mahasin al-Habush (The Colored Brocade on the Good Qualities of the Ethiopian) በሚል ርእስ መሀመድ አብዱል ባኪ አል ቡከሃሪ አል ማቅዚ (በዚህ የዐረቢኛ ስም የአማርኛ ትርጉም ላይ ሰህተት አድርጌ ከሆነ አስቀድሜ አንባቢያንን ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡) እ.ኤ.አ በ1583 ዓ.ም የጻፉትን ታሪካዊ ሰነድ ዋቢ አድርገው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በነቢዩ መሀመድና በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ያላቸውን ተወዳጅነት እና ክብርም እንዲህ ገልጸውታል፡-
«Who brings an Ethiopian man or woman into his house brings the blessings of God there.»
በሀገራችንም ሆነ በዐረብ ታሪክ ጸሐፊዎችና የእስልምና እምነት ሊቃውንቶች ዘንድ የተጻፉት የታሪክ ድርሳናት አክሱማውያን የነቢዩ መሀመድን ተከታዮችን በሞቀ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ እንዳስተናገዷቸውና በአክሱም ግዛት በነጻነት የመኖር መብት እንደተሰጣቸው በግልጽ ያስረዳሉ፡፡ በአክሱማውያን ግዛት እነዚህ በእምነታቸው ምክንያት የተሰደዱ ሰዎች በሰላም መስተናገዳቸውና በነጻነት መንቀሳቀስ መቻላቸው ቁጭትና እልህ ውስጥ የከተታቸው የመካ ሹማምንት በብዙ ስጦታና አጀብ ወደ አክሱም በላኳቸው መልእክተኞቻቸው እነዚህ በስደት ወደ ግዛትህ የገቡ ሰዎች የእኛንም ሆነ የአንተን እምነት የማይከተሉ ከሃዲያንና አረመኔዎች ናቸውና አሳልፈህ እንደሰጠን አደራ ጭምር የታከለበት መልእክት በዘመኑ ወደነበረው የአክሱም ንጉሥ ልከው እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡
አክሱማዊው ንጉሥ ግን እነዚህን ሰዎች አስቀርቦ ስለተሰደዱበትና አሁን ደግሞ በጥብቅ ስለሚፈለጉበትና ስለተከሰሱበት እምነታቸው ከጠየቃቸው በኋላ ወደ መካ ሹማምንት በላከው መልእክት እነዚህ ሰዎች ምንም ክፉ ነገር አላገኘሁባቸውምና አሳልፌ ልሰጥህ አልችልም በሚል መልእክተኞቹም ያመጡትን ስጦታና መደለያ ይዛችሁ በሰላም ወደመጣችሁበት ወደ መካ መሄድ ትችላላችሁ በማለት ቁርጣቸውን ነግሮ እንዳሰናበታቸው በተለያዩ የአረብ ሀገራት ታሪክ ጸሐፍት ሰነዶች ውስጥ በግልጽ ተጠቅሷል፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ አንዳንድ የአረብ ጸሐፊዎችና ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የሰለመው የአክሱም ንጉሥ «አልነጃሺ» ለነቢዩ መሀመድ ተከታዮች ባደረገው ውለታና እንክብካቤ የተነሳ ከነቢዩ ጋር ልዩ የሆነ ወዳጅነት መስረተው እንደነበርና ይህ መልካም የሆነ ግንኙነታቸውም አድጎ ይኸው የአክሱም ንጉሥ ነቢዩ መሀመድን ለመጎብኘት ሲጓዝ በመንገድ ላይ ማረፉንና በወቅቱም በዚህ መጥፎ አጋጣሚ ልባቸው የተነካ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሐዘናቸውን የገለጹበት ግጥም እሰከ አሁንም ድረስ በትውፊት ደረጃ በኢትዮጵያውያን ሙስሊም እንደሚታወስ ፕ/ር ሁሴን በጥናታቸው እንዲህ ያወሱታል፡-
