በየትኛው ምጣድ የምታልፍ ዐይጥ? ይሄይስ አእምሮ(

August 18th, 2012 ይመይሉ ይመይሉ ያትሙ ያትሙ

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ስለ ብፁዕ አባታችን ዜና ዕረፍትና ይህንንም ተከትሎ መከናወን ስለሚገባቸው ተግባራት የሚያወሳውን ጽሑፉን ሳነብ ሰምቻት የማላውቅ ብሂል አነበብኩ፡፡ በርዕስነትም አሁኑኑ ተጠቀምኩባት፡፡ ምክንያቱም ስለአባታችን ዕረፍት አንዳች ነገር ለመናገር እኔም አቆብቁቤ ነበርና፡፡

እንደ ዲ/ዳንኤል የተዋዛ አቀራረብ ቅድሚያውን ለቤተ ክርስቲያኗ ደኅንነትና መረጋጋት እንስጥ እየተባለ ያለ ይመስለኛል – ሌላው ቀስ ብሎ ይደረስበታል እንደማለት ነው፡፡ ከዚህ ጽሑፍ ብፁዕ አባታችን ያሳዩትን መልካም ባሕርያትም አንዘንጋ የሚል አንድምታ ተረድቻለሁ፡፡ ጥሩ ነው፡፡ እኔም እስማማበታለሁ፡፡ ከመነሻውና ከሥልጣን አያያዙ ጀምሮ ፓትርያርኩ ምንም እንኳን አነጋጋሪ የሥልጣን ዘመንና ስብዕና ያላቸው መሆኑ ቢታወቅም አሁን ወደማይቀርበቱ ሄደዋልና ተገቢው የሽኝት ሥነ ሥርዓት ቢደረግላቸው መልካም ነው፡፡ ይሁንና በበኩሌ ይቺ የምጣድና የዐይጥ ነገር ብዙም – በልጆቼ አነጋገር – አልተመቸችኝም – ጎርበጥ አደረገችኝ፡፡ ዲያቆኑ የሚለው ለምጣዱ ስንል ዐይጧን ማለፍ ይገባል፤ እንታገስ፤ በስሜታዊነት የምናደርጋቸውን ነገሮች እንተው ነው – በመርህ ደረጃ እስማማለሁ፡፡ ምጣድ ላይ ዐይጥ ብናገኝ እርሷን ለመግደል በምናነሳው ዱላ ምጣዱንም ጭምር አንክተን ከጥቅም ውጪ እንዳናደርገውና መጋገሪያ እንዳናጣ የሚመክር ሃሳብ ይሰነዝራል ጽሑፉ፡፡

እኔ ግን እላለሁ – ምጣዱ ማለትም በዚህ ዐውድ – የኦርቶዶክስ ሃይማኖት – ከተሰባበረች ቆይታለች፡፡ አሁን ዐይጥ አለፈባት አላለፈባት ለውጥ የሌለው ፍርስራሽ ገል ሆናለች፡፡ በቅርጽ እንጂ በይዘት ከጠፋች ቆይታለች፡፡ 21 ዓመት አለፋት ጨርሶላት እንክትክቷ ከወጣ እያልኩኝ ነው፤ ሰሚ ካገኘሁ፡፡

እነ እማሆይ ወይዘሮ ሮማንና በ58ዓ.ም በኢትዮጵያ የቁንጅና ውድድር አንደኛ የወጣችው ንግሥት እጅጋየሁ በየነ አለቀኖናው የሚፈተፍቱባት ቤተ ክህነት አለች የሚለኝ ሰው ካለ በጣም ትልቅ ስህተት ይመስለኛል፡፡ እናም እግዚአብሔር ምናልባትም በቅርብ ሀገሪቱንም እንደገና ሢሠራት ቤተ ክህነትንም አብሮ ከእንደገና ይሠራት ወይም ያድሳት እንደሆነ እንጂ በአሁኑ ወቅት እንደጠፋች ብትቆጠር ከተሰበረ ምጣድ ጋር ትተካከላለች፡፡ ሁለንተናዊ ስብራቷ ካልተጠገነ አለች አትባልም፡፡

