አንድነት ፓርቲ በወልዲያ ሰባት አባላት ያሉትን የአመራር አካል አስመረጠ ከአባላትም ጋር ውይይት አደረገ

October 27th, 2008 Print Print Email Email

andenet_in_woldia.gif (more…)

andenet_in_woldia.gif

PDF Version


‹‹ጠንካራ አቋም ካለው፣ ዲሞክራሲያዊ አሰራርን የሚከተልና ለአብላጫ ድምፅ ተገዢ ከሚሆን ፓርቲ ጋር ለመቀጠል ዝግጁ ነን ሲሉ በወልዲያ የቀድሞ ቅንጅት አባላት ገለፁ፡፡

በሰሜን ወሎ ዋና ከተማ ወልዲያ የዞን ቢሮ ለመክፈት ከመጡ የልኡካን ቡድን ጋር ወይይት ያደረጉት እነዚህ አባላት እስካሁን የምንጠብቀው በቅንጅት አላማ ስር የሚመራን አካል ነው፡፡ እኔ ያልኩት ካልሆነ ከማይል አካል ጋር ለመቀጠል ዝግጁ ነን ሲሉ በዞኑ የክልል ተመራጭ የነበሩ ግለሰብ ገልፀዋል፡፡

ሌላው የስብሰባው ተካፋይ ‹‹በኛ ወረዳ ህዝቡ የትደረሳችሁ፣ አሁን ምን እየሰራችሁ ነው እያለ እያስጨነቀን ነው፡፡ የምንጠብቀው አደራጅቶ ወደ ትግል የሚያስገባን መሪ ነው›› ብለዋል፡፡ ተሰብሳቢዎቹ የተለያዩ አስተያየቶችንና ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን፤ ለጥያቄዎቹ ከወ/ሪት ብርቱካንና ከአቶ ተመስገን ዘውዴ ምላሽ አግኝተዋል፡፡

ባለፈው ምርጫ ብናሸንፍም ድምፃችንን በመሳሪያ ተነጥቀናል፤ እንዲህ አይነቱ ሁኔታ እንዳይፈጠር ምን አይነት ስትራቴጂ አላችሁ፤ መንገዶች ሁሉ እየተዘጉ ነው እንዴት ወደ ምርጫ እንገባለን፤ ምርጫ አሸንፈን የገባነው ዘብጥያ ነው ህዝቡ አሁንም በእጃችን ቢሆንም ያለፈው ስህተት እንዳይደገም ምን ማረጋገጫ ትሰጡናላችሁ፤ ለዚህ ሁሉ ችግር የተጋለጥነው በናንተ በመሪዎቹ አቅም ማነስ ነው አሁንስ አቅማችሁ ምን ያህል አስተማማኝ ነው የሚሉት ከተሰብሳቢዎቹ የተነሱ ጥያቄዎች ናቸው፡፡

‹‹ቅንጅት እያለን ሳይታሰብ ትልቅ ከፍታ ላይ ወጥተን ነበር፡፡ ድጋሚ ሳይታሰብ ወለል ላይ ወድቀናል፤ አሁን ደግሞ ተመልሰን እያንሰራራን ነው›› በማለት ምላሽ መስጠት የጀመሩት ወ/ሪት ብርቱካን ‹‹ስማችንና ምልክታችን ለማይታወቁ ግለሰቦች ተሰጥቶብናል፡፡ ማንነታችንን ግን ሊነጥቁን አይችሉም፡፡›› ያሉት ሊቀመንበሯ ‹‹ቅንጅትን ከመሰንጠቅ ለማዳን የተለያዩ ሙከራዎች አድርገን አልተሳካልንም፡፡ አሁን ያን ሁሉ አልፈን አንድነትን መስርተናል፤ ዛሬ ደግሞ እናንተ ጋር ደርሰናል፡፡ ባለን ግንኙነት ተጠቅመን ሴቱን በሴት፣ ወጣቱን በወጣት ለማደራጀት ያሰብነውን ማሳካት ሲያቅተን አይታየኝም›› ብለዋል፡፡

በአሁን ሰአት በአነስተኛ መመዘኛ እንኳን ምርጫ ውስጥ የሚያስገባ ሁኔታ የለም፤ ትርጉም የሌለው ተሳትፎ ውስጥ ገብተን ለኢህአዲግ የይስሙላ መድብለ ፓርቲ ማስፈፀሚያ ልንሆን እንደማይገባ እናምናለን›› ያሉት ወ/ሪት ብርቱካን ‹‹ካሁን ጀምሮ እስከ ምርጫ ብዙ ጊዜ አለ፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ገዢው ፓርቲ በተለያዩ ጫናዎች እንዲሻሻል ማድረግ ካልቻልን ምርጫ ውስጥ አንገባም፡፡ በተወሰነ ደረጃ የተመቻቸ ሁኔታ ካለ ግን እንወዳደራለን፤ እንሸንፋለን›› ብለዋል፡፡

ፓርላማ ላለመግባት ስትወስኑ ለምን አላማከራችሁንም፤ በፓርላማ ያሉት ቢያንስ የህዝቡን ድምፅ እያስተጋቡ ነው ለሚለው ሲመልሱም ‹‹ፓርላማ ላለመግባት የወሰነው የፓርቲው ላእላይ ምክር ቤት ነው፡፡ ስለውሳኔውም ህዝቡን ለማማከር ሞሯክል፡፡ ወደ ክልል ወርዶ ለማነጋገር ያደረገው ሙከራም ባህርዳር ሲደርስ እክል ገጥሞት በዛው ቆሟል››ካሉ በኋላ ‹‹ ከትላንትናችን ነጋችን ያስፈለገናል መስራት ያለብንም ለዚያ ነው›› ብለዋል፡፡
ተሰብሳቢዎቹ ወልዲያ፣ ሀብሩ፣ መቄት፣ ዋድላን ጨምሮ ከዘጠኝ ወረዳዎች ለሶስት ሰአታት በእግር ተጉዘው የመጡ የቀድሞ ቅንጅት የወረዳ አስተባባሪዎች፣ አባላትና ወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች ሲሆኑ ‹‹ሀገርን ሊመሩ ከሚችሉት ጋር እንሰራለን፣ ለስልጣን ሳይሆን ለነፃነታችን እንታገላለን›› ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ሰባት አባላት ያሉት ጊዜየዊ አስተባባሪ ኮሚቴ በመምረጥ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

Comments are closed.