ወዳንቱ ሲመጣ ወዳንቱ ሲሸሽ፣
ትግሬ ላይ የቀረው «አህመድ አል ነጋሽ/አልነጃሺ፡፡»
አልነጃሺ ከነቢዩ መሀመድ ጋር የወዳጅነት የደብዳቤ ልውውጥ ማድረጋቸውንና እስከአሁንም ድረስ ብዙዎችን እያከራከረ ስላለውና የአክሱም ንጉስ ሰልሟል የሚለው አገላለጽና በክሱማውያን ንጉስና በነቢዩ መሀመድ መካከል ተደርገዋል የተባሉት የወዳጅነት የደብዳቤ ልውውጦችም ከአፈ ታሪክ በዘለለ ምንም ተጨባጭ ማስረጃ የሌላቸውና እንዲሁም የአክሱም ንጉስ ስለመስለሙ የሚነገሩ አፈ ታሪኮችና በአንዳንድ ጸሐፍት ዘንድ በዋቢነት የሚቀርቡ ደብዳቤዎችም ሆኑ ክርክሮች በቂ የሆኑ ታሪካዊ መረጃዎች የሌላቸው መሆኑን ፕሮፌሰር ሁሴን አህመድ በጥናታቸው ሲገልጹም፡-
የሃይማኖት ጉዳይ ዋንኛ አጀንዳና የአክሱማውያን መለያ በሆነበት ሁኔታ የአክሱም ንጉሥና አክሱማውያን ሰልመው ቢሆን ኖሮ እንዴት ያን ሊገልጹ የሚችሉ በአርኪዮሎጂ ቁፋሮም ሆነ በሌሎች የታሪክ ድርሳናት የተቀመጡ ይህን እውነት ሊያረጋግጡና ፍንጭ ሊሰጡ የሚችሉ ጥቂት እንኳን መረጃዎች እንዴት ሊገኙ እንዳልቻሉ በመጠየቅ… አሳባቸውን ሲያጠናክሩም በቅድመ ክርስትና ዘመን የግሪክን አማልክት ሲያመልኩ የነበሩ አክሱማውያን ክርስትናን በተቀበሉ ማግስት በወርቅ ሳንቲሞቻቸው ላይ የክርስትና ሃይማኖት መቀበላቸውን በግልጽ በሚያረጋግጥ መልኩ በሳንቲሞቻቸው ላይ የነበሩትን ምልክቶች በመስቀል ቅርጽ መተካታቸውንና አክሱማውያን በዘመኑ ከነበሩት ነገሥታት ጋር ባደርጓቸው የደብዳቤ ልውውጦችም ሆነ በአውደ ግንባር ስለተጎናጸፉት ድሎቻቸው ወደ ክርስትና ሃይማኖት መግባታቸውን የሚያረጋግጡ የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በግልጽ መጠቀሳቸውን በአክሱምና በአዶሊስ አካባቢ በሚገኙ በአርኪዮሎጂ ቁፋሮና የታሪክ ምርምር የተገኙ የድንጋይ ላይ ጹሑፎች በግልጽ እንደሚያስረዱና በትክክልም የአክሱም ንጉስ «አልነጃሺ» ወደ እስልምና ገብቶ ቢሆን ኖር ተመሳሳይ የሆኑ እንዴት እንዲህ ዓይነት ቢያንስ እንኳን ጥቂት መረጃዎች ሳይገኙ ቀሩ በማለት በአግራሞት ይጠይቃሉ…፡፡
በሂብሪው ዩኒቨርስቲ የመካከለኛው ምስራቅ እውቅ የታሪክ ምሁርና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሀጋይ ኤልሪችም Ethiopia and the Middle East በሚለው መጽሐፋቸው የፕሮፌሰር ሁሴን አህመድን አሳብ እንደሚጋሩ በግልጽ አስቀምጠውታል፡፡ ምናልባትም ይላሉ እነዚህ የመካከለኛው ምስራቅና የአረብ ሀገራት ታሪክ አጥኚዎች፣ ከፍተኛ ተመራማሪዎችና እንዲሁም የእስልምና ሃይማኖት ከአክሱምና አክሱማውያን ጋር ስለነበረው ታሪካዊ ግንኙነት ሰፋ ያለ ጥናት ያደረጉት ሁለቱ ምሁራን፡-
«በዘመኑ የነበሩ አንዳንድ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች እምነቱን ለማስፋፋትና ብዙዎችን ወደ እምነቱ ለመሳብ ሲሉ በጊዜው እጅግ ገናና እና ታላቅ ስልጣኔ የነበረውንና በግዛቱም በሰላም የተቀበላቸውን የአክሱምን ንጉሥ እስልምናን እንደተቀበለ አድርጎ ወሬ መስፋፋቱ በአረቢያን ምድር ሃይማኖቱ ሰፊ ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ ሲሉ የመጀመሪያዎቹ የእምነቱ ተከታዮች ዘንድ የተፈጠረ መላና ዘዴ ሊሆን እንደሚችል እነዚሁ ምሁራን ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡»