ዘርዘር አድርገን ማየት እንችላለን፡፡ አባታችን ሥልጣን ከያዙ ማግሥት ጀምሮ ያደረጉት ልክ እንደፖለቲካው ሁሉ – ያው የመለስ የፖለቲካ ሹመኛ እንደመሆናቸው – በተለይ የጎጃምንና የጎንደርን እንዲሁም የሸዋንና የወሎን የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ከያሉበት በሻማ ብርሃን እየፈለጉ ከወለፈንዴ ቅን ታዛዥ በቀር ዐዋቂ ዐዋቂውን መመንጠር ነበር፡፡ ምንጠራው በግልጽ ተካሂዶ በነዚያ ምሁራን የተተኩት -ምን ያወሻሻል- ከሰሜን የመጡ በተለይም ለርሳቸው ቅርበት የነበራቸው ከዕውቀትም ከልምድም ከችሎታም የተበደሉ ሰዎች ናቸው፡፡ የርሳቸውን ሥልጣን መያዝ ተከትሎ ቤተ ክርስቲያን ተተረማመሰች፡፡ ሙስናና ንቅዘት ከሀገሪቱ አጠቃላይ የሙስና ቅኝት ባልተናነሰና በባሰም ሁኔታ ተስፋፋ፡፡ ዘረፋው ተጧጧፈ፡፡ የቤተ ክርስቲያን ቃለ ዐዋዲ ከሚደነግገው ውጪ የአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭነት ነገሠ፡፡ ሌላው ቀርቶ ‹ንዑዳንና ቅዱሣን ጳጳሳትና የቤተ ክርስቲያን አባቶች› በመበለቶች ትዕዛዝ ሥር ገቡ፡፡ የፓትርያርክ ጽ/ቤት በወሲባዊ ቅሌቶች ሳይቀር እየተጥለቀለቀ በሚያሳዝን ሁኔታ ተደፈረ – ኩነኔውን ለኔ ጣሉት፡፡ እግዚአብሔር በጭራሽ ተረስቶ በቁም ሐውልት እስኪቆም ድረስ ግለሰብ ይመለክ ጀመር፡፡ በታጣቂ ሐሳዊ ካድሬ ጳጳሳት ቤተ ክርስቲያን ተወረረች፤ተወጠረችም፡፡ በመስቀል ከቀላጤ አገዛዝ ቤተ ክርስቲያን ሲዖልን መሰለች፡፡ ሕዝብን ሲያሻቸው ባማርኛ ‹ጭ…ቃ› በእንግሊዝኛ ‘dirty’ የሚሉ፣ ባሕታዊን ‹shoot him› በሚል ወታደራዊ ትዕዛዝ የሚያሰገድሉ ሊቀ ጳጳስ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገራችን ሊታይ በቃ፡፡ አነስተኛ ገቢ ካለው ከፍተኛ ገቢ ወዳለው ደብር ለመዘዋወር፣ በክህነት ወይም በአስተዳደር አገልግሎት ለመቀጠር፣ ለሹመትና ለዕድገት፣ ለዝውውርና ለጥሩ አበል… ለመብቃት ከፍተኛ ጉቦ የሚከፈልባት ቤተ ክርስቲያን ተፈጠረች፡፡ የነፍስ መንገድና መንፈስ ቅዱስ ተረሱ፤ ሥጋዊነትና በእርኩሳን አጋንንት መንገድ መንጎድ አለቅጥ ገነነ፡፡ ስብከቱና ቃለ እግዚአብሔሩ ለአፍና ለታይታ – መደበኛ የሥራ ግዴታን እንደምንም የመወጣት ያህል ለግብር ይውጣ – እንጂ ከልብ ቀርቶ ከአንገት በላይም መሆን አቃተው፤ ሁሉም የውሸትና የጨረባ ተዝካር ዓይነት ሆኖ ዐረፈው፡፡ ሁሉም ገንዘብ የማከማቸት ሩጫውን በሊቀ ጳጳሱ አመራር ይሽቀዳደም ያዘ፡፡ ዘረኝነት ከጫፍ እስከ ሥር ጥንቡን ጥሎ የቤተ ክርስቲያኗ የሥራ ቋንቋ በዐዋጅ ትግርኛ የሆነ ያህል እስኪመስል ድረስ የብፁዕ አባታችን ዘመድ አዝማድ ካለዕውቀት በትዕቢትና በትምክህት ይንቦራጨቁበት ገቡ፡፡ … እንዲህ እየተጓዝን ነሐሴ 8 ቀን 2004ዓ.ም ደረሰ፡፡

ሙት ለመውቀስ ፈልጌ አይደለም፡፡ በፈጣሪና በሕዝብ የኅሊና ጓዳ የተቀመጠን ግልጽ ነገር ነው እያስታወስኩ ያለሁት፡፡ እንደኔ እንደኔ ብፁዕ አባታችን የሞቱት ሰሞኑን ሳይሆን ከአሜሪካን ሀገር ተጠርተው ሕግ ዐዋቂ ሆነው ሳለ ካለሕግ – ሕግን በ“መንግሥት” ተፅዕኖ አፍርሰው በተሾሙበት ጊዜ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ የሚያደርጉት የነበረው ሁሉ ሕገ ወጥ ነበር፡፡ በመጀመሪያዎቹ የሥልጣን ዓመታቸው ‹እስካሁን በአማርኛ በመቀደሴ ይፀጽተኛል› ብለው ተናግረዋል እየተባለ ይወራባቸውም ነበር፤ እውነት ይሁን ሀሰት አላውቅም፡፡ እውነት ከሆነ ግን ፈጣሪ ይቅር ይበላቸው – ክርስቶስ ሊሰቅሉት የሚያንገላቱትን የአጋንንት ሠራዊት ምርኮኞች ‹የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው› እንዳለ የሚያደርጉትን የማያውቁ ብዙዎች ወገኖች አሉና ሁሉንም በጅምላ ይቅር ይበላቸው፡፡ ምርጫ የለንም፤ ተረጋግመንም አንዘልቀውም፡፡

