ኢትዮጵያ ውስጥ ሠራተኞች ከስራቸው ከሥራ እየተሰናበቱ መሆኑ ተገለፀ፡፡

September 10th, 2008 Print Print Email Email

ethiopia_jobs1.gif (more…)

ethiopia_jobs1.gif

የገቢዎች ሚንስትር፣ የጉሙሩክ ባለሥልጣን እና የሀገር ውስጥ ባለሥልጣን መ/ቤቶች- የኢትዮጵያ ገቢዎችና ሀገር ውስጥ ጉሙሩክ ባለሥልጣን በሚል በአንድ ባለሥልጣን ስር እንዲደራጁ ከተደረገ ጀምሮ ብዙ ሠራተኞች ትርፍ ሆነው በመገኘታቸው እየተቀነሱ ነው፡፡ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት እና ምግብ ዋስትና ዘርፍ ለ283 ሠራተኞቹ በግዳጅ እረፍት ሰጠ፣ ከ900 ሠራተኞቹ 269ኙን ብቻ የሥራ በደብ አውጥቶላቸዋል፡፡ የቀሪዎቹ እጣ ፈንታ አልታወቀም፡፡

ሦስቱ ገቢ ሰብሳቢ መ/ቤቶች አንድ አይነት ሥራ የሚሠሩ በመሆናቸው የሀብትና የሰው ሀይል እያባከኑ ነው፣ ስለዚህ አዲስ አደረጃጀት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል በሚል በፓርላማ በፀደቀ አዋጅ እንዲዋሀዱ መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡ መ/ቤቶቹ ከፍተኛ የሆነ የሰው ሀይል የያዙና የሀገሪቱን ገቢ የሚቆጣጠሩ ሲሆን፤ በአዲሱ አደረጃጀት እስካሁን ከ200 በላይ ሠራተኞች ተቀንሰዋል፡፡

የባለሥልጣኑ መ/ቤት ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ ትርፍ ሠራተኞችን የምንሸከምበት አቅም የለንም ያሉ ሲሆን በአንድ ሰው የሚሠራ ሥራ በሶስትና አራት ሰው እየተሰራ በመሆኑ ብዙ ትርፍ ሀይል አለ ብለዋል፡፡ ወደፊትም ሊቀነሱ የሚችሉ ሠራተኞች ይኖራሉ የሚሉት አቶ መላኩ በተለይ ፊናንስ ፖሊሶች በሙሉ እንደሚቀነሱና የፌደራል ፖሊስ ሥራቸውን ሊረከበው እንደሚችል ገልፀዋል፡፡

በተያያዘ ዜና የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ከሚሽን በግብርናና ገጠር ሚንስትር ሥር ከገባ በኋላ ከ900 ሠራተኞቹ 269ኙን ብቻ ሥራ መደበ፣ 283ቱን በግዳጅ እረፍት እንዲወጡ አደረገ፡፡ የሪዎቹ ዕጣ ፈንታ አልታወቀም፡፡

በቅርቡ ተጠሪነቱ ለግብርናና ገጠር ሚንስቴር እንዲሆን የተደረገው ይኸው ከሚሽን በመላ ሀገሪቱ ካሉት 900 ሠራተኞች ውስጥ እስካሁን መመደብ የቻለው 269 ብቻ መሆኑን የሚገልፁት የኮመሽኑ ባልደረቦች “ቀሪዎቻችንን ምን እንደሚያደርጉን አላወቅንም” በማለት ስጋታቸውን በመግለፅ ላይ ናቸው፡፡

ሚንስቴር መ/ቤቱ በበኩሉ በመምሪያው ስር ለመደባቸው ሰራተኞች ትላንትና እና ዛሬ (ጳግሜ 3እና4) ከምደባው ጋር በተያያዘ ስብሰባ ለማከሄድ ቀጠሮ ይዟል፡፡ “ምደባው በምን መስፈርት እንደሆነ አላወቅንም፣ በትምህርት ይሁን፣ በሥራ ልምድ ግልፅ አልተደረገልንም” የሚሉት ምጮቻችን “በትምህርትም ሆነ በሥራ ልምድ የተሻለ ዝግጅት ያላቸው ሳይመደቡ ዝቅተኛ ዝግጅት ያላቸው ተመድበዋል፤ በእድሜ እንዳይባል 20/45 ውስጥ ያሉ ተመድበዋል” ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት እና የመገናኛና ትራንስፖርት ሚንስትር መሰረታዊ የአሰራር ሥርአት ለውጥ (ቢ.ፒ.አር) አድርገን ትርፍ ሠራተኞች አግኝተናል በማለት ቅነሳ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡ የመገናኛና ትራንስፖርት ሚንስቴር ሠራተኞች ጉዳያቸውን ወደ ፍርድ ቤት ወስደው በክርክር ሲሆኑ፤ የፖስታ አገልግሎት ድርጅት ግማሾቹን ወደ ሥራ ገበታቸው መልሷል፡፡

የአቅም ግንባታ ሚንስትር አቶ ተፈራ ዋልዋ አንድም ሠራተኛ አላግባብ አይቀነስም፣ የሚቀነሱ ካሉም ሥልጠናና ብድር ሰጥተን ራሳቸውን እንዲችሉ እናደርጋለን ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡ እስካሁን አንድም ተቀናሽ ሥራተኛ ብድርና ሥልጠና ያልተሰጠ ሲሆን መንግሥት የተባረሩት በስነምግባር ብልሹነትና በብቃት ማነስ ነው በማለት እያስተባበለ ነው፡፡

በአሁኑ ሰአት በመላ ሀገሪቱ ባሉ ከተሞች ውስጥ የሥራ አጥ ቁጥር ከ40 በመቶ በላይ መድረሱን ስታስቲክሶች ያመለክታሉ፡፡

Comments are closed.