በእስከ አሁኑ አጠር ባለ መልኩ ዳሰሳ ያደረግንባቸው ታሪካዊ ሰነዶችም ሆኑ በዚህ ጹሑፍ ውስጥ የተጠቀሱት የታሪክ ምሁራንና የመካከለኛው ምስራቅ ሃይማኖቶች ታሪክ አጥኚዎች ኢትዮጵያዊው ምሁር ፕሮፌሰር ሁሴን አህመድና አይሁዳዊው ፕሮፌሰር ሀጋይ ኤልሪች የአክሱም ንጉሥም ሆነ አክሱማውያን ስለመስለማቸው የሚያረጋግጥ ታሪካዊ ሰነድም ሆነ ማረጋገጭ እንደሌለ ነው በጥናታቸው ግልጽ ያደረጉት፡፡ ታዲያ ታሪካዊው እውነታው ይህ ከሆነ በዘመናችን የሌለ ታሪክን በመፍጠርና ታሪክን በመበረዝና ተጋነው የሚነገሩት አክሱማውያንና እስልምናን በተመለከተ የሚነገሩ ታሪኮች ትክክለኛ ምንጫቸው ከየት ነው፣ ዓላማቸውስ ምን ሊሆን ይችላል ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን፡፡
እንዴትስ በእነዚህ ሁለት እምነቶች መካከል ለብዙዎች ምሳሌ እስኪሆን ድረስ የቆየውን አብሮ በሰላም ተከባብሮና ተዋዶ የመኖር ባሕል በሌለ ታሪክና ተጨባጭነት በሌለው ተረት ተረት ለመናድስ ለምን አስፈለገ፡፡ እንዴትስ እንዲህ በግብታዊነትና በማን አለብኝነት አንዳንድ ጽንፈኝነትና አክራሪነትን የሚያራምዱ ሰዎች በእንዲህ ዓይነቱ ታሪክን የመበረዝና የማጣመም ዘመቻ ውስጥ ለመግባት ደፈሩ፡፡
በዓለማችን በሚገኙ አብዛኛው ሃይማኖቶች ዘንድ ያሉ አስተምህሮዎች ከሰዎች ሁሉ ጋር በሰላም እና በፍቅር ተከባብረንና ተስማምተን እንድንኖር የሚሰብኩና የሚያተጉን ትምህርቶችና ትዕዛዛቶች የሚያስተላልፉ ሆነው ሳሉ በምን ምክንያት በሀገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት ተከባብሮና ተቻችሎ የቆዩ የክርስትና የእስልምና ሃይማኖቶች በመካከላቸው ጠብና ግጭት ይፈጠር ዘንድ ሌተ ተቀን እየተጉ ያሉ ጽንፈኝነትንና አክራሪነትን የሚሰብኩ ሰዎችን ወዴየት እየደሄዱ እንደሆነ ቆም ብለው እንዲያስቡ ልንነግራቸውና ተው ልንላቸው ጊዜው አሁን ይመስለኛል፡፡
እንዴትስ ከአክሱማውያን በኋላ በሺህ ዘመናት የጊዜ ርዝማኔ የምንገኝ ትውልዶች እንደ አክሱማውያን አባቶቻችን የሌሎችን አሳብ፣ እምነትና ፍልስፍና ለማከበር ያልቻልንበትንና ልዩነቶቻችንን በኃይልና በጉልበት ለመፍታት በተጠንቀቅ የቆምንበት የታሪክ ዝቅጠት ውስጥ ልንገኝ እንደቻልን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል… ‹‹ሀገር የጋራ ነው ሃይማኖት/እምነት ግን የልብ ምስጢር/ጉዳይ ነው›› የሚለው የቆየውና ዘመናትን የተሻገረው ብሂላችን የሚነግረን ተግባራዊው እውነታ ምን እንደሆነ ቆም ብለን ልናስተውል የሚገባን ጊዜ ላይ ያለን ይመስለኛል… የዛሬን አበቃሁ… ሌሎች የምትሉን ነገር ካላችሁ እባካችሁ አሳባችሁን በፍቅር፣ በቅንነትና በጨዋ መንፈስ ጀባ በሉን አደራችሁን…!!!
ሰላም! ሻሎም!



i think you tried to tell us Al Nejashi wasnt Islam? well,easy evedence go to Istanbule Turkish capital and you can see Prophet Mohamed’s Letter, that wrote for Alnejashi.
ዘሬ አክሱም ዉስት ለምን መስግድ መስራት ተከለከለ?