በበኩሌ እንደማምነው ፓትርያርኩ በግል መልካም የጓደኝነት፣የጉርብትና፣ የማኅበራዊ ግንኙነት፣ የልግስናና የቤተሰብ አያያዝ ባሕርያት ሊኖሯቸው ይችላል፡፡ ወደ አመራር ስንመጣ ግን ሥልጣን አያያዛቸውና አካሄዳቸው ሕገ ወጥ እንደመሆኑ ያንን ለማቆየትም መሥራት የሚጠበቅባቸው በሕገ ወጥ መንገድ ነውና መንገዳቸው ሁሉ የተጣመመ እንደነበር ዐውቃለሁ፡፡ ለጉብኝትም ሆነ ለሥራ በየሚሄዱባቸው የውጭ ሀገሮች ሳይቀር በቲማቲምና በገማ ዕንቁላል የክብር ልብሳቸው እንደበሰበሰና ሃይማኖታችንንም እንዳዋረዱ እስከሞቱበት ጊዜ ዘልቀዋል፤ እርግጥ ነው ‹መልከ ጥፉ በስም ይደግፉ› ነውና በርካታ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የሹመትና የክብር ስያሜዎች ከስማቸው በፊት ተቀጥለውላቸዋል፡፡ እነዚህ ግን የበሰበሰን ግድግዳ በቀለም እንደመሸፈን ያህል ነው እንጂ እውነተኛ ማንነትን ከቶውንም ቢሆን ሊደብቁ አይችሉም፡፡ በእውነቱ ያሳዝኑኝ ነበር፤ እየተሰቃዩና ሃይማኖትን እያሰቃዩ ከሚኖሩ ማረፋቸው ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ከዚህ በላይ የሃይማኖት ሞት ካለ አላውቅም፡፡ በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ለንግሥም ይሁን ለጉብኝንት ሲሄዱ ምዕመናን በጫማ ውርወራና ምራቃቸውን በመትፋት እያቀለሉ እንደሚመልሷቸውና የእርሳቸው ብቸኛ የሥልጣን መቆያ ክር የዓላማ ልጃቸው መለስ ዜናዊ እንደነበር የምናውቀው ነው፡፡ በበኩሌ ይይዙት የነበረውን መስቀል በመስቀል ቅርፅ ከተሠራ ተራ ብረት ለይቼ አይቼው አላውቅም፤ ልብሳቸውንም እንደዚሁ ከተራ ውራጅ ልብስ ለይቼ የማይበት የተለዬ ዐይን አልነበረኝም – መስቀሉም ልብሰ ተክህኖውም አለቦታቸው ውለው ነበርና፡፡ ነገርን በከንቱ እንዳንጠመዝዝ አደራ! (የክርስቶስ ሥጋ ወደሙ የማይገባው ሰው ቢቆርብ ወደጉሮሮው ከመግባቱ አፉ ላይ ተነጥቆ በበረሃ ለሚገኙ ግን መቁረብ ለሚፈልጉ የመነኑ አባቶች በመንፈስ ቅዱስ ልዩ ጥበብ ይዛወርና ይሰጣል)፡፡ እናም ምጣዱ አልተሰበረም ብለን ብነዋሽ ስህተት ይመስለኛል፡፡እንክትክቱ ወጥቷል፡፡

ቤተ ክርስቲያን በተሃድሶና በተዋህዶ ተከፋፍላ ትርምስ የተጀመረው በርሳቸው አመራር ነው፡፡ እነ አለቃ አያሌው ታምሩ (ዐይነ በሢሩ ሊቀ ሊቃውንት) እና ሌሎች ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በተቃወሟቸው ጊዜ ካለደመወዝና ካለጡረታ ከሥራቸው በማሰናበት ሰይጣን ብቻ ሊሠራው የሚችልን ወንጀልና ኃጢያት የሠሩት ብፁዕ አባታችን በዚያ ሥራቸው ምክንያት ከመወገዛቸውም በተጨማሪ የብዙ ርሀብተኛ ቤተሰቦች ዕንባ አለባቸው፡፡ አለቃ አያሌው ሲሞቱ እንኳን የቀብር ሥፍራና ተገቢ ጸሎተ ፍትሀት እንዳያገኙ ተደርጎ እንደውሻ በቀላልና በተድበሰበሰ ሥነ ሥርዓት እንዲቀበሩ የተደረገው በርሳቸው ትዕዛዝ ወይም በአድርባይ የቤተ ክህነት ካድሬዎች ነው፡፡ እርግጥ ነው የሞተን መውቀስ እንኳን አይገባም፡፡ እንዲያው የምጣዱን መሰባበር ለማጠየቅ ብዬ እንጂ ነው፡፡ እናም ቤተ ክርስቲያናችን አልጠፋችም ብለን ልንዋሽ አይገባም የሚል ጠንካራ አቋም አለኝ፡፡

ቤተ ክርስቲያን ከዚህም በላይ ተጎሳቁላለች፤ ክፉኛ ቆሽሻለችም፡፡ ስለሆነም መታጠብና መጽዳት ይገባታል፡፡ ለዚህም ይመስላል ፈጣሪ መጥረጊያውንና ቡርሹን ይዞ የተነሳው፡፡ አይደለም አንድ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ወዕጨጌ ዘምናምን ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ይቅርና…- አንድ ሊቀ ዲያቆን እንኳ በዘርና ቋንቋ ምድራዊ የመለያያ ልክፍት ተተብትቦ ከክርስቶስ አስተምህሮ ውጪ አንዳች ነገር ቢያደርግ ቤተ ክርስቲያንን እንዳዋረደ ይቆጠራል፡፡ ከዚህ አኳያ ቤተ ክህነትን ስናይ ከመበስበስ አልፋ ክፉኛ ከርፍታለች ማለት ይቻላል፡፡ እርግጥ ነው መጽሐፍ ቅዱስ ስለኃጢያተኝነት ሲናገር ሁሉም በኃጢያት ሥር እንደሚገኝ ያወሳል፡፡ የኛ ሀገር ግን ለየት ይላል፡፡ የዐዋጁን በጆሮ እንዳይሆንብኝ እንጂ ለምሳሌ ሲግናል አካባቢ ወደሚገኘው የምግባረ ሠናይ ሆስፒታል ጎራ በሉና የሠራተኛውን ዘውጋዊ ስብጥር ለመቃኘት ሞክሩ፡፡ ይህ ሆስፒታል ተጠሪነቱ በቀጥታ ለብፁዕ አባታችን የነበረ ሲሆን ከዘበኛ እስከ ሜዴካል ዳይሬክተሩ ከራሳቸው ብሔር የወጣ ነው – እኔ አስከማውቀው ጊዜ ድረስ፡፡ አሁን ያለበትን ሁኔታ አላውቅም- ሄጄ ስለማላውቅ፤ ግን ብዙም የሚለወጥ አይመስለኝም፡፡ በሊቀ ጳጳሱና በመለስ አገዛዝ ዙሪያ አንድ የተዛብኩትና በድፍረትም መናገር የሚቻለኝ ሃቅ ሁለቱም ይሉኝታና ሀፍረት ከሚባሉ ማኅበራዊ የአብሮነት ሕይወት ዓይነተኛ ቅመሞች ነጻ የወጡ መሆናቸው ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል የሚያደርጉትን ሁሉ ያለአንዳች ይሉኝታና ሀፍረት ሲያደርጉ ‹ሰው ምን ይለኝ? ታዛቢ ምን ይለኝ? እግዜርስ ምን ይለኝ?› በሚሉት ‹ኋላ ቀር› አስተሳሰቦች ሊጨነቁ የማይፈልጉት፡፡ ተነግሮ የማያልቅ አድልዖና በደል በተለይ በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ሲፈጸም ስናይ ትልቁ ዳቦ ሊጥ እየሆነብን በሥነ ልቦናችን ሳይቀር ብንጨነቅና የእግዚአብሔርን ኅልውና እስከመጠራጠር ብንደርስ አይፈረድብንም፡፡ በዚህ ምክንያትም ሳይሆን አይቀርም ብዙ ምዕመናን ሃይማኖታቸውን እየለወጡ ያሉት፡፡ ሰው ተስፋ ሲቆርጥ ከጫፍ የተበላሸ አካሄድ ሲታዘብ በጭንቀት የማይሆነው ነገር የለም፡፡ ‹የምንላችሁን ብቻ አድርጉ› የሚለው የማስተባበያ ትዕዛዝ የማይሠራበት ጊዜ ሞልቷል፡፡ ዋናው ደህና ካልሆነ ተከታዩ ደህና ይሆናል ማለት ደግሞ አስቸጋሪ ነው – ከየት የተማረውን ደህንነት? እንኳንስ ሃይማኖታዊ ህፀፅ አለባቸው እየተባሉ በስፋት የሚታሙና ህፀፃቸውን በሥልጣናቸው ጉልበት እየሸፋፈኑ የነበሩ አባት ኖረው ቀርቶ የዛሬ ዘመን ሰው በሚደርስበት የኑሮ ጫና ሳቢያ እንኳን ሃይማኖቱን ልጁንንና ሚስቱን ከመካድ አይመለስም፡፡ ስለዚህ ሃይማኖታችንን ድራሹን አጥፍተው በመጨረሻው እርሳቸውም ወደማይቀሩበት ሄደዋል – መልካም ጉዞ – እርሳቸው ሂሳባቸውን በዚያው እንዲያወራርዱ እንተዋቸው፤ ወደድንም ጠላንም ከዚያም የሚቀር የለም፡፡ የኛን ግን በጊዜ እናስታካክል፡፡ ብቻቸውን እንዳልሄዱ ደግሞ ልብ እንበል!