አክሱም ላይ የተጣበቁትን ታሪክ ጠምዛዦች እናውቃቸዋለን:: እስልምናን የአረብ ብሔርተኝነት ዓላማ ማስፈጸሚያ አድርገው መጠቀም የሚፈልጉ ኃይሎች ናቸው:: ይህ አስተሳሰብ ቀይ ባህርን የአረብ ባሕር ለማድረግ የሚመኝ መሆኑን ከተረዳን ኢትዮጵያን ሙስሊም አድርጎ መሳሉ የሚጠበቅ ነው::
የሚያሳዝነው ኢህአዴግ ኢትዮጵያን አፍርሼ እንደገና እሠራታለሁ ብሎ ሲንቦጀቦጅ እዚህ ላይ መድረሳችን ነው:: “የትምክህተኞች ከለላ” የሆነችውን ኦርቶዶክስ በተክርስቲያን አዳክማለሁ ብሎ አገሪቱን የሳኡዲ አረቢያ አክራሪ ትምህርት መንፈላሰሻ አድርጓት አረፈ::
ፍቅር ለየኩን
እንደምን አለህ ወገኔ? በ እውነተኛ እና ጨዋ ኢትዮጵያዊ አቀራረብ ነጃሽ የሚባል ሙስሊም በአክሱም አካባቢ እንዳልነበረ እና ቀሳውስትም እንዳልሰለሙ የሞገትክበትን መጣጥፍ ትኩረት ሰጥቸ አነበኩት።ሆኖ የግልህ ሃሳብ ነው እና አከብረዋለሁ፡፤ከ እውነታው ግን ብዙ ኪሎሜትር ርቀህ ተጉዘሃል፡ላቀረብካቸው ነገሮች ማስረጃም የለህም።
ላንተ ያልታየህ እውነታ የአለም ህዝብ ፍንትው እንዳለችው የጠዋት ጸሃይ አጣጥሞ እየሞቀው ውሎ ካደረ እነሆ 1433 አመት ተቆጥሯል።ኢትዮጵያ ማለት ለኔ እና መስል የአለም ሙስሊሞች 1ኛ ሙስሊም ስደተኞችን በመጀመሪያ ያስጠለለች ብርቅየ ሃገር ከመሆኗም በተጨማሪ ነብዩ ሙሐመድ(ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) በወቅቱ ለነበሩት ታላላቅ ነገስታት የ ስለሙ ደብዳቤ ሲጽፉ ከመልክተኞች ደብዳቤውን በክብር ተቀብሎ (ሙሃመድ ያመጣው እምነት እና እኔ የማምንበት እምነት ከአንድ ምንጭ የተቀዱ መሆኑን ነጅሽ በመመስከር ከቀሳውስቶች ጋር ስለ መርየም የሚተርከውን የቁርአን አንቀጽ በጃእፈር አማካኝነት ሲነበብላቸው በ እንባ እንደተራጩ እኛ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳንሆን የአለም ሙስሊም ህዝብ በ እንቁ ታሪክነቱ በመደበኛ የትምህርት ፕሮግራማቸው በማካተት ሲያስተምሩት እነሆ አሁንም 1433 አመት አስቆጥሯል።
መጽሃፍ ቅዱስን ብቸኛ መለኮታዊ ቃል አድርገህ እንደማስረጃ ከጠቀስከው በላይ ለኔ ለሙስሊሙም ቁርአን ሰዎች እና ጋኔኖች እንኳ ቢሰባሰቡ ቢጤውን አንድ አንቀጽ ማምጣት እንደማይችሉ (ከቻሉም እንዲያመጡ የጋበዘው ተአምረኛው ቁርአን) ስለ ነጃሽ እና ቀሳውስቶቹ ቁልጭ አድርጎ አስቀምጦታል።ይህም ብቻ አይደለም አምነናል ማለታቸውን እና ይህም የሆነበት ምክንያት ቄሶቹ የፈጣሪ ፍራቻ የነበራቸው እና የማይኮሩ መሆናቸውንም በመጥቀስ ይልቁንም ከአይሁዶች ይልቅ እነዚህ ክርስቲያኖች ለሙስሊሞች ይበልጥ የቀረቡ መሆኑም በዚሁ ቁርአን ውስጥ ይገኛል።(ቁርአን እስካሁን እንዳልተበረዘ እና ወደፊትም ከመበረዝ በአላህ እንደሚጠበቅ ልብ ይሏል)
ነጃሽ ከዚህ አለም በሞት ሲለይ ነብዩ የ እርቀት ፍታት ጸሎት እንዳደረጉለት እና የመጀመሪያው ሰላተል ጋኢብ(የሟች አስከሬን በአጠገብ በሌለበት ሁኔታ የሚደረግ የጸሎት ስነ ስር አት በነጃሽ ጊዜ እንደተጀመረ አለም አቀፍ ታዋቂ ምሁራን በመጽሃፎቻቸው አስፍረውታል።ምናልባት ይህን መረጃ በኢትዮጵያ ምሁራን ለምን አልተጻፈም ከሆነ በኔ፡እና በአብዛኛው ሙስሊሞች እምነት የኢትዮጵያ ታሪክ ሙስሊም ባልሆኑት ወገን ስለተጻፈ ከ እውነታው በብዙ ማይልስ መራቅ ብቻ ሳይሆን ለአንድ እምነት ብቻ የወገነ ጠበቃ ሆኖ አግኝተውታል።ለዚሁ ማስርጃ ከፈለግክ ዶክተር ላፒሶ አንዱ እማኝ ናቸው፡፡
እናም ወዳጄ ፍቅር ለየኩን፡_በጽሁፍህ ያንጸባረቅከው ሃሳብ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ነጃሽን በተመለከተ የምታንጸባርቀው ጽኑ አቋም ነጸብራቅ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