ወደሥልጣን ያመጣቸውና በዝምድና የሚታሙበት መለስ ዜናዊም እስካሁን እምን እንደገባ አልታወቀም፡፡ እሱ ብቻ አይደለም፡፡ ዛሬ ጧት ከኢትዮጵያን ሪቪው ድረገፅ እንደተረዳነው ዋናው የጦር አበጋዝ ሣሞራ የኑስም በጠና ታምሞ ለህክምና ወደዱባይ ማቅናቱን ውስጥ ዐዋቂ ምንጭ ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ ይህ የተቀነባበረ የሚመስል ሥልታዊ የማጥቃት እርምጃ ከማንና ለምን እንደታዘዘ መገመት አይከብድም፡፡ እኛ ያለብን የዚህን ጅምር ዕድገት በትዕግሥት መከታተል ነው፡፡ በተለይ ከሃይማኖት አባቶች ብዙ ይጠበቃል፤ አካሄድን ማስተካከል የመጀመሪያው ነው፡፡ አካሄድ ካማረ እግዜር ጣራ ሥር ነው ያለው፡፡ ሀገር ስትፈራርስ፣ የፍትህ ዐይን ሲደነቆል፣ አንድ ፓትርያርክ ሕግን እያፈራረሰ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ሲጥስ፣ ቅምጦች – ደናግል መነኮሳት መስለው ቤተ ክህነትን ሲፈነጥዙበት፣ የክርስቶስ ቤት መሻቀጫና መሸራሞጫ ስትሆን … እያዩ የሚታገሡ አባቶች፣ ወደ መሪ ቢሮ ለመግባት ጫማ እያወለቁና ከእጅ ሊለይ የማይገባ መስቀልን ደጅ ላይ እያስቀመጡ የሚገቡ ጳጳሳት የሥጋ ቢሆን እንጂ የነፍስ አባቶች ሊሆኑ በጭራሽ አይችሉም፤ ተጋድሎኣቸውን ያስጓጎለባቸው የተያዙበት ነገር – የገቡበት ሥጋዊ ቃል ኪዳን – አለ ማለት ነውና፡፡ ሥጋ ደግሞ ከነፍስ ብዙም ኅብረት የላትም፡፡(የልጅ ልጁ የምትሆንን ኮረዳ በረድነት ይዞ በሠራው ማለፊያ ቤት ውስጥ እየወለደ የሚኖር ጳጳስ ጎረቤት አለኝ አይደል? ይቺን እንኳን ሳልናገር ልፈንዳ እንዴ ታዲያ?)
የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ልመክራቸው የምደፍረው አንዳች ነገር አለኝ፡፡ በሚገባ እንተዋወቃለንና ምሥጢር የለም – አይዞን መቀሳሰፍ የሚባል ጣጣ አሁን የለም፤ ቅስፈት ዱሮ ቀረ፡፡ በስሉስ ባዛውር ስብከቴ – ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ እላችኋለሁ – የቃለ እግዚአብሔር ዕውቀት ብቻውን ምንም ማለት አይደለም፤ የትምም አያደርስም፡፡ መጽደቅ በሥራ፣ በፍቅርና በእምነት እንጂ በዕውቀት ብዛት አይደለምና፡፡ የእናንተ መበላሸት ክፉ መንፈሳዊ አባት ሰጠን፡፡ የእናንተ መበላሸት ክፉ የሀገር መሪ ሰጠን፡፡ የእናንተ መጥፋት ለበጎቻችሁ መጥፋት ምክንያት ሆነ፡፡ የእናንተ ከመንገድ መውጣት እረኛ አሳጥቶ በተኩላና በቀበሮ አስጨረሰን፡፡ ስለዚህ ለምን አትመለሱም? በርካታ ምዕመናን ለእግዜር ሲሉ እንጂ እንደ እናንተ ቢሆን አንድም ቤተ ክርስቲያን ደጅ የሚደርስ ባለልኖረ፤ ሙዳየ ምፅዋትም ባዶውን በቀረ፡፡ ለምሳሌ እኔ ቤተ ክርስቲያን አልሄድም፡፡ ምክንያት፣ በትንሹ የብፁዕ አባታችን ስም በቅዳሤ መሀል ሲጠራ በእጅጉ ስለሚያመኝ፡፡ በቃ፡፡ በትንቢት ፍጻሜ ዘመን ላይ መሆኔ በጀኝ እንጂ እንደ እናንተ ቢሆን ጨርቄን ጥዬ አብጄ ነበር – ግን ትንቢቱ ሊፈጸም የቀረው ጊዜ በጣም ጥቂት ነው፤ ለዚህም ነው ይሄ ሁሉ ዓለም አቀፍ ሕንፍሽፍሽ የበዛው – ቆንጆ የትግርኛ ቃል፡፡ ብዙ ሰው በምትሠሩት ሥራ ያፍራል፤ይናደዳል፤ እግዚአብሔር በቶሎ ፍርዱን እንዲሰጥም ይጸልያል፡፡ ምናልባት እናንተ፣ እናንተ የምትሠሩትን እኛ የማናውቅ እየመሰላችሁ ትሞኙ ይሆናል፡፡ ይህ ወቀሳ ለቀሳውስትና ለታችኛው እርካብ ካህናት አይደለም – እነሱማ እናንተን እያዩ ከእናንተ እንዴቱን አይብሱ? ለጳጳሳትና ከዚያ በላይ ላሉ በክርስቶስ ስም ለሚነግዱ አስመሳዮችና ሰው መሳይ በሸንጎዎች ነው ይህ ከጨዋ(layman) አንደበት የሚወረወር ተግሣጽና ማስጠንቀቂያ፡፡ አሁንም ልድገመው – እንተዋወቃለን፤ በመካከላችሁም ነበርኩ፡፡ ይህንን ስል ደግሞ ቅጠል ለብሰው ድንጋይ ተንተርሰው በገዳማትም ሆነ እዚሁ አጠገባችን ለሀገርና ለወገናቸው የሚጸልዩ የበቁ ንጹሓን አባቶች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ጥቂትም ቢሆኑ አሉ፡፡ በነሱም ነው ውለን ማደራችን፡፡ ጨርሶ አይበድልም፡፡ እንደኛ እንደአብዛኛዎቻችን ቢሆን ኖሮ የለንም፡፡

ወደ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሮማን ካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ ለአፍታ ልውሰዳችሁ፡፡ ስሙ አቡነ ሮደሪጎ ይባላል፡፡ የቫቲካን ሊቀ ጳጳስ ነበር፡፡ እጅግ ትዕቢተኛና ጀብደኛም እንደነበረ ታሪኩ ላይ ተዘግቧል፡፡ ከድፍረቱ ብዛት በሕገወጥ መንገድ የወለዳቸውን ሦስት ልጆቹን በቫቲካን ውስጥ በግልጽ ሹሟቸዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ መሞሰን የሚመጣው እግዚአብሔርን ከመናቅና ለሰይጣን ከማደር ነው፡፡ ከኛ አባቶችስ ስንቶቹ ይሆኑ ከዚህ ዕብሪተኛ ሊቀ ጳጳስ የሚለዩ? በእግዚአብሄር ፍርድ መግባት እንደማያስፈልግ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን እውነትን መናገር ደግሞ ስለእግዚአብሄር በሰዎች ፊት መመስከር ነውና በምናገረው አላፍርም – ለመራገም የሞራል ብቃት ያለው ሰው ካለ በምለው ነገር ውሸታም ነህ ብሎ ይርገመኝ፤ ግዴለኝም፡፡ ሃይማኖታችንን ያጠፋው ይህ ዓይነቱ ፈጣሪን ቀን ቀን፤ የሥጋ ፈቃድን ማታ ማታ የማገልገል የሁለት ዓለም ሰውነት ነውና በቶሎ እንድንመለስ ማሳሰብ እፈልጋለሁ፡፡ እውነት በሚነገርበት ቦታ ሁሉ እግዚአብሔር አለ፡፡ ስለጠፉ አባቶች ብዙ ነገር በተናገርኩና በወጣልኝ፡፡ ግን ለጊዜው በይደር ይቀመጥ፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ከተናገረው ትንሽ ልጥቀስና ላጠቃልል፡፡ ቅዱሰ ጳውሎስ ስለሚስት ማግባት ሲጠየቅ ቢችሉ እንደሱ በብቸኝነት እየኖሩ እግዚአብሔርን ቢያገለግሉ ደስ እንደሚለው ካልቻሉ ግን በሥጋ ፍላጎት ከመቃጠል በአንድ ለአንድ ጋብቻ ተወስነው ፈጣሪያቸውን እያገለግሉ እንዲኖሩ መክሯቸዋል፡፡ የቫቲካንና የኛዋ ኦርቶዶክስ ችግር ‹የማያዛልቅ ጸሎት ለመብረቅ ያጋልጣል› እንዲሉ የማያዛልቅ ሕግ ደንግገው ጳጳስ አያግባ የሚል ደንብ በመትከላቸው በሁለቱም የክርስትና እምነት ዘርፎች የሚያገለግሉ ካህናትና ቀሳውስት መከራቸውን ያያሉ – በተለይማ የካቶሊኮቹ በቅስናም የሚያገለግለው ማግባት ስለማይፈቀድለት በዚያ አካባቢ የሚደረገውን ጉድ ብትሰሙ ወደ ወፈፌነት ልትለወጡ ትችላላችሁ፡፡ እንዲያው ለመሆኑ እግዚአብሔርን ማታለል ለምን አስፈለገ? በየትኛው መጽሐፍና በየትኛውስ ምዕራፍ ነው አታግቡ ብሎ ያስገደደ? ጋብቻ ቅዱስ አይደለም ወይ? (ካቶሊኮቹ ካህናትና ሲስተሮች የእናግባ ጥያቄ ቢያቀርቡም እስካሁን አልተፈቀደላቸውም፤ በሽፍንፍን ግን ያሻቸውን ያስነኩታል!) በድብቅ ከአሥሯ ጋር ከመሸራሞጥ፣ በድብቅ ገንዘብ እየመዘበሩ ለአሥሩ ከመስጠትና ከአሥሩ ቦታ እየደቀሉ በተበታተነ ቤተሰብ አሣርን ከመብላት ቢያንስ አንዲቷን አግብቶ ዐርፎ ፈጣሪን ማገልገል ይቻል የለም እንዴ? አዎ፣ ሁሉ አማረሽን ገበያ አታውጧት ይባላል፡፡ ከፈጣሪም ሳይሆኑ ከራስም ሳይሆኑ የተምበዛበዘ ሕይወት ሲመሩ ቆይተው እንዲህ አለመላው ማለፍም አለ፡፡ አንዱን መያዝ ነው ደጉ፡፡ የድፍን ቄስ ነኝ ባዩን ገመናማ ብናይ በክሬን የማይነሳ ስንክሳር ይወጣዋል – መጽናኛችን ዘመኑ የአጅሬ – የዲያብሎስ- መሆኑ፡፡ ደግሞም በድግምትና በትብታብ እርስ በርስ የመቆላለፋቸውና በሆድ ሥራይ የመንጠራወዛቸውን ሌላ ታሪክ ስንሰማ ጥንት በጦርነት ያጣትን ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በዓለማዊ ብልጭልጭ ነገሮች አቅርቦት ላይ በተመሠረተ ድርድር ካለጦርነት ሰይጣን እንደተቆጣጠራት እንረዳለን፡፡