ለማጠቃለያም ነጃሽ የሚባል ንጉስ(በወቅቱ ሙስሊሞችን ያስጠጋ) እሱ ዘንድ ማንም ሰው የማይበደልበት እንደነበር የሚታወቀው ንጉስ አስሃማ እንደሰለመ እና ከተሰደዱት ሙስሊም ስድተኞች መካከልም አንዷንለነብዩ ሚስት ትሆን ዘንድ ከፍተኛ ስጦታ አስይዞ እሱ እንደ አባት ሆኖ እንደዳረላቸው፡ሌሎችንም ተመሳሳይ ታሪኮች አንብቤያለሁ።
ከቀሳውስት መካከል የነጃሽን መስለም የተቃወሙ በመኖራቸው ለተወሰነ ጊዜ መስለሙን ይፋ አለማድረጉንም አንዳንድ የታሪክ ምሁራን ጽፈዋል።
ይህ እንግዲህ ጽሁፍህን ካየሁ ዘንዳ በግርድፉ የግሌ አስተያየት ሲሆን በጉዳዩ ላይ ጥልቅ እውቀት ያላቸው ምሁራን አንድ እንደሚሉህ ተስፋ በማድረግ በማክበር እሰናበትሃለሁ።
سورة المائدة آية رقم 83
{وإذا سمعوا ما أنزل إلى الرسول ترى أعينهم تفيض من الدمع مما عرفوا من الحق يقولون ربنا آمنا فاكتبنا مع الشاهدين}
የዚህን ቁር አን ትርጉም ኢብን ከሲር ስለ ሃበሻ መሆኑን ከታች በአረበኛ ዘርዘር አድርገው አቅርበውታል
تفسير ابن كثير :
فقال ” وإذا سمعوا ما أنزل إلى الرسول ترى أعينهم تفيض من الدمع مما عرفوا من الحق ” أي مما عندهم من البشارة ببعثة محمد صلى الله عليه وسلم يقولون ” ربنا آمنا فاكتبنا مع الشاهدين ” أي مع من يشهد بصحة هذا ويؤمن به وقد روى النسائي عن عمرو بن علي الفلاس عن عمر بن علي بن مقدم عن هشام بن عروة عن أبيه عن عبد الله بن الزبير قال نزلت هذه الآية في النجاشي وفي أصحابه ” وإذا سمعوا ما أنزل إلى الرسول ترى أعينهم تفيض من الدمع مما عرفوا من الحق يقولون ربنا آمنا فاكتبنا مع الشاهدين” وروى ابن أبي حاتم وابن مردويه والحاكم في مستدركه عن طريق سماك عن عكرمة عن ابن عباس في قوله ” فاكتبنا مع الشاهدين ” أي مع محمد صلى الله عليه وسلم وأمته هم الشاهدون يشهدون لنبيهم أنه قد بلغ وللرسل أنهم قد بلغوا ثم قال الحكم صحيح الإسناد ولم يخرجاه وقال الطبراني حدثنا أبو شبيل عبد الله بن عبد الرحمن بن واقد حدثنا أبي حدثنا العباس بن الفضل عن عبد الجبار بن نافع الضبي عن قتادة وجعفر بن إياس عن سعيد بن جبير عن ابن عباس في قول الله تعالى ” وإذا سمعوا ما أنزل إلى الرسول ترى أعينهم تفيض من الدمع ” قال إنهم كانوا كرابين يعني فلاحين قدموا مع جعفر بن أبي طالب من الحبشة فلما قرأ رسول الله صلى الله عليه وسلم عليهم القرآن آمنوا وفاضت أعينهم فقال رسول الله صلى الله عليه وسلم : ” لعلكم إذا رجعتم إلى أرضكم انتقلتم إلى دينكم ” فقالوا : لن ننتقل عن ديننا فأنزل الله ذلك من قولهم ” وما لنا لا نؤمن بالله وما جاءنا من الحق ونطمع أن يدخلنا ربنا مع القوم الصالحين ” .