መሰናበቻ፡-
ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፡- ‹አታመንዝር› እንደተባለ ሰምታችኋል፡፡ እኔ ግን እንዲህ እላችኋለሁ፣ ‹ሴትን ተመልክቶ የተመኛት ሁሉ ፣ ያን ጊዜ በልቡ ከእርሷ ጋር እንዳመነዘረ ይቆጠራል፡፡ ስለዚህ ቀኝ ዐይንህ የኃጢያት ምክንያት ቢሆንብህ ዐውጥተህ ጣለው፤ ምክንያቱም ሰውነትህ ሁሉ ወደገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻላል፡፡ … ማቴ. 5፣ 27 – 28
ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፣ ‹ከሐሰተኞች መምህራን ተጠንቀቁ፤ እነርሱ በውጫቸው በግ መስለው ወደእናንተ ይመጣሉ፤ በውስጣቸው ግን እንደነጣቂ ተኩላ ናቸው፡፡ እነርሱንም የምታውቋቸው በሥራቸው ፍሬ ነው፡፡ ከእሾህ ቁጥቋጦ የወይን ፍሬ ይለቀማል? ከኮሸሽላስ የበለስ ፍሬ ይለቀማል? እንዲሁም ጥሩ ዛፍ ሁሉ ጥሩ ፍሬ ያፈራል፤ መጥፎ ዛፍ ግን መጥፎ ፍሬ ያፈራል፡፡ ጥሩ ዛፍ መጥፎ ፍሬ ማፍራት አይችልም፤ መጥፎ ዛፍም ጥሩ ፍሬ ማፍራት አይችልም፡፡ ጥሩ ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል፤ ወደእሳትም ይጣላል፡፡ ስለዚህ ሐሰተኞች መምህራንን በሥራቸው ፍሬ ታውቋቸዋላችሁ፡፡ ‹ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ!› የሚለኝ ሁሉ ወደመንግሥተ ሰማይ አይገባም፤ ወደመንግሥተ ሰማይ የሚገባው በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚፈጽም ነው፡፡… ማቴ. 7፣ 15 – 21

… ዲያብሎስም ኢየሱስን ‹የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ እስቲ ይህ ድንጋይ እንጀራ እንዲሆን ዕዘዝ› አለው፡፡ ኢየሱስም ‹ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጸፏል› ሲል መለሰለት፡፡ ከዚያም በኋላ ዲያብሎሰ ኢየሱስን ወደአንድ ከፍተኛ ቦታ አውጥቶ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በቅጽበት አሳየውና እንዲህ አለው፣ ‹ይህን ሁሉ ሥልጣንና ክብር ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ይህ ሁሉ ለእኔ የተሰጠኝ ስለሆነ ለፈለግሁት መስጠት እችላለሁ፡፡ ስለዚህ አንተ ለእኔ ብትሰግድልኝ ይህ ሁሉ ያንተ ይሆናል፡፡› ኢየሱስም ‹ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ብቻ ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አገልግል ተብሎ ተጽፏል› ሲል መለሰለት፡፡ … ሉቃስ 4፣ 1 – 13

እግዚአብሔር የሚያስጨንቅ አምላክ አይደለም፡፡ ብዙዎቻችን በእኛና በእግዚአብሔር መካከል በመሆንና ባለመሆን ውጥረት ውስጥ ስንገባ ነው ችግርና ትዝብት ውስጥ የምንገባው፡፡ ለሥጋችንና ለነፍሳችን በአንድ ወቅት መሆን ደግሞ አንችልም፤ አንዱን እንመርጣለን ሌላውን እንተዋለን፡፡ የጽድቅ መንገድ ጠባብ ናት – ብዙ ሰው ሊሄድባት አይደፍርም፡፡ የጥፋት መንገድ ግን ሰፊ ነው ብዙዎቻችን ያለተቀናቃኝና ያለ ተቃዋሚ እየነጎድንበት ያለው ሰፊ ጎዳና የጥፋቱ ጎዳና ነው፡፡ ከዚህ ለመውጣትና ወደ ጽድቁ መንገድ ለመግባት ግን ምርጫው በእጃችን ነው፡፡ በሁለቱም መንገዶች በአንድ ጊዜ መጓዝ የሚቻለው ግን የለም – ሁለት ተቃራኒ ነገሮችን በአንድ ጊዜ መምረጥ አይቻልምና፡፡ ሞትና ልደት፣ መሄድና መምጣት፣ ማልቀስና መዝፈን… በጊዜ ሂደት ሳይቀዳደሙ በአንድ ቅጽበት ሊከናወኑ አይችሉም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ፈጣሪንና ፍጡሩን ሰይጣንን በአንድ ጊዜ ማገልገል አይቻልም፡፡ እሱም ብሏል፡- ለሁለት ጌቶች መገዛት አትችሉም ብሎ፡፡