ይህ እንግዲህ በቀላሉ ከነጃሽ ጋር የነበሩ ሰዎች የሰጡትን የ እማኝነት ቃል ነበር የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ የሌላ ሀግር ዜጋ መሆናቸውን አሁንም ልብ ይሏል
ኢትዮ ሙስሊም
ለአቶ በፍቅር
በዚህ ጥሩ ጽሑፍህ ውስጥ ታሪክን የዳሰሰና መሰረታዊ ነገርን ስላሰፈርክ ሳናመሰግንህ ልናልፍ አይገባንም፡፡ የንጉሱ ነጃሺ ጉዳይን በተመለከተ የሚነገረው ነገር በሙሉ የተቀነባበረ የውሸት ተረት እንጂ እውነተኛ ታሪክ አይደለም፡፡ ለዚህም ማስረጃው የጠቀስከው የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ኤልሪች ነው፡፡ ፕሮፌሰሩ በሌላ መጽሐፉ ላይ የጻፈውና ለአንባቢዎቹ ያስገነዘበው ነገር ‹ኢትዮጵያ የምትባለው አገር አይናችን እያየ እየተቀየረች ነው› በማለት ነው፡፡ አዎ በውሸት በተቀናበረ እና በሳውዲ አረቢያ በሚፈስ ከፍተኛ ድጋፍ አገራችን ኢትዮጵያ፡ አዲስ ስም፣ አዲስ ባህል፣ አዲስ ሃይማኖት ኖሯት ቀድሞ ያልነበረች፣ በተለይም ክርስትያኑ ልክ እንደ ግብፅ የኮፕቲክ ኦርቶዶክሶች፣ ምንም መብት የሌለው ሁለተኛ ዜጋ የሚሆንባት አገር ልትሆን ነው፡፡
እየተከናወነ ያለው ከፍተኛ እና ስር የሰደደ፣ ጠንካራ ትግል ነው፡፡ የውሸት ታሪክ ቅንብሩም ያስፈለገው ለዚሁ ነው፡፡ ይህንን የውሸት ታሪክ በተመለከተ የተሰሩ የውሸት ፊልሞች አሉ፣ የተጻፉት የውሸት ሞልተዋል፣ የታሪክ ቅልበሳዎች ተደርገዋል፡፡ በአጠቃላይ ጽሑፎቹና ዜናዎቹ ብዙ ናቸው፣ ይህን በተመለከተ በሙስሊሞች የተቀናበረና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የተሳተፉበት ሰሚናር በመቀሌ ከተማ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ይህንን ምስጢራዊ አካሄድ በፍፁም ያላወቁና ሞኞች የሆኑ ወይንም ለጊዜያዊ ጥቅም የተገዙና ሙያቸውን ሚዛናዊ ያላደረጉ ጋዜጠኞች የሚጽፉትና የሚሰጡት አስተያየት አሳፋሪ ነው፡፡ እንደምሳሌ የምጠቅሰው የፍኖተ ሰላም መጽሔት አዘጋጅ ሰሎሞን ስዩምን ነው፡፡ እርሱ በቁጥር 39 እና 40 ላይ ያወጣቸው ጽሑፎች ገዢውን ፓርቲ ስለጠላ ብቻ ሕዝቡን ለማይወጣበት አዘቅት የሚያጋልጥ ነው፡፡ ጽሐፎቹን ማንም አጋላብጦ ሊያነባቸው ይችላል፡፡
የሚገርመው እንደ አንተ በጉዳዩ ላይ ብዙ ያሰቡ ሰዎች የሉም፡፡ በቅርቡ ጃፋር ሐሰን የሚባል ከእስልምና የወጣ ሰው፣ ወደየትኛው እምነት እንደተመለሰ ባላውቅም፣ እንዳንተ ግሩም ጽሑፍ፣ በተለይም ጋዜጠኛው የጻፈውንና አስደግፎ ያቀረበውን ቃለመጠይቅ ተንተርሶ ያቀረበው ጽፎ አነጋግሮ እንደነበረ በማየቴ ተደስቻለሁ፡፡
በዚህ የውሸት የቅንብር ተረት ብዙዎች እንደሚታለሉና ወደ ከፍተኛ ዓመፅ ውስጥ እንደሚገቡ፣ ብዙዎችም ተታልለው ድጋፍ እንደሚሰጡ (እንደ ጠቀስኩት ጋዜጠኛ) ምንም ጥርጥር የለውምና ጉዳዩ የሚያሳስበን ሁሉ ምን ማድረግ እንዳለብን ሳንዘገይ ማሰብን ያለብን ጊዜው አሁን እንደሆነ አስባለሁ፡፡
አቶ በፍቅር በርታ ደጋግመህ በአስፈላጊ ጉዳዮች ላይ ጻፍ፡፡
በፍቅር ለይኩንና በኢትዮሙስሊም የተሰጡትን የመከራከሪያ ሃሳቦች አድንቀያለሁ: ግን የራሴን ውሳኔ ለመውሰድ አስቸጋሪ ሆነብኝ:: ምክንያቱ ደግሞ ምንም ማጣቀሳ (reference)አልተጻፈም በተለይ ኢትዮሙስሊም:: አንባቢው ተጨማሪ መረጃ እንዲያገኝ አነበብን ያላችሁትን ማስረጃዎች የትኛው መጽሐፍ ወይም research article እንደሆነ ብታሳውቁን አለበለዚያ ግን ከሀይማኖት አቃም የተለይ ሆኖ አላየውም::
@ኢትዮ ሙስሊም
ለኢትዮ ሙስሊም!
የአቶ ፍቅር ጽሑፍ በጥናታዊ ማስረጃ ላይ በተለይም እውቆቹን የታሪክ ተመራማሪዎችን ማስረጃ ያጣቀሰ ነው፡፡ ለዚህ መልስ ለመስጠት መጻፍህ የሚደገፍ ቢሆንም አንተ ግን በታሪካዊ ማስረጃ ላይ የተደገፈ ነው የሚል ምንጭ አልሰጠኸንም፡፡ “የደንቆሮ ለቅሶ መልሶ፣ መልሶ” እንደሚባለው ያንኑ ታሪካዊ ማስረጃ የሌለውን የቅንብር ተረት አሁንም ደገምክልን፡፡
ለምሳሌም ንጉሱ ነጃሺ የመሐመድን ደብዳቤ ተቀብሎ ከተነበበለት በኋላ ተናገረ ያልከውና የእንባ መራጨት ከፈጠራ ተረት ያለፈ አይደለም፡፡ ለመሆኑ ጃፋር ያልከው ሰው የማርያምን አንቀፅ ከየት አምጥቶ አነበበው? የማርያም አንቀፅ የወረደው መቼ ነበር? ደግሞስ የትኛው የማርያም አንቀፅ ነበር የተነበበው? ማለትም በቁርአን ምዕራፍ ሁለት ላይ ያለው ወይንስ በቁርአን አስራ ዘጠኝ ላይ ያለው?
የተነበበው የማርያም አንቀፅ የትኛውም ቢሆን ምንም አይደለም ብለን እንውሰደው፣ ለመሆኑ የማርያም አንቀፅ ቤተመንግስት ውስጥ የነበሩትን ሰዎች እና ንጉሱን በእንባ ያራጨበት ምክንያት ምን ነበር? የተሳሳተ እና የተዛባ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ያልተመሳሰለ ስለነበረ እንደሆነስ? ለመሆኑ የማርያም አንቀፅ ከመጽሐፍ ቅዱሱ ጋር ብዙ ማይል ርቀት እንዳለውና ምንጩ ምን እንደነበረ ታውቃለህን? ምንጩ ከየት እንደሆነ እኔ እንዳውቅ ያስቻለኝን የሚከተለውን ጽሑፍ እንድታነብ እጋብዝሃለሁ http://www.answering-islam.org/amargna/books/tisdall_sources/ch4_2.html
የማርያምን አንቀፅ ከቁርአን ሁለትም ላይ ይሁን ከአስራዘጠኝ ላይ ያነበበ ክርስትያን ሁሉ ወይንም መጽሐፍ ቅዱስን ያነበበ ሁሉ ከመጽሐፍ ቅዱሱ ጋር እንደሚጋጭበትና ምንጩም አንድ ሊሆን እንደማይችል ያለምንም ምርምር የሚረዳው ነገር ነው፡፡
የማርያም ታሪክ እንባ ማራጨቱን በትምህርትነት እንደሚሰጥም ጠቅሰሃል ነገር ግን ስለምን ምክንያቱ ምንድነው? ተማሪዎቹ ቁርአን ተዓምር ነው እንዲሉ ነውን? ከሆነ ደግሞ ይገርማል፡፡ እንደዚህ በትምህርትነት የሚሰጠ ብዙ ሺ ዓመታት ያሳለፉ የፈጠራ ተረቶች ሞልተዋልና የ1433 ዓመቱ ያንተ ፈጠራ ታሪክ ብዙም አያስደንቀም፡፡
ቀጥለህም በጽሑፍህ ውስጥ የሚከተለውን አንቀፅ አስፍረሃል፡
“መጽሃፍ ቅዱስን ብቸኛ መለኮታዊ ቃል አድርገህ እንደማስረጃ ከጠቀስከው በላይ ለኔ ለሙስሊሙም ቁርአን ሰዎች እና ጋኔኖች እንኳ ቢሰባሰቡ ቢጤውን አንድ አንቀጽ ማምጣት እንደማይችሉ (ከቻሉም እንዲያመጡ የጋበዘው ተአምረኛው ቁርአን) ስለ ነጃሽ እና ቀሳውስቶቹ ቁልጭ አድርጎ አስቀምጦታል’