ለማንኛውም እግዚአብሔር ቤቱን ሲያጸዳ ከቆሻሻዎች ጋር አብሮ ላለመጠራረግ አሁንም ዕድሉ አለንና ንስሃ መግባት የሚያስፈልገንና ጥፋታችን የታየን ወገኖች በቶሎ እንመለስ፡፡ ጥፋትን ለማስተካከል የተለያዩ መንገዶች አሉ፡፡ አንድም ከወልጋዳው የኃጢያት መንገድ በአፋጣኝ ወጥቶ ቀናውን መንገድ መቀላቀልና ሕይወትን በእግዚአብሔርና በዲያብሎስ መካከል ዥዋዥዌ አለመጫወት ነው፡፡ አንድም ለዓለም አድሮ በግልጽ ቤተሰብን በመመሥረት በአወዳሽነት ቤተ ክርስቲያንን እያገለገሉ ቆብንና አስኬማን አውልቆ የተከበረ የክርስቶስን መስቀልም ወደተገቢ ቅዱስ ቦታ መልሶ በድብቅ ሳይሆን በግልጽ ሚስትን ማቀፍና ልጅን እየወለዱ ወይም የወለዱትን እያሳደጉ ዓለማዊ ሆኖ መኖር ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው አማራጭ እጅግ አደገኛና ነፍስን ለገሃነም አሳልፎ በመስጠት ለዘላለማዊ ኩነኔ የሚዳርግ ነው ፤ እርግጥ ነው ቤተ ክርስቲያንን የሚያዋርዳትና የሚንቃት ገመናዋን የሚያውቅ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ዓለም እየጠፋች ያለችው አለባበሳቸውን አሣምረው ለሁለት ጌቶች በሚገዙ ሐሳይ መሲሆች መዘዝ ነውና ይህ ወቅታዊ መልእክት ለሁሉም ቢዳረስ አግባብነት አለው ብዬ አምናለሁ፡፡ እኔ ኃጢያተኛ የእግዚአብሔር ባሪያ ነኝ፡፡ ያልኩትን ብያለሁ – መልሼ አልውጠውም፤ የሆኖ ሆኖ ግን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡

ይሄይስ አእምሮ(yiheyisaemro@gmail.com

  1. አማኙ
    | #1

    21 ኦአመት ብቻ እይደለም የደርጉን ጹም የአባ መርቆርዮስን ሲጨመር 26 አመታት በላይ ነው ምጣዱ ከተሰባበረ

  2. አማኙ
    | #2

    በውጪውም አለም ሳንሱር?

  3. ጌዲዮን
    | #3

    በእውነቱ መሬት የረገጠ ጽሁፍ ነው። ዝም ብሎ ሃሳባዊ መነባንብ አይደለም። ዲያቆን ዳንኤል የሚጽፋቸውን ፅሁፎች በብዛት አነባለሁ፣ ነገር ግን ብዙ ጊዜ መካሪና ሃሳባዊ (ideologue) ይሆኑብኛል። ይሄይስ አእምሮ በርትተህ ግፋበት እልሃለሁ። በበረሃ የሚጮህ የዮሃንስን ድምጽ እንድናስታውስ እንዳደርክ ይሰማኛል። የዲያቆን ዳን ኤልን (የ አይጧን ታሪክ ግን ከዚህ በፊት ስላየሇት ላመልክትህ፣ እዚህ ጋ ታገኛታለህ። http://www.danielkibret.com/2010/03/blog-post_6778.html

    ቸር እንሰንብት!

  4. Yiheyis A.
    | #4

    Thank you Gedeon, no. 3 above, I think you must be the one who has stated this same comment on the hebasha’s posting of this article. While I was to thank you there, power interruption occurred and now after sometime when I accessed abugida I got it here and would like to thank you again, I read the piece you gave me the link. It is so nice and didactic. It is about the ‘mechachal’ of especially spouses in ‘tidar’ or ‘gabcha’, i.e, marriage.

  5. መረተውርቅ
    | #5

    ከሁሉ ዲያቆን ዳነኤል ከተናገሩት ደስ ያለኝ አምላክ በግዜው ይህን ካፒትል ዘግቶታል ያሉት ነው! ቢቆዮ ኖሮ በርግጥ ምን አረመኔያዊ ተግባር ይቀጥል እንደሆን መገመቱ ቀላል አይደለም…….በበኩሌ ግን ዋነኛው ስራ በሃገር ላይ ማተኮር አለበት ሃገር ከሌለ የከፋ ነው ችግሩ….ሁሉንም አሰባስቦ ቅድሚያ የሃገሩን አንድነት ላይ አጥብቁ ሹመት ላይ ግዜ አታባክኑ ያለአበሳቸው ለወገኖቻቸው ፍቅርና ለሃገራቸው ሰላምና ክብር ሲሉ በአስር ቤት የሚንገላቱትን ጋዜጠኞችና የፖለቲካ እስረኞችን ነጻ ለማውጣት ቅድሚያ እንዲገኝ መስራት አስፈላጊ ነው!!!እግዚአብሔር ይፈርዳል ለድሆችና ለተንገላቱ ያዝናል ይደግፋቸውማል..
    ሆኖም እግዚአብሔር የፍትህ አምላክ ሰለሆነ ፍትሕ ይስፈን ብሎ መጠየቅ ግድ ይለናል …….
    በክፋ እጅ የወደቁትን በአስር የሚንገላቱትን ፈጣሬ አምላክ ይጠብቃቸው!!!!!ድል ለአውነትና ለሃገራችን ይሁን!! አሜን!

አስተያየት መስጫው ተዘግቷል።