ለሃይማኖትህ ቀናኢ መሆንህ በጣም ጥሩና የሚደገፍ ነው፡፡ ነገር ግን እምነትህ የሚሰጠውን ትምህርት አጥብቀህ መገንዘብ ይኖርብሃል፡፡ “ተአምረኛው ቁርአን ቢጤውን ማለትም እንደሚገባኝ ተመሳሳዩ የሆነ ጽሑፍ እንደማይኖረው” ገልፀሃል እራሱ ቁርአንም ይህንን ተግዳሮት ያቀርባል፡፡ ነቢዩ ይህን አለ በተባለበት ሰዓት፣ አንዱ ከጉባኤው ውስጥ ተነስቶ ከቁርአን ውስጥ ካሉት ግጥሞች እጅግ ያማረና የበለጠ ግጥምን ለመናገር እንደሚችልና እንደተናገረ አላነበብክምን፡፡ ደህና አላነበብክም ይሆናል፡፡ ቁርአን ብጤ የሌለው ጽሑፍ መሆኑ ምንድነው ጥቅሙ? ቁርአንን በጽሑፍነት ደረጃ የሚበልጠው ቢገኝስ ቁርአን ምን ሊሆን ነው? እነዚህን ጥያቄዎች አስበህባቸው ታውቃለህን? ለመሆኑ ከቁርአን ውስጥ የትኛው ጥቅስ ወይንስ አንቀፅ ነው ተመሳሳይ ወይንም ብጤ የማይገኝለት ስለምን አልነገርከንም ወይንስ ቁርአን ጠቅላላውን ማለትህ ነው? እንደዚያ ከሆነ አሁንም ያስገርማል አንተ ቁርአንን አንብበህ አታውቅም ማለት ነው፡፡
ንጉሱ ‘ነጃሽ ከዚህ አለም በሞት ሲለይ ነብዩ የ እርቀት ፍታት ጸሎት እንዳደረጉለት እና የመጀመሪያው ሰላተል ጋኢብ(የሟች አስከሬን በአጠገብ በሌለበት ሁኔታ የሚደረግ የጸሎት ስነ ስር አት በነጃሽ ጊዜ እንደተጀመረ አለም አቀፍ ታዋቂ ምሁራን በመጽሃፎቻቸው አስፍረውታል። ምናልባት ይህን መረጃ በኢትዮጵያ ምሁራን ለምን አልተጻፈም ከሆነ በኔ፡ እና በአብዛኛው ሙስሊሞች እምነት የኢትዮጵያ ታሪክ ሙስሊም ባልሆኑት ወገን ስለተጻፈ ከእውነታው በብዙ ማይልስ መራቅ ብቻ ሳይሆን ለአንድ እምነት ብቻ የወገነ ጠበቃ ሆኖ አግኝተውታል። ለዚሁ ማስርጃ ከፈለግክ ዶክተር ላፒሶ አንዱ እማኝ ናቸው፡፡’ የሚለውን አንቀፅህንም አንብቤዋለሁ፣ ያልካቸውን ምሁራኖች ስምና መጽሐፍ፣ የመጽሐፍ ገፅ ወይንም የኢንተርኔት መረጃ ስለምን አልጠቀስክልንም፡፡ እኛም እንማር ነበር ለማለት ያህል ነው፡፡ የኛው አገርስ ዶክተር ላጲሶስ አንተ ያልከውን የተናገረበትን መጽሐፍ ወይንም መጽሔትና ጋዜጣም ወይንም ቃለ ምልልስ እንኳን ለምን አልጠቀስክልንም፡፡
አየህ አቶ ኢትዮ ሙስሊም!!!! የኢትዮጵያዊውን ንጉስ “ነጃሺን” በተመለከተ የሚነገሩት ነገሮች በሙሉ የተቀነባበሩ ውሸቶች ናቸው፡፡ ቅንብሩም ኢትዮጵያን ሙስሊም ለማድረግ ከተያዘው ስር የሰደደ እንቅስቃሴ አንዱና ዋናው ድጋፍ እንዲሆን የታቀደ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ታሪካዊ ድጋፍ የለውም፣ ውሸት ነው፣ የፈጠራ ተረት ነው፡፡ ይህንን ለማቀናበር መነሳሳት እራሱ የሙስሊሞችን እውነተኛነት ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ነው እራስህም እንኳን ልትጠይቀው የሚገባ ነገር ነው፣ ይህን የምለው የምታስብ እና ለእውነት የምትቆረቆር ከሆንህ ነው፡፡
ለማንኛውም በጽሑፍ እንዲህ ተሳትፎ ማድረግህን አደንቀዋለሁ እንዲህ ብንጽፍ እንማማራለንና አንተም ደጋግመህ እባክህን ጻፍና እውቀትን እንጋራ፡፡ ከአቶ ፍቅር ጽሑፍ ብዙ ተምሬበታለሁ አንተም ሌሎች መሰል ሙስሊሞችም ብትማሩበት የፈጠራ ተረትን ከመከተል ትድናላችሁ ብዬ እገምታለሁ፡፡
ቸር ይግጠመን